Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርበኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት አንድ ድንጋይ ደጋግሞ እንዳይመታን

በኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት አንድ ድንጋይ ደጋግሞ እንዳይመታን

ቀን:

በዘሌማስ ይሁን

ከጣሊያን ቅኝ ተገዥነት በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን በኮንፌዴሬሽን፣ ቆየት ብሎም እንደ አንድ የኢትዮያ ግዛት አካል የነበረችው ኤርትራ ከደርግ ሥርዓት መውደቅ በኋላ ነፃ አገር ሆናለች፡፡ ነፃ አገር መሆንና ከኢትዮጽያ ጋር መቀጠል በወቅቱ ብዙ ሲባልለት የነበረ ጉዳይ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ኤርትራ ዳግማዊ ሲንጋፖር የመሆን ሕልም ይዛ ጉዞ ብትጀምርም መዳረሻዋ ሕገ መንግሥት አልባ፣ የአምባገነኖች የግል ንብረት ሆና ለዜጎቿ ለኑሮ የማትመች አገር ሆናለች፡፡ ገና ከጅምሩ ወደ አገር ምሥረታ ጉዞ ስትጀምር ከእናት አገሯ የተለያየችበት መንገድ ሕግና ሥርዓትን ያልተከተለ መሆኑ ግንኙነታቸው መርህ ላይ እንዲቆም አላስቻለውም፡፡ በዚህም ምክንያት የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት ላለፉት ሃያ ዓመታት ጦርነትና ግጭት አልባ ጦርነት መለያው ሆኖ ቆይቷል፡፡ ይሁንና አገራዊ ለውጡን ተከትሎ ግጭት አልባውን የጦርነት ፍጥጫ የሚያስቆም የሰላም ብርሃን በሁለቱ አገሮች በርቶ መሬት የወረደ ግንኙነት መጀመር ችለዋል፡፡

የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ባለፉት አምስት ዓመታት በብዙ ውጣ ውረዶች ታጅቦ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡ ቅድሚያ ለጎረቤት የሚሰጠው የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ፖሊሲ ከሁሉም ጎረቤቶቻችን ጋር የጋራ ተጠቃሚነትን ማዕከል ያደረገ ግንኙነት ሊኖረን እንደሚገባ ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት ዳግም ወደኋላ እንዳይመለስ የቀደሙ ስህተቶችን ባለመድገም እንዴት ወደፊት ይጓዝ ለሚለው ወሳኝ ጥያቄ የግል ምልከታዬን እንደሚከተለው አስቀምጫለሁ፡፡

‹‹በእናት ላይ አባወራ የመሆን ትግል›› የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት ከ1983 እስከ 1990 ዓ.ም.

ድኅረ 1983 ዓ.ም. የነበረው የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ምርቅና ፍትፍት ነበር፡፡ ልጅ በእናቱ ላይ አባወራ የነበረበት የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት በወያኔና በሻዕቢያ ውስጣዊ ስምምነት ብቻ በ1985 ዓ.ም. ኤርትራ የነፃ አገርነቷን ያወጀችበት ከፈረሱ ጋሪው የቀደመበት፣ የኤርትራ የነፃ አገርነት ከመታወጁ በፊት መቅደም የነበረበት ሁለቱን አገሮች የሚለየው ድንበር ቀድሞ ሳይካለል ኤርትራ የራሷን መንግሥት እንድትመሠርት መደረጉ፣ ሻዕብያ በኢትዮጵያ ጉዳይ አያገባኝም ብሎ ኤርትራ ላይ ጊዜያዊ መንግሥት ቢመሰርትም ራሱን ከኢትዮጵያ ጥገኝነት ሊያላቅቅ ያልቻለ መንግሥት ነበር። እንዲያውም ብዙ ጊዜ በቀጥታና በተዘዋዋሪ የኢትዮጵያ ጉዳይ ውስጥ ጣልቃ በመግባት ፖለቲካዊ፣ አስተዳደራዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ውሳኔዎች ይወስን ነበር።

የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ብዙም ሳይዘልቅ እንዲበላሽ ያደረጉት ሦስት ክስተቶች እንደሆኑ የሚናገሩ አሉ፡፡ የመጀመሪያው ከ1983 ዓ.ም. በኋላ የተፈጠረው የኢኮኖሚ ሚዛን መዛባት ነው፡፡ ኤርትራ በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ለመጠቀም ያገኘችው ወሰን አልባ መብት ችግሩን እንደቀሰቀሰው ይታመናል፡፡ በወቅቱ ኤርትራ በኢትዮጵያ ላይ የከፈተችው የኢኮኖሚ ጦርነት ማሳያው የኢትዮጵያ መንግሥት አንድ የአሜሪካ ዶላር በስድስት የኢትዮጵያ ብር ሲመነዝር፣ የኤርትራ መንግሥት ደግሞ በ7.25 ብር ይመነዝር ነበር (ለማስታወስ ያህል በወቅቱ ኤርትራ የምትጠቀመው የኢትዮጵያን ብር ነበር)። ይህም ማለት ኢትዮጵያ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ (Hard Currency) የምታገኘው ኤርትራ ነበረች። በጣም የሚገርመው በመላው ዓለም የሚገኙ የኤርትራ መንግሥት ኤምባሲዎችና የኮሙዩኒቲ ማኅበራት የብር ምንዘራው ላይ ተሳታፊ መሆናቸው ነበር። ይህ ማንም አገር የማይፈቅደው፣ እንዲያውም በአንድ አገር ላይ የተደረገ የኢኮኖሚ ጦርነት ተደርጎ ነው የሚቆጠረው። በተጨማሪም በዚያን ወቅት ኤርትራ ቡና፣ ሰሊጥና ሌሎች የቅባት እህሎች ከሚልኩ አገሮች ተርታ ውስጥም ተመድባ ነበር።

ችግሩ በመጀመሪያዎቹ ሦስት ዓመታት በዝምታ የታለፈ ይመስላል፡፡ ኢሕአዴግ በአገር ውስጥ የነበረውን የፖለቲካ ችግር ለመፍታትና መንግሥትን ለማፅናት ትኩረት ሰጥቶ ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የውጭ ገበያ፣ የገንዘብ ዝውውርና የንግድ ሥርዓት እየተበላሸ ሲመጣ ግን መንግሥት መታገስ አቃተው፡፡ ችግሩን ለማቃለል የኢሕአዴግ መራሹ መንግሥት ከኤርትራ ጋር ተደጋጋሚ ውይይቶች አካሂዷል፡፡ የመጣ ለውጥ ግን አልነበረም፡፡ በመጨረሻ የአሰብ ወደብን አጠቃቀም በተመለከተ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር ውዝግብ ተጀመረ። እያረጀ የመጣውን የአሰብ ወደብ በኢትዮጵያ መንግሥት በሚሊዮኖች ዶላር በሚቆጠር የገንዘብ ፍሰት እንዲታደስ ሻዕቢያ ለኢትዮጵያ መንግሥት ትዕዛዝ መሰል ጥያቄ አቀረበ። ጥያቄው በኢትዮጵያ መንግሥት ውስጥ አከራካሪ በመሆኑና ቶሎ ምላሽ ባለመሰጠቱ፣ ሻዕቢያ የአሰብ ወደብን የሚጠቀሙ የኢትዮጵያ ነጋዴዎችን ማዋከብ ጀመረ፡፡ የዚህ ዓላማም በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ ግፊት ለመፍጠር ነበር። በኢትዮጵያ ነጋዴዎች ለኢትዮጵያ መንግሥት የሚቀርበው አቤቱታ እየበረከተ በመምጣቱ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያ ነጋዴዎች የጂቡቲን ወደብ እንደ አማራጭ እንዲጠቀሙ ፈቀደ። የነጋዴው ማኅበረሰብ የጂቡቲን ወደብ ለመጠቀም ከፍተኛ ፍላጎት አሳየ። ይህ ውሳኔ ሻዕቢያ መቼም ይሆናል ብሎ ያልጠበቀው ነበር። ኢትዮጵያ አሰብን እንደ ወደብ ካልተጠቀመች በኤርትራ ኢኮኖሚ ላይ የሚያመጣው ጫና ቁልጭ ብሎ ታየ።

ከጥቂት ጊዜያት በኋላም ሻዕቢያ የኤርትራን ሕጋዊ ብር ናቅፋን ሲያስተዋውቅ፣ ማንም ባልጠበቀው ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግሥት የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቅ ትልቅ ዕርምጃ በመውሰድ የኢትዮጵያን የብር ኖቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ በመቀየር፣ በኤርትራና በኢትዮጵያ ድንበር የሚደረጉ ግብይቶች በዶላር እንዲሆኑ ወሰነ፡፡ ይህ ያልተጠበቀ የመንግሥት ውሳኔ ብዙ ኢትዮጵውያንን ያስደመመ፣ በእናቱ ላይ አባወራ ሆኖ ለመኖር ትልቅ ሕልም የነበረው የኤርትራ መንግሥት ያልጠበቀው ዱብ ዕዳ ነው የሆነበት። በውሳኔው መሠረት ሻዕቢያ በውጭ ምንዛሪ (Hard Currency) ሊቀይረው የነበረ ኤርትራ ውስጥ ሲሠራበት የነበረ ከአራት ቢሊዮን በላይ የሆነ የኢትዮጵያ ብር ወረቀት ሆነ። ኢትዮጵያ ውስጥ ገንዘብ የመቀየሪያ የጊዜ ገደብ በማለፉ፣ ሻዕቢያ ኤርትራ ውስጥ የሚንቀሳቀሰውን የኢትዮጵያን ብር ከሕዝብ አሰባስቦ ለመቀየር አልቻለም። በተለይ የኢትዮጵያ የመገበያያ ብር መቀየርና ድንበር ላይ ግብይት በዶላር እንዲሆን መወሰን፣ የሻዕቢያ በኢትዮጵያ ላይ ፈላጭ ቆራጭ የመሆኑ ዘመን ለማብቃቱ ትልቅ ምልክት ሆነ።

የሻዕቢያ መንግሥት በአንድ በኩል በአገር ውስጥ የሕግ የበላይነት እንዲኖር የረቀቀው ሕገ መንግሥት በሥራ ላይ ይዋል፣ የዜጎች ዴሞክራሲያዊ መብት ይከበር የሚለው ግፊት ማየሉ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ለኤርትራ ሕዝብ የተገባው ኢትዮጵያን አዳክሞ ዳግማዊ ሲንጋፖርን ለመገንባት የገባውን ቃል እውን ማድረግ የሚችልበት አቅጣጫው ስለጠፋው፣ በሥልጣን ላይ ያሉት ሰዎች ብቃት የሌላቸውና ራዕይ የጎደላቸው ከመሆን አልፈው ደምና አጥንታችንን ከስክሰን ያመጣነውን ሥልጣን አሳልፈን አንሰጥም በሚል ዕሳቤ ሥልጣን ለሕዝብ ለመስጠት ስላልፈለጉ፣ የድንበር ጦርነቱን ጥሩ መደበቂያ ምሽግ አድርገው ወደ ዳግም ጦርነት ገብተዋል። ምን እንኳን የኤርትራ ባለሥልጣናት ከኢትዮጵያ ጋር ጦርነት የጀመሩበት ምክንያት ያደረ የድንበር ጉዳይ ነው ብለው በአደባባይ ቢደሰኩሩም፣ ዋናው ጥያቄ ግን በወቅቱ ከኤርትራ ሕዝብ እየደረሰባቸው ያለውን የኢኮኖሚና የሕገ መንግሥት ጉዳይ ለመቀልበስ እንደሆነ ይነገራል።

ሻዕቢያ በእናቱ ላይ አባወራ ሆኖ ፈላጭ ቆራጭ የነበረበት ፖለቲካዊም ሆኑ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች እየተገደቡ ሲመጡ፣ አገር ከመመሥረቱ በፊት መጠናቀቅ የነበረበትን የድንበር ጉዳይ መነሻ በማድረግ ግንቦት 28 ቀን 1990 ዓ.ም. ባድሜን ግጭት መቀስቀሻ አድርጎ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት እንዲጀመር አደረገ፡፡ የኢትዮ ኤርትራ ጦርነት የሁለቱን አገሮች ግንኙነት አበላሽቶ፣ መቶ ሺዎችን በሁለቱም ወገን ሰውቶ፣ በመጨረሻም ነገሩን ሁሉ ቅርቃር ውስጥ ከቶት ነው ያለፈው፡፡ በኢትዮጵያ ይኖሩ የነበሩ ኤርትራውያን ከኢትዮጵያ ወደ ኤርትራ መባረራቸውና የተባረሩበት መንገድም ኢሰብዓዊነት የተላበሰ እንደነበር አይዘነጋም፡፡ ኢትዮጵያ ተወልደው ያደጉ ኤርትራ የሚባል አገር ፈጽመው የማያውቁ ዜጎች ሳይቀሩ ‹የዓይናችሁ ቀለም አላማረንም› ተብለው ተባርረዋል፡፡ በአስመራ ከተማ ‹አምቼ› እየተባሉ የተጠሩትና በተለየ መልኩ ይታዩ የነበሩት እነዚህ ወገኖች ነበሩ፡፡ እነዚህ ሦስት ሁኔታዎች የኢትዮጵያና የኤርትራን ግንኙነት አበላሽተውት አልፈዋል፡፡  ምንም እንኳን ጦርነቱ ከአድካሚ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች በኋላ ታኅሳስ 3 ቀን 1993 ዓ.ም. የአልጀርሱ ስምምነት ተፈርሞ ቢቆምም፣ ከዚያ በኋላ የነበሩት አሥራ ሰባት ዓመታት ግን ጦርነትም ሰላምም የሌለባቸው ነበሩ፡፡ ሁለቱ አገሮች ሠራዊታቸውን ድንበር ላይ ተፋጠውና ስምምነቱም ሳይተገበር በኢትዮጵያ በ2010 ዓ.ም. አገራዊ ለውጥ ተከሰተ፡፡

‹‹አዲስ ምዕራፍ›› ድኅረ 2010 የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት 

በጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው የለውጥ መንግሥት መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. ኢትዮጵያን ማስተዳደር ከጀመረ ጀምሮ በይቅርታ እንደመር፣ በፍቅር እንሻገር በሚል መርህ አገራዊ አንድነትን ለማምጣት ከተሠሩት አስደናቂ ሥራዎች በተጨማሪ ከጎረቤት አገሮች ጋር ሰላማዊ ግንኙነትን ለማጠናከር መንግሥታቸው የአልጀርሱን ስምምነት ተግባራዊ እንደሚያደርግ በመግለጽ፣ ለኤርትራ መንግሥት ይፋዊ የሰላም ጥሪ በማቅረብ በሁለቱ አገሮች ለአሥራ ሰባት ዓመታት የነበረውን የድንበር ላይ መፋጠጥ ለማስቆም ወሰኑ፡፡ በኤርትራ መንግሥት በኩልም በአጭር ጊዜ የሰላም ጥሪው ተቀባይነት አገኘ፡፡ ከ20 ዓመታት በኋላ የኢትዮጵያና የኤርትራ የግጭት ምዕራፍ በሐምሌ 2010 ዓ.ም. መጀመሪያ የኢትዮጵያ መሪዎች፣ በሳምንቱም የኤርትራ መሪዎች በሁለቱ አገሮች ያደረጉት ጉብኝት፣ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት ወደ አዲስ ምዕራፍ መሸጋገሩን በተግባር ተገለጸ፡፡ የአውሮፕላን ትራንስፖርት መጀመር ሁለቱን አገሮች የሚያገናኙ የድንበር በሮች መከፈት፣ የኤምባሲዎች መከፈት፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት መጀመር ግንኙነቱን ይበልጥ ያጠናከሩ ክንዋኔዎች ነበሩ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይም በሁለቱ አገሮች ለሃያ ዓመታት የቆየውን የጠብ ግድግዳ በማፍረሳቸውና ለወሰዱት አስደናቂ ዕርምጃ በሥልጣን ላይ እያሉ በዓለም ከፍተኛ ክብር የሚሰጠውን የኖቤል የሰላም ሽልማት እንዲያገኙ አስችሏቸዋል፡፡ በተጨማሪም ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትና ከአገር ውስጥ ድርጅቶች ለአስደናቂው ተግባራቸው ዕውቅና ሲያገኙ፣ ከሁሉም በላይ ከኤርትራና ከኢትዮጵያ ሕዝቦች ትልቅ ምሥጋናና ክብር ተችረዋል፡፡

ይሁንና የሁለቱ አገሮች ግንኙነት እንደገና በታደሰበት ጊዜ ዲፕሎማቶችና የፖለቲካ ምሁራን የሚያነሷቸው ጥያቄዎች ነበሩ፡፡ ኤርትራ ኢትዮጵያን በተመለከተ የምትከተለው ፖሊሲ ተቀይሯል ወይ? ግንኙነቱ በምን መርህ ላይ የተመሠረተ ነው? ወደፊትስ የአልጀርሱ ስምምነት አፈጻጸም እንዴት ይሆናል? የድንበር ማካለሉ ይጠናቀቃል ወይ? የሚሉ ጥያቄዎች ይነሱ ነበር፡፡ በእርግጥ በወቅቱ የመንግሥትና የሕዝቡ ዋና ትኩረት የነበረው ተፈጥሮ የነበረውን ውጥረት ማርገብ እንደነበረ ውስጥ አዋቂዎች ሲናገሩ ተደምጧል፡፡ በወቅቱ የኢትዮጵያ መንግሥት ‹መጀመሪያ ግንኙነቱ ይመሥረትና ሌሎች ጉዳዮች በሚመለከታቸው አካላት በኩል እየተጠኑ ይተገበራሉ› የሚል አካሄድ የተከተለ ይመስላል፡፡ ይህ ግን በኤርትራ በኩል በተመሳሳይ የታመነበት አካሄድ ለመሆኑ እርግጠኛ መሆን አይቻልም፡፡ 

ኤርትራ እንደ አገር ከተመሠረተች ጀምሮ ኢትዮጵያ ላይ የምትከተለው ፖሊሲ ‹ኢትዮጵያ የጋራ፣ ኤርትራ የብቻዬ› ዓይነት ነበር፡፡ ኤርትራውያን በኢትዮጵያ ውስጥ ኢንቨስት እንዲያደርጉ ይፈለጋል፣ ይጠበቃልም፡፡ ኢትዮጵያውያን ግን በኤርትራ ኢንቨስት እንዲያደርጉ አይፈለግም፡፡ ኤርትራውያን እንደ ማንኛውም የኢትዮጵያ ዜጋ የመታየት መብት ይፈልጋሉ፡፡ በተቃራኒው ኢትዮጵያውያን ይህንን አያገኙም፡፡ ኤርትራውያን በኢትዮጵያ ያላቸውን መብት፣ ኢትዮጵያውያን በኤርትራ አያስቡትም፡፡ ኢትዮጵያ የኤርትራ የገበያና የሀብት ምንጭ ሆና እንድትኖር ይፈለጋል፡፡ ኤርትራ የኢትዮጵያ ታላቅ ወንድም ሆና እንድትኖር ይታቀዳል፡፡

እነዚህ ነገሮች እንዲሳኩ ደግሞ አንድነቷ የተጠበቀ፣ ነገር ግን ደካማ የሆነች፣ የኤርትራ ድጋፍ ሁልጊዜ የሚያስፈልጋት ኢትዮጵያ እንድትፈጠር ይታሰባል፡፡ አንድነቷ የተፈለገው ሰፊና አስተማማኝ ገበያ ለማግኘት ነው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የኢትዮጵያ ሰላም መሆን ለኤርትራ ሰላም እጅግ ተፈላጊ ነው፡፡  የኢትዮጵያ ጥንካሬ ግን ሁለት ነገሮች ሊያመጣ ይችላል ተብሎ በኤርትራ ዘንድ ይፈራል፡፡ የመጀመሪያው ከኢትዮጵያውያን ልብ ውስጥ ያልወጣውን የባህር በር ጥያቄ መልሶ ሊያመጣው እንዳይችል በኤርትራ ልሂቃን ዘንድ ሥጋት አለ፡፡ ኢትዮጵያ በሁለንተናዊ መልኩ ከተጠናከረች የኤርትራን ፍላጎት ከሚዛን በላይ ለማስተናገድ ፈቃደኛ ላትሆን ትችላለች የሚል ሥጋትም አለ፡፡ በዚህም የተነሳ በኢትዮጵያ ልሂቃን ዘንድ አሁን ያለችው ኤርትራ ታክቲካል እንጂ፣ ስትራቴጂካዊ አጋር ለመሆን አትችልም የሚል መግባባት ያለ ይመስላል፡፡ ሕወሓት የሰሜኑን ጦርነት ተደናብሮ ባይጀምር ኖሮ የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት መልክ የሚያገኝበት በቂ ጊዜ ያገኝ እንደነበር ይታመናል፡፡

ሕወሓት ከሻዕቢያ ጋር የቆየ ግንኙነት አለው፡፡ ግንኙነታቸው ግን የበላይና የበታች ስሜት የተጠናወተው ነው፡፡ የሻዕቢያ ሰዎች ራሳቸውን የሕወሓት ፈጣሪ፣ አሳዳጊና ሞግዚት አድርገው ይወስዳሉ፡፡ በትግሉ ጊዜ የነበራቸው ግንኙነትም ይህንን መሠረት ያደረገ ነበር፡፡ ኢትዮጵያ ስለኤርትራና ስለሻዕቢያ እንድታስብ የሚፈለገውን ነገር ሁሉ ሻዕቢያ ያስፈጸመው በሕወሓት በኩል ነበር፡፡ የኤርትራ ጥያቄ የቅኝ ግዛት ጥያቄ እንደሆነ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እንዲገባ የተደረገው በሕወሓት በኩል ነው፡፡ የባህር በር ጉዳይ ፈጽሞ የማይታሰብ እንደሆነ እንዲታመን የተደረገው በሕወሓት አማካይነት ነው፡፡ ኤርትራ በኢትዮጵያ ሁለንተና ላይ ከዜጋው ያላነሰ ጥቅም እንደሚኖራት ሻዕቢያ ሕወሓትን በበረሃ ዘመኑ አጥምቆታል፡፡ የደርግ ሥርዓት ወርዶ በሕወሓት የሚመራው ሥርዓት ሲዘረጋ እነዚህ አስተሳሰቦች ፖሊሲና ሕግ ሆነው የኢትዮጵያን ፖለቲካዊ መልክዓ ምድር ቀይረውታል፡፡ ሕወሓት ከሻዕቢያ ጋር ወደ ጠብ የገባውም ቀንበሩ ከሚሸከመው በላይ እየከበደበት በመምጣቱ ነበር፡፡ ያ ግጭት የኢትዮ ኤርትራን ጦርነት ወልዷል፡፡

በእርግጥ ስለአካባቢው ያጠኑ የታሪክ ምሁራን እንደሚሉት የሕወሓትና የሻዕቢያ ጠብ ከነባር የልሂቃን ጠብ የመነጨ ነው፡፡ የኤርትራና የትግራይ የአገዛዝ፣ የሃይማኖት፣ የዕውቀትና የባህል ልሂቃን ከጥንት ጀምሮ ሲቀዋወሙ ኖረዋል፡፡ የሐማሴንና የአካለ ጉዛይ ፉክክር ወደ ሻዕቢያና ሕወሓት ፉክክር ሳያድግ እንዳልቀረ ይገመታል፡፡ ሐማሴኖች አካለ ጉዛዮችን የሚያዩበት አመለካከት ሻዕቢያ ሕወሓትን ወደ የሚመለከትበት ተለውጧል ይባላል፡፡

የኢትዮጵያና የኤርትራ ግንኙነት ከአገራዊ ለውጡ በኋላ ሲሻሻል በሰከነና ያለፈውን ስህተት ሊያርም በሚችል መልኩ ግንኙቱን ለማስቀጠል የሚያስችል ዕድል አልተገኘም፡፡ የዚህ ምክንያቱ ደግሞ ሕወሓት ከማዕከላዊ መንግሥቱ ተለይቶና ራሱንም አካባቢያዊ ኃይል አድርጎ በመውጣቱ ነው፡፡ ሕወሓት በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የተፈጠረውን ግንኙነት ከመጀመሪያውም በበጎ አልተመለከተውም፡፡ ለዚህ ደግሞ ሦስት ምክንያቶች ይጠቀሳሉ፡፡ የመጀመሪያው ከጥንት ጀምሮ የነበረው የሁለቱ አካባቢዎች ልሂቃን ሽኩቻ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ ለኢትዮ ኤርትራ ጦርነት የኢትዮጵያ ተጠሪ አድርጎ ሕወሓት ራሱን በመመልከቱ ነው፡፡ ምንም እንኳን ጦርነቱ በአንድ በኩል የሕወሓት የአመራር ስህተት ውጤት ቢሆንም፣ በጦርነቱ አፈጻጸም ላይ በተሠራው ስህተት ግን ሕወሓት ራሱን የጦርነቱ ዕዳ ተሸካሚ አድርጎ እንዲከስ አድርጎታል፡፡ ከጦርነቱ በኋላ በሕወሓት አመራር መካከል የተፈጠረው ‹ህንፍሽፍሽ› ትዝታ ይህንን ቁስል እንዲያመረቅዝ ሳያደርገው አልቀረም፡፡ በእነዚህ ሁለት አስተሳሰቦች የተነሳ ሕወሓት ‹ሻዕቢያ የፌዴራል መንግሥቱን ተጠቅሞ ያጠቃኛል› የሚል ፍርኃት እንዲያድርበት አድርጎታል፡፡ ይህ ደግሞ ሦስተኛው ምክንያት ነው፡፡ 

‹‹ዝምድና ሳይፀና ወደ ፈተና›› በሰሜኑ ጦርነት ጊዜ የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት

ሕወሃት ራሱ በፈጠረው ሥጋት ራሱን እያስፈራራ ለሁለት ዓመታት ቆየ፡፡ ከፌዴራል መንግሥቱ በተደጋጋሚ የቀረበለትን የሰላም ጥሪ አሻፈረኝ አለ፡፡ በፌዴራል ፖሊስና በመከላከያ ውስጥ የነበሩ የአካባቢውን ተወላጆች ሰብስቦ ሌላ ‹መከላከያ ኃይል› መገንባት ጀመረ፡፡ ዘመን ቢለወጥም ተቸክሎ መቅረት ልማዱ የሆነው ሕወሓት፣ እንደ 1983 ዓ.ም. ሁሉ ከትግራይ ወደ አዲስ አበባ ለመምጣት ከ30 ዓመታት በኋላ እንደገና ጦርነት ከፈተ፡፡ ሰሜን ዕዝን ጥቅምት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. አጠቃ፡፡ በመቀጠልም በኤርትራ ላይ በተከታታይ ሮኬት ማስወንጨፍ ጀመረ፡፡ በአንድ ጊዜም ከሁለት ኃይሎች ጋር ጦርነት ገጠመ፡፡ ዓለም አድናቆቱን በሽልማት ያፀናው የኢትዮ ኤርትራ የአዲስ ምዕራፍ ግንኙነት በቀዳሚነት ሰላምና ቅርርብን በማስቀደም ወደ መደበኛ ባለዘርፈ ብዙ የዲፕሎማሲ ምዕራፍ ለመሸጋገር ዳዴ እያለ ባለበት፣ ግንኙነቱን የሚፈትኑ ጉዳዮች ከሚዲያ ዘመቻ ተሻግረው ወደ ተግባራዊ ጥቃት እንዲያመሩ ሆነው ዝምድና ሳይፀና ዳግም ወደ ፈተና የሁለቱ አገሮች ግንኙነት እንዲገባ ተደረገ፡፡

ሕወሓት እዚህ ላይ ሁለት ስህተቶች ሠራ፡፡ በአንድ በኩል ከ20 ዓመታት በላይ በኢትዮ ኤርትራ ድንበር ሲጠብቀው የነበረውን የሰሜን ዕዝን አጠቃ፡፡ ይህንን ሲያደርግ ድንበር ላይ ማን እንዲጠብቀው እንደፈለገ ፈጣሪ ነው የሚያውቀው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአንድ ጊዜ ከሁለት ኃይሎች ጋር ተጋጨ፡፡ ግጭቱ ከሁለት ኃይሎች ጋር መሆኑ ብቻ አይደለም፡፡ ከሁለት አገሮች የመከላከያ ሠራዊት ጋር መሆኑ ነው ትልቅ የፖለቲካ ሂሳብ ስህተት የሚያደርገው፡፡

የኤርትራ ጦር በተደጋጋሚ የተሰነዘረበትን ጥቃት ለመመከት ወደ ትግራይ ገባ፡፡ ‹በራቸውን ከፍተው እየሄዱ ሰው ሌባ ይላሉ› ነው ነገሩ፡፡ ይህ ጦር ወደ ትግራይ ሲገባ እነዚያን የቆዩ የትግራይና የኤርትራ ልሂቃን የሻከሩ አመለካከቶች ይዞ እንደሚገባ ጥርጥር አልነበረውም፡፡ በኢትዮ ኤርትራ ጦርነት ጊዜ የኢትዮጵያ ጦር ወደ ኤርትራ ሲገባ አያሌ የትግራይ ሰዎች ወደ ኤርትራ ገብተው እንዲዘርፉ ተፈቅዶላቸው ነበር ይባላል፡፡ በወቅቱ የነበሩ የመከላከያ ሠራዊት አመራሮችና አባላት ቢቃወሙትም የፖለቲካ አመራሩ ግን ዝርፊያውን ተቀብሎ አስፈጽሞታል፡፡ እስከ 80 ኪሎ ሜትር ድረስ ዘልቀው የገቡ የትግራይ ሰዎች የጣራ ቆርቆሮና የማድቤት ጭልፋ ሳይቀር ይዘው እንደመጡ ከተከዜ ወዲህና ወዲያ በሚኖረው ሕዝብ ውስጥ ትዝታው አልጠፋም፡፡ ይህንን ቂም ሕወሓት ያውቃል፡፡ ይህንን እያወቀ የኤርትራን ጦር እየተነኮሰ መጋበዝ አልነበረበትም፡፡ ጂኒውን ስትጠራው መመለሻውን ድግምት መያዝህን ማረጋገጥ አለብህ፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት በሁለት ምክንያቶች የኤርትራን ጦር መግባት በዝምታ ሳያየው አልቀረም፡፡ በአንድ በኩል ሰሜን ዕዝ በገዛ ወገኖቹ ተመትቷል፡፡ ድንበሩን የሚጠብቀው የለም፡፡ ወደ አስመራም የሕወሓት ሮኬቶች እየተተኮሱ ነው፡፡ የኤርትራን ጦር አትግባ ማለት ከንግግር ያለፈ ትርጉም አይኖረውም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የኢትዮጵያ ወታደሮች ከሕወሓት ታጣቂዎች አምልጠው መግባት የቻሉት ወደ ኤርትራ ምድር ነው፡፡ በወቅቱ በሕወሃት የተካደው ሰሜን ዕዝ ከኤርትራ የቀረበ ወዳጅ አልነበረውም፡፡ ቢያንስ ሁለቱንም የሚመታ አንድ የጋራ ጠላት ተፈጥሯል፡፡ የኤርትራ መንግሥትና ሕዝብ ተገቢውን ወንድማዊ ድጋፍ አድርገው ተቀብለዋቸዋል፡፡ እንደገና ተደራጅተው ሕወሓትን ለመዋጋት የኤርትራን መሬት እንደ መነሻ ከመጠቀም የተሻለ አማራጭ ለኢትዮጵያ ሠራዊት አባላት አልነበራቸውም፡፡ ስለዚህም የኢትዮጵያ ወታደሮች በጦርነት እየገፉ ወደ መሀል ትግራይ ሲገቡ ከኋላ የኤርትራ ወታደሮች መከተላቸው አይቀሬ ነበር፡፡ ለዘመናት በደቡብ በኩል እረፍት ያሳጣቸውን ሕወሓትን ለማዳከም፣ ከቻሉም ለማስወገድ ይህንን አጋጣሚ የኤርትራ ሰዎች ሳይጠቀሙበት አልቀሩም፡፡ ይህ ደግሞ የስትራቴጂ ሀሁ ነው፡፡

የኤርትራ ሠራዊት ወደ ትግራይ ምድር በገባ ጊዜ የፈጸማቸው ጥፋቶች መኖራቸው ምንም ጥርጥር አይኖረውም፡፡ እንዲያውም በጠቅላላው ጦርነት ያለ ጥፋት የሚከናወንም አይደለም፡፡ ዋናው ነገር ጥፋቱን ለመከላከልና በኋላም ተጠያቂነት ለማምጣት የሚኬድበት ርቀት እንጂ፡፡ የኤርትራ ጦር ሲገባ የቆየውን ቂም ይበቀላል፣ ሕወሓት ዳግም አቅም አግኝቶ ችግር እንዳይሆንበት ማዳከም ይፈልጋል፡፡ የሁለቱ አካባቢዎች ልሂቃን ፉክክር በኤርትራ ልሂቃን አሸናፊነት እንዲጠናቀቅም ይፈልጋል፡፡ በዚህ ሒደት ጥፋት ይፈጸማል፡፡ በእርግጥ የኢትዮጵያ መንግሥት ለምን ዕዳውን ወሰደ? የሚለው በሚገባ ሊፈተሽ የሚገባ ጥያቄ ይመስለኛል፡፡

ከሕወሓት ጋር በተደረገው ጦርነት ጥፋት የፈጸሙ የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አባላት ተከሰው ተፈርዶባቸዋል፡፡ የትግራይ ሕዝብም የመከላከያ ሠራዊት አባላትን በተመለከተ በአብዛኛው የሚያነሳው በበጎ ነው፡፡ በትግራይ የተፈጸሙት አብዛኞቹ የሕግ ጥሰቶች በኤርትራ ወታደሮች እንደተፈጸሙ ይታወቃል፡፡ ይህንንም በአካባቢው ጥናት ያደረጉ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ሪፖርቶች ጭምር አረጋግጠውታል፡፡ ታዲያ የኢትዮጵያ መንግሥት የኤርትራ ወታደሮች ወደ አካባቢው መግባታቸውን ከማረጋገጥ ባሻገር ጥፋቶቹን በይፋ ለምን አልተናገረም?

ለዚህ የተለያዩ ግምቶች ይቀመጣሉ፡፡ የመጀመሪያው የኤርትራ ወታደሮች ገብተው የፈጸሙትን ጥፋት የኢትዮጵያ መንግሥት መናገር ከጀመረ፣ ከኤርትራ ጋር የሚኖረው ግንኙነት ሊበላሽ ይችላል ብሎ በማሰቡ ይሆናል፡፡  በሌላ በኩል ደግሞ ጦርነቱን በአሸናፊነት ከመቋጨቱ በፊት እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን ማንሳት ታክቲካል አጋርነቱን ይጎዳዋል ብሎ አስቦም ይሆናል፡፡ ነገር ግን እንደ እኔ ግምት መንግሥት ለዘላቂ በሚሆነው ስትራቴጂ እንጂ በጊዜያዊ ታክቲክ ላይ ተመሥርቶ ገጽታውንም፣ ፖለቲካውንም፣ ዲፕሎማሲውንም መጉዳት ያለበት አይመስለኝም፡፡ ከዚህ በላይ ዕዳ ተሸካሚ ሆኖ መቀጠልም የለበትም፡፡ የትግራይ ሕዝብ በጦርነቱ ዋጋ ከፍሏል፡፡ ዋጋ ያስከፈለውም የሕወሓት አመራር ነው፡፡ የሕወሓት አመራር ጉዳይ በሽግግር ፍትሕ ጊዜ ሊታይ ይችል ይሆናል፡፡ የሕዝቡ ጉዳት ግን ዛሬ መጠገን አለበት፡፡ ነገሩ ከዘላቂ የኢትዮጵያ አንድነት አንፃር ሊታይም ይገባዋል፡፡

‹‹ለጋራ ጥቅም ወይስ ለተናጠል›› ቀጣይ የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት

የሰሜኑ ጦርነት የኢትዮጵያን የግዛት አንድነት ባስጠበቀ መንገድ በሰላም ስምምነት ተጠናቆ  ሕወሓትም ከጥጋቡና ከማይጨበጠው ቅዠቱ ነቅቶ ትግራይ በጊዚያዊ አስተዳደር እየተዳደረች ወደ መልሶ ግንባታ ገብታለች፡፡ ነገር ግን ጦርነቱ በዚህ መልኩ በሰላም በመቋጨቱ የኤርትራ መንግሥት ደስተኛ ይሆናል ብዬ አላምንም፡፡ ምክንያቱም  የኤርትራ መንግሥት ጦርነቱ ሕወሓትን እንዲያጠፋለት ብቻ ሳይሆን፣ በውስጠ ታዋቂነት ኢትዮጵያንም እንዲያዳክምለት እንደሚፈልግ ስለማምን ነው፡፡ በዚህም ምክንያት የተራዘመ ጦርነት ከኢትዮጵያ ይልቅ ለኤርትራ መንግሥት ይበልጥ ሁለንተናዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡

የፌዴራል መንግሥት ከሕወሓት ጋር ባደረገው ጦርነት የኤርትራ መንግሥት እንደደገፈው ይታወቃል፡፡ የዚህ ድጋፍ ዓላማ የኢትዮጵያን ጥቅም ማስከበር አልነበረም፡፡ ሻዕቢያ በአካባቢው ያለውን የበላይነት ማስከበርና ኢትዮጵያን እግረ መንገድ ማዳከም እንጂ፡፡ ለዚህም እንደ ማሳያነት የኤርትራ መንግሥት በአንድ በኩል ሕወሓትን እየተዋጋ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ኦነግ ሸኔን ኢትዮጵያን እንዲያተራምስ ሲደግፍ እንደነበር በአንድ ወቅት አንድ ከፍተኛ የፌዴራል መንግሥት ባለሥልጣን ሲናገሩ ሰምቻለሁ፡፡ ይህን በወዳጅነት ስም የሚደረግ ሸፍጥ እንዲያቆሙ በፌዴራል መንግሥት በኩል በተደጋጋሚ ሲነገራቸውም ‹እናጣራለን› የሚል መልስ ብቻ በመስጠት ጉዳዩን ያድበሰብሱ እንደነበር ከፍተኛ አመራሩ ነግረውኛል፡፡ በመሆኑም የሻዕቢያን በወዳጅነት ማር የተለወሰው መርዝ የተቀላቀለበት ስትራቴጂ ዓላማው ምንድነው ካልን? አንደኛው ሕወሓትን የሚወጉት ታሪካዊ ተቀናቃኛቸውን በማጥፋት በአካባቢው የበላይነትን ለማስከበር ሲሆን፣ ሁለተኛው ሸኔን የሚደግፉት ደግሞ ቋሚ ዓላማቸው የሆነውን ለኤርትራ ሥጋት የማትሆን ደካማዋን ኢትዮጵያን ለመፍጠር በማሰብ ነበር፡፡

በመሆኑም በጦርነቱ ሻዕቢያ ዓላማውን ባለማሳካቱ የተፈጠረውን የሰላም ስምምነት ለማጨናገፍ እንደሚሠራ የሚጠበቅ ነው፡፡ እንደ እኔ ግምት ሻዕቢያ በቀጣይነት አራት ዓይነት አካሄዶች በኢትዮጵያ ላይ የሚከተል ይመስለኛል፡፡ ሁኔታዎችም የሚጠቁሙት ይህንኑ ነው፡፡ የመጀመሪያው የተለያዩ ኃይሎችን መጠቀም ነው፡፡ ጥንት ሻዕቢያ ሕወሓትን ይዞ ኢትዮጵያን ለማዳከም እንደሠራው ሁሉ፣ አሁን ደግሞ የተለያዩ ኃይሎችን ይዞ መሥራቱ አይቀርም፡፡ ለዚህ ደግሞ በቅርብ ያሉትን የአፋርና የአማራ ክልልን አንዳንድ ነውጠኛ ኃይሎች ይጠቀማል፡፡ እነዚህ ያኮረፉ ኃይሎች የመሣሪያና የፕሮፓጋንዳ ድጋፍ ከሻዕቢያ ሊያገኙ ይችላሉ፡፡ እነርሱም በተቃራኒው ፌዴራል መንግሥትን በማወክ ብድራቸውን ይመልሳሉ፡፡

በሁለተኛ ደረጃ ይህንን የሚያግዝ የሚዲያ ጦርነት መክፈት ለሻዕቢያ ከጥንት እስከ ዛሬ የተካነበት ነው፡፡ ጥንት ከኤርትራ ጋር ጡት የተጣቡ አካላት ዛሬ ዛሬ ፊታቸውን በለውጡ መንግሥት ላይ አዙረው በአፍራሽ ፕሮፓጋንዳ ላይ እንዲጠመዱ የተደረጉት ለዚህ ሳይሆን አይቀርም፡፡ የኤርትራ የነፃነት ቀን ሲከበር ከፕሬዚዳንቷ በፊት የደስታ መልእክት ያስተላለፉት እነዚህ የአስመራ ቀለብተኞች ነበሩ፡፡ በተጨማሪም በአማራ ክልል በጽንፈኞች እዚህም እዚያም በቁጥ ቁጥ ጀምረነዋል ለሚሉት የትጥቅ ትግል ትልቁን የሚዲያ ቅስቀሳ የሚያደርጉት፣ እነዚሁ ወደ ቀደመው ባንዳነታቸው የተመለሱ የእናት ጡት ነካሾች ናቸው፡፡ በሙሉ አቅማቸው ጥላቻዎችን በመስበክ ሕዝብን ከሕዝብ በማጫረስ የሻዕቢያ የመጨረሻ ሕልም የሆነውን በኢትዮጵያ ፍርስራሽ ላይ ታላቋን ኤርትራ የመገንባት የቀደመ ሕልም፣ በአዲስ ስትራቴጂ እንዲሳካ የሙሉ ጊዜ ሥራቸውን አድርገው እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ የእነዚህ ባንዳ ቀለብተኞችን ሰሞናዊ ሁኔታ በአትኩሮት ለተመለከተው ዘመናዊ ባንዳነት ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ መታዘብ ይችላል፡፡ በእናት አገር ላይ በዚህ ደረጃ ክህደት ምንም ዓይነት የአገር ፍቅር ማስተባበያ ሳይሆን፣ ከደም የተቃባ የማይጠረቃ የንዋይ ፍቅርን ፍንትው አድርጎ አሳይቶናል፡፡ ታሪክና ሰፊው ሕዝብም ፍርድ እንዲሰጥ እኛም መዝግበናል፡፡ 

ከሰሞኑ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ወደ ቤጂንግና ሩሲያ አምርተው ነበር፡፡ ይህ ጉዞ ኤርትራውያንን ካስደሰተው በላይ የኢትዮጵያን ነውጠኞች አስደስቷል፡፡ ለአንድ መሪ የሚደረገው አቀባበል በተቀባዩ አገር ፕሮቶኮል ብቻ ሳይሆን፣ በጎብኚው መሪ ፍላጎትም ጭምር የሚደረግ ነው፡፡ በቅርቡ ወደ ኢትዮጵያ የመጡት የጀርመኑ ቻንስለር አቀባበል ቀዝቀዝ ያለው በራሳቸው በመሪው ፍላጎት ነበር፡፡ ይህ እየታወቀ የኢትዮጵያ ነውጠኞች ግን የፕሬዚዳንት ኢሳያስን ጉብኝት የክብር መጨረሻ አድርገው ለማሳየት የፈለጉት ለሌላ ተልዕኮ ነበር፡፡

በሦስተኛ ደረጃ ደግሞ ሰርጎ ገብነትን ኢትዮጵያን እንደ ማተራመሻ መንገድ ሊጠቀሙበትም ይችላሉ፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል በተከፈተው የዲፕሎማሲ ግንኙነት የተነሳ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱ ጨምሯል፡፡ በተለይም ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ሰዎች ቁጥር ከዕለት ዕለት እያሻቀበ ይገኛል፡፡ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ፣ ከኢትዮጵያ ውጭ የሚኖሩ ኤርትራውያን ቁጥርም ከፍ እያለ ነው፡፡ ይህ የሚበረታታና የሁለቱንም ሕዝቦች አብሮነት የሚያጠናክር ነው፡፡ እነዚህን አጋጣሚዎች ግን ለሰርጎ ገቦች የመጠቀም ልማድ ከጥንትም ያለ የሻዕቢያ ልማድ ነው፡፡ በቀጣይም መጠቀሙ አይቀሬ መሆኑ የሚታዩ ምልክቶች አሉ፡፡

የሻዕቢያ ሰዎች አሁንም ቅድመ 1990 ዓ.ም. የነበረውን ኢኮኖሚውን የመቆጣጠር ሁኔታ ለመድገም ይፈልጋሉ፡፡ በዚህም ምክንያት በሕገወጥ የሰዎችና የገንዘብ ዝውውር እየተሰማሩ መሆኑን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ ሌላው ቀርቶ በጎዳና ላይ ንግድ ሳይቀር መሰማራት ጀምረዋል፡፡ በመጠጥ ቤቶችና በአልኮል ንግድ ለመዘፈቅ ዳር ዳር እያሉ ነው፡፡ በአዲስ አበባ የኑሮ መወደድ በተለይም የኮንዶሚኒየም ቤቶች ኪራይ ዋጋ መወደድ ዋነኛ ምክንያት ኤርትራዊያን እንደሆኑ ነዋሪዎች በምሬት የሚያነሱት ጉዳይ ከሆነ ውሎ አድሯል፡፡ በተጨማሪም በመዲናዋ እየተስፋፋ ለመጣው የደረቅ ወንጀል ዋና ተዋናይ ኤርትራዊያኑ እየሆኑ እንደመጡ የፖሊስ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡ በመሆኑም መንግሥት ይህንን ሥርዓተ አልበኝነት ሥርዓት ማስያዝ ካልቻለ ከተሞቻችን የሰርጎ ገቦች መፈንጫ የመሆን ዕድላቸው ከፍተኛ እንዲሆን ያደርገዋል፡፡

አራተኛውና ፍንጩን እያሳየ የመጣው ዳያስፖራውን በመንግሥት ላይ ማነሳሳት ነው፡፡ ከኤርትራ ጋር ጡት በተጣቡ አካላት አማካይነት ዳያስፖራውን በገዛ አገሩ ላይ ለማሳመፅ መሥራታቸው አይቀርም፡፡ በኢትዮጵያ ላይ የሚደረገውን አመፅ የሚመሩ ኃይሎችን የኋላ ታሪክ ካየነው የአስመራ ትዝታ ያለባቸው ናቸው፡፡ አስገራሚው ጉዳይ በሠለጠነ አገር እየኖሩ በዓለም ከዘመናዊነትም ሆነ ከሥርዓተ መንግሥትም በእጅጉ ወደኋላ ከቀረች አገር፣ ለኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ መንግሥት ለማምጣት በጋራ የሚሠሩ በአገር ፍቅር ስም የተወሸቁ አገር ጠሎች በዚህ ዘመን መኖራቸው ነው፡፡ የሚጋጩ ሕልሞች ማለት ይህንን ነው፡፡

የሻዕቢያ መንግሥት ባለፉት ሃያ ዓመታት በኢትዮጵያ የተወሰደበትን የቀጣናው የበላይነት ለማስመለስ አሁን ላይ የሞት የሽረት ትግል እያደረገ ነው፡፡ ይህ ሕልሙ ወደ ተግባር ሊቀየር የሚችለው ደግሞ ሰላም የራቃት፣ በጦርነት አዙሪት የምትናውዝና አስመራ ቁጭ ብለው በሪሞት የሚያንቀሳቅሷት ኢትዮጵያን መፍጠር ሲችሉ ብቻ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ወደ ዘላቂ ሰላምና ወደ መደበኛ የልማት ተግባሮቿ እንድትመለስ አይፈልጉም፡፡ ይህንን ሕልማቸውን ለማሳካትም የውስጥ ባንዳዎችን በሙሉ አቅማቸው ይደግፋሉ፡፡ በሁሉም የኢትዮጵያ ክፍል ጭስ ባዩበት ቦታ ሁሉ ነዳጅ ለማርከፍከፍ ይሽቀዳደማሉ፡፡ ትግል ሲጀምሩ ዓላማቸው ያደረጉትን ‹‹ኤርትራ እስክትለማ ኢትዮጵያ ትድማ›› የሚለውን መርሐቸውን አልቀየሩም፣ ሰዎቹም አልተቀየሩም፡፡ ዕሳቤያቸውም አልተቀየረም፡፡ ሁሉም ነገር እንደ ነበረ ነው፡፡

ባለበት ከሚረግጥ መንግሥት ጋር በዘመኑ የዲፕሎማሲ ቋንቋ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ግንኙነት ይኑረን ማለት ቅቡልነት አይኖረውም፡፡ ለምን ቢባል ዓለም ላይ ብዙ ነባራዊ ሁኔታዎች ቢቀያየሩም በኤርትራ ግን መሪዎቹ አልተቀየሩም፣ አቋማቸውም እንደዚያው ባለበት ነው፡፡ በዚህ ምክንያት በትብብርና በፉክክር ሚዛን በእኩልነት ላይ የተመሠረተ ሀቀኛ ወዳጅነት ከኤርትራ መንግሥት ጋር መመሥረት ፈታኝ ይሆናል፡፡

‹‹የጋራ ተጠቃሚነትን›› ማዕከል ያደረገ አዲሱ የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት እንዴት?

የትኛውም አገር ከሌላ አገር ጋር የሚኖረው ግንኙነት የጋራ ተጠቃሚነትን ማዕከል ያደረገ መሆን እንዳለበት የዓለም አቀፍ የውጭ ግንኙነት መርህ ነው፡፡ የኢትዮጵያም የውጭ ግንኙነት ቅድሚያ ለጎረቤት ይሰጣል፡፡ ሁሉም ዓይነት የኢትዮጵያ መንግሥት የውጭ ግንኙነቶች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም ማስጠበቅ ቅድሚያ መስጠት እንዳለበትም ያስቀምጣል፡፡ በመሆኑም መንግሥት ከኤርትራ መንግሥት ጋር የሚኖረው ቀጣይ ግንኙነት ማዕቀፎቹ የጋራ ተጠቃሚነትና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጥቅሞችን ማስከበር ማዕከሉ ሊያደርጉ ይገባል፡፡ ከኤርትራ መንግሥት ተፈጥሯዊ ሥሪት አንፃር እነዚህን ጉዳዮች ለማሳካት ፈታኝ ቢሆንም፣ ኢትዮጵያ ምንጊዜም ወዳጅ አገሮችን ማበራከት እንጂ ጠላት የማብዛት መርህ ስለሌላት ፈተናዎችን በድል በመሻገር፣ የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ እንዲመሠረት በልዩ ትኩረት መንግሥት ሊሠራበት እንደሚገባ አምናለሁ፡፡

በ‹በጋራ ክብር፣ ለጋራ ተጠቃሚነት› መሆን አለበት መርሐችን ሲባል ከኤርትራ ጋር ሰላማዊ፣ ፍትሐዊና በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ወዳጅነት ሊኖረን ይገባል ማለት ነው፡፡ በምንም መልኩ ጠላትነትን የሚያመጡና ግጭትን የሚቀሰቅሱ ነገሮችን ማራቅ ያስፈልጋል፡፡ ከጋራ ተጠቃሚነት መርህ ያፈነገጡ ጣልቃ ገብነቶች ሊኖሩ አይገባም፡፡ ለኢትዮጵያ ከኤርትራ፣ ለኤርትራም ከኢትዮጵያ የተሻለና የቀረበ ጎረቤት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ ከሁሉም ጎረቤት አገሮቻችን ውስጥ የኤርትራን ያህል በባህል፣ በእምነት፣ በታሪክና አብሮ በመኖር የሚቀርበን የለም፡፡ የኤርትራ መንግሥት ግንኙነት ከፌዴራሉ መንግሥት ጋር ብቻ  መሆን ይገባዋል፡፡ አካባቢያዊ ውሽማ አያስፈልግም፡፡

ባህላዊና ማኅበራዊ ግንኙነቶች የጋራ ክብርን ለሁለቱም ሕዝቦች የሚያመጡ መሆን አለባቸው፡፡ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ግንኙነቶችም የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረጉ እንዲሆኑ ይጠበቃል፡፡ በሰሜኑ ጦርነት ጊዜ የኤርትራ ኃይሎች የፈጸሟቸው ጥፋቶች  በሚዛናቸው ተጠያቂነት ሊረጋገጥባቸው ይገባል፡፡ አሁን እየሆነ እንዳለው አጠቃላይ ዕዳውን የፌዴራል መንግሥቱ እየተጠየቀና ቀንበር እየተሸከመ መቀጠል የለበትም፡፡ ምክንያቱም ይህ አካሄድ የጋራ ክብርን አያመጣም፣ የጋራ ተጠቃሚነትን መርህ አያስጠብቅም፡፡ የጥፋቱ መሸፈን ለኤርትራ ክብር ሊሆን ይችላል፡፡ ለኢትዮጵያ ግን ሸክም ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር የሚኖራት ግንኙነትም በግልጽ የፖለቲካና የኢኮኖሚ መርሆች ላይ የተመሠረተ፣ ግልጽ ግብ ያለውና የሁለቱን አገሮች የጋራ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጥ መሆን ይገባዋል፡፡

የሁለቱን አገሮች ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ለመምራት ያደሩ የቤት ሥራዎች በሁለቱም በኩል በእኩል ኃላፊነት መቋጨት ይገባቸዋል፡፡ በዋነኝነትም  የተወረሱ ንብረቶች፣ የጠፉ ሰዎችና የድንበር ጉዳይን የኢትዮጵያ መንግሥት ከኢሕአዴግ ጊዜ ጀምሮ የኤርትራውያንን ንብረት አስመላሽ ብሔራዊ ኮሚቴ አቋቁሞ ሰፊ ርቀት ሄዷል። በኤርትራ በኩል እንኳን ንብረት ሊመልሱ በባንክ የነበረውን የኢትዮጵያውያንን ገንዘብ ለመመለስ አልፈቀዱም፡፡ ባለሥልጣኖቻቸው በግፍ ቀምተው የሚኖሩባቸውን የግል፣ የንግድና የመኖሪያ ቤቶችን የመመለስ ፍላጎት አያሳዩም። በመሆኑም የፌዴራል መንግሥት በልዩ ትኩረት ይህ ጉዳይ ምላሽ እንዲያገኝ ሊሠራ ይገባል፡፡

በተጨማሪም ከደርግ ጋር በነበረው ጦርነት ጊዜ በኤርትራ የቀሩ ሰዎች ጉዳይ ምን ደረሰ? በኢትዮጵያ በኩል የጠፉ ካሉም የት ሄዱ? ሁለቱም አገሮች ሊመልሱ ይገባቸዋል፡፡ የእነዚያ ሰዎች ልጆችና ቤተሰቦች ዛሬም ይጠይቃሉ፡፡ ግንኙነቱ የሰመረና ከዕዳ የተላቀቀ እንዲሆን የእነዚህ ሰዎች ጉዳይ ፍፃሜ ማግኘት አለበት፡፡ በአልጀርሱ ስምምነት መሠረት የሁለቱ አገሮች ወሰን መካለል አለበት፡፡ ይህ ጉዳይ በሁለቱም ወገኖች ዘንድ የሚያስከትለው ሕመም ይኖር ይሆናል፡፡ አማራጩ ግን ሕመሙን ችሎ ዘላቂውን መፍትሔ ማምጣት ነው፡፡ ያልተቋጨ ነገር እንደገና የመጀመር ዕድሉ ሰፊ ነውና፡፡

በሁለቱ አገሮች መካከል የሚኖረው ንግድ የሚመራበት ግልጽ አሠራር ሊኖረው ይገባል፡፡ ኢትዮጵያ በአሰብ ወደብ እንድትጠቀም መደረግ አለበት፡፡ የኤርትራ ሕዝብ ከኢትዮጵያ የሚፈልጋቸው ምግብና ሌሎች ሸቀጣ ሸቀጦች ሊቀርቡለት ይገባል፡፡ በሁለቱ አገሮች መካከል የሰዎችን ዝውውርና ቋሚ የመኖሪያ አሰጣጥን በተመለከተ ግልጽ ሕግና አሠራር ሊኖር ይገባል፡፡ እነዚህ ሁሉ የጋራ ክብርንና የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ማድረግ አለባቸው፡፡

በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ሚዛን የጠበቀ ግንኙነት ለአገሮች ወዳጅነት መዝለቅ ወሳኝ ነው፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ለምትፈልጋቸው ጥቅሞች ሁሉ በምላሹ ለኢትዮጵያ ፍላጎት ምላሽ መስጠት መቻል ይገባታል፡፡ ይህ ካልሆነ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት በጋራ ተጠቃሚነት ላይ ሳይሆን፣ በተናጠል ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ይሆናል፡፡ የተናጠል ተጠቃሚነት ፍላጎት ዳግም የሚሰፍን ከሆነ ትናንት የመታን ድንጋይ ዛሬም እንዲመታን ዕድል መስጠት ይሆናል፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር  ዳግም ወደ ጠላትነት መግባት አይገባትም፡፡ ይልቁኑም ግንኙነቷ በጋራ ተጠቃሚነት መርህ ላይ እንዲመሠረት በማድረግ፣ ያልተቋጩ ጉዳዮችን በሕግና በሥርዓት እንዲቋጩ በማድረግ ጎረቤትን እንደ አመሉ መያዝ ይገባል፡፡ ነገር ግን እንደ አመሉ ጎረቤትን መያዝ አለብን ሲባል መስመር እያለፈ በውስጣዊ ጉዳይ ላይ መፈትፈትም ይፈቀድለታል ማለት አይደለም፡፡

የጋራ ተጠቃሚነትን ማዕከል ያደረገ ግንኙነት ለመገንባት በኢትዮጵያ ኪሳራ የሚጠበቅ የኤርትራ ብሔራዊ ጥቅም እንደማይኖረው ሁሉ፣ በኤርትራ ኪሳራም የሚጠበቅ የኢትዮጵያ ጥቅም አይኖርም፡፡ በመሆኑም በሸፍጠኝነት በሆድ ቂም ይዞ ወዳጅ እየመሰሉ አንዱ ሌላውን አገር ለመጉዳት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በማንኛውም ሂሳብ የተናጠል ጥቅምን ሊያረጋግጥ አይችልም፡፡ ወዳጅ እየመሰሉ በሥውርም በግልጽም መጠቃቃት ውስጥ መግባት ችግሮችን ያባብስ እንደሆነ እንጂ ዘላቂ ጥቅሞችን ማረጋገጥ አያስችልም፡፡ ዘላቂ ጥቅሞች እንዲረጋገጡ በጋራ ተጠቃሚነት ላይ የተመሠረተ ግልጽ ዓላማ ያለው ባለዘርፈ ብዙ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት፣ በሁለቱ አገሮች መካከል እንዲመሠረት ማድረግ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡

ምንም እንኳን ኢትዮጵያ ሁሌም ሰላማዊ ግንኙነቶችን ብታስቀድምም፣ የኤርትራ መንግሥት ሁለንተናዊ አስተሳሰቡ ዘመኑን የዋጀ አይደለም፡፡ ለእኩልነትና ለጋራ ተጠቃሚነት ዝግጁ ሆኖ በመተማመን ላይ የተመሠረ ግንኙነት እንዲፈጠር ሁኔታዎችን ቀላል ላያደርጋቸው እንደሚችል ከተፈጥሯዊ ሥሪቱ መገመት ብዙም አዳጋች አይሆንም፡፡ በዚህ ሁኔታ የኢትዮጵያ መንግሥት ከዛሬ ነገ ይስተካከላል በሚል ሊቀየር የማይችል አቋም ያለውን ኃይል እያባበለና በብሔራዊ ጥቅሙ ላይ አደጋ እየመጣበት እጁን አጣጥፎ እንዲቀመጥ ባይጠበቅም፣ የጋራ ተጠቃሚነትን መርሁ ያደረገ ግንኙነት በሁለቱ አገሮች እንዲፈጠር በሙሉ አቅሙ መሥራት እንዳለበት አምናለሁ፡፡

የኢትዮ ኤርትራ ግንኙነት ሰላማዊ መሆን ለቀጣናው አገሮች ሁለንተናዊ ዕድገት በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡ ግንኙነቱ ግን የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ መሆን እንደሚገባውም ዕሙን ነው፡፡ ለዚህም መተመማን ያለበት ጎረቤታምነት በእጅጉ ገዥ ነው፡፡ ደስታና ሐዘንም እኩል መካፈል የሚችል ሆኖ ጉርብትና ሲመሠረት ደግሞ ይበልጥ ሰላማዊ ይሆናል፡፡ ነገር ግን ሸክምን እኩል ለመሸከም የማይፈልግ፣ የተናጠል ጥቅሙን በጎረቤቱ ላይ ለማሳካት ብቻ የሚፈልግ ወዳጅ ሲሆን ወዳጅነት አይኖርም፡፡ በምትኩ ጠላትነት ይነግሳል፡፡ ጠላትነት አብሮት ቡዙ ጥፋት ይዞ ስለሚመጣ ኢትዮጵያ መርህ ላይ ቆማ የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ያደረገ ግንኙነት ከኤርትራ ጋር እንዲኖራት በመስራት፣ መርህ የጣሱ ጉዳዮች ሲከሰቱ ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል የማድረግ አቅሟን ማሳየት ይጠበቅባታል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...