- ከቀረበው አጠቃላይ በጀት 159 ቢሊዮን ብር ለብድር የሚከፈል ነው
በሚኒስትሮች ምክር ቤት ፀድቆ ለፓርላማው በተመራው የ2016 ዓ.ም. በጀት፣ ለካፒታል ወጪዎች የተመደበው ገንዘብ ማነስ በፓርላማው ከፍተኛ ጥያቄ አስነሳ፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴ ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ረቂቅ በጀቱን አስመልክተው ባቀረቡት ማብራሪያ፣ ከቀረበው 801.65 ቢሊዮን ብር ውስጥ 370 ቢሊዮን ብር ለመደበኛ ወጪ፣ 203 ቢሊዮን ብር ለካፒታል ወጪ፣ 214 ቢሊዮን ብር ለክልሎች ድጋፍ፣ እንዲሁም 14 ቢሊዮን ብር ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያ ድጋፍ በፓርላማ ተደልድሎ ቀርቧል፡፡
በረቂቅ በጀቱ እንደተመለከተው የ2016 በጀት ዓመት ገቢ ከአገር ውስጥ ታክስ ገቢ 440 ቢሊዮን ብር፣ ታክስ ካልሆኑ ገቢዎች 36 ቢሊዮን፣ እንዲሁም ከካፒታል ገቢ 1.9 ቢሊዮን ብር በድምሩ 479 ቢሊዮን ብር ነው፡፡ በሌላ በኩል ከዓለም አቀፍ ተቋማት ዕርዳታ 30 ቢሊዮን ብር፣ ከመንግሥታት ዕርዳታ አራት ቢሊዮን ብር፣ ከመሠረታዊ አገልግሎቶች ከለላ ድጋፍ ስድስት ቢሊዮን ብር፣ በድምሩ 41 ቢሊዮን ብር እንደሚገኝ ታቅዷል፡፡ በተጨማሪም ከዓለም አቀፍ ተቋማት ብድር 23 ቢሊዮን ብር፣ ከመንግሥታት ብድር ስምንት ቢሊዮን ብር፣ ከመሠረታዊ አገልግሎቶች ከለላ ድጋፍ ሰባት ቢሊዮን ብር፣ እንዲሁም ከአገር ውስጥ ብድር 242 ቢሊዮን ብር ይገኛል ተብሏል፡፡
በ2016 በጀት ዓመት ከውጭ ዕርዳታ እንደሚገኝ የታቀደው ገቢ በ2015 በጀት ዓመት ይገኛል ተብሎ ከተገመተው ገቢ አንፃር የ33.4 በመቶ ጭማሪ እንዳለው የተገለጸ ሲሆን፣ ከጠቅላላ ገቢው የ2016 ዓ.ም. የገቢና የዕርዳታ ዕቅድ 7.9 በመቶውን ድርሻ ይይዛል፡፡
የበጀት ማብራሪያውን ተከትሎ የካፒታል በጀቱ ዝቅተኛ መሆኑን በርካታ የምክር ቤት አባላት ጥያቄ አንስተዋል፡፡ አንድ የምክር ቤት አባል፣ ‹‹በየዓመቱ አዳዲስ ፕሮጀክቶችን ማስጀመር አይቻልም እየተባለ ለምክር ቤቱ በጀት እየቀረበ የምናፀድቅ ከሆነ፣ የሕዝቡን የልማት ፍላጎትና በምርጫ ጊዜ ለሕዝብ የተገቡ ቃሎችን እንዴት ማስፈጸም ይችላል?›› በማለት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
አቶ እሱባለው መብራቱ የተባሉ የምክር ቤት አባል ደግሞ በተከታታይ ለአራት ጊዜያት የመረጣቸውን አካባቢ ሕዝብ ለማነጋገር በሄዱበት ወቅት፣ ፓርቲው በምርጫ ወቅት ለሕዝቡ ቃል የገባቸውን ጉዳዮች ማስፈጸም ያልተቻለበትን ምክንያት ማስረዳት መቸገራቸውን ተናግረዋል፡፡ ለአብነትም በካፒታል በጀት ዕቅድ ተይዞላቸው ይገነባሉ ተብለው የነበሩ መንገዶች ባለፈው ዓመት መታጠፋቸው መገለጹን አስታውሰው፣ ‹‹አሁንም ለመንገዶቹ በጀት ባለመመደቡ በቀጣይ የመረጠንን ሕዝብ ለማወያየት ስንሄድ ለሚቀርበው ጥያቄ የምንሰጠው መልስ ምን ይሆናል?›› ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
