Thursday, September 28, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊየአብዮታዊት ኢትዮጵያ የጦር ሜዳ ጀብዱ ኒሻን ተሸላሚው ሻለቃ ባሻ ዓሊ በርኬ ...

የአብዮታዊት ኢትዮጵያ የጦር ሜዳ ጀብዱ ኒሻን ተሸላሚው ሻለቃ ባሻ ዓሊ በርኬ (1943-2015)

ቀን:

ከአርባ ስድስት ዓመታት በፊት፣ ኢትዮጵያ ከወራሪው የሶማሊያ ሠራዊት ጋር ጦርነት የገጠመችበት ነበር፡፡ በ‹‹ታላቋ ሶማሊያ›› ቅዠት የተለከፉት የሶማሊያ ፕሬዚዳንት ዚያድ ባሬና ተከታዮቻቸው በ1969 ዓ.ም. በምሥራቅና በደቡብ ምሥራቅ ኢትዮጵያ 700 ኪሎ ሜትር ድረስ ዘልቀው ተቆጣጥረው ነበር፡፡ በዚህን ጊዜ ነበር የወቅቱ መሪ የኅብረተሰብአዊት ኢትዮጵያ ጊዜያዊ ወታደራዊ አስተዳደር ደርግ ሊቀመንበር ሌተና ኮሎኔል መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ታሪካዊውን የእናት አገር ጥሪ ሚያዝያ 4 ቀን 1969 ዓ.ም. ያቀረቡት፡፡

ሕዝቡ የሶማሊያን ወረራ እንዲገታ በሬዲዮና በቴሌቪዥን ጥሪ ያቀረቡት እንዲህ በማለት ነበር።

‹‹…ታፍራና ተከብራ የኖረች ኢትዮጵያ ተደፍራለች፡፡ በአሁኑ ሰዓት የአብዮታዊት እናት አገራችን ዳር ድንበርና የማይገሰሰው አንድነታችን በውጭ ኃይል እየተደፈረ ነው፡፡ በአብዮታችንና በአንድነታችን በጠቅላላው በብሔራዊ ህልውናችን ላይ የሚደረገው ወረራና ድፍረት እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ ላይ ደርሷል… ለብዙ ሺሕ ዘመናት አስከብሮን የኖረው አኩሪ ታሪካችን በዚህ አብዮታዊ አዲስ ትውልድ ጊዜ መጉደፍ የለበትም፡፡ አገር ወዳድ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ ክብርንና ነፃነትህን ለመድፈር፣ አገርህን ለመቁረስ… የተጀመረውን ጣልቃ ገብነትና ወረራ ከመለዮ ለባሹ ጋር ተሠልፈህ ለመደምሰስ የምትዘጋጅበት ጊዜ አሁን ነው፡፡ ተነስ! ታጠቅ! ዝመት! ተዋጋ! እናሸንፋለን!!››

የሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማርያም ‹‹ተነስ ታጠቅ ዝመት››ን ተከትሎ ቀድሞ ሥጋ ሜዳ ይባል በነበረውና በክተቱ አዋጅ መሠረት ታጠቅ የጦር ሠፈር በተባለው ቦታ ለሦስት ወራት የሠለጠነው 300 ሺሕ ሚሊሺያ (ሕዝባዊ ሠራዊት)፣ ከመደበኛው ጦር ጋር ሆኖ በአብዮት አደባባይ ታላቅ ሠልፍ አሳየ፡፡ በዘመኑ አጠራርዋ ከአብዮታዊት ኢትዮጵያ ጎን በሶቪየት ኅብረት አማካይነት ሶሻሊስት አገሮች ከጎኗ ሲቆሙ በተለይም ኩባ እና ደቡብ የመን እግረኛ ሠራዊት፣ ታንከኞችና መድፈኞችን በመላክ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡

በወቅቱ፡-

 ‹‹ሆ ብሎ ተነሳ

ሕዝባዊ ሠራዊት

ጉዞ ጀመረ እየዘመረ

አቀበት ጋራ ቁልቁለት

ወጣ ወረደ ሠራዊቱ

አገሬ መመኪያ ክብሬ

አትደፈርም እናት አገሬ…›› እያሉ እየዘመሩና እየሸለሉ እየፎከሩ ከዘመቱ እርመኛና ቆራጥ ወታደሮች አንዱ ሻለቃ ባሻ ዓሊ በርኬ ናቸው፡፡

ሻለቃ ባሻ ዓሊ ከቀድሞ ወለጋ ክፍለ ሀገር አሶሳ አውራጃ ቤጊ ወረዳ ወደ ኦጋዴን በመዝመት፣ በአንዱ ግንባር የወራሪው የሶማሊያ ኃይል T-55 ታንኮች በእጅ ቦምብ በማጋየት ታላቅ ጀብዱ መፈጸማቸው ይወሳል፡፡

ዓሊ በርኬ ካቃጠሏቸው ታንኮች በተጨማሪ የሌላኛው ታንክ  ሹፌር ዓሊ በርኬ እንዳይገሉት በመማፀኑ ማርከው ከነታንኩ ለአለቆቻቸው አስረክበዋል፡፡

ለዚህም ነው፡-

‹‹ጠላትን ቆጣሪ ልክ እንደኮርኬ
ታንክ ማራኪ ጀግና ዓሊ በርኬ›› ተብሎ የተገጠመላቸው፡፡

የኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት በኢትዮጵያ ድል አድራጊነት ካበቃ በኋላ የአራተኛውን የአብዮት በዓል ተከትሎ፣ በነበረው የኒሻንና ሜዳይ ሽልማት አሰጣጥ ክብር ከተቀዳጁ ጀግኖች አንዱ ሻለቃ ባሻ ዓሊ በርኬ ነው፡፡ ከሻለቃ ባሻነት በተጨማሪ ከርዕሰ ብሔሩ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እጅ የጦር ሜዳ ጀብዱ ኒሻንን ተቀብለዋል፡፡

በትግል አጋሮቻቸው ‹‹የጦርነትን መልክና ታሪክ ቀያሪ ሰው ነው›› የተባሉት ሻለቃ ባሻ ዓሊ በርኬ፣ የመንግሥት ለውጥን ተከትሎ ለዘጠኝ ዓመታት መታሰራቸውና ቤተሰባቸውም መበተኑ በገጸ ታሪካቸው ተመልክቷል፡፡

የሚገባቸውን ክብር ሳያገኙ፣ የተሸለሙት የጦር ሜዳ ጀብዱ ኒሻን የሚያስገኝላቸው ጥቅማ ጥቅም ሳይከበርላቸው መቆየታቸው የሚነገርላቸው ሻለቃ ባሻ ዓሊ በርኬ፣ ግንቦት 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በ72 ዓመታቸው ከዚህ ዓለም በሞት መለየታቸው ተገልጿል።

የካራማራውን ድልና ጀብዱ የፈጸሙ ጀግኖች ታሪክን በሚያወሳው የመቅደስ ዓብይ ‹‹የካራማራ ግራሮች” መጽሐፍ ሻለቃ ባሻው እንዲህ ተዘክረዋል፡፡ ‹‹ጀግና፣ ቆራጥ ወታደር ግን ደግሞ ትሁት ሰው- ዓሊ በርኬ››

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...