Sunday, September 24, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢንሹራንስ ኩባንያዎች ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ ተጨማሪ ታክስ እንዲከፍሉ መጠየቃቸውን ተቃውሙ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የገቢዎች ሚኒስቴር ከዚህ ቀደም ባንኮች ለካፒታል ማሳደጊያ ካዋሉት ትርፍ ላይ ታክስ እንዲከፍሉ አቅርቦት የነበረውን ጥያቄ፣ ለኢንሹራስ ኩባንያዎች ማቅረቡ ተቃውሞ ማስነሳቱ ተገለጸ፡፡

ለካፒታል የዋለ ትርፍ ላይ ታክስ መከፈል እንደሌለበት እየታወቀ፣ የገቢዎች ሚኒስቴር ትርፋቸውን ለካፒታል ማሳደጊያ ያዋሉ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች፣ ለካፒታል ማሳደጊያ ባዋሉት ትርፍ ላይ ተጨማሪ ታክስ እንዲከፍሉ ጥያቄ ማቅረቡ አግባብ እንዳልሆነ በማመልከት፣ ለሚመለከተው የመንግሥት አካል አቤት እያሉ ነው፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር ሰሞኑን ለኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሊከፍሉት ይገባል ያለውን የገንዘብ መጠን ባስቀመጠው የጊዜ ገደብ እንዲከፍሉ እያሳሰባቸው ይገኛል፡፡

የኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ግን ለካፒታል ማሳደጊያ ባዋሉት ትርፍ ላይ ታክስ እንዲከፍሉ ከገቢዎች ሚኒስቴር የቀረበላቸውን ጥያቄ አግባብ አለመሆኑን እያሳወቁ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የገቢዎች ሚኒስቴር የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ጽሕፈት ቤት ግን ኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ በተጠቀሰው ጊዜ የተጠየቁትን መክፈል ካልቻሉ ‹‹ዕርምጃ እወስዳለሁ›› እያለ ነው፡፡ ይህ የሚኒስቴሩ ማሳሰቢያ ካፒታላቸውን ያሳደጉና የትርፍ ክፍፍልላቸውን ለዚሁ ካፒታል ማሳደጊያ ያዋሉትን ሁሉ የሚመለከት ነው፡፡ ጥያቄው የቀረበላቸው የኢንሹራንስ ኩባንያዎችም ለካፒታል ማሳደጊያ የዋለ ትርፍ ግብር የሚጠየቅበት ባለመሆኑ፣ ‹‹ልንከፍል አይባንም›› በማለት በማኅበራቸው በኩል ለሚመለከታቸው መንግሥታዊ ከአካላት አቤቱታቸውን በማቅረብ ምላሽ እየተጠባበቁ ነው፡፡   

ከኢንሹራንስ ኩባንያዎቹ ሪፖርተር ያገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፣ ለካፒታል ማሳደጊያ ያዋሉት ትርፍ ላይ እንዲከፍሉ የተጠየቁት የታክስ ክፍያን በ21 ቀናት ውስጥ እንዲፈጽሙ ጫና ማድረጉ ደግሞ ጉዳዩን አወሳስቦታል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸው አንዳንድ የኢንሹራንስ ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎች እንደጠቆሙት፣ የገቢዎች ሚኒስቴር ጥያቄ ያልጠበቁትና ሕጋዊ አለመሆኑን ነው፡፡ ባለፉት ዓመታት የትርፍ ክፍፍላቸውን ለካፒታል ማሳደጊያ ያዋሉ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ሁሉ፣ ገቢዎች ሚኒስቴር እያስጨነቃቸው መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ማሳሰቢያው ከደረሳቸው የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ውስጥ አብዛኞቹ ከ30 ሚሊዮን ብር በላይ የተጠየቁ መሆናቸውንም የኢንሹራንስ ኩባንያ የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡

‹‹ሕጋዊ አይደለም›› የተባለውን ግብር ክፈሉ ከተባሉት የኢንሹራንስ ኩባንያዎች መካከል አንዱ የሆነው ኅብረት ኢንሹራንስ፣ ለካፒታል ማሳደጊያ ባዋለው ትርፍ ላይ 46 ሚሊዮን ብር ተጨማሪ ታክስ መጠየቁን ለማወቅ ተችሏል፡፡ ፀሐይ ኢንሹራንስ 13 ሚሊዮን ብር፣ ንብ ኢንሹራንስ 41 ሚሊዮን ብር መጠየቃቸው ለአብነት ተጠቅሷል፡፡ በአጠቃላይ ለካፒታል ማሳደጊያ ከዋለው ትርፍ ላይ ኩባንያዎቹ የተጠየቁት አጠቃላይ የገንዘብ መጠን ከ300 ሚሊዮን ብር በላይ እንደሚሆንም ተጠቁሟል፡፡ የኅብረት ኢንሹራንስ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወ/ሮ መሠረት በዛብህ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ጥያቄው ያልተገባ ብቻ ሳይሆን ፈተና ሆኖብናል ብለዋል፡፡

‹‹ካፒታል ሲያድግ በየዓመቱ የሚደርስህን ትርፍ ከወሰድህ 10 በመቶ የትርፍ ክፍፍል ታከስ ይከፈላል፤›› ያሉት ወ/ሮ መሠረት፣ ትርፍህን ሪኢንቨስት ካደረግህ ግን ታክስ እንደሌለው በአዋጅ ተቀምጧል፡፡

በገቢዎች ሚኒስቴር ግን ከትርፍ ክፍፍል ላይ ኢንቨስት ይደረግ የሚል የተቀመጠ ነገር ስለሌለ፣ የትርፍ ክፍፍሉን ባለአክሲዮኑ ባይወስድም አሥር በመቶውን ከትርፍ ክፍፍል ታክስ መክፈል ይኖርበታል በማለት ያቀረበው ጥያቄ አግባብ እንዳልሆነ ወ/ሮ መሠረት ይገልጻሉ፡፡ 

የኢትዮጵያ የመድን ሰጪዎች ማኅበር በበኩሉ፣ የማኅበሩ አባላት ባቀረቡት አቤቱታ መሠረት ጉዳዩን በመመርመር የገቢዎች ጥያቄ አግባብ ባለመሆኑ፣ በቀጥታ ለገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ግንቦት 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ደብዳቤ ጽፏል፡፡ ከማኅበሩ የተጻፈው ደብዳቤ እንደሚያመለክተው፣ የገቢዎች ሚኒስቴር ለካፒታል ማሳደጊያ በዋለ ትርፍ ላይ የጠየቀው ተጨማሪ የታክስ ክፍያ አግባብነት የሌለው መሆኑን ነው፡፡

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በየዓመቱ ያገኙትን ትርፍ የባለአክሲዮኖች መደበኛና ድንገተኛ ጉባዔዎች በሚወስኑት መሠረት፣ የብሔራዊ ባንክን አሠራር ተከትለው ለካፒታል ማሳደጊያነት እያዋሉ የሚገኙ በመሆኑና በዚሁ አግባብ የሚሠሩ በመሆኑም አሁን ያቀረበው ጥያቄ ሕጋዊ ያለመሆኑንም አመላክቷል፡፡ በርካታ የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ለካፒታል ማሳደጊያ ያዋሉትን ትርፍ ተቆጣጣሪው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተመልክቶ ባፀደቀው መንገድ ትርፋቸውን ለካፒታል ማሳደጊያነት እያዋሉ ስለመሆናቸውም ማኅበሩ በደብዳቤው አስታውቋል፡፡ በመሆኑም በገቢዎች ሚኒስቴር የከፍተኛ ግብር ከፋዮች ጽሕፈት ቤት የካፒታል ዕድገቱ በንግድ ፈቃድ ዕድሳት ላይ በተሰጠው የጊዜ ገደብ (12 ወራት) አልተመለከተም በማለት ብቻ፣ ኩባንያዎቹ ለካፒታል ማሳደጊያነት በግልጽ ያዋሉትን ትርፍ እንዳልተከፋፈለ ትርፍ በማሰብ፣ ተጨማሪ ታክስ እንዲከፍሉ በመጠየቃቸው አግባብ አለመሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ሕጋዊ መሠረት የለውም የተባለውን የግብር ጥያቄ የገንዘብ ሚኒስትሩ ተመልክተው መፍትሔ ይሰጡት ዘንድ ከማመልከትም በላይ፣ የገቢዎች ሚኒስቴር ጥያቄ አግባብ ያለመሆኑን ለማሳየት፣ ከዚህ ቀደም ተመሳሳይ ጥያቄ ለባንኮች ቀርቦ ገንዘብ ሚኒስቴር ጥያቄውን ውድቅ አድርጎ እንደነበር የሚያሳይ ማስረጃ ለገቢዎች በማስረጃነት ማኅበሩ አቅርቧል፡፡ ቀደም ሲል ገቢዎች ተመሳሳይ ጥያቄ ለባንኮች አቅርቦ የባንኮች ማኅበር ለሚኒስቴሩ ባቀረበው ጥያቄ መሠረት፣ ጉዳዩ በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከታየ በኋላ፣ የፌዴራል የገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 አንቀጽ 61 ድንጋጌና ሊያስፈጽም የተነሳውን ዓላማ በተገቢው መንገድ በሚገባ ሁኔታ በመተርጎም፣ የገቢዎች ጥያቄ ተፈጻሚ እንዳይሆን መደረጉንም የማኅበሩ ደብዳቤ አስታውሷል፡፡ ስለሆነም በወቅቱ የኩባንያዎቹ (ባንኮች) ባለአክሲዮኖች ትርፍን በመከፋፈል ፈንታ ቃል ለገቡበት አክሲዮን ማሳደጊያ መዋሉ ከተረጋጠ፣ ሳይከፈል በቀረ የአክሲዮን ድርሻ ላይ የሚፈለገው ግብር ሊመለከታቸው የማይገባ መሆኑን በመግለጽ፣ ለገቢዎች ሚኒስቴር ደብዳቤ እንደጻፈው  ሁሉ  አሁንም ተመሳሳይ ዕርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀዋል፡፡  

በአሁኑ ወቅት በተመሳሳይ ሁኔታ ለኢንሹራንስ ኢንዱስትሪ የቀረበው የተጨማሪ ታክስ ጉዳይም፣ ለአክሲዮን ማሳደጊያ በዋለ ትርፍ ላይ መሆኑንና አግባብነት ያለው ጥያቄ እንዳልሆነ በመግለጽም፣ ሚኒስቴሩ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥበት አሳስቧል፡፡ ከዚህ ቀደም ለባንኮች እንደተደረገው ሁሉ የኢንሹራስ ኩባንያዎች ባለአክሲዮኖች ያገኙትን ትርፍ በመከፋፈል ፈንታ፣ የአክሲዮን ድርሻ መጠናቸውን ለማሳደግ መዋላቸው ከተረጋገጠ ሳይከፋፈል በቀረ የአክሲዮን ትርፍ ድርሻ ላይ የማይመለከታቸው በመሆኑ፣ ይሄው ተገልጾ ለገቢዎች ሚኒስቴር እንዲጻፍላቸውም ማኅበሩ ጠይቋል፡፡  

ማኅበሩ ለገንዘብ ሚኒስቴር ከጻፈው ደብዳቤ ሌላ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም የገጠመውን ችግር አስታውቋል፡፡ ግንቦት 29 ቀን 2015 ዓ.ም. ለብሔራዊ ባንክ በጻፈው ደብዳቤ፣ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች በየዓመቱ ያገኙትን ትርፍ የባለአክሲዮኖች መደበኛና ድንገተኛ ጉባዔዎች በሚወስኑት መሠረት፣ የብሔራዊ ባንክን አሠራርን ተከትለው ለካፒታል ማሳደጊያነት ያዋሉና እያዋሉ የሚገኙ መሆናቸውን ያስታውሳል፡፡

አያይዞም በርካታ ኢንሹራንስ ኩባንያዎች የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሚያውቀው ሕጋዊ መንገድ፣ ትርፋቸው ለካፒታል ማሳደጊያነት እያዋሉ በመሆኑ፣ ለካፒታል ማሳደጊያነት በግልጽ ያዋሉትን ትርፍ እንዳልተከፋፈለ ትርፍ በማሰብ፣ ተጨማሪ ታክስ እንዲከፈል መጠየቃቸው ትክክል ስላልሆነ፣ በጉዳዩ ላይ ከሚመለከታቸው ጋር በመነጋገር መፍትሔ እንዲያፈላልግ፣ ብሔራዊ ባንክ የበኩሉን እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡  

የገቢዎች ሚኒስቴር ጥያቄ በተለይ ከፍተኛ የፋይናንስ እጥረት ባለበት ወቅት መቅረቡም በእጅጉ እንዳሳሰባቸው ሪፖርተር ያነጋገራቸው የኢንሹራንስ ኩባንያዎች የሥራ ኃላፊዎች ገልጸዋል፡፡ እንደ ወ/ሮ መሠረት ገለጻ ይህ ጥያቄ ከዚህ ቀደም ለባንኮች ቀርቦ ከሕግ አንፃር ተመዝኖ ገቢዎች ሪኢንቨስት በተደረገ ትርፍ ላይ ግብር መሰብሰብ እንደማይችል ተገልጾ ተፈጻሚ ሳይሆን ቀርቷል ይላሉ፡፡

አሁንም ማኅበራችን ለገንዘብ ሚኒስቴር ደብዳቤ ሲጽፍ ለባንኮች የሰጠውን ውሳኔ የያዘ ደብዳቤ ተያይዞ የተላከው ጉዳዩ በቀላሉ ይቋጫል ከሚል የተነሳ ሲሆን፣ ገንዘብ ሚኒስቴር አዎንታዊ ምላሽ ይሰጠናል የሚል እምነት እንዳላቸው አክለዋል፡፡     

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች