በእውቀቱ ሥዩም
አዲስ አበባ ውስጥ እንደ ቦሌ መድኃኔዓለም እሚገርመኝ ሰፈር የለም፤ ከመድኃኔዓለም ፊትለፊት አስፓልቱን ተሻግሮ ትልልቅ ሕንፃዎች ይበቅላሉ፤ ምርጥ ካፌዎች ሬስቶራንቶችና በርገር ቤቶች ያብረቀርቃሉ! አስፓልቱ ሁሌም በእግረኞች እንደተሞላ ነው፡፡
ከመድኃኔዓለም ጀርባ ደግሞ ሌላ እዩኝ እዩኝ የማይል አለም አለ፤ በቆርቆሮና በሰማያዊ ሸራ የተዋቀሩ የንግድ ቤቶች ተደርድረዋል፤ ባብዛኛው ምግብ ቤቶች ናቸው፤ ”የኛ ሽሮ፥ እድላዊት ምግብ ቤት“ ወዘተ የሚል መጠርያ አላቸው፡፡ እንደ “ቃተኛ“ ያሉ የቅንጦት ምግብ ቤቶች ውስጥ የመብላት አቅም የሌላቸው የመንግሥት ሠራተኞች እዚህ በተመጣጣኝ ዋጋ ደና ምግብ ይሸምታሉ፤ ለመጨረሻዎቹ ድሆች ”ርጥብ“ የተባለ ምግብ ይቀርባል! ርጥብ የቅቅል ድንች ክትፎ ነው፤ በዳጣ ሠላሳ ብር ሲሆን እንቁላል ሲታከልበት ስድሳ ብር ያስከፍላል፡፡
ሁሌም ከምግብ ቤቶች ፊትለፊት ሞተርሳይክሎች ተደርድረው ቆመው ይታያሉ፤ እቃ ለማመላለስ ላይ ታች ሲሉ የሚውሉ ልጆች ባብዛኛው የዚህ ሰፈር ታዳሚ ናቸው::
ቅድም በዚያ ሳልፍ ቤቶች እየፈረሱ ነው፤ ተወዳዳሪ የሌለው ሐዘን ወረረኝ፡፡ በቅርቡ እየተደረገ ያለው የዶዘር ዘመቻ፥ የትምና መቼም ታይቶ የሚታወቅ አይደለም፡፡ በአውሮፓ፣ በአሜሪካ፣ በቻይና የዙረት እድል የገጠመን ሰዎች እንደምንመሰክረው ጉሊት ዓለምአቀፍ ነው፡፡ በየትኛውም ትልልቅ ከተማ ምግብ ሠርተው መንገድ ላይ የሚሸጡ ሰዎች ይኖራሉ፤ መንግሥት መብታቸውን ያከብርላቸዋል፡፡
“ሰው በላው ካፒታሊዝም” የሚባለው ሥርዓት በሰፈነባቸው አገሮች ሳይቀር ድሆች በዚህ መጠን አይገፈተሩም፤ ቤቶች መስጊዶች ያለ ነዋሪው ፈቃድ አይፈርሱም፤ የግድ ሆኖ ሲፈርሱ እንኩዋ ለባለቤቶች ካሳ እና ምትክ ቦታ ይሰጣቸዋል::
አዲስ አበባ እኔ ሳውቃት፥ ትልቁንና ትንሹን አቻችላ የምታሳድር ሆደ ሰፊ ከተማ ነበረች፤ አሁን ይሄ እየቀረ ነው! የተወሰኑ ሰዎች መሬት ሸጠው ሌክሰስ እንዲነዱ፣ በላባቸው የሚተዳደሩ አያሌ ድሆች መድረሻ አልባ መሆን አለባቸው? እየተስተዋለ እንጂ ጎበዝ!
በግሌ አቅመቢስ ነኝና፥ የመዲናዪቱ ጌቶች እና እመቤቶች ሰሞኑን ለሚያደርጉት ነገር በሙሉ ለህሊናቸው አሳልፌ እሰጣቸዋለሁ፤ በዚያ ላይ፥ አማኞች ስለሆኑ የፈጣርያቸውን ቃል ላስታውሳቸው (መጽሐፈ ምሳሌ ምዕራፍ 29)፥
“ጻድቅ የድሆችን ፍርድ ይመለከታል!
ኃጥእ ግን እውቀትን አያስተውልም!
ፌዘኞች ግን ከተማቸውን ያቃጥላሉ!
ለድሀ በእውነት የሚፈርድ ንጉሥ፥
ዙፋኑ ለዘላለም ይጸናል“
- ጸሐፊው በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንዳሰፈረው