Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው አሠራር ወጣ ያለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት በይፋ አስጀመረ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ከተለመደው የማገበያየት ተግባሩ ወጣ ያለና በኢትዮጵያ የግብይት ታሪክ የመጀመርያ ነው የተባለውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት (Customized Forward Trade) በይፋ ጀመረ፡፡ የመጀመርያዎቹ ተገበያዮችም ባለፈው ሐሙስ ግብይት ፈጽመዋል፡፡ 

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ እስካሁን ሲያካሂደው ከነበረው አሠራር ልዩ የሆነውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት ባለፈው ሐሙስ ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ሲጀመር የመጀመርያዎቹ ተገበያዮች ሆነው የቀረቡት ሀንድ ቱ ሀንድ ቢዝነስ ኩባንያና አለባቸው ቢያዝን ባዬ የሚጠራ ድርጅት ናቸው፡፡ በዚህ የግብይት ሥርዓትም ሁለቱ ወገኖች 500 ኩንታል ደረጃ ሦስት ቀይ በነጭ ዥንጉርጉር ቦሎቄ ለመገበያየት የወደፊት ግብይት ውል ተፈራርመዋል። በሁለቱ ወገኖች መካከል የተካሄደው የወደፊት ግብይት ውል ስምምነት ሻጭ ምርቱን ወደ ምርት ገበያው መጋዘን ሳያስገባና የምርት ማረጋገጫ ሳይሰጠው ለማቅረብ፣ በገዥ በኩል ደግሞ የተስማሙበትን ግዥ ክፍያ ከውሉ ማብቂያ ከሁለት ቀናት በፊት በአቅራቢው የባንክ ሒሳብ ውስጥ ለማስገባት ተስማምተው ግብይቱ ተፈጽሟል፡፡ 

የሻጭ ሀንድ ቱ ሀንድ ቢዝነስ ኩባንያ ተወካይ የሆኑት አቶ በላይ ዘለቀ በሰጡት አስተያየት፣ ይህ ግብይት ሥርዓት የተራዘመ የግብይት ሰንሰለትን በማሳጠር ምርቱም ጥሩ ዋጋ እንዲያገኝ የሚረዳ ነው ብለዋል። በተጨማሪም የግብይት ሥርዓቱ በምርት ገበያው በኩል መመቻቸቱ የክፍያ ዋስትናን እንደሚያረጋግጥ አስታውቀዋል፡፡ 

በአዲሱ የግብይት ሥርዓት 500 ኩንታል ቦሎቄ ለመረከብ ውል የፈጸሙት አቶ አለባቸው ቢያዝን በበኩላቸው ግብይቱን የፈጸሙት ለምርቱ ጥራት ራሳቸው ኃላፊነቱን ወስደው እንደሆነና ይህም በተገበያዮች መካከል መተማመን እንደሚፈጥር ተናግረዋል። አክለውም፣ ምርት ለማግኘት ያጋጥማቸው የነበረውን ችግር እንደቀረፈላቸውና የወጭ ንግዳቸውን እንደሚያሳድግላቸው እምነታቸውን ገልጸዋል፡፡ 

ምርት ገበያው የጀመረውን አዲስ አሠራር በተመለከተ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ኮርፖሬት የኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ነፃነት ተስፋዬ፣ የግብይት ሥርዓት ዘመናዊ ግብይትን በአገሪቱ ለማሳለጥ በአማራጭነት የቀረበ መሆኑን ለሪፖርተር ገልጸዋል።

‹‹የኢትዮጵያ ምርት ገበያ እስካሁን ሲያገበያይ የነበረው ከአርሶ አደርና ከአቅራቢ የሚመጣውን ምርት በመጋዘኖቹ ተቀብሎ የምርቱን ደረጃ ካወጣ በኋላ ግብይቱ ከምርት ገበያው መጋዘን የሚፈጸም ነበር፤›› ያሉት አቶ ነፃነት አሁን ግን ምርቱ በምርት ገበያው መጋዘን ቢገባም ባይገባም ተገበያዮች በፈለጉት አማራጭና በፈለጉት ቦታ ግብይት መፈጸም የሚያስችላቸው እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ 

ለዚህም የተለያዩ አማራጮች መቀመጣቸውን ያመለከቱት አቶ ነፃነት፣ አቅራቢዎች ምርታቸውን ወደ ምርት ገበያ መጋዘን በማምጣት የምርቱ ደረጃ በኢትዮጵያ ምርት ገበያ እንዲወጣላቸው ማድረግ እንደኛው ነው ብለዋል፡፡ አቅራቢዎች በራሳቸው መንገድ የምርቱን ደረጃ መወሰን ከቻሉም ይህንኑ በማድረግ ምርቱን ወደ ምርት ገበያው መጋዘን ሳያስገቡ መገበያየት እንደሚያስችላቸውም ገልጸዋል፡፡ 

በመሆኑም ይህ የወደፊት ግብይት ሥርት ምርት ገበያው እስካሁን እንደሚያካሂደው ምርት ገበያው የግብይት መድረክ ላይ ተገኝተው የሚካሄድ ሳይሆን ሻጭና ገዥ አስቀድመው ተነጋግረው ዋጋ ተስማምተው ባሉበት ቦታ የሚፈጽሙት እንደሆነ አብራርተዋል፡፡ 

በዚህ የግብይት ሒደት ውስጥ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ሚና ግብይቱ በሕጋዊ መንገድ መካሄዱን ማረጋገጥና ማስፈጸም እንደሚሆንም ታውቋል፡፡ ሻጭና ገዥ በሚገቡት ውል መሠረት ሕጋዊ በሆነ መንገድ ግብይት መፈጸሙን ብቻ ሳይሆን በስምምነቱ መሠረት ሻጭ የተስማማበትን ክፍያ የግብይት ውሉ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ እንዲያገኝ ማስቻልም የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ኃላፊነት ይሆናል፡፡ 

‹‹አቅራቢዎችና አርሶ አደሮች በዚህ ግብይት ውስጥ ክፍያቸው በትክክል እንዲፈጸም ዋስትና የሚፈልጉ በመሆኑ ላስረከቡት ምርት ገንዘባቸውን እንዲያገኙ ማድረግ የምርት ገበያው ይሆናል፤›› ያሉት አቶ ነፃነት፣ በወደፊት ግብይት ሥርዓት ክፍያዎች ወደ ኢትዮጵያ ምርት ገበያ ገንዘቡ አስቀድሞ ከገባ በኋላ ወደ ሻጭ አካውንት እንደሚተላለፍ አስረድተዋል፡፡ ይህም ክፍያ የሚፈጸመው ገዥው ምርቱ ደርሶኛል ብሎ ለምርት ገበያው ሲያረጋግጥ ምርት ገበያው ደግሞ ገንዘቡን ወዲያውኑ ወደ ሻጭ አካውንት ገቢ በማድረግ ግብይቱን የማሳለጥ ሚና እንደሚኖረው ገልጸዋል፡፡ 

በመሆኑም በዚህ ግብይት ውስጥ ሻጩ ገንዘቡን የማግኘት ሥጋት እንዳይፈጠርበት ምርት ገበያው ዋስትና እንደሚሆነው የተናገሩት አቶ ነፃነት፣ ይህም በገዥና በሻጭ መካከል መተማመንን በመፍጠር ግብይቱን እንደሚያሳልጠው አስረድተዋል።

ክፍያው በምርት ገበያው በኩል መከናወኑ ሌላው ትልቁ ጠቀሜታ ደግሞ የገንዘብ ዝውውሩ በባንኩ በኩል የሚተላለፍ በመሆኑ ሁሉም ተገበያይ የግብር ግዴታቸውን ስለመወጣታቸው የሚያረጋግጥ አስተማማኝ ሥርዓት እንደሚፈጥር ገልጸዋል።

የተጀመረው የወደፊት ግብይት ሥርዓት ምርት ገበያው በሚያገበያያቸው ሁሉም ምርቶች ላይ ተፈጻሚ እንደሚሆን የተገለጸ ሲሆን፣ አሠራሩም ለሁሉም ተገበያይ ክፍት መሆኑ ታውቋል፡፡ በዚህ የግብይት ሒደት የምርቶች ደረጃ አወጣጥ ላይ ከምርት ገበያው ውጪ የሚከናወን መሆኑ በተለይ ወደ ውጪ የሚላክ ምርት ላይ ተፅዕኖ አያሳድርም ወይ? የሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ነፃነት ይህ ችግር አይሆንም ብለዋል፡፡ ነገር ግን እንደ ተገበያዮች ፍላጎት የምርት ደረጃው በኢትዮጵያ ምርት ገበያ በኩል መከናወን የሚችልበት ዕድል ክፍት መሆኑን፣ በራሳችን መንገድ እንጠቀማለን ካሉም ይህንኑ ማድረግ እንደሚችሉ ጠቁመዋል፡፡ በምርት ደረጃው አወጣጥና ከደረጃ በታች የመሆን ችግር ቢከሰት እንኳን ጉዳዩ የሁለቱ ተዋዋዮች ኃላፊነት እንደሆነ የገለጹት አቶ ነፃነት፣ ይህንን የግብይት መንገድ የሚመርጡ ወገኖች በምርቱ ደረጃ ላይ ተማምነው የሚገቡበት መሆኑንና ይህም በንግድ ሥርዓቱ ውስጥ መተማመንን በመፈጠር ረገድ አዎንታዊ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል። ይህ እስኪፈጠር ድረስ ደግሞ የምርት ደረጃን በምርት ገበያው በኩል የማስወጣት አማራጭ መኖሩን አስረድተዋል።

