በተለያዩ አገሮች ሲከናወን የከረመው የሊግ ውድድር እየተገባደደ ነው፡፡ ሻምፒዮን መሆናቸውን ያረጋገጡ ክለቦችና ወደ ታችኛው ሊግ የወረዱ ክለቦችም ተለይተዋል፡፡
ዘመናዊ እግር ኳስ ባየለበት በዚህ ዘመን፣ አንድ ክለብ ከሌላው ክለብ የሚለይበት የአጨዋወት ቴክኒክ እየጠበበ ሄዷል፡፡ ምንም እንኳን አሸናፊና ተሸናፊ አቻነት በ90 ደቂቃ ውስጥ መለየታቸው የእግር ኳሱ ሕግ ቢሆንም፣ ክለብ ከክለብ ጋር ያለው ልዩነት እየጠበበ መጥቷል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ2016 በኋላ የአውሮፓ እግር ኳስ ከዓመት ዓመት እየተለወጠና እየተሻሻለ መምጣቱ ይነሳል፡፡ ይህም የዘመኑ እግር ኳስ በፍጥነት የተሞላ እንዲሁም ተጫዋቾች በተቃራኒ ቡድን ሜዳ ጫና ፈጥረው መጫወትን እያዘወተሩ መምጣታቸውን ያነሳሉ፡፡
በሜዳ ለሚታየው እንቅስቃሴ አሠልጣኞች አዳዲስ ታክቲኮችን ወደ መሬት በማውረድ እግር ኳሱ የበለጠ እንዲቀራረብ አስችለውታል፡፡
ክለቦች ስኬታማ ጊዜ ለማሳለፍና ማራኪ የአጨዋወት ዘይቤን ለመከተል ዘመናዊ መንገድ መከተል ግድ ይላቸዋል፡፡
በአውሮፓ የዓለምን ቀለብ መግዛት የቻለ እግር ኳስ ማስመልከት የቻሉ ክለቦች ከሜዳ እንቅስቃሴ ባሻገር በፋይናንስና በአስተዳደራዊ መዋቅራቸው የዘመኑ ናቸው፡፡ ዘመናዊ የክለብ አስተዳደር ከመከተል በዘለለ ራሳቸውን ወደ ገበያ በማውጣት ዘላቂ የሆነ የገንዘብ ምንጭ ይፈጥራሉ፡፡
ምንም እንኳ የአውሮፓ እግር ኳስ ያለበት ደረጃ ከሌሎች አኅጉራት ጋር ሲተያይ ተመጣጣኝ ባይሆንም፣ በአፍሪካ የሚገኙ ክለቦች የሚከተሏቸው መንገዶች ተስፋ የሚሰጥ ነው፡፡ በተለይ የሞሮኮ፣ አልጀሪያ፣ ቱኒዝያ፣ ግብፅ፣ ደቡብ አፍሪካና የታንዛኒያ ሊጎች የተሻሉ ናቸው፡፡ የእነዚህ አገሮች ክለቦች በአስተዳደራዊ መዋቅራቸው እንዲሁም በፋይናንስ አቅም ከመፍጠር አንፃር የተሻሉ ናቸው፡፡
ጊዜው ዘመናዊ መንገዶችን ለመከተል የሚያስችል ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ የእግር ኳስ ክለቦች ጉዞ ግን ውኃ ቅዳ ውኃ መልስ ሆነው ቀጥለዋል፡፡ ከ20 ዓመታት በላይ የተሻገረው የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እያደገ ይሄዳል ቢባልም በተቃራኒው መጓዙን ቀጥሏል፡፡
16 ክለቦችን የሚያሳትፈውና በአክሲዮን ማኅበር መተዳደር የጀመረው ፕሪሚየር ሊጉ፣ በውድድር ሒደት ወደ ታችኛው ሊግ የሚወርዱና ወደ ላይ የሚወጡ ክለቦች ቢኖሩም ከውስብስብ ችግራቸው መላቀቅ አልቻሉም።
