Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ፀደይ ባንክ ካፒታሉን ወደ 65 ቢሊዮን ብር ከፍ ሊያደርግ ነው

ተዛማጅ ፅሁፎች

ፀደይ ባንክ አክሲዮን ማኅበር አሁን ካለበት 11.6 ቢሊዮን ካፒታል ወደ 65 ቢሊዮን ብር ለማሳደግ የአክሲዮን ድርሻ ሊሸጥ መሆኑን አስታወቀ፡፡

ባንኩ ይህንን ያስታወቀው ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. በስካይ ላይት ሆቴል የብራንድ አምባሳደር የመሰየም መርሐ ግብር ባካሄደበት ወቅት ባንኩ ካፒታሉን ለማሳደግ እያደረገ ስላለው እንቅስቃሴ ከሪፖርተር ጋዜጣ ለተጠየቀው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጥ ነው፡፡

የፀደይ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መኮንን ያለውወሰን፣ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን (ዳያስፖራውን) እና ሌሎች የኅብረተሰብ ክፍሎች አክሲዮን እንዲገዙ ለማድረግ ሥራዎችን እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡

ባንኩን ለማሳደግ ያቀደውን 65 ቢሊዮን ብር ካፒታል በተያዘለት የሥራ ቀደም ተከተል መሠረት እየተከናወነ መሆኑን፣ በቅርቡም ሽያጩን ለሕዝብ ይፋ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡

ባንኩ በአሁኑ ወቅት ካፒታሉ 11.6 ቢሊዮን ብር ሲሆን፣ አጠቃላይ ሀብቱ ደግሞ 49.7 ቢሊዮን ብር መድረሱንና ደንበኞቹም ከ13 ሚሊዮን በላይ መብለጣቸው ተገልጿል፡፡

የባንኩ የተፈረመና የተከፈለ ካፒታል ከ7,749,050,000 ሲሆን፣ የባንኩ ካፒታል እያንዳንዳቸው 10 ሺሕ ብር ዋጋ ባላቸው 774,907 አክሲዮኖች የተመዘገቡና የተከፋፈሉ ናቸው፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ባንኩ የግብርና ማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ላይ ኢንቨስት ለማድረግ የተለያዩ ሥራዎች እየሠራ መሆኑንና ያለውን ዕምቅ ሀብት ለማውጣት ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ ባለው ተጨባጭ ሁኔታ የግብርናው ዘርፍ 80 በመቶ የኅብረተሰብ ክፍሉን ያቀፈ መሆኑን ጠቅሰው፣ ይኼ ትኩረት ሳይሰጠው ሌላው ዘርፍ ላይ ወይም 20 በመቶ ላይ ብቻ ትኩረት ማድረግ ለአገር ጠቃሚ አይደለም ይላሉ፡፡

እምቅ ሀብት ያለው 20 በመቶ መሆኑን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ እነዚህ ላይ ብቻ ኢንቨስትመንት ከቀጠለ ድህነቱና ያለው የኑሮ ውድነት እየተጠናከረ ይሄዳል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የኑሮ ውድነቱ ምንጭ በአገር ውስጥ የሚመረተው ምርት ዝቅተኛ መሆኑን እንደ ምክንያት አንስተው፣ የሚመረተው አንሶ ከፍላጎት ጋር የሚጣጣም ባለመሆኑ ችግሩ መጉላቱን ገልጸዋል፡፡

በዚህም ባንኩ በግብርናውና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፎች ኢንቨስት ለማድረግ ዘርፉ ብዙ ስትራቴጂዎችን በመቅረፅ ላይ እንደሚገኝ ተናግረዋል፡፡

በማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ከግብርናው በተጨማሪ ኢንቨስት የማድረግ ዕቅድ ያለው ፀደይ ባንክ፣ ዘርፉ ላይ ትኩረት በማድረግ እንደሚሠራ ገልጿል፡፡

እንደ አቶ መኮንን ገለጻ፣ የታሰበውን ዕቅድ ለማሳካት መንግሥት በግብርናና በማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ላይ እጁን ማስገባት አለበት፡፡

ግብርናው ብዙ ግብዓትና ዕገዛ ያስፈልገዋል ያሉት አቶ መኮንን፣ መንግሥት የተወሰነ ጣልቃ ቢገባና ባንኩ ደግሞ ለዘርፎቹ ኢንቨስት ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በዕለቱ በባንኮች የተከሰተውን የጥሬ ገንዘብ እጥረት ዙሪያ ምላሽ የሰጡት አቶ መኮንን፣ ፀደይ ባንክ ግን የዚህ ችግር ገፈት ቀማሽ ነው ለማለት አያስደፍርም ብለዋል፡፡

በ1988 ዓ.ም. የአማራ ብድርና ቁጠባና የገጠር ብድር አገልግሎት በሚል ብድር ሲቀርብ መቆየቱ ይታወሳል፡፡

በፌዴራል መንግሥት አዋጅ ቁጥር 40/88 መሠረት፣ ‹‹የገጠር ብድር አገልግሎት›› ወደ ‹‹አማራ ብድርና ቁጠባ ተቋም አክሲዮን ማኅበር›› አድጓል፡፡

የቀድሞ ብድርና ቁጠባ አክሲዮን ማኅበር የዛሬ ፀደይ ባንክ በሦስት ሚሊዮን ብር ካፒታል በመነሳት፣ ጠቅላላ ሀብቱ ወደ 45.6 ቢሊዮን ብር ማደጉን ተገልጿል፡፡

የተጣራ ካፒታሉ 11.3 ቢሊዮን ብር፣ ከ600 ያላነሱ ቅርንጫፎችን በመክፈት አገልግሎቱን በማሳለጥ ላይ እንደሚገኝ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች