Sunday, July 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአዲስ አበበ መምህራን ማኅበር የደመወዝ ጥያቄው ምላሽ ካላገኘ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚያቀርብ አስታወቀ

የአዲስ አበበ መምህራን ማኅበር የደመወዝ ጥያቄው ምላሽ ካላገኘ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚያቀርብ አስታወቀ

ቀን:

የአዲስ አበባ መምህራን ማኅበር ለረጅም ዓመት ያገለገሉ መምህራን ደመወዝና የደረጃ ዕድገት እንዲስተካካል በተደጋጋሚ የሚያቀርበው ጥያቄ በአፋጣኝ ምላሽ ማግኘት ካልቻለ፣ ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚወስደው አስታወቀ፡፡

የመምህራን አገልግሎትና የደመወዝ አለመጣጣምን በተመለከተ በኢትዮጵያ መምህራን ማኅበር አማካይነት በተደጋጋሚ ለትምህርት ሚኒስቴር ጥያቄ ቢቀርብም፣ የትምህርት ሚኒስቴር መልስ ሊሰጥበት አለመቻሉን የአዲስ አበበ መምህራን ማኅበር ፕሬዚዳንት አቶ ድንቃለም ቶሎሳ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

ለመምህራን አገልግሎታቸውን መሠረት ያደረገ የጎንዮሽ የደረጃ ዕድገት ባለመኖሩ ምክንያት፣ አንድ 17 ዓመት ያገለገለ መምህርና 40 ዓመት ያስተማረ መምህር፣ በአንድ ደረጃ ውስጥ ተመሳሳይ ደመወዝ እየተከፈላቸው እንደሚገኝ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡

ለአብነትም የመምህራኑ ደመወዝ ሲተነተን አንድ 17 ዓመት ልምድ ያለውና በሰርተፊኬት ደረጃ የሚያስተምር መምህር፣ በተመሳሳይ የትምህርት ደረጃ 40 ዓመት ካስተማረው መምህር ጋር 10,150 ብር፣ በዲፕሎማ 17 ዓመትና ከዚያ በላይ ያገለገለ ማንኛውም መምህር 11,305፣ በዲግሪ 17 ዓመትና ከዚያ በላይ ያገለገለ ማንኛውም መምህር 12,579 እንዲሁም ማስተርስ ዲግሪ ይዞ 17 ዓመትም ይሁን ከዚያ በላይ የመምህርነት አገልግሎት ዘመን ያቸው ሁሉ 13,926 ብር ያልተጣራ ጥቅል ደመወዝ እንደሚከፈላቸው አቶ ድንቃለም ተናረዋል፡፡

በዚህም የተነሳ መምህራን እያገለገሉ የአገልግሎታቸው ዘመን በጨረሱ ቁጥር፣ አገልግሎታቸው ትርጉም አልባ እየሆነ ስለመሆኑ የጠቀሱት አቶ ድንቃለም፣ አንዳንዶቹ መምህራን ያስተማሯቸው ተማሪዎች ከዩኒቨርሲቲ ተመርቀው መምህር ሆነው  ተመልሰው ከአንጋፋ መምህራኑ፣ ከቀድሞ ተማሪዎቻቸው ጋር እኩል ደመወዝ እየተከፈላቸው ነው ብለዋል፡፡ በዚህም ‹‹አገሪቱ አንጋፋ መምህራን የሚገባቸውን ክብር እየሰጠቻቸው አለመሆኑን ጠቅሰው፣ ለዓመታት አገልግለው የደረጃ ማስተካከያ ሳይደረግ ጡረታ እየወጡ ነው፤›› ብለዋል፡፡

የአንጋፋ መምህራን የደመወዝና ደረጃ ጉዳይ ከ2011 ዓ.ም. ጀምሮ ሲጠየቅ የነበረ ቢሆንም፣ ትምህርት ሚኒስቴር ምላሽ እየሰጠ አለመሆኑን ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ቀደም መምህራን አገልግሎታቸውን ማዕከል ያደረገ የደረጃ ዕድገት ያገኙ የነበረ ቢሆንም፣ በ2011 በመቋረጡ አሁን ላይ የሆነው ግን የአንድ መምህር ዕድገት  ከፍተኛ መሪ የሚባለው ደረጃ ላይ ይቆማል፡፡ በሥራ ላይ ያሉት የመምህራን ደረጃዎች ጀማሪ መምህር፣ መለስተኛ መምህር፣ ከፍተኛ መምህር፣ ከፍኛ መሪ፣ መሪ የሚሉ ናቸው፡፡ አቶ ድንቃለም እንደ ገለጹት ጉዳዩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ መፍታት የማይችል በመሆኑ፣ ትምህርት ሚኒስቴር ቶሎ በአፋጣኝ መልስ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡

በቀጣይ የአንጋፋ መምህራንን ጥያቄ የማይመልሱ ከሆነ፣ መምህራኑ አቋማቸውን ይዘው ወደ ትምህርት ሚኒስቴር ሄደው እንዲጠይቁ ይደረጋል ብለዋል፡፡ በተጨማሪም ጉዳዩ አሳሳቢ በመሆኑ የአንጋፋ መምህራኑን ጥያቄ መልስ እንዲያገኙ በኅብረት ፊርማ በጋራ ተፈራርመው ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደሚያቀርቡ ተናግረዋል፡፡

የአገር መሪዎችና ከፍተኛ አመራሮችን ያፈሩ እነዚህ አንጋፋ መምህራን ጥቅማቸው ተከብሮ በክብር መሰናበት ሲገባቸው፣ የአገልግሎት የደረጃ ዕድገት ልመና ውስጥ መግባታቸው አሳዛኝ ስለመሆኑ ፕሬዚዳንቱ ተናግረዋል፡፡

ሪፖርተር ያነጋገራቸውና ከ29 ዓመታት በላይ በመምህርነት ያገለገሉ፣ በኮከበጽባህ ትምህርት ቤት የሚያስተምሩት መምህር ዮሐንስ አየለ እንደሚሉት፣ ከዚህ ቀደም ዘጠኝ የነበረው ደረጃ ወደ ሰባት መውረዱን ጠቅሰው2 ትምህርት ተምረው የትምህርት ማሻሻያ ይዘው የሚመጡ መምህራን የተፈቀደውን ደረጃ እንዳያገኙ መደረጋቸውን ገልጸዋል፡፡

በሌላ መልኩ አንድ መምህር የመጨረሻ አገልግሎት ዘመን ሲደርስ የሚከፈለው ክፍያ 17 ዓመት ካገለገለ መምህር ጋር እኩል መሆኑና በዚህም ረዥም ዓመታት ያገለገሉ መምህራን ያለምንም ዕድገት በሙያው ውስጥ ቆዝመው እንዲያረጁ የሚያደርግ አሠራር ስለመሆኑ ተናግረዋል፡፡

ይህን ሁሉ ዓመት አገልግዬ የሚከፈለኝ ገንዘብ 13,000 ብር ነው የሚሉት መምህሩ ይህ ደግሞ ‹‹ተስፋ ቆርጠህና ቆዝመህ የምትኖርበት አኗኗር ነው›› ብለዋል፡፡     መምህርነት የተከበረ ሙያ ሆኖ እያለ መምህራኑ በኢኮኖሚ፣ በማኅበራዊ እጅግ ተጋላጭ እየሆኑ በፍጥነት እያደገ በመጣ የኑሮ ውድነት ውስጥ ተቋቁመው ለመኖር ስለመቸገራቸው አብራርተዋል፡፡

በመሆኑም መንግሥት አገራዊ ሁኔታውን ያገናዘበ ጥናት በማድረግ መምህራኑ የሚጠበቅባቸውን አገራዊ ኃላፊነት እንዲወጡ ተገቢው የደረጃ ዕድገትና የደመወዝ ማስተካከያ እንዲደረግ መምህር ዮሐንስ ጠይቀዋል፡፡     

በተመሳሳይ በመድኃኒያለም አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት  የሚያስተምሩት መምህር ታረቀኝ ወልደሃና፣ ይህ ጉዳይ በየትኛውም የትምህርት ደረጃ ያሉ ነገር ግን 17 ዓመት አገልግሎት ሲደርስ የትኛውም ዓመት አገልግሎት ይኑረው ተመሳሳይ ክብርና ደመወዝ እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በዚህም በኢትዮጵያ የትምህርት ሥርዓት ውስጥ የመምህር አገልግሎት ዋጋ ያጣበት ጊዜ ደርሷል ብለዋል፡፡

መንግሥት በአንድ በኩል ስለትምህርት ጥራት መሻሻል ሲነገር ቢሰማም፣ ነገር ግን ለዚህ ጥራት መምጣት ከፍተኛ ድርሻ የሚይዙት መምህራን አገልግሎት ያልተከበረበትና ዋጋ ያጣበትና ጥቅም እንደሌላው መተውን ተናግረዋል፡፡

የመምህራኑ የህልውና ጉዳይ የሆነውን የደመወዝ ጥያቄ በተገኘው መድረክ ሁሉ ለማሰማት በሚሞክሩበት ወቅት፣ ጥያቄውን የፖለቲካ ይዘት እንዳለው የሚያደርጉ አካላት ስለመኖራቸውም መምህር ታረቀኝ ተናግረዋል፡፡

የመምህራኑን ጥያቄ በተመለከተ ሪፖርተር ማብራሪያ ለመጠየቅ ለትምህርት ሚኒስቴር በተደጋጋሚ የስልክ ጥሪና አጭር መልዕክት ቢላክም ምላሽ ማግኘት አልቻለም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...