Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዝንቅያለ ፈቃዷ አይሆንም

ያለ ፈቃዷ አይሆንም

ቀን:

የጎጃሙ ንጉሥ ተክለሀይማኖት ከሞቱ ከጥቂት አመታት በሁዋላ ሴት ልጃቸው ወይዘሪት ንግስት የዚህን ዓለም ጣጣ ሸሽታ በዲማ ገዳም ተቀምጣ ነበር፤ ብዙ ሳይቆይ አድራሻዋ ተደረሰበት! በዘመኑ ያሉት ሀያላን ወንዶች ካላገባናት ብለው መፎካከር ጀመሩ፤ ከፖለቲካ ፋይዳው አንጻር ካየነው በጊዜው፥ የንጉሡን ልጅ ማግባት ሙሉ ጎጃምን እንደማግባት ነው! አንዱ የእቴጌ ጣይቱ የእህት ልጅ ደጃዝማች ገሰሰ ሲሆን ሁለተኛው ተፎካካሪ የዳሞቱ ገዢ ራስ መርእድ ነበር፤

እንደምትገምቱት ፥ በጊዜው ሴቶች በራሳቸው ላይ የመወሰን መብት አልነበራቸውም፤ ይመረጣሉ እንጂ አይመርጡም! ወይዘሮ ንግስትን የቱ ይሻልሻል ብሎ የጠየቃት የለም፤ እንደ አስቴር አወቀ ‘ ነጻ ነኝ ! ነጻ ነኝ “ እያለች የመቀመጥ እድሉን አልሰጧትም::

የዳሞቱ ገዢ ንግስትን ለማግባት ወስኖ በርበሬ መቀነጣጠስ ጀመረ፤ በዚያ በኩል፥ እቴጌ ጣይቱ ለዘመዳቸው በማዳላት “ ደጃች ገሰሰ ይሻልሻል “ የሚል ይዘት ያለው ደብዳቤ ጻፉላት፤ ሴቲቱ ቢጨንቃት ለአጼ ምኒልክ “ እናቴም አባቴም እርስዎ ነዎት! እርስዎ ለወደዱት ይዳሩኝ “ የሚል ደብዳቤ ወደ ሸዋ ሰደደች::

አጼ ምኒልከ የመለሱት ምላሽ በአለቃ ተክለየሱስ ዋቅጅራ ታሪክ ውስጥ ተመዝግቧል ፥ በከፊል እንዲህ ይላል፤

“ አንቺ ልብሽ ከወደደው ፥ከሰዎች ጋራ መክረሽ ሂጂ ፥ ቢከፋሽ እኔ አለሁልሽ “

ይህንን ያጼ ምኒልክ ምላሽ የዳሞቱ ገዢ በሰማ ጊዜ ፥ ላጼ ምኒልክ የተቃውሞ አቤቱታ አቀረበ፤ ንጉሱ ቃል በቃል እንዲህ ብለው መለሱ፤

“ እሺ ታለች እኔ አልከለክልም ! ያለ ፈቃድዋ ግን አይሆንም! እዚያው እርስዋን ማቆላመጥ ነው፡”::

ዘመናይ ከተሜ አንባቢያን ፤ ማቆላመጥ የሚለውን ቃል መጀንጀን፤ ማሞጋገስ ብላችሁ ልትረዱት ትችላላችሁ::

በወይዘሪት ንግስት ጉዳይ ዙርያ፥ የእቴጌ ጣይቱንና የባልየውን ምላሽ ሳነጻጽር፥ ለካ የመጀመርያው የሴቶች መብት ሻምፒዮን ወንድ ኑሯል እላለሁ፡፡

በሌላ በኩል፤ ከመቶ አመት የዘገየ አስተሳሰብ ያለው ወንድ በዘመናችን በመኖሩ እገረማለሁ፤

ሰሞኑን የወልቂጤዋን ቆንጆ ጠለፋ ዜና ሲወጣ “ የኔ ባረገው ! ወይም በረከትሽ ይደርብን” አይነት ቀልድ ቀመስ አስተያየት የጻፉት ሴቶች ታይተዋል፤ በነዚህ ሴቶች ዙርያ ቁጣ አዘል ምላሽ ከወዳጆቻችን ሲሰነዘር ነበር፤ ምላሹ ተገቢ መሰለኝ: :

ግን ግን እኒህ ሴቶች ኦሪጅናል ገልቱ፥ ወይም አምስት ኮከብ ሰገጤ መሆናቸውን እያወጁ ነው? ወይስ ሴዲስት ናቸው? ( በሌላው ስቃይ የሚደሰት ሰው ሴዲስት ይባላል) ፤ ወይስ የራሳቸውን ፌንታዚ በልጂቷ ዜና ላይ እያንጸባረቁ ይሆን ?

ፌንታዚ (Fantasy)

ፌንታዚ ከራሳችን ያልተገደበ ሀሳብ ጋራ መጫወት ማለት ነው፤ ሰዎች እንደየ ምናባቸው ስፋት መጠን የተለያዩ ስእሎችን በአአምሮቸው ይፈጥራሉ፤ ለመቀበል ከባድ ቢሆንም የመጠለፍ ፌንታዚ ያላቸው ሴቶች አሉ፤ እዚህ ጋ ወንዶች ልብ አድርጉ! ፌንታዚ ፍላጎትን የሚያንጸባርቅ ላይሆን ይችላል፤ ሰዎች ድንገት በልቦናቸው ሽው የሚልባቸውን ሀሳብ ሁሉ በገሀድ እንዲፈጸም ይፈልጋሉ ማለት አይደለም! ከሞላ ጎደል ሁላችንም የአደጋ ስሜት ይስበናል!፤ የአደጋ ስሜት ልብን በፍጥነት ያስመታል! ቀልብን ሰቅዞ ይይዛል፤ ከመሰላቸት ከመታከት ይገላግላል፤ ሆረር ፊልም ላይ የምንቸከለው ለዚያ ነው፤

ይሁን እንጂ የገሀዱ አለም ከህልም አለም የበለጠ ውስብስብ መሆኑን የኖረ ያውቀዋል፤ ስልጣኔና ህግ የተፈጠረው ሰዎችን ካላስፈላጊ መከራ ለመታደግ ነው፤ የስልጣኔ ተካፋይ ነን ብለን የምናምን ከሆነ፥ “ ያለ ፈቃድዋ አይሆንም “ማለት አለብን !

  • በዕውቀቱ ሥዩም በማኅበራዊ ትስስር ገጹ እንደጻፈው

*******

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...