Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዋሽ ባንክ የብድር ክምችት ከ161 ቢሊዮን ብር በላይ መድረሱ ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዋሽ ባንክ አጠቃላይ የሀብት መጠን ከ217 ቢሊዮን ብር እንዲሁም አጠቃላይ የብድር ክምችቱ ከ161 ቢሊዮን ብር እንደላቀ ተገለጸ፡፡

ባንኩ ሰሞኑን ‹‹ታታሪዎቹ›› በሚል የፈጠራ ሥራ ባለቤቶችን ለመደገፍ ባሰናዳው የአሸናፊዎች ሽልማትና ያመቻቸውን ከወለድ ነፃ ብድር ይፋ ባደረገበት ፕሮግራም ላይ የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ፀሐይ ሽፈራው እንደገለጹት፣ ባንካቸው በሁሉም ዘርፍ አፈጻጸሙ ከቀደሙት ዓመታት የላቀ ውጤት አስመዝግቧል፡፡

በተለይ የሀብት መጠኑን በማሳደጉ ረገድ በሒሳብ ዓመቱ አስረኛ ወር ላይ አጠቃላይ የሀብት መጠኑን ከ217 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ መቻሉን ጠቁመዋል፡፡

አዋሽ ባንክ በዚህ የሒሳብ ዓመት የተቀማጭ ሒሳብ ደንበኞቹን ቁጥር ከ10 ሚሊዮን በላይ ማሻገር የቻለ ሲሆን፣ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑንም ከ173 ቢሊዮን ብር በላይ ማድረስ እንደቻለ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡

ባንኩ በተለይ የሀብት መጠኑ በኢንዱስትሪው ውስጥ ከግል ባንኮች ከፍተኛው ሆኖ የተመዘገበ ሲሆን፣ የሀብት መጠኑን ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ ያሻገረ የመጀመርያው የግል ባንክ እንደሚያደርገው ለማወቅ ተችሏል፡፡

ባንኩ ማኅበራዊ ኃላፊነቱን ከመወጣት አኳያ እየሠራ ያለውን ሥራ በተመለከተ፣ ‹‹ታታሪዎቹ›› በሚል መርሐ ግብር ባዘጋጃቸው ሁለት ፕሮግራሞች ለአሥራ አንድ የሥራ ፈጣሪዎች እንደ ደረጃቸው ሽልማትና ብድር ማመቻቸቱን አስታውቋል፡፡ 

ግንቦት 22 ቀን 2015 ዓ.ም. በተካሄደው መርሐ ግብር ከበርካታ ተወዳዳሪዎች የመጨረሻዎቹ አሸናፊዎች በዳኞች ውሳኔ ተለይተው ሽልማታቸውን ተቀብለዋል፡፡ በዚሁ መሠረት አንደኛ ለወጣው አሸናፊ 1 ሚሊዮን ብር፣ ለሁለተኛ አሸናፊው 700 ሺሕ ብር፣ ለሦስተኛ አሸናፊው 500 ሺሕ ብር፣ ለአራተኛው አሸናፊ 300 ሺሕ ብር እንዲሁም ለአምስተኛው አሸናፊ 200 ሺሕ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡

በኦቢኤን ቴሌቪዥን ሲካሄድ የነበረው በሌላው የታታሪ ውድድሮች ላይ አሸናፊ የሆኑት ስድስት ተወዳዳሪዎችም በየደረጃቸው ተመሳሳይ ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ ሁሉም የሥራ ፈጠራ አሸናፊዎች እስከ አምስት ሚሊዮን ብር ከወለድ ነፃ ብድር የተመቻቸላቸው መሆኑ ተገልጿል፡፡   

ታታሪዎቹ መርሐ ግብር በዋነኛነት የሚያተኩረው የሥራ ፈጣሪዎች የሚገጥማቸውን የክህሎት፣ የሥራ መነሻ ካፒታልና ብድር ማመቻቸት ሲሆን፣ የዚህ ዕድል ተጠቃሚ ሥራ ፈጣሪዎችም ከራሳቸውና በሥራቸው ከሚኖሩ ተጨማሪ ሠራተኞች አልፈው ለአገራቸው የሚተርፉ ብቁ ዜጎች ይሆናሉ ተብሎ የሚታመን መሆኑን አቶ ፀሐይ ተናግረዋል፡፡  

በዚህ የሥራ ፈጠራ ውድድር ላይ አዳዲስና ችግር ፈቺ የሆኑ የሥራ ሐሳብ ያላቸው ዜጎች የተሳተፉበት ነው፡፡ ለውድድሩ ከስምንት ሺሕ በላይ ተወዳዳሪዎች ተመዝግበው፣ ከ1,200 በላይ የሚሆኑት ሥራ ፈጣሪዎች ባንኩ የውድድር ሒደቱን ከመጀመርያው እስከ መጨረሻው እንዲመራው በመረጠው ፈርስት ሪዛልት በተባለ አማካሪ ድርጅት አማካይነት ተለይተዋል፡፡ በሁሉም ክልሎችና በሁለቱ ከተማ መስተዳድሮች በተመረጡ ማዕከላትም የክህሎት ሥልጠና እንዲወሰዱ ተደርጎ እንደነበር ተገልጿል፡፡

እንደ ባንኩ፣ በመጀመርያው ዙር ለተሳተፉ ሁሉም ሠልጣኞች ሰርተፊኬትና መጠነኛ የኪስ ገንዘብ እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡ ሥልጠናውን ከወሰዱ 1,200 በላይ ተሳታፊዎች ውስጥ ከሥልጠናው በኋላ በቀረበ የቢዝነስ ፕላንና አስቀድሞ በተቀመጠ የምዘና መሥፈርት ተገምግሞ የተሻለ የሥራ ፈጠራ ሐሳብና ሥራ ላይ ሊውል የሚችል የቢዝነስ ዕቅድ ያቀረቡ 133 የሥራ ፈጣሪዎች ወደሚቀጥለው እንዲያልፉ ተደርጓል፡፡  

የሥራ ፈጠራ ውድድር በፋና ብሮድካስቲንግና በኦቢኤን ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ለስምንት ተከታታይ ሳምንታት እየተላለፈ ይገኛል፡፡ የውድድሩ አማካሪ ድርጅት ባቀረባቸው ታዋቂ ባለሙያዎችና የከፍተኛ የትምህርት ተቋማት መምህራንና ተመራማሪዎች በተውጣጡ የዳኞች ኮሚቴ እንዲመራ ተደርጓል፡፡ ውድድሩም ሥራ ፈጣሪዎች ሐሳባቸውን በሚገባ የሚገልጹበት እንዲሆን በማሰብ በአማርኛና በአፋን ኦሮሞ መካሄዱንም ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች