Tuesday, October 3, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

አገር አጥፊ ድርጊቶች በአገር ገንቢ ተግባራት ይተኩ!

ኢትዮጵያ ውስጥ በስፋት የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት በመንስዔዎች ላይ መግባባት ያስፈልጋል፡፡ መግባባት ሊኖር የሚችለው ደግሞ በሠለጠነ መንገድ ለመነጋገር የሚያስችል ዓውድ ሲፈጠር ነው፡፡ ለዚህ ስኬት ዕውን መሆን ሁሉም የአገሪቱ ዜጎችም ሆኑ የፖለቲካ ኃይሎች ኃላፊነት አለባቸው፡፡ ሥልጣን ላይ ያለውን መንግሥት የሚመራው ገዥው ፓርቲም ሆነ ሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ ከአገር ህልውና በፊት የሚቀድም ምንም ነገር እንደሌለ በመረዳት ወደ ሕጋዊና ሰላማዊ ንግግር መመለስ አለባቸው፡፡ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በኃይል ለመፍታት የሚኬድበት ርቀት ያተረፈው ቢኖር ዕልቂትና ውድመት ብቻ ነው፡፡ በዚህ መሀል የሚጎዱት የፖለቲካ ተዋንያኑ ሳይሆኑ ያለ ኃጢያታቸው የሚገደሉ፣ የሚፈናቀሉና ንብረታቸውን የሚያጡ ንፁኃን ስለመሆናቸው መስካሪ አያሻም፡፡ ሌላው ቀርቶ በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸውን ወገኖች መመልከት በቂ ነው፡፡ ከዚያ ዘግናኝ ጦርነት ውስጥ በቅጡ ሳይወጣ በተለያዩ ምክንያቶች ግጭቶች ሲቀጥሉ፣ በሕግ አምላክ ተብሎ ማስቆም ካልተቻለ ከአቅም በላይ የሆነ መከራ ሊከተል እንደሚችል ለመረዳት ነብይ መሆን አያስፈልግም፡፡ በአሁኑ ጊዜ አስፈሪ ምልክቶች ከመጠን በላይ እየታዩ ነው፡፡

ቀደም ሲል ከብሔር ጋር የተያያዙ በርካታ ግጭቶች ያደረሱትን ዕልቂትና ውድመት ምዕራፍ መዝጋት ሳይቻል፣ አንዴ ከኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ቀጥሎ ደግሞ ከእስልምና እምነት ተከታዮች እየተሰማ ያለው ቅሬታና ተቃውሞ መርገብ ካልቻለ ለአገር ህልውና ጠንቅ ነው፡፡ ችግሮች መቼም ቢሆን ማጋጠማቸው የታወቀ ነው፡፡ ነገር ግን ችግሮችን በሆደ ሰፊነት ተቀራርቦ ለመፍታት የሚደረገው ጥረት በጣም ዝቅተኛ በመሆኑ፣ ኢትዮጵያ ከጊዜ ወደ ጊዜ የማትወጣው ቀውስ ውስጥ የሚከታት ጎዳና ላይ እንድትገኝ እያደረጋት ነው፡፡ መንግሥት በተለያዩ ምክንያቶች ከሕዝብ የሚቀርቡለትን አቤቱታዎች በቅደም ተከተል ተመልክቶ የመፍታት ኃላፊነት ሲኖርበት፣ አቤቱታ አቅራቢዎችም ሕግና ሥርዓት ተከትለው ችግራቸው እንዲፈታ የማድረግ ግዴታ አለባቸው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን የመንግሥት ኃላፊነት ይዘው ሕዝብ የማገልገል ግዴታ ያለባቸው ግለሰቦችም ሆኑ ስብስቦች፣ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ መወጣት ባለመቻላቸው ብቻ ችግሮች ከመጠን በላይ እየተደራረቡ ነው፡፡ ቅሬታም ሆነ አቤቱታ ሲቀርብላቸው እግራቸውን የሚጎትቱ በመብዛታቸው አገር የማትወጣው ማጥ ውስጥ እንድትገባ ሰበብ እየሆኑ ነው፡፡

አገር እያስተዳደረ ያለው ብልፅግና ፓርቲ በሕዝብ ድምፅ በተመረጠ ማግሥት ከትግራይ ክልል በስተቀር፣ በአብዛኞቹ የአገሪቱ ክፍሎች ከሕዝብ ጋር ውይይት ማካሄዱ አይዘነጋም፡፡ የብልፅግና ከፍተኛ አመራሮች ሳይቀሩ በተገኙባቸው መድረኮች ከሕዝብ ጠቃሚ ግብዓቶችን ማሰባሰቡን ማስታወቁም አይረሳም፡፡ ከሕዝብ የተገኙ ምክረ ሐሳቦችን መሠረት በማድረግ አገር ለመምራት ታጥቆ መነሳቱን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ ይህ ሁሉ መልካም ጅምር ግን ሳይውል ሳያድር የተረሳ ይመስላል፡፡ ሕዝብ በበርካታ መንግሥታዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ያለ ጉቦ መገልገል እያቃተው ነው፡፡ ለመግለጽ የሚያስቸግሩ ሙያዊ ልሽቀቶች እየታዩ ነው፡፡ ለሥራው የማይመጥኑ ኃላፊዎችና ሠራተኞች መሥራት አቅቷቸው የሕዝቡን ናላ እያዞሩት ነው፡፡ ይህንና መሰል እሮሮዎች በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ባሉ ሚዲያዎች ጭምር ገንፍለው ወጥተው ተሰምተዋል፡፡ ተቃውሞዎች በሚኖሩበት ጊዜ የፀጥታ ኃይሎች ከመጠን በላይ ኃይል እንዳይጠቀሙ በተደጋጋሚ ማሳሰቢያ ቢሰጥም፣ የሰላማዊ ሰዎች ሕይወት በአሳዛኝ ሁኔታ ሲያልፍ ተጠያቂነት የጠፋ ይመስላል፡፡

እዚህ ላይ መዘንጋት የሌለበት የሕግና ሥርዓት መከበር ጉዳይ ነው፡፡ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን መንግሥት ብቻ ሳይሆን፣ ሁሉም ዜጎችና የፖለቲካ ኃይሎች ኃላፊነት አለባቸው፡፡ መንግሥት ግን በተለየ ሁኔታ በሕግ የተሰጠው ኃላፊነትና ግዴታ ስላለበት፣ ሕግና ሥርዓት ሲያስከብር በግልጽነትና በተጠያቂነት መርህ መሆን ይኖርበታል፡፡ ለዚህም ደግሞ ብቁ አመራሮች፣ ባለሙያዎች፣ ሠራተኞችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ሊኖሩትም ይገባል፡፡ ከፓርቲ ወገናዊነት ወይም ከብሔርና ከእምነት አጉል ቁርኝት የፀዳ አሠራር ሲኖረው፣ ለቅሬታም ሆነ ለተቃውሞ የሚያነሳሱ ምክንያቶች ሊኖሩ አይችሉም፡፡ ነገር ግን በብልሹ አሠራሮች ሲተበተብ የተከማቹ ችግሮችን ለመፍታት ቀርቶ፣ አዲሶቹን እንኳን በወጉ መልክ ለማስያዝ ያዳግተዋል፡፡ ሕግና ሥርዓት ሲከበር መንግሥት ሥራውን በአግባቡ መወጣት ሲችል፣ ሕዝብም መሠረታዊ አገልግሎቶችን በተገቢው መንገድ ከማግኘቱም በላይ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹም ይከበራሉ፡፡ ለቅሬታና ለአቤቱታ ሰበብ ሊሆኑ የሚችሉ ብልሹ አሠራሮች ይወገዳሉ፡፡ ግለሰቦችም ሆኑ ስብስቦች እንዳሻቸው የሚሆኑበት ዕድል አይኖርም፡፡ ሕግና ሥርዓት እንዳይኖር የሚፈልጉ ግን ለተቃውሞና ለሁከት ምክንያት እየሆኑ ነው፡፡

የቀድሞም ሆኑ የአሁን ችግሮች መንስዔዎቻቸው ተመሳሳይ ናቸው፡፡ በብሔራዊ ጉዳዮች ላይ በእኩልነትና በወዳጅነት ስሜት በጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጦ ለመነጋገር በነበረው ዳተኝነት ሰበብ፣ ኢትዮጵያ በተደጋጋሚ መልካም ዕድሎች ያመለጣት አገር ናት፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክም ሆነ በአገረ መንግሥት ግንባታ የተለያዩ ዕሳቤዎችን ፈር ለማስያዝ ሥልጣን ላይ በሚወጡ አካላት ካለመፈለጉም በላይ፣ ጥያቄ አለን የሚሉ ወገኖችን ማሳደድና ጥግ ማስያዝ ላይ ስለሚተኮር ችግሮች እንዲበራከቱና እየተንከባለሉ እዚህ እንዲደርሱ ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህ አባዜ አሁንም ሊቆም ባለመቻሉ ከየአቅጣጫው ቅሬታዎችና አቤቱታዎች ሲቀርቡ ማዳመጥ አይፈለግም፡፡ ወይም ደግሞ ከቅሬታዎቹና ከተቃውሞዎቹ በስተጀርባ ስላለ ሴራ እየተተረከ ማድበስበስ ውስጥ ይገባል፡፡ እንዲህ ዓይነት ድርጊቶች ሲበራከቱ ችግሮችን በጋራ መፍታት ቀርቶ፣ በዓይን ለመተያየት እንኳ የማይቻልበት ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ ልዩነትን በሠለጠነ መንገድ ከመፍታት ይልቅ ጠመንጃ ውልወላ ውስጥ እየተገባ፣ ኢትዮጵያ የጦር ዓውድማ ከመሆን መላቀቅ አልቻለችም፡፡ ከምንም ነገር በላይ የአገር ህልውናን በማስቀደም በጋራ ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ መነጋገር ይለመድ፡፡

ኢትዮጵያ ውስጣዊ ችግሮቿን ማስተካከል እየቻለች ተግባራዊ ማድረግ ካቃታት፣ ሁከት የዘወትር መገለጫው በሆነው የአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ህልውናዋን ለማስቀጠል ያዳግታታል፡፡ አገር የሚመራው ብልፅግናም ሆነ ተፎካካሪዎቹ አንድ መገንዘብ ያለባቸው መሠረታዊ ጉዳይ፣ ስትራቴጂካዊ በሆነው የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ የሚያንዣብቡ ኃያላኖች ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በአካባቢው ላይ ትኩረት ማድረጋቸውን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ኃያላኑ የጦር ሠፈሮቻቸውን ከመሠረቱበት የቀይ ባህር በቅርብ ርቀት ላይ መሆኗ፣ ምዕራባውያን ከሩሲያና ከቻይና ጋር የጀመሩት ፍጥጫ ወደ አካባቢው ሊስፋፋ የሚችልባቸው ምልክቶች እየታዩ መሆናቸው፣ የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት መሠረት በተወሰነ ደረጃ ጋብ ያለ ቢመስልም ያልጠሩ ጉዳዮች መኖራቸው፣ እንዲሁም በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ምክንያት በተለይ ከግብፅ ጋር የሚደረገው ንትርክ ገጽታውን እየቀያየረ መፍትሔ መታጣቱ ተጠቃሽ ሥጋቶች ናቸው፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታ ውስጥ ያለችን አገር ውስጣዊ ችግሮቿን በሰላም በመፍታት ሰላም ማስፈን አለመቻል፣ ይዞት የሚመጣው ጦስ በቀላሉ የሚገላገሉት ሳይሆን አጥፊ ነው፡፡ ስለዚህም አገር አጥፊ ድርጊቶች በአገር ገንቢ ተግባራት ይተኩ!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የባለሥልጣናትና የባለሀብቶች ግንኙነት ሥርዓት ይኑረው!

በሕዝብ ድምፅ ሥልጣን የያዘ ፓርቲ የሚመሠርተው መንግሥት ከምንም ነገር በፊት ለሕግና ለሥርዓት መከበር ኃላፊነት ሊኖረው ይገባል፡፡ ይህንን ኃላፊነት በሚገባ ሊወጣ የሚችለው ሥራውን በግልጽነትና በተጠያቂነት...

የመላው ሕዝባችን የአብሮነት ፀጋዎች ይከበሩ!

ሕዝበ ሙስሊሙና ሕዝበ ክርስቲያኑ የመውሊድ፣ የደመራና የመስቀል በዓላትን እያከበሩ ነው፡፡ በኢትዮጵያ አገረ መንግሥት ግንባታ ውስጥ እኩልና ጉልህ ድርሻ ያላቸው ኢትዮጵያውያን፣ በዓላቱን እንደ እምነታቸው ሕግጋት...

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...