‹‹ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል›› የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ
‹‹ከ12 ሺሕ በላይ ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ ሆነዋል››
የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ
‹‹2.4 ሚሊዮን ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ እንጠብቃለን›› የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ
በኢዮብ ትኩዬ
በአማራ፣ በአፋርና በትግራይ ክልሎች በሰሜኑ ጦርነት ወቅት ሙሉ በሙሉና በከፊል ከወደሙ 6,942 ትምህርት ቤቶች መካካል፣ 6,688 ያህሉ ጥገና እንዳልተደረገላቸው የክልሎቹ ትምህርት ቢሮዎች ለሪፖርተር ገለጹ፡፡
የሦስቱም ትምህርት ቢሮ ኃላፊዎች ያስረዱት፣ በየክልላቸው በሚገኙ ትምህርት ቤቶች በጦርነት ወቅት ከወደሙት ትምህርት ቤቶች አብዛኛዎቹ እንዳልተጠገኑ፣ በዚህም ምክንያት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ መሆናቸውን ነው፡፡
ውድመት ከደረሰባቸው 4,068 ትምህርት ቤቶች ውስጥ 103 ያህሉ እንደ አዲስ መገንባታቸውን፣ 126 ደግሞ መጠገናቸውን፣ በአጠቃላይ 229 ትምህርት ቤቶች አዲስ ግንባታና ጥገና ቢደረግላቸውም ቀሪዎቹ 3,839 ግን ጥገና እንዳልተደረገላቸው የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድወሰን አቢ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
‹‹ይህ በየአካባቢው የተደረገውን መለስተኛ ጥገና ሳይጨምር ነው፤›› ያሉት አቶ ወንድወሰን፣ 22 በክልሉ መንግሥት፣ 45 በትምህርት ሚኒስቴር፣ ቀሪዎቹ ትምህርት ቤቶች ደግሞ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ እንደተገነቡ ገልጸዋል፡፡
በመጀመሪያና በሁለተኛው ዙር ጦርነት ብቻ 4,068 ትምህርት ቤቶች በከፊልና ሙሉ በሙሉ ውድመት እንደደረሰባቸው፣ ከእነዚህም መካከል 1,151 ሙሉ በሙሉ እንደወደሙ፣ ቀሪዎቹ 2,917 ትምህርት ቤቶች ደግሞ በከፊል ጉዳት እንደደረሰባቸውም አስረድተዋል፡፡
በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት በክልሉ ስንት ተማሪዎች ከትምህርት ገበታ ውጪ እንደሆኑ፣ የወደሙ የትምህርት ተቋማት እስከ ዛሬ ያልተጠገኑት ለምን እንደሆነ ከሪፖርተር ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡም፣ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሕፃናት ከትምህርት ገበታ ውጭ መሆናቸውን ገልጸው፣ ቀሪዎቹ ትምህርት ቤቶች ያልተገነቡት በበጀት እጥረት ምክንያት ነው ብለዋል፡፡
የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ኪሮስ ግዑሽ (ዶ/ር) በበኩላቸው ‹‹2,492 ትምህርት ቤቶች በጦርነት የወደሙ ናቸው፡፡ ገና የተለቀቀ በጀት ስለሌለ ጥገናም አልተደረገላቸውም፤›› ሲሉ ገልጸዋል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት ምን ያህል ተማሪዎች ትምህርት እንዳቋረጡ ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ፣ መጀመሪያ በጦርነቱ ትምህርት ሲቋረጥ በክልሉ 1.46 ሚሊዮን ተማሪዎች እንደነበሩ፣ አሁን በዳስ ጥላ ሥር ትምህርታቸውን እየተከታተሉ ያሉት 560 ሺሕ ተማሪዎች ብቻ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡
ለተማሪዎቹ ቁጥር መቀነስ ምክንያቱን ሲያብራሩም፣ ‹‹በምዕራብ ትግራይ 222፣ በደቡብ ትግራይ 118፣ በሰሜን ምዕራብ 90፣ በምሥራቃዊ ዞን 46፣ በማዕከላዊ ዞን 12 ትምህርት ቤቶች በአማራ ክልል ታጣቂዎችና በኤትርራ ወታደሮች ቁጥጥር ሥር በመሆናቸው ነው፤›› ብለዋል፡፡
በጦርነቱ ምክንያት በትግራይ ክልል ለሰባት ሴሚስተሮች ትምህርት ተቋርጧል ያሉት ኪሮስ (ዶ/ር)፣ ተቋማት ተገንብተው ትምህርት ሙሉ ለሙሉ ሲጀመር ከ2.4 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ እንጠብቃለን ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ዕንባ ጠባቂ ተቋም እስከ ነሐሴ 2013 ዓ.ም. ብቻ በትግራይ በጦርነቱ ሳቢያ በመምህራን ላይ የደረሰውን ሞት አደረግኩት ባለው ዳሰሳ ብቻ፣ 2,146 መምህራን እንደሞቱ መረጋገጡን የገለጹት ኃላፊው፣ ከ2013 ዓ.ም. ወዲህ በክልሉ ጦርነት ስለነበር ከዚያም በላይ መምህራን መሞታቸው ዕሙን መሆኑንና በዚህም የመምህራን እጥረት እንዳጋጠማቸው አክለው ተናግረዋል፡፡
የአፋር ክልል ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱ ሐሰን በሰሜኑ ጦርነት ወቅት 382 ትምህርት ቤቶች እንደ ወደሙና ከእነዚህም መካከል 96 ሙሉ ለሙሉ፣ 286 የሚሆኑት ደግሞ በከፊል እንደወደሙ ገልጸው፣ በተራድኦ ድርጅቶችና በክልሉ መንግሥት ጥገና ተደርጎላቸው ወደ ሥራ የገቡት 25 ትምህርት ቤቶች ብቻ ናቸው ብለዋል፡፡
በጦርነቱ ሳቢያ ከወደሙት 382 ትምህርት ቤቶች መካከል 352 ያህሉ እንዳልተጠገኑ፣ በአጠቃላይ ከደረሰው ውድመት ለማገገም ከአንድ ቢሊዮን በላይ ብር እንደሚያስፈልግ፣ ከ12 ሺሕ በላይ የሚሆኑ ተማሪዎች አሁንም ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዳልተመለሱ ገልጸዋል፡፡
ሙሉ ለሙሉ ወደሙ ከተባሉት ትምህርት ቤቶች ውስጥ አምስቱን ትምህርት ሚኒስቴር ጥገና እያደረገላቸው በመሆኑ፣ ለ2016 ዓ.ም. የትምህርት ዘመን እንዲደርሱ ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል፡፡