Tuesday, September 26, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

የመንግሥት ውሳኔዎች ከሕዝብ ፍላጎት ጋር አይጋጩ!

የሕዝብን ጥቅምና ፍላጎት ያላገናዘበ የመንግሥት ውሳኔም ሆነ ዕርምጃ፣ እንደ ሌሊት ወፍ ከተገኘው ነገር ጋር ከማላተም የዘለለ ፋይዳ የለውም፡፡ መንግሥት በሕግ በተሰጠው ሥልጣን መሠረት በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካ፣ በማኅበራዊ፣ በዲፕሎማሲያዊም ሆነ በሌሎች ጉዳዮች ላይ ውሳኔ የማስተላለፍም ሆነ ዕርምጃ የመውሰድ ኃላፊነት እንዳለበት ለማንም ግልጽ ነው፡፡ የሚተላለፈው ውሳኔም ሆነ ዕርምጃ ግን ግራና ቀኙን ያገናዘበ፣ የአገርን ብሔራዊ ደኅንነትና ጥቅም ያስቀደመ፣ የመላውን ሕዝብ ሰላምና ፍላጎት ያማከለ፣ በትውልድ ቅብብሎሽ እዚህ የደረሱ ማኅበራዊ መስተጋብሮችንና እሴቶችን ያከበረ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን የሚያስጠብቅ፣ ከጎረቤት አገሮችም ሆነ ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰቡ ጋር በጋራ ጥቅም ላይ የተመሠረተ ግንኙነት የሚያዳብር፣ እንዲሁም ለአገር ሁለንተናዊ ዕድገት ፋይዳ የሚኖረው መሆን ይጠበቅበታል፡፡ ከዚህ ውጪ ግልጽነት የጎደለውና ተጠያቂነት የሌለበት የብልሹ አሠራር መገለጫ የሆነ ውሳኔም ሆነ ዕርምጃ፣ ከሕዝብ ጋር ሆድና ጀርባ ከማድረጉም በላይ የሕግና የሞራል ተጠያቂነት ያስከትላል፡፡ በአሁኑ ጊዜ በስፋት የሚስተዋሉ የማናለብኝነት ድርጊቶች መግቻ ካልተደረገላቸው ዋጋ ያስከፍላሉ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንግሥት የንብረት ወይም የይዞታ ግብር (Property Tax) ማስከፈል ጀምሯል፡፡ ይህ የግብር ዓይነት በበርካታ አገሮች የታወቀ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ተግባራዊ ለማድረግ እየተነገረ ያለው ምጣኔ ግን ከአቅም በላይ ነው፡፡ የዘርፉ ባለሙያዎች እንደሚሉት በጣም ከአደጉ አገሮች ጋር ሲነፃፀር፣ በከፋ ድህነት ውስጥ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን የማይቻል ነው፡፡ ከሰሃራ በታች የአፍሪካ አገሮች ጋር ሳይቀር በጣም ዝቅተኛ የሆነ የነፍስ ወከፍ ገቢ ባለባት፣ የኑሮ ውድነቱ ከሚቋቋሙት በላይ በሆነባት፣ መሠረታዊ ፍላጎቶችን በቅጡ ለማሟላት ባልተቻለባትና ዜጎች እያደር ቁልቁል የሆነ ኑሮ በሚመሩባት ኢትዮጵያ ውስጥ እየተጣለ ያለው የንብረት ግብር ካልታሰበበት ውጤቱ አደገኛ ነው፡፡ መንግሥት ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ ችግር ቢኖርበት እንኳ የተለያዩ የገቢ አማራጮችን ለማስፋት ይተጋል እንጂ፣ የዜጎችን የድህነት ሕይወት ይበልጥ የሚያመሰቃቅል ውሳኔ እያስተላለፈ ዙሪያውን ገደል ማድረግ የለበትም፡፡ አሁንም ጊዜው አልረፈደምና ከፍተኛ ማኅበራዊ ምስቅልቅልና ቀውስ ሊያስከትል የሚችለውን ውሳኔውን ቢያጤን ይሻላል፡፡ በአጉል ምክር ሕዝብ ላይ ጭነት ማብዛት መዘዙ የከፋ ነው፡፡