በሌላው ዓለም የወደፊት ግብይቶች የተለመዱ ናቸው ያሉት አቶ ነፃነት፣ ለፋብሪካ ውጤቶች፣ ለኢንዱስትሪ ውጤቶችና ለማዕድን ውጤቶች ሁሉ እንዲህ ያለው ግብይት ጥቅም ላይ እንደሚውል ገልጸዋል፡፡ ይህ የግብይት ሒደት በኢትዮጵያ ገና ተግባራዊ መሆን ቢጀምርም፣ የወደፊት ግብይት ሥርዓቱ ተግባራዊ መደረጉ ተገበያዮች የተሻለ ዋጋ እንዲያገኙ ዕድል የሚሰጥና በግብይት ሥርዓቱ ውስጥ መሠረታዊ ለውጥ ይዞ እንደሚመጣ ተስፋ እንደተጣለበት ገልጸዋል።

የወደፊት ግብይት ሐሙስ ዕለት የመጀመርያው የወደፊት ግብይት በዚህ ሳምንት በሁለቱ ተገበያዮች በተመሳሳይ መንገድ ለመገበያየት ኮንትራት የፈረሙና ለምርት ገበያው ያመለከቱ ተወያዮች በዚሁ መንገድ ግብይቱን ለመፈጸም መዘጋጀታቸውን አቶ ነፃነት አስታውቀዋል፡፡ የወደፊት ግብይት ሥርዓቱ በተለይ በተገበያዮች ዘንድ በእጅጉ የተደገፈ ስለመሆኑ በዚህ ግብይት ሥርዓት ለመጠቀም እያመለከቱ ያሉ ተገልጋዮች ምስክር መሆን ይችላሉ፡፡  

የመጀመርያውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ያከናወኑት ሀንድ ቱ ሀንድ ቢዝነስ ኩባንያ ተወካይ አቶ በላይ ዘለቀ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ አሠራሩ በገዥና ሻጭ መካከል የነበረውን ሰንሰለት የሚቀንስ መሆኑ አንዱ ጠቀሜታ አለው ብለዋል። ሌላው ጠቃሚ ጎኑ ደግሞ ገዥዎች ምርቱን በቀጥታ ተመልክተው ዋጋ ተደራድረው እንዲገዙ የሚያስችል ስለሚሆን ብዙ ጊዜ እንደ እሳቸው ያሉ ላኪዎች ይቸገሩበት የነበረውን አሠራር እንደሚያስቀርላቸው ተናግረዋል፡፡ 

ከዚህም በላይ ለውጭ ገበያ መቅረብ ያለበትን ምርት በቀላሉ ለማቅረብና ምርት የለም በሚል ይሰጡ የነበሩ ሰበቦችን በማስቀረቱ ረገድ ጠቀሜታ እንደሚኖረው አቶ በላይ ገልጸዋል፡፡ 

በገዥና በሻጭ መካከል የሚደረገውን ግብይት የገንዘብ ቅብብሎሽ ምርት ገበያው መሀል ላይ ሆኖ የሚያስፈጽም መሆኑ ግብይቱ መተማመን የሚፈጥር ስለመሆኑም ጠቅሰዋል፡፡ ከዚህ በፊት የሻጭና የግዥ ሠራተኛ ያከናውነው የነበረውን ግብይት ባለቤቶች በቀጥታ ከአምራችና አቅራቢዎች ጋር በመገናኘት የሚፈጽሙት ግብይት መሆኑም በዚህ መካከል ሲፈጽሙ የነበሩ ችግሮችን ያስቀራል የሚል እምነት አላቸው፡፡ 

በአጠቃላይ ይህ አሠራር ገበሬው የተሻለ ዋጋ እንዲያገኝ ለውጭ ገበያ የሚቀርበውንም ምርት ለማሳደግ የሚያስችል ምርት ለማግኘት የሚረዳ በመሆኑ አማራጭ የገበያ ዕድል መሆኑን ያስረዱት አቶ በላይ በኮንትሮባንድ መልክ የሚወጣውን ምርት በማስቀረትም የራሱ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ በተለይም ለውጭ ገበያ መቅረብ ያለበትን ምርት በመሸሸግ ይፈጸሙ የነበሩ ማጭበርበሮችን ለማስቀረት ጭምር ይህ የግብይት ሥርዓት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ስለሚኖረው ከዚህ አንፃርም አገራዊ ፋይዳው ከፍተኛ እንደሚሆን ያምናሉ፡፡ 

የመጀመርያውን ‹‹የወደፊት ግብይት›› ገዥ በመሆን የፈጸሙት የአለባቸው ቢያዝን ባዬ ድርጅት ባለቤት አቶ አለባቸው አክለው እንደገለጹት ደግሞ የወደፊት ግብይት መጀመሩ እስካሁን በአጠቃላይ የግብይት ሥርዓት ውስጥ የነበሩ ክፍተቶችን የሚያስቀር ነው፡፡ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ገቢ ዕድገት ጭምር ከፍተኛ የሆነ ለውጥ የሚያመጣ መሆኑን የገለጹት አቶ አለባቸው በኢትዮጵያ ምርት ገበያ ብቻ የተገበያየ ካልሆነ ለውጭ ገበያ ማቅረብ አይቻልም የሚለውን አሠራር የሚያስቀር ምቹና አማራጭ ገበያ የተፈጠረ መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ 

እንደ አንድ ኤክስፖርተር ‹‹የወደፊት ግብይት›› ሥርዓት መጀመር ከዚህ ቀደም ወደ ውጭ የምንልከውን ምርት የምናገኘው በምርት ገበያ በጨረታ ስናሸንፍ ብቻ ነበር ያሉት አቶ በላቸው ይህም በምንፈልገው መጠን ለውጭ ገበያ ለማቅረብ እንቅፋት ሆኖባቸው ነበር፡፡ አሁን ግን በቀላሉ ያውም በፍጥነት ምርት ያለበት ቦታ ድረስ በመሄድ ማግኘትና ለውጭ ገበያ ለማቅረብ የሚችሉትን ምርት በቀላሉ ለመግዛት በመሆኑ በእጅጉ መደሰታቸውንም ሳይጠቅሱ አላለፉም፡፡

የዚህ አማራጭ ገበያ ሥርዓት መከፈት በተለይ ከምርት ደረጃ ጋር በተያያዘ ይፈጠሩ የነበሩ ውዝግቦችን ጭምር የሚያስቀር በመሆኑ በሁሉም ወገን ተቀባይነት አግኝቶ በሰፊው ይተገበራል የሚል እምነት እንዳላቸውም በዚህ ጉዳይ ያነጋገርናቸው ሁሉ ይስማሙበታል፡፡ 

እንደ አቶ በላቸው ምልከታ ከሆነ ደግሞ ከሁሉም በላይ የወደፊት ግብይት መጀመር የወጪ ንግድ ምርቶችን በቅልጥፍና ለማካሄድ ያስችላል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም በየቦታው ያሉ ሊሸጡ ያልቻሉ ምርቶችን በቀላሉ ገዝቶ ለውጭ ገበያ ማቅረብ የሚችልበትን ዕድል መፍጠሩና ላኪዎች በምርት ገበያው የሚካሄደውን ጨረታ ብቻ እንዲጠብቁ የተገደዱበት የአሠራር ሌሎች ተገቢ ያልሆኑ አማራጮችን እንዲሞክሩ ያለማመደ በመሆኑ አዲሱ የግብይት ሥርዓት ይህንን ችግር በመፍታት ለላኪዎች መልካም ዕድል እንደሚፈጥር ዕምነታቸውን ገልጸዋል።

በውጤቱም ምርቶችን ለተራዘመ ጊዜ የማከማቸት ያልተገባ አሠራርን በመቀርፍ ምርት በወቅቱ እንዲላክና አገሪቱ ከወጪ ንግድ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ በወቅቱ እንድታገኝ ይረዳል ብለው እንደሚያምኑም አቶ አለባቸው ገልጸዋል።

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች