Tuesday, September 26, 2023

ከፍተኛ መጠን ያለው የዕርዳታ ምግብ እንደተመዘበረ ማረጋገጡን የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት አስታወቀ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

  • ዕርዳታው እንዲቋረጥ በመደረጉ 20 ሚሊዮን ዜጎች እንደሚጎዱ ተጠቁሟል
  • የአስቸኳይ ዕርዳታ ፈላጊዎችን ቁጥር ከፍ የሚያደርጉ ባለሥልጣናት እንዳሉ ተገልጿል

የአሜሪካ መንግሥት የዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ)፣ ባደረገው የምርመራ ውጤት ከፍተኛ መጠን ያለው የዕርዳታ ምግብ  አቅርቦት ምዝበራ መፈጸሙን በማረጋገጡ፣ በኢትዮጵያ የሚያደርገውን ዕርዳታ እንዳቆመ አስታወቀ፡፡ ውሳኔውም አስቸኳይ ዕርዳታ የሚያስፈልጋቸው ሃያ ሚሊዮን ዜጎችን እንደሚጎዳ ተገልጿል፡፡

ድርጅቱ እንደገለጸው፣ በፌዴራልና በክልሎች መንግሥታት አማካይነት ወታደራዊ ክፍሎች ከሰብዓዊ ዕርዳታው ተጠቃሚ ነበሩ፡፡

ዩኤስኤአይዲ ባደረገው ምርመራ ደርሼበታለሁ እንዳለው ከሆነ፣ ባለሥልጣናት  ለተረጂዎች ተብሎ የቀረበን የዕርዳታ ምግብ ወታደራዊ ኃይሎችንና የቀድሞ ተዋጊዎችን ለመመገብ ከመዋላቸው በተጨማሪ፣ ዱቄቱን ወደ ውጭ ለሚልኩ ድርጅት በግልጽ ገበያ ቀርቦ እንዲሸጥ ማድረጋቸውን አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡

ከፍተኛ መጠን ያለው የዕርዳታ ምግብ እንደተመዘበረ ማረጋገጡን የአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት አስታወቀ | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር

ጉዳዩን በተመለከተ የኢትዮጵያ መንግሥት ቃል አቀባይና የብሔራዊ የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን አስተያየት እንዲሰጡ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ አልሰጡም መባሉን ሪፖርተር የተመለከተው የዩኤስኤአይዲ ሰነድ ያስረዳል። ነገር ግን ስለጉዳዩ ዋሽግተን ፖስት የተሰኘው የሚዲያ ተቋም ባደረጋቸው ቃለ መጠይቆችና በተመለከታቸው ሰነዶች የድርጊቱን እውነትኝነት ተረጋግጧል ተብሏል፡፡

ለተረጂዎች የቀረበ የዕርዳታ ድጋፍ ለሌላ ዓላማ እንዲውል ማድረግ ሆን ተብሎ የሚደረግ የወንጀል ድርጊት ከመሆኑ ባሻገር፣ የሕይወት አድን ድጋፍ ለማድረግ የሚደረገውን ርብርብ የሚያሰናክል መሆኑ በሪፖርቱ ተጠቅሷል፡፡ ዩኤስኤአይዲ አረጋግጫለሁ እንዳለው፣ የተፈጸመው ድርጊት የፌዴራልና የክልል መንግሥታት አካላት በተቀናጀ ሁኔታ የወታደራዊ ክፍል አባላት፣ የሰብዓዊ ዕርዳታ ተጠቃሚ እንዲሆኑ አድርገዋል፡፡

ምን ያህል መጠን ያለው የዕርዳታ እህል እንደመተመዘበረ ባይታወቅም፣ ለጋሽ አካላት ያዋቀሩት የምርመራ ቡድን በሰባት ክልሎች በሚገኙ 63 የሚደርሱ የዱቄት ፋብሪካዎች ላይ ጉልህ ግኝት መገኘቱን በሪፖርቱ አቅርቧል፡፡ በተለይም ከአሜሪካ፣  ከዩክሬን፣ ከጃፓንና ከፈረንሣይ ለተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የዓለም ምግብ ፕሮግራም የተለገሰው የዕርዳታ ምግብ እንደመተዘበረ ተጠቅሷል፡፡ ሌሎች ለጋሽ አገሮች የላኩት ዕርዳታ እንዴት ጥቅም ላይ እንደዋለ እንደሚመረምሩ ጥያቄ ቀርቧል፡፡

የአሜሪካ የልማት ተራድኦ ድርጅቱ የተለየ የአሠራር ለውጥ ካልመጣ በስተቀር የዕርዳታ ምግብ ለማሠራጨት አልችልም ብሏል፡፡

ለመገናኛ ብዙኃን ራሳቸውን ከመግለጽ ተቆጥበው አስተያየት ሰጡ የተባሉ የዕርዳታ ሠራተኞችና ሌሎች ዲፕሎማቶች፣ የአገር ውስጥ ባለሥልጣናት የአስቸኳይ ዕርዳታ ፈላጊ አባወራዎችን ዝርዝር አኃዝ ከፍ ማድረግን ጨምሮ፣ በረሃብ ለተጠቁ ዜጎች የዕርዳታ ምግብ እንዳይዳረስ እንቅፋት እንደሚሆኑ ምስክርነት መስጠታቸው ተመላክቷል፡፡

ሪፖርቱን ይፋ ከተደረገ በኋላ የአሜሪካ መንግሥት የዓለም አቀፍ ልማት ተራድኦ ድርጅት (ዩኤስኤአይዲ) እና የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጡት የጋራ መግለጫ፣ በኢትዮጵያ የዕርዳታ ምግብ ዝርፊያን በተመለከተ ያጋጠመውን ችግር ለመፍታት ያላቸውን ቁርጠኝነት አስታውቀዋል፡፡

ሁለት አካላት በጉዳዩ ላይ ምርመራ እያደረጉ እንደሚገኙና ምርመራውን መሠረት በማድረግ የድርጊቱ ፈጻሚ ሆነው የተገኙ አካላት ተጠያቂ እንደሚሆኑ፣ ቀልጣፋ የዕርዳታ ድጋፍ ሥርጭት ሥርዓት እንዲዘረጋ ሁለቱም መንግሥታት ተባብረው እንደሚሠሩ ያላቸውን ቁርጠኝት መግለጻቸው በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

ከጥቂት ወራት በፊት ዩኤስኤአይዲና የዓለም ምግብ ፕሮግራም በተመሳሳይ ሁኔታ ትግራይ ክልል ውስጥ ስርቆት ተከስቷል በማለት፣ ለክልሉ ተረጂዎች ይቀርብ የነበረውን የዕርዳታ ምግብ ማቋረጣቸው ይታወሳል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ የዓለም ምግብ ፕሮግራም በኢትዮጵያ የሚያደርገውን የምግብ ድጋፍ ላልተወሰነ ጊዜ ማቋረጡን ዓርብ ሰኔ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -