Sunday, September 24, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ማን ይቻለን?

በጠዋት የተሳፈርንበት ታክሲ ውስጥ በተከፈተው ሬዲዮ፣ ‹‹ይኼኛው ተራራ ያን እየጋረደው፣ የት ይታይ አካልህ ርቆ የሄደው?›› ትላለች ዘፋኟ ለዛ ባለው ድምጿ። ከሜክሲኮ ወደ ቄራ እየተሳፈርን ነው። ትዝታ የታክሲዋን የውስጥ ድባብ ለስለስ አድርጎታል። እንደ ነጠላ ገላ የምትለሰልሰው የማለዳ ፀሐይ ሙቀት በመስኮቱ እየሰረገ የሚያገኘንን ብቻ ይዳስሳል። ቀትር ከመሆኑ በፊት የጠዋት ፀሐይን ማንም ይጓጓታል። ‹‹ልጅነትና ይህች ፀሐይ ይመሳሰሉብኛል…›› ይላል አንድ ከኋላ የተቀመጠ ተሳፋሪ። ‹‹እውነት ነው ልጅነት ካለፈ አይገኝም…›› እያለ ይጨማምራል። ‹‹አሁንማ አንዴ ካለፈ ተመልሶ የሚገኝ ምን ነገር አለ? ሁሉ እያለፈን ሁሉን ስናባርር አይደል እንዴ ቀኑ መሽቶ የሚነጋው? ዕድሜስ በዛው ልክ የሚሸመጥጠው?›› ይለዋል አዲስ የገባው ተሳፋሪ። ‹‹እውነት ነው… እውነት ነው…›› ይላል መልሶ የቀደመው። አብዛኞቻችንን ባገኘነው አጋጣሚ ሁሉ በብዙ ጉዳዮች ስለሚያስተሳስረን ሕይወታችን እንጫወታለን። እየተጨዋወትን እንጓዛለን። መራራውን ስንጋፈጥ፣ ጣፋጩን ስናጣጥም ብዙ ድካምና ብዙ ዕድሜ እየከፈልን መጓዝ አይሰለቸንም። ‹‹ቢሰለቸንስ በምን ጉልበታችን ተፈጥሮ ላይ እናምፃለን?›› ይላል በውስጡ የሚያስበውን ከወዳጁ ጋር የሚጨዋወት አንድ ተሳፋሪ። ‹‹ታዲያስ እንኳን ተፈጥሮ ላይ እርስ በርሳችንም መብታችንን አስከብረን ግዴታችንን መወጣት አልቻልንም…›› ይለዋል። ረጅሙ የትዝታ ሙዚቃ እስኪገባደድ ተሳፋሪዎች ታክሲዋን እየሞሉ በጠዋቱ የሐሳብ እሳት ላይ ተጥደዋል። አዳሜ እንዳሰበው ለመዋል እየታገለ እንዳላሰበው የኖረውን ያውጠነጥናል፡፡ አሁንማ የምንጣድበት የሐሳብ ምድጃ ግለቱ የሚቻል አልሆነም፡፡ መጥኔ ያሰኛል!

የማለዳዋ ታክሲ ሞልታ ወያላው ‹‹ሳበው!›› ሲለው ሾፌሩን ምንም እንኳ ሾፌሩ የወያላውን ቁርስ በልቶ መጨረስ እየጠበቀ እንደነበር አላጣነውም። ‹‹ኤድያ ቲክቶክ እያለ በየት በኩል ሥራ ይሠራል?›› አለ አንድ ጎልማሳ የእጅ ስልኩን እየወዘወዘ። መልኩ ሰሞነኛ ጭንቀትና ሐሳብ እንዳለበት ያሳብቃል። ‹‹ከምን ተነስተህ ነው ወዳጄ?›› አለው አጠገቡ የተቀመጠ ወጣት። ‹‹ሰው ሥራ ፈታ ብዬ ነዋ፣ እርግፍ አድርጎ መሥራት ትቷል እኮ ነው የምልህ? ጭንቅላታችን አለቅጥ ፈዞ እውነትን ማየት አቃተው። ‘አፍ ሲከፈት ጭንቅላት ይታያል’ የሚባለው አባባል አሁን ‘ቲክቶክ ሲከፈት ገመና ይገለጣል’ ተብሎ ቢቀየር የህዳሴ ጉዟችን በትክክል ወዴት እንደሚያመራ ባሳየ…›› ብሎ ራሱን አወዛውዞ፣ ‹‹…ኧረ ተወኝ ወንድሜ፣ ማን እንደ ሞዴል እየተቀናጣን የምንነሳውን ፎቶ ይጠቋቆምልን?›› ብሎት በረጅሙ ተነፈሰ። ወያላው ‹‹ሾፌር›› መባሉን ስለሰማ ስለምን እንደሚወራ ለመስማትና ራሱን ከተሳፋሪዎች ‹‹ሙድ›› ጋር ለማጣመር ትኩረቱን ይሰበስባል። የቲክቶክ አፍቃሪያን ደግሞ፣ ‹‹እኛ ታዲያ በምን እንደበር? ምድረ ሙሰኛ እኛን እያራቆተ ሲደበር እኛ በቲክቶክ ካልተደበርን በምን ልንደበር ነው?›› ይባባላሉ። ዘመናዊነትና ቴክኖሎጂን ማን የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች እንዳደረጋቸው መርምረን መድረስ ከብዶናል፡፡ ወያላው ወሬው ከአቅሙ በላይ ስለመሰለው ወደ ደጅ አንጋጦ ወሬ ማየት ይዟል። ‹‹ጣልቃ ገቦች በበዙበት ዓለም ዝምተኞች የምሽት ከዋክብት ናቸው›› ያለው ማን ነበር? እንጃ!

ታክሲዋ መንገዱዋን ይዛ ፍጥነቷን ስታበረታ ወያላው ወደ ሥራው ተሰማራ። ‹‹እሺ ዝርዝር ያላችሁ እባካችሁ እየተባበራችሁኝ…›› አለ ድምፁን ከፍ አድርጎ። ‹‹እንዴ አላበዛችሁትም ግን እናንተ? የእናንተን ሥራ እኛ መሥራት አለብን?›› አሉት አንዲት ወይዘሮ። ‹‹እንደ እሱ አይደለም፣ ሃምሳና መቶ ብሮችን የምንዘረዝረው በርካታ አሥር ብሮችን ገብረን ስለሆነ ነው። እንዴት ያዋጣናል እንዲህ እየዘረዘርን ታዲያ?›› አለ ረጋ ብሎ። ‹‹አንተ እሱን ትላለህ ዶላር ከ120 ብር በላይ ሊመነዘር እየተጣደፈ አይደል እንዴ?›› አለው ከኋላ የተቀመጠ ጎልማሳ። ‹‹ታዲያ እንዴት ነው በፈንጠዚያ የምናከብርለት?›› አለው አጠገቡ የተቀመጠው ተሳፋሪ ድንገት። ‹‹ምኑን?›› አለው ጎልማሳው ግራ ተጋብቶ። ‹‹ማለቴ አንድ ዶላር በ120 ብር መዘርዘር ሲጀምር መቼም የሆነ ነገር አዘጋጅተን እንኳን ደስ አለህ ማለት ያለብን ይመስለኛል። ከዚህ ወዲያ ምን ማድረግ እንችላለን?›› ሲል የንዴት ፈገግታ ጥርሳችንን አስገለፈጠው፡፡ ‹‹እኛ እሱን እንላለን፣ ኢኮኖሚስቶቻችን ደግሞ የውጭ ምንዛሪ መጨመሩ ለአገር ውስጥ ምርት ማደግ ትልቅ ባለውለታ ነው ከማለት አልፈው፣ እንደ ጃፓን ዓይነቶችን አገሮች ይጠቁሙሃል…›› አለው ጎልማሳው በቅርቡ ያነበባትን አንዲት መጣጥፍ እየጠቀሰ። ወዲያው ደግሞ፣ ‹‹በዕውቀት የተሞሉ ኢኮኖሚስቶች ሳይሆኑ እነሱ የካድሬ የገደል ማሚቶዎች ናቸው…›› ሲል አንዱ ድንገት ሌላው ተቀብሎ፣ ‹‹እነሱማ የዓለም ባንክና የአይኤምኤፍ ደላሎች ናቸው›› አለ ትክት ባለው ድምፅ። ‹‹ማን የማን ደላላና ተላላኪ እንደሆነ እናውቃለን፡፡ እነሱ በዶላር እየጨረገዱ እኛን እንደ እሳት ለሚለበልብ ኑሮ እንደሚዳርጉንም አላጣነውም…›› ሲል ወዳጁ ብዙዎች በንዴት የቀሉ ዓይኖቻቸው እንደ እሳት ይንቀለቀሉ ነበር፡፡ ንዴት ብቻ!  

ጉዟችን እንደቀጠለ ነው። ታክሲዋ አልፎ አልፎ ለማውረድና ሰው ለማሳፈር ትቆማለች። በዚህ መሀል የሚያነጋግረን ጉዳይ አይጠፋም፡፡ አንድ ከመጨረሻ ወንበር የተቀመጠ ወጣት ድንገት ‹‹ወራጅ›!› አለና ታክሲዋ ቆመች። የቆምንበት መንገድ ዳር አጠገብ ሁለት የቤት አውቶሞቢል አሽከርካሪዎች ተጣልተው ካልተደባደብን እያሉ ነበር። አንደኛው እጁን ወደ ወገቡ ሰዶ ሽጉጥ ቢያወጣ አካባቢው በጩኸት ተደበላለቀ። ‹‹እንዴ… እንዴ… ይኼ ነው የቀረን?›› አለ አንድ ተሳፋሪ። ‹‹በስንት ትግልና መስዋዕትነት ሰላም የነበረች አገራችን መጨረሻዋ ደረሰ እንዴ?›› አለ ጎልማሳው በአደባባይ ሽጉጥ መመዘዙ አብከንክኖት። ‹‹ምን ዓይነት ከንቱ ዘመን ላይ ደረስን እባካችሁ…›› አሉ ሌላ አዛውንት። ወዲያው ፖሊስ ደርሶ ሰዎቹን ገላግሎ ወደ ጣቢያ እንዲያመሩ ሲያዛቸው ወያላው ሾፌራችንን ‹‹እንሂድ!›› ብሎ አዘዘው። ‹‹ወይ ወሬ፣ ለመሆኑ ለስንት ደቂቃ እዚህ እንደቆምን አውቀሃል?›› አለኝ አጠገቤ ያለው ተሳፋሪ። ‹‹የለም!›› አልኩት በረባ ባልረባው መንገድ ላይ እየቆምን የምናባክነው ጊዜ እየቆጨኝ። ለነገሩ መንገድ በአደገኛ ትዕይንት ተሞልቶ ቆሞ አለመታዘብ እንዴት ይቻላል ብላችሁ ነው? ያውም በእኛ ወሬ ወዳድነት? ቻይናዎቹ የአዲስ አበባ የባቡር መስመር ሥራ ፕሮጀክት ሲያጣድፉ በነበረበት ወቅት፣ የእኛ ሰው ስታዲየም ውስጥ ኳስ ጨዋታ እንደሚያይ ሲጋፋ ያዩ አንድ እናት፣ ‹‹ኧረ ወሬ በቃ!›› ቢሉ ማን ሰምቷቸው? መደማመጥ ድሮ ቀረ አትሉም!

ከመንቀሳቀሳችን በፊት ሁለት ቆነጃጅት ጉሮሮዋቸው እስኪደርቅ ተጣርተው አስቆሙንና ተሳፈሩ። ‹‹አንተ ጆሮህን ተኝተህበታል እንዴ?›› አለችው አንደኛዋ ወያላውን እየገላመጠች። ወያላው ፈገግ ብሎ እየተቅለሰለሰ ዝም አለ። ዝምታው ያበሸቃት ጠያቂ ደጅ ጀምራው የነበረውን ወሬ ለመቀጠል ተጣደፈች። ‹‹… እና ይገርምሻል ከእኔ ጋር ፍቅር እንደያዘው ነግሮኝ በአካውንቴ 500 ሺሕ ብር አያስገባልኝ መሰለሽ…›› እያለች መናገር ስትጀምር፣ ‹‹እንዴ እሱ ሙሉ የአዲስ አበባን መሬት ነው እንዴ የሸጠው…›› ስትላት ደነገጥን። ‹‹አሁን ያስገባልኝ 500 ሺሕ ብር እኮ ለመተዋወቂያ ያህል ለሽቶና ለጫማ መግዣ ብሎ እንጂ፣ ገና ምን ዓይተሽ ሀብታም አደርግሻለሁ ብሎኛል…›› ስትላት ጓደኛዋ ብቻ ሳትሆን መላው የታክሲ ተሳፋሪዎች ደነገጥን፡፡ ‹‹ዘመናዊ ልኳንዳዎች ውስጥ ባለሚኒዎችን ከጎልድ ሌብል ጋር ማወራረድ ትተው ወደ እናንተም መጡ…›› ከማለቱ አንዱ፣ ‹‹አይ አንተ እነሱ በመሬት ወረራ ከብረው ለሚፈነጩበት ንፋስ አመጣሽ ገንዘብ ምን ነዳጅ አስጨረሰህ?›› አለው አጠገቡ የተቀመጠ። ‹‹ትናንት የጫትና የድራፍት የጠረረበት ሁሉ ዛሬ ዕድሜ ለፌዴራል ሥርዓታችን አጥንቱን እየቆጠረ በሚወረው መሬት ላያችን ላይ ኑሮን ያክብድብን እንጂ ምን ይባላል…›› እያለ ሲመረር ቆንጆዎቹ ሴቶች በድንጋጤ ተውጠው እያዩት ነበር፡፡ ያስደነብራል እኮ!

መዳረሻችን እየተቃረበ ነው፡፡ ከአንዱ ርዕሰ ጉዳይ ወደ ሌላው የሚደረገው ሽግግር እየተሳለጠ ቄራ ስንቃረብ፣ ‹‹እኔ እኮ ድንቅ የሚለኝ ሌብነት እንዲህ ዓይን አውጥቶ አገር በጠራራ ፀሐይ ስትዘረፍ ምንም እንዳልተፈጠረ ዝም የሚባለው ነገር ነው…›› ሲሉ አንድ አዛውንት፣ ‹‹አይ አባታችን እኛ ምስኪኖች እኮ በየደረስንበት ከሚደርሱብን በደሎች ባልተናነሰ አገር እየተዘረፈች ነው ብለን ስንጮህ ማንም ማዳመጥ አይፈልግም…›› ብሎ አንድ ጎልማሳ መለሰላቸው፡፡ ‹‹እሱስ እውነትህን ነው፣ ሌብነት ብሔር የለውም የሚል መፈክር በግራም በቀኝም ያሰሙናል፡፡ የራሳቸው ብሔር ሰዎች ግን እስከ አንገታቸው ተነክረውበት ኧረ በሕግ አምላክ ስንል፣ እኛው ላይ ሌላ ሰሌዳ ተለጥፎብን እንደ ወንጀለኛ እንሳደዳለን…›› እያሉ በንዴት ተናገሩ፡፡ ወያላው የተጀመረውን ወግ ለማስቆም ፈልጎ ነው መሰል ወደ ሾፌሩ አንጋጦ፣ ‹‹እኔና አንተ ብቻ የሕዝብ ብሶት አዳማጭ ሆነን ቀረን አይደል… ከንጋት እስከ ምሽት ድረስ ወጪ ወራጁ እኛ ላይ ሲያላዝን ይውላል… አዳማጭ ሲያጣ ደግሞ እኛን መገላመጥና መዝለፍ ይቃጣዋል…›› እያለ አዲስ አጀንዳ ሲጀምር፣ ‹‹እናንተማ ሁሉን ችላችሁ መኖራችሁን እናውቃለን፡፡ ብሶታችንን የምንተነፍስበት ሥፍራ ጠፍቶ እኮ አንድ የቀረን ቦታ ይኸው ታክሲ ነውና እባካችሁ ቻሉን…›› ሲሉ አንዲት እናት፣ ሁላችንም በአነጋገራቸው እየተሳሳቅን ቄራ ደርሰን ‹‹መጨረሻ!›› ተብለን ተሸኘን፡፡ መልካም ጉዞ!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት