Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምበሱዳን የተኩስ አቁም ስምምነት ካበቃ በኋላ ያገረሸው ጦርነት

በሱዳን የተኩስ አቁም ስምምነት ካበቃ በኋላ ያገረሸው ጦርነት

ቀን:

የሱዳን መከላከያን በሚመሩት የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄኔራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃንና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን በሚመሩትና ሄሜቲ በሚል ስማቸው በሚታወቁት ጄኔራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ መካከል ሚያዝያ 7 ቀን 2015 ዓ.ም. የተጀመረው ጦርነት፣ በተኩስ አቁም ስምምነት ጋብ ቢልም፣ የስምምነቱን ማብቃት ተከትሎ ዳግም አገርሽቷል፡፡

በሁለቱ አካላት በኩል ግንቦት 14 ቀን የተደረሰው የተኩስ አቁም ስምምነት ግንቦት 26 ቀን ማብቃቱን ተከትሎ፣ በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም የተለያዩ ሥፍራዎች ጦርነት መፋፋሙን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

በሰሜን ዳርፉርም አዲስ ግጭት መቀስቀሱና 40 ያህል ሰዎች መገደላቸውም ተሰምቷል፡፡ በሳዑዲ ዓረቢያና በአሜሪካ አማካይነት የተጀመረው ሁለቱን ተቀናቃኞች የማግባባት ሥራ፣ በሱዳን ለጥቂት ቀናትም ቢሆን ጦርነት እንዲቆም አስችሎና የተወሰነ ሰብዓዊ ድጋፍ ለማድረግ ዕድል ፈጥሮ የነበረ ቢሆንም፣ መዝለቅ አልቻለም፡፡

በጦርነቱ ምክንያት 1.2 ሚሊዮን ዜጎች ከቀዬአቸው የተፈናቀሉ ሲሆን፣ 400 ሺሕ ያህል ደግሞ ወደ ጎረቤት አገሮች ተሰደዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም በቀጣናው ባሉ አገሮች ሥጋትን ደቅኗል፡፡

‹‹በካርቱም ደቡባዊ ክፍል የሚካሄደው በጦር መሣሪያ የታገዘ ጥቃት በፍርኃት እንድንኖር አድርጓል፡፡ የአየር መቃወሚያ መሣሪያ ድምፅ እንዲሁም የኃይል አቅርቦት አለመኖር ሕይወታችንን ገሀነም አድርጎታል፤›› ስትል የ34 ዓመቷ ሳራ ሀሰን በስልክ መግለጿን ሮይተርስ አስፍሯል፡፡

በመካከለኛውና በደቡብ ካርቱም፣ በባህሪ፣ በብሉ ናይል ሰሜናዊ ክፍል ካለው ጦርነት በተጨማሪ በምዕራብ ሱዳን በምትገኘው ዳርፉርም ግጭት ተቀስቅሷል፡፡

ለረዥም ዓመታት በቀውስና በሰብዓዊ ድጋፍ ፈተና ውስጥ በምትገኘው ዳርፉር በተቀሰቀሰው ጦርነት በርካቶች መቁሰላቸውም ተነግሯል፡፡

በዳርፉር የመብት ጥሰቶችን የሚቆጣጠረው የዳርፉር ጠበቆች ማኅበር እንዳለው፣ ከዚህ ቀደም በነበሩ ግጭቶች የተፈናቀሉ ነዋሪዎች የተጠለሉበት የካሳብ ካምፕ ነዋሪዎች ጭምር የጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል፡፡

በሰሜን ዳርፉር የንግድ ማዕከል በሆነችው ኩቱም ጥቃት ያደረሰው፣ ከሥፍራው እንደወጣ የሚነገርለትና በጄኔራል መሐመድ ሀምዳንና (ሄሜቲ) የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ነው ቢባልም፣ ቡድኑ ውንጀላውን አስተባብሏል፡፡

የዓይን እማኞች እንደሚሉት፣ የጦር አውሮፕላን በሱዳን ከሚገኙ ትላልቅ ከተሞች አንዷ በሆነችው በኦምዱሩህማን ቢከሰከስም፣ በሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጄኔራል አብዱል ፈታሕ አልቡርሃን የሚመራው የሱዳን መከላከያ ሚኒስቴር ምላሽ አልሰጠም፡፡

በጦር ጄት ጭምር የታገዘው የሱዳናውያን የእርስ በርስ ጦርነት በአገሪቱ ንብረቶች እንዲወድሙ፣ ስርቆት እንዲስፋፋ፣ የጤና መሠረተ ልማቶች እንዲሽመደመዱ፣ የኃይልና የውኃ እጥረት እንዲከሰት አድርጓል፡፡ የምግብ አቅርቦት ችግርም ፈተና ሆኗል፡፡

በቅርቡ የጀመረው ዝናብ እንደተለመደው ጎርፍ የሚያስከትል ሲሆን፣ ይህም ዜጎችን ለውኃ ወለድ በሽታ የሚያጋልጥ ነው፡፡ የዝናቡ መምጣት ከጦርነት ጋር ተዳምሮ የሰብዓዊ ዕርዳታውን ያስተጓጉላል የሚል ስጋት ደቅኗል፡፡ በየቦታው የወዳደቁ አስከሬኖች አለመነሳትም ሌላው ችግር ነው፡፡

ሱዳንን ለሠላሳ ዓመታት የመሯት የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር በሚያዝያ 2011 ዓ.ም. በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ሱዳናውያን በፈለጉት መሪ የመተዳደርም ሆነ ሰላም የማግኘት ዕድል አላገኙም፡፡

በሽር ከሥልጣን እንዲወርዱ ምሁራንን ጨምሮ የተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ አባላት፣ የዴሞክራሲ አቀንቃኞችና ፖለቲከኞች እንዲሁም መከላከያው የተሳተፉበት አብዮት ቢካሄድም፣ ዛሬም ሱዳናውያን በሲቪል መንግሥት እንተዳደር የሚለው ጥያቄያቸው አልተመለሰም፡፡

በሽር ከሥልጣን ከተነሱ ማግሥት ጀምሮ በሱዳን መከላከያና በሲቪሎች  በኩል የነበረው ሽኩቻ፣ ሱዳን በሁለቱ ጥምረት እንድትመራ፣ ጥምር የሽግግር መንግሥቱም አጠቃላይ ምርጫ አድርጎ በሱዳን የሲቪል መንግሥት ሥልጣን እንዲቆጣጠር እንዲያደርግ ከስምምነት ተደርሶ የነበረ ቢሆንም አልተሳካም፡፡

‹‹የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት አልበሽርን ለመገርሰስ የተጀመረው አብዮታችን ግቡን እስኪመታ ድረስ ተቃውሟችን ይቀጥላል፤›› የሚሉት ሲቪሎች፣ ነፃነትና ሰላም፣ ፍትሕ፣ ሲቪል አገዛዝ እንዲሰፍንና መከላከያው ወደ ካምፑ እንዲገባ እንደሚፈልጉ ሲወተውቱ ቢከርሙም፣ እስካሁን ምላሽ አላገኙም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አስጨናቂው የኑሮ ውድነት ወዴት እያመራ ነው?

ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ የኑሮ ውድነት እንደ አገር ከባድ ፈተና...

‹‹ወላድ ላማቸውን አርደው ከደኸዩት ወንድማማቾች›› ሁሉም ይማር

በንጉሥ ወዳጅነው   የዕለቱን ጽሑፍ በአንድ አንጋፋ አባት ወግ ልጀምር፡፡ ‹‹የአንድ...

የመጋቢቱ ለውጥና ፈተናዎቹ

በታደሰ ሻንቆ ሀ) ችኩሎችና ገታሮች፣ መፈናቀልና ሞትን ያነገሡበት ጊዜ እላይ ...

ጥራት ያለው አገልግሎት መስጠት የሚያስችል ሥርዓት ሳይዘረጉ አገልግሎት ለመስጠት መነሳት ስህተት ነው!

በተለያዩ የመንግሥትና የግል ተቋማት ውስጥ ተገልጋዮች በከፈሉት ልክ የሚፈልጉትን...