በአሁኑ ጊዜ መንግሥት በሚወስዳቸው በርካታ ዕርምጃዎች እየተጎዱ ያሉ የኅብረተሰብ ክፍሎች አሉ፡፡ ለዓመታት የኖሩባቸው መኖሪያ ቤቶቻቸው የፈረሱባቸው፣ በጊዜያዊነት ይሠሩባቸው የነበሩ ኪዮስኮቻቸው ፈርሰውባቸው ምትክ መሥሪያ ቦታ ያላገኙ፣ በጦርነትም ሆነ በተለያዩ ምክንያቶች ተፈናቅለው ዕርዳታ የማይደርሳቸው ወገኖች፣ በመንግሥት ድርጊት ደስተኛ ባለመሆናቸው ድምፃቸውን በማሰማታቸው ለእስርና ለእንግልት የሚዳረጉና በሌሎች የተለያዩ ምክንያቶች ያኮረፉ ወገኖች በርካቶች ናቸው፡፡ ትናንት ለለውጡ መንግሥት ሽንጣቸውን ገትረው ሲሟገቱ የነበሩ ዛሬ አቋማቸውን ቀይረው ተቃውሞ ጎራ ውስጥ በብዛት እየተገኙ ነው፡፡ እዚህ ላይ ልብ ሊባል የሚገባው ጉዳይ በሒደት ብዙ ነገሮች መለዋወጣቸው አይቀሬ መሆኑን ነው፡፡ ነገር ግን በአገር ዋና ዋና ጉዳዮች ላይ መስማማት የማያስችሉ ጉዳዮች ሲበረክቱ ግን ለምን ተብሎ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ እነ እከሌ ወይም እነ እከሊት በፊትም የተጠጉት ጥቅም ወይም ሥልጣን ፈልገው ነው እንጂ፣ ለአገር አስበው አይደለም አቋማቸውን የለወጡት ማለት ጤነኝነት አይደለም፡፡ በበርካታ ጉዳዮች ልዩነት ቢኖርም በአገር ህልውና ላይ ግን ጽንፍ መያዝ ተገቢ አይደለም፡፡

በሥራ ላይ ባለው ሕገ መንግሥት መሠረት መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡ መንግሥትና የሃይማኖት ተቋማት በአገር ልማትና በሕዝብ ኑሮ ዕድገት ከመተባበር ውጪ፣ አንዳቸው በሌላቸው ጉዳይ ጥልቅ ማለት የለባቸውም፡፡ ሁለቱን የማያስማሙ ጉዳዮች ቢኖሩ እንኳ በሰከነ መንገድ ችግሮችን መፍታት ይኖርባቸዋል፡፡ ከዚህ በዘለለ ምዕመናንን አስቆጥተው የሚያስነሱ ውሳኔዎችም ሆኑ ዕርምጃዎች እንዳይወሰዱ ጥንቃቄ ማድረግም ተገቢ ነው፡፡ ከክርስትናም ሆነ ከእስልምና እምነቶች ጋር የሚያገናኙ ጉዳዮች ሲያጋጥሙም፣ ለአገር አንድነትና ደኅንነት የሚበጁ ነገሮች ላይ በማተኮር ችግሮችን መቅረፍ ትልቅ ፋይዳ አለው፡፡ ከዚህ ውጪ ግን በከፍተኛ ደረጃም ሆነ በዝቅተኛ ደረጃ ላይ የሚገኙ የመንግሥት ሹማምንት ከፍተኛ ጥንቃቄ ማድረግ ያለባቸው፣ ከእምነት ተቋማት ጋር በሚደረግ ግንኙነት አላስፈላጊ ድርጊቶች እንዳይፈጸሙ ነው፡፡ በሃይማኖት ተቋማት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባትም ሆነ የእምነት ቦታዎችን በሕገወጥነት ፈርጆ ማፍረስ፣ ሊያስከትለው የሚችለው አደጋ በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት ሊጤን ይገባል፡፡ አማኞች የእምነት ቦታዎቻቸው ተነክተው ለተቃውሞ ሲወጡ የሚወሰዱ ዕርምጃዎች የሚያስከትሉት መዘዝም ይታሰብበት፡፡

መንግሥት የአገርና የሕዝብ አደራ ያለበት ትልቅ ተቋም ነው፡፡ ይህንን ትልቅ ተቋም በየደረጃው የሚመሩ ሰዎች ደግሞ ሆደ ሰፊነት ይጠበቅባቸዋል፡፡ በሁሉም የሥልጣን እርከኖች ላይ የሚገኙ ግለሰቦች ከምንም ነገር በፊት የአገርና የሕዝብ ጉዳይ ሊያሳስባቸው ይገባል፡፡ ከተወሰኑ ግለሰቦችም ሆነ ቡድኖች ጋር በርዕዮተ ዓለምም ሆነ በሌላ ምክንያት ባይግባቡ እንኳ፣ በአገርና በፓርቲ ወገንተኝነት መካከል ያለው ልዩነት ሊያጤኑ ግድ ይላቸዋል፡፡ የብሔርም ሆነ የሃይማኖት መሳሳብም ሆነ መገፋፋት ከአገር በላይ ሊያስጨንቃቸው አይገባም፡፡ እነሱ የተቀመጡበት ወንበር ከትናንት ወዲያና ትናንትና ሌሎች ሰዎችም ተቀምጠውበት ነበር፡፡ ይልቁንም ከቀደምቶቹ ጠንካራና ደካማ ጎኖች በመማር የተሻለ አበርክቶ እንዲኖራቸው ጥረት ያድርጉ፡፡ ትናንት ከተፈጸሙ የባሱ ስህተቶችን ከመሥራት ራስን መከላከል የሚቻለው፣ ታሪክን በአግባቡ በመገንዘብ ለዘመኑ የሚመጥን ሥራ በማከናወን ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ በዕውቀት፣ በልምድና በሥነ ምግባር የተመሰከረላቸውን አማካሪዎች መጠቀም ብልህነት ነው፡፡ እንደ ጭልፊት ጥቅም ላይ ያሰፈሰፉ ግብረ በላዎችን ይዞ ጥፋት እንጂ ልማት አይታሰብም፡፡

መንግሥት ከሕዝብ ጋር በመቀራረብ ለአገር የሚበጁ ተግባራት ላይ ሲያተኩር፣ ከአገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ለአገራቸው ሙያዊ አስተዋፅኦ ማበርከት የሚፈልጉ ዕውቀትና ሀብት ያላቸው ዜጎች ይነቃቃሉ፡፡ ሁሉንም ኢትዮጵያውያን በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ እኩል የማሳተፍ ፍላጎት ሲኖር፣ ለፀብና ለግጭት የሚያነሳሱ ጉዳዮች በሰላማዊ መንገድ መፈታት ይችላሉ፡፡ ሁሉም ዜጎችና የፖለቲካ ኃይሎች በእኩልነት የሚስተናገዱበት ዓውድ ሲፈጠር፣ ሕግና ሥርዓት ተከብሮ ከቦታ ወደ ቦታ መዘዋወርም ሆነ መሥራት አያዳግትም፡፡ በሁሉም አገራዊ ጉዳዮች ላይ በሥርዓትና በዕርጋታ መነጋገርም ሆነ መከራከር የዘወትር ተግባር ይሆናል፡፡ የአንድ ወገን የበላይነት ብቻ ሲፈለግ ግን ሌብነትና ምዝበራ ቅጥ ያጣሉ፡፡ የመንግሥታዊ አገልግሎቶች አሰጣጥ ሥርዓት ብልሹ ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ሕጋዊነትና ሰላማዊነት ርቆት በየቦታው ግጭት መደበኛ ሥራ ይደረጋል፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እየተጣሱ ሥርዓተ አልበኝነት ይሰፍናል፡፡ መንግሥትም ሆነ የአገር ጉዳይ ይመለከተናል የሚሉ ኃይሎችና ዜጎች እንዲህ ዓይነቱ አስከፊ ሁኔታ እንዲለወጥ ኃላፊነታቸውን ይወጡ፡፡ የመንግሥት ውሳኔዎች ደግሞ ከሕዝብ ፍላጎት ጋር አይጋጩ! 

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...