የ2015 ዓ.ም. የእግር ኳስ ውድድሮች መጠናቀቃቸውን ተከትሎ ከከፍተኛ ሊግ ንግድ ባንክ፣ ሻሸመኔ ከተማና ሀምበሪቾ ዱራሜ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ማደጋቸውን ያረጋገጡ ክለቦች ሆነዋል፡፡ ክለቦቹ ወደ ፕሪሚየር ሊግ ማደጋቸውን ተከትሎ በከፍተኛ ሊግ ከነበረው የተሻለ ቡድን ይዘው ለመቅረብና በሊጉ መቆየት የሚያስችላቸውን ዕቅድ ይዘው ይቀርቡ ይሆን የሚለው እየተነሳ ነው፡፡
‹‹አብዛኛው ወደ ከፍተኛ ሊግና ወደ ፕሪሚየር ሊግ የሚያድግ ክለብ በታችኛው ሊግ የነበረውን አመለካከት ይዞ ነው የሚቀርበው፤›› በማለት የሶከር ኢትዮጵያ የስፖርት ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ ታከለ አስተያየቱን ይሰጣል።
ክለቦቹ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ማደጋቸውን እንጂ መከተል ስለሚገባቸው መንገድ ግንዛቤ የሌላቸው መሆኑን ይገልጻል፡፡
ዓምና ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደገው ለገጣፎ ለገዳዲ በመጣበት ዓመት ተመልሷል፡፡ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በተመሳሳይ ወደ ከፍተኛ ሊግ መውረዱን አረጋግጧል።
ለገጣፎ ወደ ሊጉ ሲያድግ የፋይናንስና አስተዳደር ችግሮች ሲፈትኑት እንደቆዩ ይጠቀሳል፡፡ በዚህም ምክንያት ለአራት ወራት ለተጫዋቾች ደመወዝ ሳይከፍል መቆየቱ ይነገራል፡፡
‹‹ለገጣፎ ሲቲ ካፕ ላይ የነበረው እንቅስቃሴ ጥሩ ስለነበር በሊጉም ጥሩ ተሳትፎ ይኖረኛል የሚል እምነት ይዞ ነበር ሲሳተፍ የነበረው፡፡ በአንፃሩ ሊጉን በአግባቡ ባለመረዳቱና በአሠራር ችግር መታጠሩ ከሊጉ በጊዜ እንዲወርድ አስችሎታል፤›› ሲል ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ አስተያየቱን ለሪፖርተር ሰንዝሯል፡፡
የክለቦች የሥልጠና እና የፋይናንስ አካሄድ፣ የአሠልጣኞች ከቡድን መሪ እንዲሁም አስተዳደሮች ጋር ያላቸው የጥቅም ትስስር ሊጉን እየፈተነው ይገኛል፡፡ አብዛኛዎቹ አሠልጣኞች ወደ ፕሪሚየር ሊግካደጉ በኋላ፣ ‹‹የገንዘብ እንጂ የተጫዋች ልዩነት የለም›› በሚል አመለካከት እንዳላቸው ይገለጻል፡፡ በአንፃሩ በክለብ ውስጥ ያሉት ተጫዋቾች፣ ልምድ ካላቸው ተጫዋቾች ጋር አጣምረው መጓዝ ሲሳናቸው ይስተዋላል፡፡
ከዚያም ባሻገር ቡድኑ ጨዋታ አሸንፎ ጉርሻ ማግኘት ሲገባቸው፣ ወርኃዊ ደመወዝ እንኳን በቅጡ መክፈል እንደሚሰናቸው ይስተዋላል፡፡ በዚህም በመጡበት ዓመት ወደ ወደ ታችኛው ሊግ ሲወርዱ መመልከት ተለምዷል።
ከበርካታ ክለቦች ጋር መጫወት የቻለው የለገጣፎ ለገዳዲ የፊት መስመር አጥቂ ካርሎስ ዳምጠው ክለቡ ለአራት ወራት የተጫዋቾችን ደመወዝ መክፈል አለመቻሉን ያነሳል፡፡
ተጫዋቹ ቡድኑ ጨዋታ ሲያሸንፍ ተጨማሪ ጉርሻ ሊሰጠው ሲገባ፣ ደመወዙን እንኳን በቅጡ አለመከፈሉ ያነሳል፡፡
‹ደመወዝ ይከፈለን› የሚል ጥያቄ ስናቀርብ፣ የወጣቶች ሊግ እየመሠረትን ነው፤›› የሚል ምላሽ ነው የሚሰጡን በማለት ሁኔታውን ለሪፖርተር ያስረዳል፡፡
በዚህም መሠረት ክለቡን የሚመሩና የሚያስተዳድሩ አካላት ስፖርቱን የሚያውቁ ወይም ባለሙያዎች መሆን እንደሚገባቸው ያስረዳል፡፡
በተጨማሪም ቡድኑን የሚመሩ አሠልጣኞች ሊጉን በቅጡ መረዳት የሚችሉ፣ያላቸውን ተጫዋቾች ተጠቅመው መጫወት የሚችሉ መሆን አለባቸው ይላል።
በሌላ በኩል አንድ አንድ ክለቦች አቅም ኖሯቸው ውጤት መቀየር የሚችል አሠልጣኝ በማጣትና ያላቸውን ተጫዋቾች መጠቀም ባለመቻላቸው በደመ ነፍስ የሚጓዙ መኖራቸው ይጠቀሳል፡፡
ኤሌክትሪክ በኢትዮጵያ ስፖርት ታሪክ ውስጥ የሚነሳ ትልቅ ክለብ ነው፡፡ ክለቡ የገንዘብ ችግር የለበትም፡፡ በአንፃሩ ዘንድሮ ሦስት አሠልጣኞችን ቢቀያይርም በሊጉ መቆየት ተስኖታል፡፡
ሌላው ዘንድሮ ወደ ፕሪሚየር ሊጉ ያደገው መድን የዋንጫ ተፎካካሪ መሆን ችሏል፡፡ ክለቡ 26 ጨዋታዎችን አድርጎ 36 ነጥብ በማስመዝገብ ሦስተኛ ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ክለቡ ከሌሎች ክለቦች የተለዩ ተጫዋቾችን ያልተጠቀመ ሲሆን፣ በአንፃሩ በባለሙያዎች መመራት መቻሉና ልምድ ያለው አሠልጣኝ በማግኘቱ ውጤታማ ጊዜ ማሳለፍ ችሏል፡፡
ይህም ክለቦች ዕውቀትና ልምድ ያላቸውን አሠልጣኞችን መቅጠር እንደሚገባቸው እንደ ማሳያ ተደርጎ ይነሳል፡፡
በፕሪሚየር ሊጉ ከሚሳተፉ 16 ክለቦች፣ ዘጠኝ ክለቦች አሠልጣኞቻቸውን አሰናብተዋል፡፡ የዚህም ምክንያት ክለቦች ግባቸውን ያለማወቅና ጤናማ አስተዳደር፣ እንዲሁም የፋይናንስ ችግር ስላለባቸው እንደሆነ ይነሳል፡፡
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ በዲኤስቲቪ ከመተላለፉ ባሻገር ምንም ዓይነት ለውጥ እንዳልተስተዋለበት የሚያነሳው ጋዜጠኛ ቴዎድሮስ እግር ኳሱ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ይላል፡፡
ደረጃቸውን የጠበቁ የመጫወቻ ሜዳዎች ያለመኖር ችግሩን የበለጠ እንዳባባሰውና ክለቦችም የመንግሥት ካዝናን የሙጥኝ ማለታቸው፣ እንዲሁም አስተዳደራዊ ችግር እግር ኳሱን አንቆ መያዙ ጉዳዩን አሳሳቢ አድርጎታል፡፡
ዘንድሮ ወደ ሊጉ ያደጉት ክለቦች በቀጣይ በሊጉ ሊጠብቃቸው የሚችለውን ፈተና መረዳት ካልቻሉና ከወዲሁ ችግሩን ተገንዝበው መፍትሔ ካላበጁለት እንደሌሎቹ ክለቦች ዕጣ ፈንታቸው በመጡበት ዓመት የመመለስ ዕድል ሊሆን እንደሚችል ተነስቷል፡፡