Sunday, September 24, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

በራሳቸው የተጣመረ ሥራ ፈውስን የሚያስገኙት ምግቦች

በኤፍሬም ያሬድ

አዲሱ ሳይንሳዊ አመለካከት ምግቦች ቀድሞ ወደነበሩበት የተከበረ ቦታ፣ ማለትም በአጭር የጊዜ ርቀት ውስጥ በዘመናውያኑ የፋርማሲውቲካል መድኃኒቶች በሞኖፖል ከመያዙ በፊት ወደነበረውና ሲወርድ ሲዋረድ፣ ወደመጣው የሕክምና ጥበብ ይመልሰናል፡፡ በሕክምና አዋቂዎቹ ዘንድ ለምግብ ያለው የተለየ ፍቅር ጥንታዊ ነው፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት ከአራት ሺሕ ዘመን አንስቶ በድንጋይና በመሳሰሉት ላይ ተጽፈው የሚገኙት እንደሚመሰክሩት ምግቦችን ለተወሰኑ በሽታዎች ማዘዝ የተለመደ ነበር፡፡

የዘመናዊው ሕክምና አባት ሒፖክተራተስ ምግብና ሕክምና ከቶውንም ሊለያዩ እንደማይችሉ አስቀምጧል፡፡ ለዚህም ነው «ምግብዎ መድኃኒትዎ ይሁን መድኃኒትዎም ምግብዎ ይሁን» የሚለው፡፡

በምሥራቃዊው የዓለም ክፍል ባህልም ምግብና ሕክምና የማይለያዩ አንድ ገጽታዎች ናቸው፡፡

ፔኒሲሊን የተገኘው ከሸጋታ ዳቦ ነው፡፡ በደሴት አካባቢ የሚኖሩ አያሌ ሰዎች አንዳንዴ ለፀረ ተህዋስያን (አንቲባዮቲክ) መድኃኒቶች አልበገሬ የሚሆኑት የምግቦቻቸው ውስጥ በብዛት የፀረ ተህዋስያንነት ተግባር ያላቸውን በማግኘታቸው መሆኑ ተደርሶበታል፡፡ ቴትራሳይክሊን በሱዳን ኑቤያውያን አባቶች በናይል ወንዝ አካባቢ በ350 ክፍለ ዘመን አልነበረም? አንትሮፖሎጂስቶች በእነዚህ ሕዝቦች የአጥንት ኢንፌክሽን በጣም አናሳ እንደነበር ዘግበዋል፡፡ ምናልባትም ከጥራጥሬዎች፣ ከቤራና ከመሳሰሉት ፀረ ጀርሞችን በመመገባቸው ሊሆን እንደሚችል አያይዘው ጠቁመዋል፡፡ የቼዮፕሰን ፒራሚድን በገነቡ ሰዎች የኢንፌክሽን በሽታ መዛመት በጣም አናሳ እንደነበር ተመልክቷል፡፡ አንድ አንትሮፖሎጂስት ስለዚህ ጉዳይ ሲያብራራ «ፍጅል ሽንኩርትና ነጭ ሽንኩርትን» አዘውተረው በመመገባቸው የተነሳ መሆኑን አስቀምጧል፡፡

በርግጥም ዛሬ እንዲህ ሳይንስ በመጠቀበትና በረቀቀበት ዘመን በምግብና በሕክምና መካከል ስላለው የአንድነት ዝንባሌ ሥልጣኔ የገባቸው እውቀት የጠለቃቸው የምርምር ወረቀቶችን በጥበብ የቀለሙ፣ በጥንታዊ ሰነዳቸው ኅብረተሰቡን የጠቀሙ የሥነ ሕይወት ሊቃውንት ደግፈውት የመገኘታቸውን ሁኔታ ስናጤን አስገራሚ ይሆንብናል፡፡ ይህም በአጭር ጊዜ ርቀት ውስጥ የመጠቃለሉ አጋጣሚ ይበልጡን አስደናቂ ሊሆን ይበቃል፡፡

በካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የሎስ አንጀለስ የሕክምና ኮሌጅ ፕሮፌሰር አርዎን ዚመንት (ዶ/ር)፣ «ምግብን እንደ መድኃኒት መውሰድ ዘመናዊዎች የፋርማሲውቲካል ኢንዱስትሪዎች እስከ ተስፋፉበት አሥራ ዘጠነኛው ክፍለ ዘመን ድረስ ዓይነተኛ መፍትሔ ነበር፤» ያሉትን ከእዚህ መጥቀሱ የተገባ ይሆናል፡፡ ዶ/ር ዚመንት የምግቦችን ኃይለኛ መድኃኒትነት የተቀበሉት የቀደምቱን «መድኃኒተኞች» አስተሳሰብን በማጤን ነው፡፡

ቢያንስ በሦስት ምክንያቶች በተለይም ሳይንስና ቴክኖሎጂ ባዘመነው የባሕር ማዶው አህጉር የሚገኙ ጠቢባን ክህሎቱ ሞገስ ይሁንላቸውና የፍተሻ ሰነዳቸውን አደባባይ በማውጣት በምግብ መድኃኒትነት ላይ እየተገኙ ያሉትን አዳዲስ ሳይንሳዊነትን የተላበሱ አስደናቂ ክንዋኔዎችን ይፋ አድርገውታል፡፡ እነዚህም ሳይንሳዊ አስተሳሰቦች ከተለያዩ ባህሎች በተለይም ከሩቅ ምሥራቅ መሻገራቸው፣ ተፈጥሮአዊ የሆኑ ነገሮችን ማድነቅ መጀመሩ/ጤናማ ምግቦች፣ ሆሌስቲክ ሜዲስን /ጠበል/ ወዘተና የሳይንስ ዕድገት ምግብ በሽታ ላይ ያለውን ተፅዕኖ እያስረገጠው መምጣቱ ነው፡፡

በማንኛውም ቅፅበት በሰውነትም ህዋሳት/ሴል/ ውስጥ ኬሚካላዊና ሥነ ሕይወታዊ ጦርነት ይከናወናል፡፡ በሽታ የሚከሠተው በህዋሳት ጠቅላላ መታወክና የሥራ እንቅስቃሴያቸው መሰናክል ሲፈጠር ሲሆን፣ ይህ ደግሞ በአጠቃላይ የሰውነት ተግባር ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል፡፡ የበሽታ ምልክቶችን እስካስተዋሉ ድረስ መለከፍዎን ሊያውቁ አይችሉም፡፡ ሁሌም ቢሆን ይህ ሁኔታ የሚፈጠርበት ዋናው ምክንያት እያንዳንዱ ህዋስ ወራሪውን ኃይል ለመጋፈጥ ያለውን ኃይል ሲጨምርና ሲሸነፍ ብቻ ነው፡፡  

በሥነ ሕይወት ሒደት ውስጥ መድኃኒትነት ያላቸው የምግብ ኬሚካሎች እያንዳንዱን ህዋስ ለመደምሰስ የሚጠጋውን ጠላት በማንኛውም መጠን ቢሆን ይከላከላል፡፡ አንዳንዶቹ ከበሽታ ፈውስን ቢያጐናፅፉም፣ ነገር ግን ባብዛኛው በረዥም የጊዜ ሒደት ውስጥ የሰውነትን ሕብረ ህዋሳት እየሸረሸሩ ወደ ካንሰር፣ የልብ በሽታ፣ ስር የሰደደና እስከአሁኗ ደቂቃ ምንም ልንረዳቸው ወዳልቻልናቸው ለምሳሌ ስኳር፣ አሪትራይስት፣ የአንጀትና የአዕምሮ ችግሮች እንዳይዳረግ በማይታይ መልኩ መሠረታዊነት ያለውን የመከልከል ዕርምጃ እንደሚወስዱ በምርምር የታቀፈ፣ በማስረጃ የተደገፈ የሊቃውንቱ የምርምር ውጤት ያበስራል፡፡

የምርምር ግኝቶች ብቅ ያሉት ከተለያዩ የዓለም ክፍሎች ሲሆን፣ ምግብም ሆነ በውስጡ የያዘው እያንዳንዱ ንጥር ያሠራር ሒደቱ ከዘመናዊ መድኃኒቶች ጋር በተመሳሳይ ሲሆን፣ አንዳንዱም በተሻለ ሁኔታ ያለምንም አስፈላጊ የጐን ውጤት መሆኑም ታውቋል፡፡ ለምሳሌ የፀረ ተህዋስያን መድኃኒቶች ቁስልን መፈወስ ሲሳናቸው ስኳር ብዙውን ጊዜ ይጠቅማል፡፡ እርጐ የአካል በሽታ መከላከያን በማዳበር አንፃር በተፈጥሮ ፈውስ አጋዥነቱ ለዚሁ ተብሎ ከተዘጋጀው መድኃኒት ተሽሎ ሲገኝ፣ ተቅማጥንም በማዳን ከመደበኛው መድኃኒት ፈጣን ነበር፡፡ በተጨማሪም እርጐ ከእውቁ ፔንሲሊን የሚጠነክሩ ልዩ ቁሶችን መያዙ ተደርሶበታል፡፡ ሽንኩርት የጠቀሜታውን /ኤችዲኤል/ ኮሌስትሮል ዓይነት መጠን በደም ውስጥ ከመጨመር አንፃር በቅርቡ አደባባይ የወጣውን ጨምሮ አብዛኛዎቹን የልብ መድኃኒቶች በውጤታማነት ልቆ መገኘቱን የምርምር ውጤቶች ያመላክታሉ፡፡ የነጭ ሽንኩርት ዉሕዶች አደገኛውን የደም መርጋትን በመከላከል ከእውቁ አስፕሪን ይመሳስላሉ፡፡ አሳ /በተለይም ማክሬል/ መለስተኛ የደም ግፊትን በመቀነስ ለዚሁ ተብለው የሚታዘዙ ዳዩሬቴክስ ተስተካክሏል፡፡ ዝንጅብል በጉዞ ወቅት የሚያጋጥም ሕመምን ከማስወገድ አንፃር ከድራማሜን ተሽሎ ተገኝቷል፡፡ ሁለት የሾርባ ማንኪያ ስኳር በመኝታ ሰዓት እንደ እንቅልፍ ክኒኖች ውጤታማ ነው፡፡ ቀይ የወይን ጠጅ ባክቴሪያን በመደምሰስ እንደ ፔኒሲሊን ጠቀሜታ ድርሻ ያበረክታል፡፡ እነዚህ የቀረቡት ከብዙ በጥቂቱ ነው፡፡

አብዛኛዎቹ በልማዳዊው ሕክምና ላይ የሚውሉ ቅመሞችና ቅጠላ ቅጠሎች የፀረ ተህዋስያን  ፀባይ እንዳላቸው ተጠቅሷል፡፡ አንዱ በሳል ተመራማሪ ከተፈጥሮ ምግቦችና ተክሎች የሚገኙት የፀረ ባክቴሪያነት ባሕርይ ያላቸው 63 የተለያዩ ኬሚካሎችን ወይም ንጥረ ነገሮችን በምርምር ድርሳናቸው ላይ ዘርዝረዋል፡፡ ፀረ ተህዋስያን የሆኑ ንጥረ ነገሮች ከተገኘባቸው የምግብ ዓይነቶች ፖም፣ በርበሬ፣ እንቁላል፣ ነጭ ሽንኩርት፣ ማር፣ ዝንጂብል፣ ሆንስ፣ ወተት፣ ሽንኩርት፣ ፍጁል፣ ሻይ፣ እርጐና ዝነኛው ጥቁር ማርና ቀይ እንጀራ ይገኙበታል፡፡

በላኤ ፍሬ አትክልት (አትክልትና ፍራ ፍሬ የሚመገቡ) የሆኑ ሰዎች ከዕድሜና ጾታ አንፃር ተወስደው የደም ግፊታቸው /ዝቅተኛው ቁጥር/ ሥጋን አዘውትረው ከሚመገቡ ዜጐች በ18 በመቶ መቀነስ ማሳየቱ ተደርሶበታል፡፡ መደበኛ የደም ግፊት ባለባቸው ተሞክሮ ከአምስት እስከ ስድስት መቀነስ ታይቷል፡፡ ምግብ በየቀኑ ወደሰውነታችን የምናስገባው መድኃኒት መሆኑን ለመቀበል የሚከተለውን ምጥን ትንታኔም እንመልከት፡፡