ሌላ የምክር ቤቱ አባል ከዚህ በፊት ለአዳዲስ የመንገድ ፕሮጀክቶች ዕቅድ አልተያዘም ሲባል ቆይቶ፣ በዚህኛው በጀትም በ2015 ዓ.ም ለካፒታል ወጪዎች ተመድቦ ከነበረው በስድስት በመቶ ቀንሶ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ አክለውም በርካታ የመንገድ ፕሮጀክቶች ጨረታ ወጥቶባቸው፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ደብዳቤ በመጻፍ ያገዳቸው ፕሮጀክቶች እንዴት ሊፈጸሙ ታስቧል ሲሉ ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
አቶ ነዚፍ ዝናቡ የተባሉ የምክር ቤት አባል በበኩላቸው ከቀረበው የበጀት ክፍፍል አንፃር የካፒታል በጀት መቀነሱን ጠቅሰው፣ አሁን ያለው የሕዝብ ጥያቄ የመንገድ ከፕሮጀክቶች አለመጠናቀቅና የመንገድ ካሳ ክፍያ አለመከፈል ጋር በመሆኑ፣ ቀንሶ በመጣው የካፒታል በጀት ፕሮጀክቶችን እንዴት ለማጠናቀቅ ታስቧል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስትሩ ለተነሱት ጥያቄዎች ማብራሪያ ሲሰጡ፣ አዳዲስ ፕሮጀክቶች ለምን አይኖሩም ተብሎ ለቀረበው ጥያቄ፣ አሁን አዳዲስ ፕሮጀክቶች ለመጀመር የሚያስችል የገቢ አቅም ስለሌለና የበጀት ጉድለቱ የዋጋ ዕድገት እንዳያመጣ ጥንቃቄ ተደርጎበት የተሰናዳ በጀት ነው በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
ይሁን እንጂ በቀጣይ ዓመት የአገሪቱ አቅም ጨምሮና ከልማት አጋሮች የሚገኘው ገንዘብ ታይቶ ተጨማሪ በጀት ሊመደብ እንደሚችል በማሰብ፣ አሁን ባለው በጀት ግን ገበያ ማረጋጋት ላይ ይሠራል ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ የተጀመሩ የመንግሥት ፕሮጀክቶችን ለመጨረስ አንድ ትሪሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ጠቁመው፣ ከዚህ ውጪ የተጀመሩ የመስኖና የዩኒቨርሲቲ ፕሮጀክቶች በተመሳሳይ ግዙፍ ገንዘብ እንደሚያስፈልጋቸው ገልጸዋል፡፡ ‹‹ይሁን እንጂ ፓርላማው ያፀደቀውን ፕሮጀክት በመንግሥት ደረጃም ሆነ በገንዘብ ሚኒስቴር በኩል የታጠፈ ፕሮጀክት የለም፡፡ ፕሮጀክት ተሰርዟል ብሎ የተናገረ መሥሪያ ቤት ካለ ስህተት ነው፡፡ የፀደቀ ፕሮጀክት ቢዘገይም የመንግሥት ገቢ እየታየ ወደ ሥራ እንዲገባ ይደረጋል፤›› ብለዋል፡፡ ለ2016 ዓ.ም የቀረበው ረቂቅ የፌዴራል መንግሥት በጀት ካለፉት ዓመታት በጀት ጋር ሲነፃፀር፣ የአገሪቱን የልማት ፍላጎት ለማሳካት በቂ ባይሆንም፣ የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማስጨረስ እንደሚበቃ ግን ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
መንግሥት ለ2016 ዓ.ም. ከያዚው አጠቃላይ በጀት ውስጥ 159 ቢሊዮን ብር ለዕዳ ክፍያ መመደቡን አስታውቋል፡፡ ይህም የፌዴራል መንግሥቱን መደበኛና ካፒታል ወጪ 27 በመቶ የሚሆነውን ገንዘብ ይወስዳል ተብሏል፡፡
አቶ አህመድ የመንግሥት ገቢ አሰባሰብን ለማሻሻል ግብር ከፋይ ተኮርና ውጤታማ የታክስ አስተዳደር ሥርዓት መዘርጋት የሚያስችሉ ተግባራትን ለማከናወን መታቀዱን፣ አካታች የኢኮኖሚ ዕድገትንና የታክስ ገቢ አሰባሰብን የሚደግፉ የታክስ ፖሊሲዎችና ሕጎችም ተግበራዊ እንደሚሆኑ አስታውቀዋል፡፡