Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ከሕገ መንግሥቱ ውጪ በተግባር እንደሌለ ፓርቲዎች ተናገሩ

የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ከሕገ መንግሥቱ ውጪ በተግባር እንደሌለ ፓርቲዎች ተናገሩ

ቀን:

  • ብልፅግና ስለመድበለ ፓርቲ ለውይይት ጥሪ ቢደረግለትም አልተገኘም

በኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲኖር የሚያስችሉ ሕገ መንግሥታዊ መርሆች ቢኖሩም፣ መሬት ላይ ባለው አጠቃላይ አተገባበር የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት አለ ለማለት እንደማይቻል ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በአገር አቀፍና በክልል ደረጃ ዕውቅና ካላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር፣ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓትን በተመለከተ ግንቦት 28 ቀን 2015 ዓ.ም. ውይይት አድርጎ ነበር፡፡

በውይይቱ የቦሮ ዴሞክራቲክ ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚና የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ዋና ሰብሳቢ መብራቱ ዓለሙ (ዶ/ር) እንደተናገሩት፣ በአገሪቱ በጽሑፍ የተቀመጡ ሕጎች ቢኖሩም ተግባራዊነታቸው ግን እጅግ ዝቅተኛ ነው፡፡ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲያድግ የፖለቲካ ብዝኃነትን የሚያስተናግድ አገራዊ ዓውድ መፈጠር ያለበት ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች እንደ ገዥው ፓርቲ ለሚዲያ ያላቸው ተደራሽነት ሰፊ ባለመሆኑ በምርጫ ወቅት ፖሊሲያቸውንና ፕሮግራማቸውን አቅርበውና ተደምጠው የመመረጥ ዕድላቸው በጣም ዝቅተኛ ነው ብለዋል፡፡

 በዚህም ትልቁን ድርሻ የሚወስደው የገዥው ፓርቲ ሚዲያዎችን በመጠቀም የበለጠ የመመረጥ ዕድሉን ማስፋቱን በመጥቀስ፣ የሕግ የበላይነት፣ አሳታፊ የዴሞክራሲ ሥርዓት፣ የሦስቱ የመንግሥት አካላት መለያየት፣ ገለልተኛነትና ለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ማደግ ወሳኝ መሆናቸው ቢሆንም፣ በሚታሰበው ልክ ባለመሆኑ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ በሚጠበቀው ልክ እንደማይተገበር ተናግረዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) ፓርቲ ዋና ጸሐፊ አቶ አበበ አካሉ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ ፓርቲዎች በመካከላቸው ያለው ግንኙነት የሻከረና ጭቅጭቅ የበዛበት መሆኑን፣ ሁሉም ፓርቲዎች ለአንድ አገር እንደሚሠሩ ግምት ውስጥ በማስገባት ፖለቲካው ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥል በጋራ መሥራት እንዳለባቸው አስረድተዋል፡፡

መድበለ ሥርዓት እንዳያድግና የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንክረው እንዳይወጡ ከሚያደርጓቸው ጉዳዮች መካከል፣ የፋይናንስ ችግር መሆኑን የገለጹት አቶ አበበ፣ ገዥው ፓርቲ በየመሥሪያ ቤቱ ከሠራተኞች ደመወዝ ጭምር እየቆጠረ በሚወስድበት አገር፣ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት ለሚደግፉት ፓርቲ ወርኃዊ መዋጮ ለመክፈል ከፍተኛ ፍርኃት አንዳለባቸውና አባል ለመሆን እንኳ በሚስጥር እንደሚመዘገቡ ተናግረዋል፡፡ አቶ አበበ አክለውም ይህን ዓይነት የፖለቲካ እንቅስቃሴ ባለበት ሁኔታ ፓርቲዎች አቅማቸውን አጠናክረውና መድበለ ፓርቲ ሥርዓቱ አድጎ የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዴት ሊሰፋ ይችላል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

በተመሳሳይ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንዲያድግ ከተፈለገ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከውጭ አገር የሚያገኟቸውን ድጋፎች ከቀረጥ ነፃ ፈቃድ እንዲፈቀድና የብሔራዊ ምርጫ ቦርዱም ሕጉን ሊዳስስ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ ፓርቲያቸው በየወሩ ለቢሮ የሚከፍለው የኪራይ ዋጋ በጣም ከባድ መሆኑን የገለጹት አቶ አበበ፣ ፓርቲያቸው የፖለቲካ ምኅዳሩን እንዲያሰፋ ከተፈለገ ነፃ ቢሮና የቀረጥ ነፃ ዕድል ሊሰጥ ይገባል ብለዋል፡፡

አቶ ምርጫ ስንሻው የተባሉ የአማራ ግዮናዊ ንቅናቄ ፓርቲ አባል፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ከአባላት መዋጮ ሰብስበው የተቋቋሙለትን ዓላማ ማሳካት ፈታኝ መሆኑን ጠቅሰው፣ ሕዝቡ ለተፎካካሪ ፓርቲ አባልነት መመዝብም ሆነ ወርኃዊ መዋጮ መክፈል መዘዙ ከባድ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በላይ በአገሪቱ ያሉ ሀብቶችን ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች እኩል የመጠቀም መብት ቢኖራቸውም፣ መንግሥታዊ የተባሉ አዳራሾችን እንኳ ብልፅግና እንደፈለገ ሲያዝበት ተፎካካሪ ፓርቲዎች ግን ለምነው እንኳ መሰብሰብ አለመቻላቸውን ተናግረዋል፡፡ በዚህም የተነሳ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት አለ ብሎ ለመናገር አያስደፍርም ብለዋል፡፡

የቦሮ ዴሞክራቲክ ፓርቲ የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ዮሐንስ ተሰማ፣ መንግሥት የሚያከብረውና የሚፈራው በትጥቅ ትግል የሚታገለውን አካል እንጂ፣ ሰላማዊና ሕጋዊ ትግል ላይ ያለውን የፖለቲካ ፓርቲ እንዳልሆነ፣ በዚህም ሕጋዊ ፓርቲዎች ለአፈናና ለእስር እየተዳረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በዚሀም በኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ትግል እንዲያድግ የሚደረገው ትግል ትርጉም አልባ ነው የሚሉት አቶ ዮሐንስ፣ በአገሪቱ ፓርላማ ሆነ በክልሎች ምክር ቤት ወንበር የሌላቸው ፓርቲዎች ባሉበት ሁኔታ መነጋገር የሚቻለው፣ ስለመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ሳይሆን ስለአንድ ፓርቲ ሥርዓት ብቻ ነው ብለዋል፡፡

ምርጫ ሲቀርብ በተፎካካሪ አካላትና አመራሮች የሚደረግ የውሸት ክስ፣ እስር፣ ወከባና አፈና ባልቆመበት የመድበለ ፓርቲም ሆነ ዴሞክራሲ እንዴት ሊያድግ ይችላል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሥራ አስፈጻሚ አባል አቶ ጀቤሳ ገቢሳ በበኩላቸው፣ በኢትዮጵያ ሕገ መንግሥት ውስጥ ስለ መድበለ ፓርቲ ሥርዓት ቢደነገግም፣ በመንግሥት የአፈጻጸም ችግር የተነሳ በዚህ አገር መሬት ላይ የሚታይ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ይኖራል የሚል እምነት እንደሌላቸው ተናግረዋል፡፡ ‹‹በመሆኑም ለሕግ ታማኝ የሆነ መንግሥት እስካልተፈጠረ ድረስ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ይፈጠራል የሚል እምነት፤›› የለኝም ብለዋል፡፡

የኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አቶ ሙላቱ ገመቹ እንደሚሉት ደግሞ፣ በኢትዮጵያ አለ የሚባለው የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ለዓለም አቀፍ ማኅበረሰብና ዲፕሎማቶች የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት እንዳለ ለማስመሰል የተፈጠረ እንጂ፣ በእውነት መሬት ላይ የሚታየው ግን ተቃራኒው ነው፡፡ መንግሥት ሁለት ባርኔጣ ይዞ አንዱን ከፓርቲዎቹ ጋር፣ አንዱን ባርኔጣ ደግሞ መንግሥት ሆኖ ፓርቲዎችን የሚወጋበት ነው በማለት ወቀሳቸውን ሰንዝረዋል፡፡

ከኦጋዴን ብሔራዊ ነፃነት ግንባር (ኦብነግ) የተወከሉት ዩስራ አህመድ በበኩላቸው፣ ለገዥው ፓርቲ እናት፣ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የእንጀራ እናት በሆነችበት አገር ውስጥ እንዴት ብሎ ስለእኩልነትና መድበለ ፓርቲ ሥርዓት ማውራት ይቻላል በማለት ጠይቀዋል፡፡

የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ምክትል ሰብሳቢ አቶ ውብሸት አየለ በሰጡት ማብራሪያ፣ የአገሪቱ ሕገ መንግሥትም ቢሆን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አዋጅ መድበለ ፓርቲ አካሄድን የሚፈቅድ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት 21 አገራዊና 41 ክልላዊ የፖለቲካ ፓርቲዎች በቦርዱ ዕውቅና አግኝተው ሥራ ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡ በዚህም ቦርዱ የመዘገባቸው ፓርቲ ከአባላቶቻቸው ጋር እንደሚገናኙ፣ ፕሮግራማቸውን እንደሚያስተዋውቁና የጋራ ውይይት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል፡፡ ምክትል ሰብሳቢው አክለውም፣ ‹‹ፓርቲዎች ያለውን መደላድል ለመጠቀም ዝግጁ መሆናቸውን ዓይተናል፤›› ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ ምርጫ ቦርድ ከፖለቲካ ፓርቲዎች የሚቀርቡለትንና ለዴሞክራሲ ሥርዓት እንቅፋት ናቸው ብሎ የሚያስባቸውን ሁሉ ማስተካከያ እንዲደረግ ከመንግሥትና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በመመካከር መፍትሔ እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡ አቶ ውብሸት እንዳሉት ቦርዱ በመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ላይ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ምክክር ለማድረግ በጠራው ስብሰባ ብልፅግና ፓርቲ ጥሪ ቢደረግለትም ተወካዩ አለመላኩን አስረድተዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...