Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊኩዌት ኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞችን ለመቀበል መዘጋጀቷን አስታወቀች

ኩዌት ኢትዮጵያውያን የቤት ሠራተኞችን ለመቀበል መዘጋጀቷን አስታወቀች

ቀን:

  • የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከኦማን ጋር አዲስ ስምምነት ላይ መድረሱን አስታውቋል

የኩዌት ባለሥልጣናት የቤት ሠራተኞችን ከኢትዮጵያ ለማስገባት መግባባት ላይ መደረሱን አስታወቁ፡፡ የኩዌት የቤት ሠራተኞች ምልመላ ተቋማት ኅብረት ባለሥልጣናት ይፋ እንዳደረጉት፣ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት ጋር መደበኛ ስምምነት እንደተፈረመ ሠራተኞቹ ወደ ኩዌት መግባት ይጀምራሉ ተብሏል፡፡ ወደ ኩዌት የሚገቡት ኢትዮጵያውያን ሠራተኞችም በ300 ዶላር ወርኃዊ ደመወዝ እንደሚቀጠሩ ባለሥልጣናቱ ይፋ አድርገዋል፡፡

ኩዌት ከኢትዮጵያ በተጨማሪ ከዩጋንዳና ከኬንያ ሠራተኞችን ለመቅጠር እየሠራች መሆኑ ተገልጿል፡፡ አገሪቱ ወደ ምሥራቅ አፍሪካ አገሮች ፊቷን ያዞረችው ፊሊፒንስ ሠራተኞችን ወደ ኩዌት እንደማትልክ ማስታወቋን ተከትሎ መሆኑ ተዘግቧል፡፡ የኩዌት ባለሥልጣናት ይህን የፊሊፒንስ ሠራተኞችን እጥረት ለመሙላት እንደ ኢትዮጵያ ወዳሉ አገሮች ፊታቸውን አዙረዋል ተብሏል፡፡

በወር አማካይ የ300 ዶላር መነሻ ደመወዝ የሚቀጠሩት ኢትዮጵያውያን ክፍያ በሒደት እንደሚሻሻል ተዘግቧል፡፡ ወደ ኩዌት የሚሰማሩ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ሥልጠና የወሰዱ እንደሆነም ተነግሯል፡፡

የኢትዮጵያ የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ከሰሞኑ ይፋ እንዳደረገው ወደ ኦማንም ሠራተኞችን ለመላክ ስምምነት ላይ ተደርሷል ብሏል፡፡

በሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የሥራ ስምሪትና ገበያ ዘርፍ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ንጉሡ ጥላሁን ከኦማን የሥራ ስምሪት ልዑካን ቡድን ጋር ተገናኝተው መወያየታቸው ተነግሯል፡፡ በዚህ ውይይትም ወደ ኦማን የሚሰማሩ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች መብት የሚሻሻልበት ሁኔታ ተነስቷል ተብሏል፡፡

ሁለቱ ወገኖች ከዚህ ቀደም የነበረውን የሁለትዮሽ የሥራ ስምሪት ስምምነት ለማደስ ከመግባባት ላይ መድረሳቸውንም የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል፡፡ አዲስ ረቂቅ የሥራ ስምምነት ተረቆ በሕግ ባለሙያዎች ከተገመገመ በኋላ በኤምባሲዎች በኩል ይፀድቃል ያለው ሚኒስቴሩ ይህን ተከትሎም ኢትዮጵያውያን ሥራ ፈላጊዎች ወደ ኦማን ይላካሉ ብሏል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር መረጃ እንደጠቀሰው ወደ ኦማን የሚላኩት ሠራተኞች የቤት ውስጥ ሠራተኞች ብቻ ሳይሆኑ በምህንድስናና በሌሎች ሙያዎች ጭምር የሠለጠኑ ሠራተኞች ይሆናሎ ተብሏል፡፡

የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር በአሁኑ ወቅት በ77 የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ሥራ ፈላጊዎች እየሠለጠኑ መሆኑን ይፋ አድርጓል፡፡ ሥራ ፈላጊዎቹ ዓረብኛ ቋንቋን ጨምሮ የጠቅላላ ዕውቀት (አፕቲቲዩድ) እና ሌሎችም የክህሎት ሥልጠናዎች እየወሰዱ መሆኑን ሚኒስቴሩ ይፋ አድርጓል፡፡

ሚኒስቴሩ ከአንድ ወር ቀደም ብሎ ለሪፖርተር እንደተናገረው ከመላ አገሪቱ የተመለመሉ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የሚላኩ የመጀመርያ ዙር 36 ሺሕ ሥራ ፈላጊዎች ወደ ሥልጠና ተቋማት ገብተዋል ብሎ ነበር፡፡

እነዚህ ወደ ሳዑዲ የሚላኩ ሥራ ፈላጊዎችም በ1,000 የሳዑዲ ሪያል (በወቅቱ ምንዛሪ 14 ሺሕ የኢትዮጵያ ብር) ወርኃዊ ደመወዝ እንደሚቀጠሩ ሚኒስቴሩ ይፋ አድርጎ ነበር፡፡ በቅርቡ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጪ ጉዳይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን የተመራ ከፍተኛ ልዑክ ወደ ሳዑዲ እንደሚያቀናም ተሰምቷል፡፡

በእነዚህና በሌሎች ተያያዥ መረጃዎች ከሚኒስቴሩ ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት የተደረገው ጥረት ለጊዜው አልተሳካም፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...