Wednesday, September 27, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊመስማት ለተሳናቸው ተስፋ የፈነጠቀው ሥልጠና

መስማት ለተሳናቸው ተስፋ የፈነጠቀው ሥልጠና

ቀን:

በኢትዮጵያ መስማት የተሳናቸው ወገኖች የትምህርት ዕድል አግኝተው ቢማሩም፣ ትምህርታቸውን ከጨረሱ በኋላ ሥራ የማግኘት ዕድላቸው ጠባብ እንደሆነ ይወሳል፡፡ ይህ የዓይነ ሥውራንና የሌሎች የአካል ጉዳተኞችን  ችግር ጭምር ነው፡፡

ያለውን ችግር ለመፍታት ከሚደረጉት ጥረቶች አንዱ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁና ሥራ የሌላቸውን የአካል ጉዳተኞች የሥራ ዕድል በራሳቸው እንዲፈጥሩ ለማድረግ በመንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ተቋማት ሥልጠና መሰጠቱ ነው፡፡

ኮካ ኮላ ቤቨሬጅስ አፍሪካ ከወጣት ሴቶች ማቋቋሚያ ማኅበር ጋር በመሆንም 50 መስማት የተሳናቸው ወጣቶችን ለሦስት ወራት በቀርከሃ ሙያ በማሠልጠን አስመርቋል፡፡

በቀርከሃ ሙያ ሠልጥነው የሥራ ዕድል ካገኙት መካከል ወጣት አብርሃም የራስወርቅ ይገኝበታል፡፡ ኮካ ኮላ ቤቨሬጅስ አፍሪካ መስማት ለተሳናቸው ወጣቶች ባዘጋጀው ሥልጠና ተሳትፎ በቂ ክህሎት ማግኘቱን (በአስተርጓሚ በኩል) ለሪፖርተር ተናግሯል፡፡ በቀርከሃ ሙያ ሥልጠና ካገኘ በኋላ፣ ከጓደኞቹ ጋር በማኅበር በመደራጀት ጎተራ አካባቢ መንግሥት በሰጣቸው ሼድ ሱቅ ከፍተው ለመሥራት ቅድመ ዝግጅት ማድረጋቸውን ይናገራል፡፡ ከቀርከሃ የተለያዩ ጌጦችን፣ የልብስ ማስቀመጫ ቅርጫት፣ ወንበር፣ መሶብ፣ ሶፋና ሌሎች መሰል ቁሳቁሶችን በመሥራት ለገበያ የሚያቀርቡ መሆኑን ያስረዳል፡፡

በዚህ ሥራም ከራሱ አልፎ ቤተሰቦቹን ለመለወጥ ፍላጎት እንዳለው፣ መንግሥት ለአካል ጉዳተኞች የሰጠው ትኩረት በቂ ባለመሆኑ በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎች ችግር ውስጥ ወድቀዋል ይላል፡፡ አሥራ ሁለተኛ ክፍልን ማለፍ ባለመቻሉ ሥራ እንዳልነበረው፣ የሥልጠናውን አጋጣሚ ያገኘው በጓደኞቹ ምክንያት መሆኑን ይናገራል፡፡

መስማት የተሳናቸው ቢማሩም ሥራ እንደማያገኙና በሕይወታቸው ለውጥ እንደማይታይ፣ በአሁኑ ወቅት ያገኘነው ሥልጠና ሕይወቱን ለመለወጥ ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የሚናገረው አብርሃም፣ መንግሥት ለአካል ጉዳተኞች እንዲህ ዓይነት ዕድሎችን በማመቻቸት የበኩሉን ሊወጣ እንደሚገባም ይጠቁማል፡፡

በተመሳሳይ በዚሁ ሥልጠና የተሳተፈችው ወጣት ራሔል ወንድወሰን (በአስተርጓሚ በኩል) እንደገለጸችው፣ መስማት የተሳናቸው የሥራ ዕድል ባለማግኘታቸው የተነሳ ችግር ውስጥ ወድቀዋል፡፡ በኮካ ኮላ በኩል የተደረገላቸውን ሥልጠና ያገኘችው በሶሻል ሚዲያ አይታ እንደሆነና አሥራ ሁለተኛ ክፍልን ጨርሳ ቤት መቀመጥ ከጀመረች ረዥም ጊዜ እንደሆናት፣ አሁን ግን ይህንን ሥልጠና ማግኘቷ ለሕይወቷ ለውጥ እንደሚያመጣ ታስረዳለች፡፡  

ሥልጠናውን ካገኙ በኋላ መንግሥት ለተወሰኑ ሠልጣኞች ቦታ እንደሰጠ፣ በቀጣይ ግን የራሷን የቀርከሃ ጌጣ ጌጦችና የተለያዩ ምርቶች መሸጫ ሱቅ ለመክፈት ዕቅድ እንዳላት ትናገራለች፡፡ በዚህ ሥልጠናም በዘርፉ የተሻለ ዕውቀት እንዳገኘች የምትናገረው ወጣቷ፣ ይህን ሙያዋን በማስፋት ከጓደኞቿ ጋር ሆና ለመሥራት ዕቅድ እንዳላት ገልጻለች፡፡

የኮካ ኮላ ቤቨሬጅስ አፍሪካ የሕግና የሕዝብ ግንኙነት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ንጉሥ ዓለሙ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ኮካ ኮላ ቤቨሬጅስ ከኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች ማቋቋሚያ ማኅበር ጋር በመተባበር 50 መስማት የተሳናቸው ወጣቶችና ሴቶችን በቀርከሃ የዕደ ጥበብ ሙያ አሠልጥኗል፡፡

ሥልጠናውንም ለወሰዱት ወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር ቋሚ ገቢ እንዲያገኙ የሚያደርግ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ከዚህ በፊት የተለያዩ ሥልጠናዎችን በመስጠት ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል መፈጠሩን አስረድተዋል፡፡

ሴቶችና ወጣት አካል ጉዳተኞች ቀጣይነት ባላቸው የኢኮኖሚ አካታች ፕሮግራሞች አካል ሆነው የተሻሉ ዕድሎችን እንዲያገኙ ተቋሙ የበኩሉን ድርሻ እየተወጣ መሆኑንም አክለዋል፡፡

ለሦስት ወራት ተከታታይ ሥልጠና ከወሰዱት ውስጥ አብዛኛዎቹ ሴቶች መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ንጉሡ፣ እነዚህን ወጣቶች በማደራጀት መንግሥት በሰጣቸው ሼድ ውስጥ እንዲሠሩ ይደረጋል ብለዋል፡፡

ለተከታታይ ጊዜ ሥልጠናውን እንዲወስዱ ለማድረግ አንድ ሚሊዮን ብር ወጪ መደረጉን፣ መንግሥትም በቂርቆስ ክፍለ ከተማ አካባቢ 180 ካሬ ሜትር ሼድ መሰጠቱን ገልጸዋል፡፡

ለሠልጣኞች ሥራ ማከናወኛ መነሻ ገንዘብ ተቋሙ እንደሚሰጣቸው ገልጸው፣ በቀጣይም የተለያዩ ሥራዎችን ለመሥራት ዕቅድ ይዞ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

የወጣት ሴቶች ማቋቋሚያ ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ መንግሥቱ ጥላሁን ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የወጣት ሴቶች ማቋቋሚያ ማኅበር ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ በችግር ውስጥ ያሉ ወጣቶችና ሴቶች ለአልባሌ ነገር ተጋልጠው ሕይወታቸው እንዳይበላሽ ሥልጠናዎችን ይሰጣል፡፡

ማኅበሩ ከ15 እስከ 35 የዕድሜ ክልል ውስጥ ላሉ ወጣቶች አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን፣ በቀርከሃና በቆዳ ሥራ፣ በስልክ ስክሪን ሙያ ሥልጠናዎችን በመስጠት ዜጎችን ለቁምነገር ማብቃቱን ገልጸዋል፡፡

ማኅበሩ ከለጋሽ ድርጅቶች የሚያገኘው ድጋፍ እየተቆራረጠበት መሆኑንና ይህም ለሥራው እንቅፋት መፍጠሩን ሳይገልጹ አላለፉም፡፡

ባለፉት ዓመታት በቀርከሃ ሙያ ብቻ 293 ሠልጣኞችን ተቀብሎ ማሠልጠኑንና 216 ማስመረቁን ገልጸው፣ 77 ሠልጣኞች ደግሞ ሥልናውን ማቋረጣቸውን አክለዋል፡፡

በቆዳ ሥራ ሙያ ከተሳተፉት 88 ሠልጣኞች የተመረቁ ሲሆን፣ 61 ሠልጣኞች ሥልጠናውን ማቋረጣቸውን ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል በስልክ ስክሪን ሙያም 45 ሠልጣኞችን ተቀብሎ ሁለት ሠልጣኞች ያቋረጡ መሆኑን፣ በአጠቃላይም ሥልጠናውን በአግባቡ ወስደው ለምርቃት የበቁ ባለሙያዎች በአሁኑ ወቅት በማኅበር ተደራጅተው ራሳቸውን ችለው እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ከዚሁ ጋር ተያይዞም የኮካ ኮላ ፋብሪካ ባደረገው ድጋፍ፣ 50 መስማት የተሳናቸው ወጣቶች በቀርከሃ ሙያ ለሦስት ወራት በማሠልጠን ለቁምነገር እንዲበቁ ማድረግ ተችሏል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ ሥልጠናው ሰፍቶ ወጣቶችና ሴቶችን ለማብቃት ተቋሙ እየሠራ ቢሆንም፣ የበጀት እጥረት እየፈተነው መሆኑን ሥራ አስኪያጁ ገልጸዋል፡፡

ኮካ ኮላ ቤቨሬጅስ አፍሪካ ሥልጠናን ከመደገፍ ባሻገር በውኃ መስመር ዝርጋታና የፕላስቲክ ቆሻሻን መልሶ ከጥቅም ለማዋል እየሠራ መሆኑን፣ በቅርቡም የፕላስቲክ ቆሻሻን መልሶ ከጥቅም ለሚያውሉ 30 ማኅበራት 10 ሚሊዮን ብር መደገፉን ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአማራ ክልል ወቅታዊ ሁኔታ

እሑድ ጠዋት መስከረም 13 ቀን 2016 ዓ.ም. የፋኖ ታጣቂዎች...

ብሔራዊ ባንክ ለተመረጡ አልሚዎች የውጭ አካውንት እንዲከፍቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የፈቀደበት መመርያና ዝርዝሮቹ

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ አጠቃቀምንና ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮችን...

እነ ሰበብ ደርዳሪዎች!

ከሜክሲኮ ወደ ዓለም ባንክ ልንጓዝ ነው። ሾፌርና ወያላ ጎማ...