በአፍሪካ ከጀርባ ሕመም ጋር በተያያዘ በርካታ ሰዎች ለከፍተኛ የአካል ጉዳት እንደሚጋለጡ ይነገራል፡፡ በተለይ በሽታው ለረዥም ጊዜ በአንድ ቦታ ተቀምጠው በሚሠሩ ሰዎች የሚፀና ሲሆን፣ የጀርባን አከርካሪ አካል ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል፡፡
ቀድሞ ዕድሜን አስታኮ የሚከሰተው በሽታው አሁን ግን ለረዥም ጊዜ በአንድ ቦታ ተቀምጦ ስልክ እየነካኩ መዋል፣ እንዲሁም በቢሮ ውስጥ ለረዥም ጊዜ መቀመጥ በሽታው እየተባባሰ እንዲመጣ ማድረጉን ጥናቶች ያመለክታሉ፡፡
የበሽታው ስሜት ቀስ በቀስ እያደገ የሚመጣበት ባህሪ ስላለው በቶሎ ሕክምና ማግኘት ካልተቻለ ውጤቱ የከፋ ሊሆን ይችላል፡፡ በዓለም በሽታው በሒደት እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ፣ እ.ኤ.አ. ከ1895 ጀምሮ የአከርካሪ ካይሮፕራክቲክ (Spine Chiropractic) ሕክምና መጀመሩን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በአጥንት፣ በጡንቻና በመገጣጠሚያዎች ላይ ያሉ ችግሮችን ለማስወገድ ባለሙያዎቹ በእጆቻቸው የሚጠቀሙበት ሕክምና ካይሮፕራክቲክ ይባላል፡፡ ካይሮፕራክቲክ ደግሞ ባለሙያው ይጠራበታል፡፡
በዓለም በየዓመቱ ከ100 ሚሊዮን በላይ የጀርባ ሕመም እንደሚያጋጥም፣ በተለይ በአፍሪካ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ እንደመጣ ይገለጻል፡፡
በኢትዮጵያ አርሶ አደሩን፣ የቀን ሠራተኛውን እንዲሁም ቢሮ የሚውለው ሠራተኛ ላይ እየተዛመተ መምጣቱን ባለሙያዎች ያስረዳሉ፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞም በተለይ በኢትዮጵያ የሕሙማንና የጤና ተቋማት ቁጥር ተመጣጣኝ ባለመሆኑ ለጀርባና ለአከርካሪ አጥንት በቂ ሕክምና ማግኘት አዳጋች መሆኑ ይጠቀሳል፡፡
በአንፃሩ በኢትዮጵያ ከሁለት ዓመት በፊት የተቋቋመው ስፓይን ኢንስቲትዩት ኬር አክሲዮን ማኅበር በዘርፉ ያለውን ችግር ለመቅረፍ እየሠራ ይገኛል፡፡
ተቋሙ እ.ኤ.አ. በ2001 በዘርፉ ስፔሻሊስት የሆኑት ኪሮፕራክተር ሰላም አክሊሉ (ዶ/ር) አማካይነት ‹Spine First Chiropractic and Rehabilitation Wellness Clinic› በሚል ስያሜ ተቋሙን በአክሲዮን አቋቁሞ እየሠራ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡
ባለሙያዋ ሰላም (ዶ/ር) ባለፉት 20 ዓመታት ያካበቱትን ልምድ ተጠቅመው ወደ አክሲዮን ማኅበር በማሸጋገር በጤናው ዘርፍ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ ተጠቁሟል፡፡
ተቋሙ በጤናው ዘርፍ ያተኮሩ ፕሮጀክቶችንና የቢዝነስ ሥራዎችን የሚያስተዳድር ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል አንደኛው የአከርካሪ አጥንት ሕክምና የሚሰጡ በአዲስ አበባ ሦስት፣ በቢሾፍቱ ከተማ አንድ በድምሩ አራት ክሊኒኮችን ከፍቶ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
የጀርባ፣ የወገብና የአጥንት ሕመም በዓለም እየተስፋፋ በመምጣቱ፣ በአገር ኢኮኖሚ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ እንደሆነ የሚያስረዱት ዋና ሥራ አስኪያጇ ሰላም (ዶ/ር)፣ በተለይ አፍሪካን በአራት እጥፍ እያስቸገረ እንደሚገኝ ይገልጻሉ፡፡
‹‹ችግሩ የኑሯችን ዘይቤና ባለመረዳት ሕመሙ እየጎዳን ነው፡፡ ምክንያቱም ግንዛቤ ባለመኖሩ የመሥራት አቅም ያለውን ወጣት እያፈረሰ ነው፤›› በማለት ሰላም (ዶ/ር) ያብራራሉ፡፡
እንደ ባለሙያዋ ማብራሪያ ከሆነ፣ ኅብረተሰቡ የዕለት ከዕለት ሥራውን እንዴት መከወን እንዳለበት ባለመረዳት አብዛኛው የሕመሙ ተጋላጭ አድርጎታል፡፡
በተቋሙ ሥር የተቋቋሙ ክሊኒኮች የመጀመርያ ሥራቸው በኅብረተሰቡ ዘንድ ግንዛቤ ፈጥሮ፣ ቀድሞ በሽታውን መከላከል እንዲቻል ማድረግ እንደሆነ ዋና ሥራ አስኪያጇ ይናገራሉ፡፡
በክሊኒኮቹ የሚሰጠው የቴራፔ አገልግሎትም የአከርካሪ አጥንትን ቀጥ በማድረግ የነርቭ ሥርዓቱን በሙሉ እንዲስተካከል የሚረዳ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
አራተኛ ቅርንጫፉን በቢሾፍቱ ከተማ ግንቦት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. የከፈተው ስፓይን ዋን የፊዚዮ ቴራፒ ክሊኒክ በአከርካሪ አጥንት፣ በነርቭና ጡንቻ ሕክምና ላይ አተኩሮ እንደሚሠራ ሰላም (ዶ/ር) አብራርተዋል፡፡
ሕክምናው በዘመናዊ መሣሪያዎች (Electro Therapy, Muscle Stimulation Leather therapy) እንዲሁም በንዝረት (Shock Therapy) የታገዘ መሆኑም ተጠቁሟል፡፡
ሰዎች በሽታው እንዳያጋጥማቸው በመደበኛው ሥራቸው መካከል ለአሥር ደቂቃ ያህል የነርቭ ሥርዓታቸው እንዲንቀሳቀስ በማድረግ፣ ራሳቸውን ከበሽታው መከላከል እንደሚችሉ ባለሙያዋ ይመክራሉ፡፡
ተቋሙ በጤናው ዘርፍ የሚያደርገውን ተሳትፎ አጠናክሮ ለመቀጠል እንዲችል፣ ጀሞ አካባቢ ከመንግሥት በተረከበው መሬት እየገነባ ያለው ሆስፒታል (Spine Care and Rehabilitation Hospital) እየተጠናቀቀ መሆኑን፣ የስፓይን ኢንስቲትዩትና ኬር አክሲዮን ማኅበር ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሲሳይ ጌታቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
የሆስፒታሉ የመጀመርያ ሕንፃ በከፊል ተጠናቆ ሥራ ሲጀምር፣ በአንድ ጊዜ እስከ ከአከርካሪ አጥነት ሕመም ጋር ተያያዥነት ያላቸው 29 ታማሚዎችን ለማከም እንደሚያስችል አቶ ሲሳይ ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ በክሊኒኮቹ ከሚሰጠው የሕክምና አገልግሎት ባሻገር፣ በዘርፉ ተጨማሪ ባለሙያዎችን ለማፍራት በዲፕሎማ ደረጃ ትምህርት እየሰጠ እንደሚገኝ ተጠቁሟል፡፡