Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

አሽከርካሪዎች የዲጂታል ነዳጅ አሞላል ሲስተምን እንዳይለማመዱ አድርገዋል የተባሉ ባለሙያዎች ከማደያዎች ሊነሱ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከረቡዕ ሰኔ 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ለነዳጅ ግዥ ጥሬ ገንዘብን ወደ ኤሌክትሮኒክ ገንዘብ የሚቀይሩ የኢትዮ ቴሌኮምና የባንክ ባለሙያዎች አሽከርካሪዎቹ የዲጂታል ነዳጅ አሞላል ሲስተሙን እንዳይለማመዱ አድርገዋል በመባሉ ከማደያዎች እንዲነሱ፣ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን መወሰኑን አስታወቀ፡፡

ባለሥልጣኑ ለነዳጅ አከፋፋይ ኩባንያዎች በላከው ደብዳቤ እንዳስታወቀው፣ በስልክ መተግበሪያዎች አማካይነት የነዳጅ ግብይትን ከጥሬ ገንዘብ ወደ ኤሌክትሮኒክ ግብይት በአስገዳጅ ሁኔታ ከተቀየረ ወዲህ፣ ‹‹ሁሉም ባለድርሻ አካላት ባደረጉት የተሟላ ቅድመ ዝግጅት›› አማካይነት አመርቂ ውጤቶች ተገኝተዋል፡፡

ሆኖም በግብይቱ ላይ ‹‹አሁንም አንዳንድ ያልተደፈኑ ክፍተቶች እንዳሉ የሚጠቁሙ መረጃዎች›› ስለደረሱት ውሳኔውን ማስተላለፉን ገልጿል፡፡ ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ባለሥልጣኑ በጻፈው ደብዳቤ ደረሱኝ ያላቸውን ክፍተቶች ጠቅሷል፡፡

ባለሥልጣኑ ካያቸው ክፍተቶች መካከል በጥሬ ገንዘብ የሚደረጉ በርካታ የነዳጅ ግብይቶች መኖራቸው ሲሆን፣ ለዚህም ማሳያ ብሎ የገለጸው በኤሌክትሮኒክ ግብይት የሚከናወነው የዕለት የሽያጭ መጠን ከሚጠበቀው መጠን ጋር ሰፋ ያለ ልዩነት እንዳለው ነው ያስታወቀው፡፡

‹‹በተለያዩ አካባቢዎች ካካሄድናቸው የመስክ ምልከታዎች የተገኘው ሪፖርትም ይህንኑ ጥርጣሬ የሚያጠናክር ሆኖ ተገኝቷል፤›› ሲል የገለጸው ባለሥልጣኑ፣ ይህን ክፍተት ለመድፈን በማሰብ እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሱን ጠቁሟል፡፡

የቴሌና የባንክ ባለሙያዎች በማደያዎች ተገኝተው ድጋፍ ሲያደርጉ መቆየታቸው ነዳጅ ለመቅዳት የሚመጡ ተገልጋዮች ከኤሌክትሮኒክ አሠራር ጋር እንዳይለማመዱ፣ እንዲሁም በራሳቸው የሚፈልጉትን ነዳጅ ከፍለው መቅዳት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል ይላል በባለሥልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ አህመድ ሰይድ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ፡፡

ይህንን ችግር ለማስተካከልም የነዳጅ ግዥና ሽያጩን ማሳለጥ ‹‹በማዕከላዊ ሲስተሙ አማካይነትና በነዳጅ ማደያዎች በኩል ብቻ›› እንዲሆን በማስፈለጉ ነው፣ ባለሙያዎችና ኤጀንቶች እንዲነሱ የተወሰነው ሲልም አክሏል፡፡

በተጨማሪም የኤጀንትነት አካውንት የሌላቸው ማደያዎች የቴሌ ብርም ሆነ የባንኮች ኤጀንትነት አካውንት ከፍተው እንዲሠሩ፣ ነዳጅ ለሚያራግፉላቸው ኩባንያዎች መመርያ እንዲሰጥ ባለሥልጣኑ አሳስቧል፡፡

በተያያዘ ዜና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ለክልልና ለከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮዎች ግንቦት 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ፣ አንዳንድ ማደያዎች በጥሬ ብር ነዳጅ እንደሚሸጡ ጥቆማ እንደደረሰው ገልጾ ነበር፡፡

በሚኒስትር ደኤታው አቶ ተሻለ በልሁ ተፈርሞ የወጣው ደብዳቤ፣ መንግሥት ከግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በመላው አገሪቱ የነዳጅ ግብይት በኤሌክትሮኒክ ብቻ እንዲሆን ያስተላለፈውን ውሳኔ ተላልፎ በሚገኝ አካል ላይ ዕርምጃ እንዲወስዱ ለንግድ ቢሮዎች ያስታወቀ ሲሆን፣ የተወሰደውንም ዕርምጃ ሪፖርት እንዲያደርጉ ሲል ጠይቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች