የፈረንሣይ መንግሥት በፈረንሣይ ልማት ኤጀንሲ በኩል በኢትዮጵያ ያለውን የመንግሥትና የግል አጋርነት መድረክ ለማጎልበት የሚውል የተጨማሪ 146 ሚሊዮን ብር መደበ፡፡
የተደረገው ድጋፍ በተለይም ኬር ፍራንስ፣ ኢጌት እና በኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንስቲትዩት በኩል የሴቶች ንጽሕና መጠበቂ ምርትን ለማሳደግና ለማሠራጨት የሚደረግ ድጋፍ ላይ እንደሚያተኩር ታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ 72 በመቶ የሚሆኑ ሴቶች ከወር አበባ ንጽሕና ጋር ተያያዥ በሆኑ ጉዳዮች የተደራሽነት ችግር እንዳለባቸው ይገለፃል፡፡በፈረንሣይ መንግሥት ድጋፍ የሚደረግለት ፕሮጀክት በዋናነት በኢትዮጵያ ያለውን የሴቶች የወር አበባ ንጽሕናና ጤና ዘርፍ ጥረት ለማጎልበት የሚያግዝ እንደሆነ የፈረንሣይ ልማት ኤጀንሲ ለሪፖርተር በላከው መግለጫ ገልጿል፡፡
በተለይም የወር አበባ ንጽሕና መጠበቂያ ምርትና ሥርጭት ላይ ያለውን የገበያ ትስስር፣ በተለይም የግሉን ዘርፍ ሚና በማሳደግ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ሴቶች ጥራት ያለው፣ ያልተቆራረጠና ተመጣጣኝ ዋጋ ያለው ምርት እንዲያገኙ ፕሮጀክቱ እንደሚያግዝ ተጠቅሷል፡፡
ፕሮጀክቱ ሁለት ቁልፍ ግቦችን ለማሳካት የተነደፈ ነው የተባለ ሲሆን፣ የመጀመሪያው በኤጌት ድጋፍ የግሉ ዘርፍ እድገት የሚያደናቅፉ መሰናክሎችን ለመቅረፍ የመንግሥትና የግሉ ዘርፍ የውይይት መድረክ መዘርጋት እንደሆነ ተብራርቷል።
በሁለተኛ ደረጃ በአገር ውስጥ ጥሬ ዕቃዎች የተመረቱ፣ወጪ ቆጣቢ እና ጥራት ያላቸው የሴቶች ንጽሕና መጠበቂ ምርቶችን ማሳደግ እንደሆነና ለዚህም በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የኢትዮጵያ ጨርቃ ጨርቅ ኢንስቲትዩት አስተዋፅኦ ጉልህ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የገንዘብ ድጋፍ ስምምነቱ በተደረገበት ሁነት የፈረንሣይ የልማት ኤጀንሲ ዳይሬክተሮች አንዱ አሌክሳንደር ሞሬል፣ ካንትሪ ዳይሬክተር የሆኑት ቫሌሬ ቴሂዮ እንዲሁም በኢትዮጵያና በአፍሪካ ኅብረት የፈረንሣይ አምባሳደር ሬሚ ማርሾ ታድመዋል፡፡