ዳግማዊ አፄ ምኒልክ በ19ኛው ክፍለ ዘመን መገባደጃ መናገሻ ከተማቸውን ከእንጦጦ አዲስ ወደ መሠረቷት አዲስ አበባ ሲያዘዋውሩ ወጣቷ ከተማ ብዙም ሳትቆይ የመንግሥቱ ሹማምንት መኳንንቱና የውጭ ባለ ሀብቶች ጭምር በሠሯቸው ቤቶች ተሞላች፡፡ ከእነዚህም መካከል በ1893 ዓ.ም. አካባቢ የተገነባውና ግንቦት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. በከፊል የተናደው ታሪካዊው የመሐመድ ዓሊ ቤት ተጠቃሽ ነው፡፡
አዲስ አበባ ከተመሠረተች ከ14 ዓመታት በኋላ፣ ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የኢትዮጵያ ዋና ከተማ ብለው ካወጁ ከስምንት ዓመታት በኋላ ነው፣ የመሐመድ ዓሊ ቤት በፋና ወጊው አርመናዊ መሐንዲስ ሚናስ ኬርቤኪያን በተነደፈው መሠረት የተገነባው፡፡ ቤቱ የህንድና ዓረባዊ ኪነ ሕንፃን ሥልትን የተከተለና ውበትን የተላበሰ መሆኑ በባለሙያዎቹ ይነገርለታል፡፡

ታሪካዊው ሕንፃ መፍረሱን ተከትሎ የኢትዮጵያ ኪነ ሕንፃና ሥነ ከተማ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ ቤቱ የፈረሰው ‹‹በከባድ እርጅናና ዕድሳት በማጣት ምክንያት ነው›› ብሏል፡፡ ቤቱ ከማርጀቱ የተነሳ አገልግሎት ካቆመ ብዙ አሠርታት መቆጠሩን ያወሳው ገጹ፣ ያልተሳካ ዕድሳት በየጊዜው እየተደረገለት የቆየ መሆኑም አስታውሷል፡፡
ቤቱ ለዓመታት አገልግሎት ሳይሰጥ ቢቆይም፣ እስከ ጥጉ ድረስ አነስተኛና መካከለኛ ተሸከርካሪዎች ተጎራብተው የሚቆሙበት/ለፓርኪንግ የሚጠቀሙበት መሆኑ በንቅናቄ ምክንያት ጉዳት ሳይደርስበት እንዳልቀረ ለሪፖርተር ግምታቸውን የሰነዘሩ አሉ፡፡
ሪፖርተር በሥፍራው ያገኛቸው አንድ አባት፣ ቤት ሰው ካልኖረበት የሚንከባከበውም ካልኖረ ለዚያውም ከ100 ዓመት በላይ ያስቆጠረ ቤት እንዴት ሊዘልቅ ይችላል ብለው በቁጭት ይጠይቃሉ፡፡ ቅርስ መሆኑ እየታወቀ ድሮ ንጉሡ የተቀመጡበት ቤትን እንዴት መንግሥት ችላ አለውም ይላሉ፡፡
ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ፣ ደጃዝማች ተፈሪ መኰንን በሚባሉበትና የአውራጃ ገዥ ሳሉ በ1897 ዓ.ም. አዲስ አበባ ሲመጡ ባረፉበት የመሐመድ ዓሊ ቤት ከባለሀብቱ ጋር ፎቶ ተነስተው ነበር፡፡
የዜናው ምንጭ እንደሚያሳየው፣ መሐመድ ሼክ ሸረፍ አሊ የጉጃራት ህንዳዊ ከበርቴ ሲሆኑ፣ በ20ኛው ምዕት ዓመት መሐመድ ዓሊና ኩባንያው በሚለው ተቋሙ አማካይነት በኢትዮጵያ መዋዓለ ንዋዩን አፍሶ እስከ ፋሺስት ጣልያን ወረራ ድረስ የሚያንቀሳቅስ ባለሀብት ነበር፡፡ ይህ አሁን የፈረሰው መኖሪያ ቤቱ ከአሮጌው ፖስታ ቤት ጀርባ የሚገኝ ሲሆን፣ የኩባንያው መሥሪያ ቤት ደግሞ ራሱ አሮጌው ፖስታ ቤት ነበር፡፡
ስለአዲስ አበባ ከተማ ታሪካዊ ሕንፃዎች በአንድ ወቅት ጥናታዊ ጽሑፍ ያቀረቡት ባህሩ ዘውዴ (ፕሮፌሰር)፣ የአዲስ አበባን ታሪካዊ ፋይዳን ነውን ከነበር እያጣቀሱ፣ ወቅትን ከክስተት እያመሳከሩ ሲዘረዝሩ የዕድገት ምዕራፎቿን በተለያዩ ምዕራፎች በመክፈል አሳይተዋል፡፡
ቀዳሚው ብለው ያነሱት ከ1928 ዓ.ም. በፊት ወይም ቅድመ ጣሊያን ወረራ የነበረው ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ የጥንታዊ ሕንፃዎችና ታሪካዊ ቅርሶች መሠረት የሆነው የአፄ ምኒልክ ግቢ (ታላቁ ቤተ መንግሥት) የተገነባበት ነው ብለዋል፡፡ ሌላው ማዕከል ደግሞ ጥንታዊው ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ጊዮርጊስ ሲሆን፣ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ የንግሥ ሥርዓት የተደረገበትና መናገሻ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሰኘበት ነው፡፡ ወደ ንግድ ማዕከልነት በመለወጥም አራዳን ሲወልድ፣ ብዙ ታሪካዊ ቅርሶችና ሕንፃዎች የመሐመድ ዓሊን ቤት ጨምሮ የተሠራበት ነው፡፡
ሦስተኛው ማዕከል ለገሀር ሲሆን፣ የባቡር ጣቢያው ሕንፃ መሠረት አዲስ አበባን ዱሮ ከነበረችበት ወደ ታች ስቦ የደቡብ አዲስ አበባን ዕድገት በሙሉ በእሱ ዙሪያ በማሽከርከር በዘመኑ ውብ ሕንፃዎች የህንድና ዓረባዊ ሥነ ሕንፃን ሥልትን የተከተሉም ተሠርተውበታል ብለዋል፡፡ በእነዚህ ዘመን የተሠሩት ከሁሉም የበለጠ ውበት ያላቸው ሕንፃዎች ናቸው ብለውም ጠቁመዋል፡፡