ምንም እንኳ ጥበብ በተሰየመባቸው በነዚያ የጉባኤ አዳራሾች ብቻ በግልጽ ቢወያዩበትም የዓይነ ምድር መጠን መብዛት ለአንጀት ጤና የሚያበረክተው ድርሻ ቀላል ሆኖ አልተገኘም፡፡ ከአንጀትና ፊንጢጣ ካንሰር ሥጋት ለመገላገል፣ ከኪንታሮት በሽታ ነፃ ለመሆን፣ በተወሰነ ሰዓት ደጅ የመውጣት ቋሚ ልምድን ለማዳበር የዓይነ ምድር መጠንን የሚጨምሩት ባቄላንና  የመሳሰሉት አሠር የበዛባቸውን ምግቦች አዘውትሮ መመገብ ጠቃሚ እንደሆነ የሙያው ሰዎች አበክረው ይገልጻሉ፡፡

መመገብ ዛሬ ትልቅ የፋርማኮሎጂካል ሙከራ እየሆነ መጥቷል፡፡ በአንዳንድ ሳይንቲስቶች ግምትና አስተሳሰብ በቅርብ ጊዜያት ውስጥ ምግቦች በተናጠል እንደ መድኃኒት እየታዘዙ የጤንነትን ልክ ወደር በሌለው ሁኔታ ለማሻሻል ያላቸው ውጤታማነት ከጥቅም እንደሚውልና ይህ ደግሞ በግኝቱ ልዩ ምዕራፍ እንደሚጨብጥ አስምረውበታል፡፡ የቶሮንቶ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰርና በማዕድና የደም ስኳር ዋና ኤክስፐርቱ ዳውድ ጃንኪንስ (ዶ/ር)፣ ምግቦች በውስጣቸው ድንገተኛ መድኃኒቶችን አምቀው እንደያዙ ገልጸዋል፡፡

ፕሮፌሰሩ አያይዘው እንዳስታወቁት «ሰዎች ሁል ጊዜ ስለ ፋርማኮሎጂ ሲያወሩ የተጣመረ ሕክምናን እያጠኑ ነው፡፡ አንዳንድ ምግቦች የሚያከናውኑት እኛ ግን ሊከሰትልን ያልቻለ ሐቅ ይህ ነው፤ ማለትም ምግቦች በራሳቸው የተጣመረ ሥራ ፈውስን ያስገኛሉ የሚለውን ነው፤» ብለዋል፡፡

ዶ/ር ጃንኪንስ ሲያጠቃልሉ እስከ አሁን ድረስ ምግቦችን በልዩ ሁኔታ ሳይንሳዊ በሆነ መንገድ አንጠቀምባቸውም፣ ቢሆንም ግን ይህ የሚመጣው በጣም ከመጠቀ እውቀት እንደሆነ አላጣሁትም ብለዋል፡፡ ለማጠቃለል እነዚህን ነጥቦች መመልከቱ አስፈላጊ ይሆናል፡፡

ምግቦች አካል የሚጠግኑ፣ ኃይልና ጥንካሬ የሚያጎናፅፉ፣ ከበሽታ ነፃ የሚያደርጉ ሁለገብ መድኃኒቶች መሆናቸውን፤ ስለምንመገበው ምግብ ሥሪትና ጥራት ግንዛቤና ጥንቃቄ ትኩረትም ማድረግ ይገባናል፡፡ በአመጋገብ ላይ አነስተኛ ለውጦችን በማድረግ በአብዛኛው የጤና ውጤት ሊያስገኝልዎ የሚችሉትን /ይሄኛውን አልወድም ከማለት/ በመምረጥ ብዛት ያላቸውን ስር የሰደዱ ሕመሞችን ለምሳሌ እንደ ኢንፌክሽን፣ ልብ በሽታ፣ ካንሰር፣ ስኳር፣ ደም ግፊት፣ ሆድ ድርቀት፣ አልሰር አሪትራይተስ፣ የጨጓራና የአንጀት ሕመሞች፣ ራስ ምታት፣ ኢንፍላሜሽን፣ እንቅልፍ ማጣትና የመሳሰሉት ሕመሞች ለማስታገስም ሆነ ለመከላከል እንደሚጠቅምዎት ይወቁበት፡፡

ስለ ምግብ መድኃኒትነት ያለን አስተሳሰብ  ዓይነታዊ ለውጥን እየያዘ መጥቷል፡፡ ምንኛ አስደናቂ መሠረታዊ  ለውጥ ነው፡፡ እኛም እንደ ሒፖክራተስ ምግብ እንደ ኃይለኛ መድኃኒት መቆጠር እንደሚገባው መገንዘብ ጀምረናል፡፡

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_imgspot_img
- Advertisment -

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

Related Articles