Tuesday, September 26, 2023

ለትግራይ ክልል የአፈር ማዳበሪያ ግዥ እየተከናወነ መሆኑ ተነገረ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ምክንያት የ2015/16 የምርት ዘመን የአፈር ማዳበሪያ ግዥ ቀድሞ ሳይደርግለት ለቆየው የትግራይ ክልል፣ ግዥ እየተፈጸመ ነው ተባለ፡፡

በአሁኑ ወቅት ለትግራይ ክልል እየተገዛ ያለው የማዳበሪያ አጠቃላይ መጠን 700 ሺሕ ኩንታል ሲሆን፣ ከዚህ ውስጥ 300 ሺሕ ኩንታል የሚሆነው የኤንፒኤስ ማዳበሪያ ዓይነቶች ሲሆኑ፣ ቀሪው 400 ሺሕ ኩንታል የዩሪያ አፈር ማዳበሪያ ዓይነት መሆኑ ታውቋል፡፡

የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ ወልደ ማርያም ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ የዘንድሮ በጀት ዓመት የክልሎች የማዳበሪያ ፍላጎት ሲቀርብ በትግራይ ክልል የሕግ ማስከበር ሥራ እየተሠራ ስለነበረ በክልሉ የነበረውን መረጃ የግብርና ሚኒስቴር በወቅቱ ማግኘት አልቻለም ነበር፡፡

የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ የተጨማሪ ማዳበሪያ ግዥ በመንግሥት ግዥና ንብረት ባለሥልጣን ተፈቅዶ የዩሪያ ማዳበሪያ በውስን ጨረታ ውል ተገብቶ፣ በአሁኑ ወቅት የሌተር ኦፍ ክሬዲት ሒደት ላይ እንደሚገኝ ተጠቅሷል፡፡

በሌላ በኩል የኤንፒኤስ የአፈር ማዳበሪያ ዓይነቶችን ሲያቀርብ ከቆየው የሞሮኮው ኩባንያ ኦሲፒ አንድ መርከብ የማዳበሪያ ግዥ ለመፈጸም የሚያስችል ስምምነት የሌተር ኦፍ ክሬዲት ሒደት ላይ እንደሚገኝ አቶ ክፍሌ ገልጸዋል፡፡ ሒደቱ ሲጠናቀቅ ማዳበሪያው ተጓጉዞ እንደሚደርስ ዋና ሥራ አስፈጻሚው አክለዋል፡፡

በግዥ ሒደት ላይ ያለው የአፈር ማዳበሪያ እስኪደርስ ግን የግብርና ሚኒስቴር በግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን መጋዘኖች ከሚገኝ የማዳበሪያ ክምችት ውስጥ፣ 100 ሺሕ ኩንታል ለትግራይ ክልል እንዲሰጥ ተፈቅዶ በዚያ መሠረት ለክልሉ እየተጓጓዘ እንደሚገኝ ታውቋል፡፡

ይህ በዚህ እንዳለ የግብርና ሚኒስቴር እስከ ግንቦት 30 ቀን 2015 ዓ.ም.፣ ከ5.7 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች መሠራጨቱን አስታውቋል፡፡

የግብርና ሚኒስቴር የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦትና ሥርጭትን በተመለከተ ዓርብ ሰኔ 2 ቀን 2015 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ ከጂቡቲ ወደብ ወደ አገር ውስጥ ከገባው 6.2 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ 5.7 ሚሊዮን ኩንታል የሚሆነው ለአርሶ አደሮች መሠራጨቱን ገልጿል፡፡

በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ኢንቨስትመንትና ግብዓት ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) በሰጡት ማብራሪያ፣ ክልሎች በመጋዘን ያለውን የአፈር ማዳበሪያ ለአርሶ አደሮች በፍጥነት እንዲያሠራጩ አሳስበው፣ በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ከሁለት ሚሊዮን በላይ ተጨማሪ የአፈር ማዳበሪያ ወደ አገር ውስጥ እንደሚገባ አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል የአገሪቱን የአፈር ማዳበሪያን ግዥ በብቸኝነት የሚያከናውነውና የእርሻ መሣሪያዎችን ጨምሮ ምርጥ ዘርና አግሮ ኪሚካሎችን የሚያቀርበው የግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን፣ ተቀማጭነቱ ቼክ ሪፐብሊክ ከሆነውና ዜቶር ከተሰኘ ትራክተር አምራች ኩባንያ አስመጥቶ በከፊል የገጣጠማቸውን 75 ትራክተሮች ይፋ አድርጓል፡፡

የኮርፖሬሽኑ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ክፍሌ እንዳስታወቁት፣ ዜቶር ከተባለው ድርጅት ጋር የንግድ ስምምነት በማድረግ በከፊል ተገጣጥመው ወደ አገር ውስጥ የገቡት ትራክተሮች ሌሎች በአውሮፓ ውስጥ ከሚገኙ ትራክተር አምራቾች ጋር ተወዳድረው ለኢትዮጵያ ሥነ ምኅዳር ተስማሚ መሆናቸው ተረጋግጦ የተገዙ ናቸው፡፡

ኮርፖሬሽኑ በቀጣይ የትራክተር ክፍሉን ሙሉ ግብዓቶች ወደ አገር ውስጥ በማስገባት ገጣጥሞ ለገበያ በማቅረብ የውጭ ምንዛሪ ለማዳንና የሥራ ዕድሎችን ለመፍጠር ማቀዱን፣ ይህንንም ተጠሪ ለሆነለት የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግስ አቅርቦ ይሁንታ እንዳገኛና ከትራክተር አምራች ድርጅቱ ጋር ድርድሮች እንደተጀመሩ አስረድተዋል፡፡

ዜቶር ትራክተር አምራች ቴክኖሎጂውን ለማቅረብ ጥናት እየሠራ እንደሚገኝ፣ ጥናቱን እንዳጠናቀቀም ለመንግሥት ቀርቦ ውሳኔ ሲያገኝ ወደ ትግበራ እንደሚገባ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -