ገዳ ስታር ቢዝነስ ግሩፕ አክሲዮን ማኅበር በቅርቡ አስጀምራለሁ ላለው የእርሻ ልማት፣ ከ500 ሔክታር በላይ መሬት ማዘጋጀቱን አስታወቀ፡፡
የገዳ ስታር ቢዝነስ ግሩፕ አክሲዮን ማኅበር መሥራች አቶ ቢንያም ቶሌራ በ500 ሔክታር መሬት ላይ ለማልማት በሒደት ላይ እንደሚገኙ ጠቁመው፣ የጨርቃ ጨርቅና የቆዳ ምርት በቅርቡ ወደ ሥራ እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡
ቢዝነስ ግሩፑ በቅርቡ የአክሲዮን ሽያጭ መጀመሩን ያሳወቀ ሲሆን፣ አክሲዮን ሽያጩ እስከ መቼ ነው? ከመሥራች አባላት ምን ያህል ሰብስባችኋል? ከአክሲዮን ሽያጩ ምን ያህል ለመሰብሰብ አቅዳችኋል? የሚሉ ጥያቄዎች መሥራቹ ቢቀርብላቸውም፣ ለጊዜው ይህንን መመለስ እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡
የአክሲዮን ሽያጭ ከሰኔ 5 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ እንደሚጀምር፣ በቅርቡ በሚደረግ የእራት ግብዣ ላይ የማኅበሩን ድርጅቶችና መሰል እውነታዎች ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረጉ አቶ ዘሪሁን አስረድተዋል፡፡
በ28 ቢሊዮን ብር የመነሻ ካፒታል አራት ግዙፍ ድርጅቶችን በማቋቋም ወደ ሥራ እንደሚገባ የተነገረለት ገዳ ቢዝነስ ግሩፕ፣ በሥሩ የሚገኙ ድርጅቶችን ግንባታ መጀመሩ ተገልጿል፡፡
በቅርቡ ወደ ሥራ ይገባሉ የተባሉት ጂ ፕላስ ፋስት ፉድ፣ ጂ ጄላ የጨርቃ ጨርቅና ሌዘር ምርት መሆናቸው መገለጹ ይታወሳል፡፡
አንድ አክሲዮን በ250 ሺሕ ብር እንደሚሸጥና አንድ ባለአክሲዮን የሚገዛው ዝቅተኛ የገንዘብ መጠን አንድ ሚሊዮን ብር መሆኑ ታውቋል፡፡