Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ተጨማሪ ክፍያ የተጠየቀበት የኢትዮ ቴሌኮም ሕንፃ ግንባታ ድርድር መጠናቀቅ እንዳልቻለ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • ግንባታውን በጀመረው ኮንትራክተር ለማስጨረስ ወይም ለማቋረጥ አማራጮች እየታዩ ነው ተብሏል

በቦሌ አይሲቲ ፓርክ ውስጥ በግንባታ ላይ የነበረው የኢትዮ ቴሌኮም ግዙፍ ሕንፃ፣ የቻይናው ሲጂኦሲ ኩባንያ ባቀረበው ተጨማሪ የማጠናቀቂያ ክፍያ ምክንያት እየተደረገ የነበረው ድርድር መጠናቀቅ አልቻለም ተባለ፡፡

ከተጀመረ ሰባት ዓመታት ያስቆጠረውን ባለአሥራ አራት ወለል ሕንፃ የቻይናው ሲጂኦሲ የኮንስትራክሽን ኩባንያ በ4.5 ቢሊዮን ብር አጠናቆ ለማስረከብ ቃል ገብቶ የነበረ ቢሆንም፣ ኩባንያው ያቀረበው ተጨማሪ 4.8 ቢሊዮን ብር ክፍያ ድርድር ላይ ስምምነት ባለመደረሱ ግንባታው ሳይጠናቀቅ ተቋርጧል፡፡

የኢትዮ ቴሌኮም ቺፍ ፋሲሊቲና ፍሊት ኦፊሰር አቶ ዓይናለም አልበኔ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኮንትራክተሩ የሕንፃውን ግንባታ እ.ኤ.አ. ከ2016  ተጀምሮ በ2019 አጠናቆ ለማስረከብ ስምምነት የፈረመ ቢሆንም፣ ከስምምነቱ ውጪ 4.8 ቢሊዮን ብር ተጨማሪ ክፍያ በመጠየቁ ግንባታው መቋረጡን ገልጸዋል፡፡ ኮንትራክተሩ ከአጠቃላይ ዋጋ ውስጥ አሁን እየጠየቀ ያለው 20 ሚሊዮን ዶላር በመጀመሪያው ስምምነት ያልተካተተ መሆኑን አቶ ዓይናለም አስረድተዋል፡፡ በድርድሩ ምክንያት የሕንፃው ግንባታ ከአንድ ዓመት በላይ መቆሙን አስረድተዋል፡፡

ኢትዮ ቴሌኮም ስለግንባታውና በቀጣይ ምን መደረግ አለበት በሚለው ላይ ጥናት በማስደረግ ግንባታውን የጀመረው ኩባንያ ይጨርሰው? ወይስ ከኩባንያው ጋር ያለው ውል ይሰረዝ? የሚሉ አማራጮችን እያየ መሆኑን አቶ ዓይናለም ተናግረዋል፡፡

በቀጣይ ቀሪውን ሥራ ከዚሁ ኮንትራክተር ጋር ማስጨረስ የሚቻል ከሆነ በመጪው ዓመት በጀት ሊታይ የሚችልበት አማራጭ መኖሩን የጠቆሙት አቶ ዓይናለም፣ ከኩባንያው ጋር ያለው ውል የሚሰረዝ ከሆነ ግን ሕንፃው ባለመጠናቀቁ የደረሱ ኪሳራዎችን ኢትዮ ቴሌኮም ሊጠይቅ ይችላል ብለዋል፡፡

ሁለቱ አካላት ውል ተዋውለው የሕንፃውን ግንባታ ሲጀመር ኮንትራክተሩ በገባው የመጀመሪያው ውል ምንም ዓይነት ገንዘብ ለመጨመር የሚያስገድድ ሕግ ባለመኖሩ፣ መጨረስ በነበረበት ጊዜ ባለመጨረሱም ተጠያቂ ሊደረግም እንደሚችል አክለው ገልጸዋል፡፡

ይሁን እንጂ ኮንትራክተሩ ውል ከተፈረመ በኋላ በውጭ ምንዛሪ ለውጥና በገበያ ውስጥ የዋጋ ንረት በመታየቱ፣ ይህን ግምት ውስጥ በማስገባት ደረሰ የተባለውን ኪሳራ መጋራት የሚል አማራጭ እንደቀረበም ተናግረዋል፡፡ በኢትዮ ቴሌኮም በኩል ተጠንቶ የቀረበው ፕሮፖዛል በቅርብ ጊዜ ውስጥ ለኢትዮ ቴሌኮም ቦርድ ቀርቦ በሚሰጠው ውሳኔ መሠረት በመጪው ዓመት በጀት እንዲጠናቀቅ ለማድረግ እንደሚሠራ የገለጹት አቶ ዓይናለም፣ ባለፈው ዓመት በተደረገው ጥናት መሠረት መጀመሪያ ከነበረው ዋጋ በተጨማሪ ሦስት ቢሊዮን ብር ድረስ ተጨማሪ ወጪ ሊኖር ይችላል ብለዋል፡፡

ከኮንትራክተሩ ጋር ያለውን ውል ለማቋረጥ ወይም በአዲስ ኮንትራክተር ማስጨረስ በሚለው ጉዳይ ላይ ለኢትዮ ቴሌኮም ቦርድ ቀርቦ ስምምነቱን መሰረዝ የሚለው አማራጭ ላይ ከተደረሰ ግን፣ በኮንትራት ውሉ መሠረት ከኩባንያው ጋር ያለው ስምምነት ተቋርጦ ለሌላ ኩባንያ ሊሰጥ እንደሚችል ገልጸዋል፡፡

የግዙፉ ሕንፃ ድርድር የዘገየው ኢትዮ ቴሌኮም አሁን በገባበት የቴሌኮም ገበያ ውድድር ምክንያት፣ የሕንፃውን ጉዳይ ለመጨረስ በቂ ጊዜ ማግኘት ባለመቻሉና ቅድሚያ የሚሰጠው ጉዳይ በመግጠሙ ነው ተብሏል፡፡

ሰማኒያ በመቶ ግንባታ ተከናውኖለታል የተባለው ባለአሥራ አራት ወለልና አራት የተያያዙ ሕንፃዎችን የያዘው ፕሮጀክቱ ሲጠናቀቅ ከ5,000 በላይ ሠራተኞችን እንደሚችል፣ 1,500 ሰዎችን ማስተናገድ የሚችል የስብሰባ አዳራሽ እንደሚኖረው፣ ሦስት ቤዝመንቶች፣ 22 አሳንሳሰሮችና ሁለት ስካሌተሮች እንደሚገጠሙለት ለማወቅ ተችሏል፡፡

እ.ኤ.አ. በ2016 ሕንፃውን ለማስገንባት ስምምነቱ የቀድሞው የኮሙዩኒኬሽንና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ደብረ ጽዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር)፣ እንዲሁም የቀድሞው የከተማ ልማትና ኮንስትራክሽን ሚኒስትር አቶ መኩሪያ ኃይሌና የቻይናው ኮንትራክተር ሲጂኦሲ ኃላፊ በተገኙበት በተፈጸመ ፊርማ ነበር ግንባታው የተጀመረው፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች