Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊሃምሳዎቹ የሚሸለሙበት የብሩህ ኢትዮጵያ የፈጠራ ውድድር

ሃምሳዎቹ የሚሸለሙበት የብሩህ ኢትዮጵያ የፈጠራ ውድድር

ቀን:

በየዓመቱ ብሩህ ኢትዮጵያ የተሰኘ ውድድርን በማዘጋጀት የፈጠራ ሐሳብ ያላቸውን ዜጎች እያወዳደረ የሚገኘው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ነው፡፡ ዘንድሮም በአገር አቀፍ ደረጃ የተለያየ የሥራ የፈጠራ ሐሳብ የያዙ ወጣቶችን አወዳድሮ በተሻለ ለማብቃት ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም. የተጀመረው ውድድር እስከ ሰኔ 17 ቀን ድረስ ይዘልቃል፡፡

ውድድሩን አስመልክቶ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ደኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን እንደገለጹት፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ አዳዲስ የፈጠራ ውጤቶች ዕውቅና አግኝተው ተወዳዳሪ እንዲሆኑ ውድድሩ ትልቅ አስተዋጽኦ አለው፡፡

በቀድሞ የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽንና በማስተር ካርድ ፋውንዴሽን አዘጋጅነት ከ2013 ዓ.ም. ጀምሮ ለተከታታይ ዓመታት ሲካሄድ በቆየው በዚህ ውድድር፣ ከሦስት መቶ በላይ ወጣቶች የሥራ ዕድል ማግኘታቸውን አስረድተዋል፡፡

በብሩህ የሐሳብ ፈጠራ ውድድር ባለፉት ሁለት ዓመታት ብቻ 552 ወጣቶች መሳተፋቸውን፣ ከጊዜ ወደ ጊዜም በውድድሩ ለመሳተፍ የሚፈልጉ ቁጥር ከፍ እያለ መምጣቱንም ገልጸዋል፡፡

የፈጠራ ሐሳቦችን ይዘው ለውድድር ከመብቃት አኳያ በሴቶች በኩል ከፍተኛ ክፍተት እንዳለ፣ ችግሩም በአገር አቀፍ ደረጃ መሆኑና እስካሁን ድረስ ውድድር አድርገው ዕውቅና ከተሰጣቸው ዜጎች ውስጥ ሴቶች 29 በመቶ ብቻ ድርሻን እንደሚይዙም አቶ ንጉሡ ተናግረዋል፡፡

ይህም ከወንዶች ጋር ሲነፃፀር ሰፊ ክፍተት መኖሩ ችግሩን ያሳያል ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በግልባጩ ሲመዘን በሴቶች የሚመሩ ኢንተርፕራይዞች ከወንዶች ከሚመሩ ኢንተርፕራይዞች ጋር ሲነፃፀር የመክሰም አደጋ እንደማያጋጥማቸው ገልጸዋል፡፡

ዘንድሮ በሚካሄደው ውድድር በአገር አቀፍ ደረጃ 1,137 ሐሳቦችን የያዙ ወጣቶች ለውድድር ቀርበው 200 ሐሳቦች መለየታቸውን፣ ከእነዚሁ ሐሳብ አመንጪዎች ውስጥ 70ዎቹ እንደሚለዩና የመጨረሻዎቹ 50ዎቹ ተሸላሚዎች እንደሚሆኑ ጠቁመዋል፡፡

ለእነዚህ ሃምሳ የውድድሩ አሸናፊዎች ለእያንዳንዳቸው አምስት ሺሕ ዶላር እንደሚሸለሙና ከውድድሩም በኋላ በቂ ሥልጠና አግኝተው የሥራ ዕድል እንደሚፈጠርላቸውም ሚኒስትር ደኤታው አስታውቀዋል፡፡

ከሶማሌ ክልል በውድድሩ በመሳተፍ የራሱን ሐሳብ እያቀረበ ያለው ወጣት ጀማል ዓሊ ለሪፖርተር እንደገለጸው፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ወጣቶች የሚሳተፉበት ውድድር የፈጠራ ሐሳብ ላላቸው ሁሉ ትልቅ ዕድል ይፈጥራል፡፡

በውድድሩ ሶማሌ ክልልን ወክለው የመጡ 13 የፈጠራ ሐሳብ ያላቸው ወጣቶች መኖራቸውን የገለጸው ጀማል፣ ከክልሉም ሆነ በአገሪቱ በቲማቲም ኢንዱስትሪ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍ የሚያግዝ የፈጠራ ውጤት ይዞ መምጣቱን ገልጿል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ የቲማቲም ምርት ቢኖርም፣ በአብዛኛው በአፍሪካ ደረጃ የሚቀርበው ከውጭ አገር መሆኑን፣ ይህንንም ታሳቢ በማድረግ የፈጠራ ውጤት ይዞ መምጣቱን ይናገራል፡፡

የሶማሌ ክልል ነዋሪዎች በፋብሪካ ደረጃ በውጭ አገር የተመረተ የቲማቲም ውጤት የሚጠቀሙ መሆኑንና የፈጠራ ውጤቱም ይህንን ለማስቀረት እንደሚረዳ ጠቁሟል፡፡

‹‹በአጠቃላይ ከውጭ አገር የሚገቡ የፋብሪካ ውጤቶችን በአገር ውስጥ በማምረት የዶላር ምንዛሪን ማስቀረት ያስፈልጋል፤›› የሚለው ወጣቱ፣ መንግሥት ውድድሮችን በማዘጋጀት የፈጠራ ሐሳብ ያላቸውን ዜጎች ለቁምነገር ማብቃት ይኖበታል ይላል፡፡

በሌላ በኩል የመጀመርያው የብሩህ ኢትዮጵያ የሐሳብ ውድድር አሸናፊ የነበረው ወጣት ሳምሶን ዓለሙ እንደገለጸው፣ በተለያዩ መድረኮች በመሳተፍ የፈጠራ ሐሳባቸውን ለሚያቀርቡ ወጣቶች ውድድሩ ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡

የባክቴሪያ ፈርትላይዘርን ለማምረት ያለመ የፈጠራ ሐሳብን ይዞ ለውድድር በቅቶ እንደነበርና ውድድሩንም በተሻለ ሁኔታ በማሸነፍ የ200 ሺሕ ብር ተሸላሚ መሆኑን ይናገራል፡፡

በአሁኑ ወቅት ከባክቴሪያ የተሠራ ፈርትላይዘር በማምረት ለገበያ እያቀረበ መሆኑን፣ እነሱ በተወዳደሩበት ወቅት አሥር የፈጠራ ሐሳብ አመንጪ ተወዳደሪዎች ብቻ ለሽልማት መብቃታቸውን ያስታውሳል፡፡

ለተለያዩ ምርቶች የሚሆኑ ማዳሪያ ውጤቶች በማምረት ለገበያ እያቀረቡ እንደሆነ የሚናገረው ወጣቱ፣ ገና ከዩኒቨርሲቲ እንደወጣ በብሩህ ኢትዮጵያ የሐሳብ ፈጠራ ውድድር ላይ ተሳትፎ ዕድል ማግኘቱን ያስረዳል፡፡

በቡድን ተደራጅተው የሚያመርቱት ፈርትላይዘር ለአርሶ አደሮች አንድ ኪሎ ከግማሽ ተጠቅመው አንድ ሔክታር መሬት መሸፈን የሚያስችላቸውን ሁኔታ እያመቻቹ መሆኑንና ማዳበሪያውም የበለጠ ትርፋማ እንደሚያደርጋቸው ገልጿል፡፡

በአሁኑ ወቅት በአጠቃላይ ሰባት የሚሆኑ የማዳበሪያ ዓይነቶች እንዳሉ እነዚህም ለተለያዩ ምርቶች እንደሚያገለግሉ ጠቁሟል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...