የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) የመንግሥት የፀጥታ አካላት በማንኛውም ሕዝባዊና ሃይማኖታዊ ሠልፎች እንዲሁም ሌሎች ስብስባዎች፣ ተመጣጣኝ ካልሆነና ሞት ከሚያስከትል የኃይል ዕርምጃ መውሰድ እንዲቆጠቡ አሳሰበ፡፡
የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዳንኤል በቀለ (ዶ/ር) የመንግሥት የፀጥታ አካላት አላስፈላጊና ተመጣጣኝ ያልሆነ ኃይል የመጠቀም አዝማሚያ እየጨመረ መምጣቱንና በዚህም ሳቢያ በሰዎች ላይ ሞት፣ የአካልና የሥነ ልቦና ጉዳት፣ እንዲሁም ሌሎች የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እየደረሱ መሆናቸውን፣ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጨምሮ፣ ለሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት በተለያዩ ወቅቶች ውትወታ መደረጉን ገልጸዋል።
ኮሚሽኑ በሸገር ከተማ ከመስጊዶች መፍረስ ጋር ተያይዞ የተነሱ ተቃውሞዎችንና የደረሰ ጉዳትን በተመለከተ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው፣ በተለይ ሰላማዊ በሆኑ ሃይማኖታዊ ስብስቦች ወቅት የሚወሰድ ዕርምጃ የመንግሥት የፀጥታ አካላትን ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነው ብሏል፡፡
ኢሰመኮ ከግንቦት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በተለይም በአዲስ አበባ አንዋር መስጊድ ውስጥና በተወሰኑ አካባቢዎች በሸገር ከተማ በመንግሥት አካላት ከፈረሱ መስጊዶች ጋር ተያይዞ የተነሱ ተቃውሞዎችን ተከትሎ የደረሰውን የሰዎች ሞትና ጉዳቶችን በተመለከተ፣ ከኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት፣ ከመንግሥት የፀጥታ አካላት ኃላፊዎች፣ ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች የሕክምና አገልግሎት ካገኙባቸው የጤና ተቋማት ኃላፊዎች፣ ከዓይን እማኞችና ከተጎጂዎች ማስረጃ በማሰባሰብና ክትትል በማድረግ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
ዋና ኮሚሽነሩ በጉዳዩ ላይ በሰጡት አስተያየት፣ ለሰው ሕይወት እልፈትና አካል ጉዳት ተጠያቂ የሆኑ የፀጥታ አካላት ተለይተው በሕግ እንዲጠየቁ፣ በቁጥጥር ሥር የዋሉ ሰዎች ወንጀል ስለመፈጸማቸው በቂ ጥርጣሬ ከሌለና ተዓማኒ ክስ የማይቀርብ ከሆነ በአፋጣኝ እንዲለቀቁ፣ ወይም በሕግ አግባብ በእስር ላይ ያሉ ሰዎች የዋስትና መብት ሊከበር ይገባል ብለዋል።
ኮሚሽኑ ያነጋገራቸው የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ኃላፊዎች ምክር ቤቱ የራሱን ምርመራ በማድረግ ላይ መሆኑን እንደገለጹለት አስታውቆ፣ የመንግሥት የፀጥታ ኃላፊዎች በበኩላቸው የደረሰውን ጉዳት በማጣራትና ጉዳት ያደረሱ የፀጥታ አካላትን ለመለየት ምርመራ በማድረግ ላይ መሆናቸውን መግለጻቸውን አክሏል።
በተለይም በክስተቱ የሞቱና አካል ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች ጉዳይ በሚመለከት፣ ከአዲስ አበባና ከፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽኖች የተውጣጣ የምርመራ ቡድን መቋቋሙን ኃላፊዎቹ ጨምረው አስረድተዋል ተብሏል፡፡
ኢሰመኮ እስከ ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ባሰባሰበው መረጃና ማስረጃዎች መሠረት፣ የመንግሥት ፀጥታ ኃይሎችና የአድማ ብተና ኃይል ወደ ታላቁ አንዋር መስጊድ ግቢ ጭምር በመግባትና አስለቃሽ ጋዝ በመተኮስ ምዕመናንን ለመበተን እንቅስቃሴ በማድረጋቸው በተፈጠረው ሁከት የሰዎች ሕይወት ማለፉን፣ በበርካቶች ላይ አካላዊ ጉዳት መድረሱን፣ በፀጥታ አስከባሪ አባላት ላይም ጉዳት መድረሱንና በወቅቱ በርካታ ሰዎች በጥፋተኝነት ተጠርጥረዋል በሚል በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ውለዋል በማለት አስረድቷል፡፡
በሌላ በኩል ዓርብ ግንቦት 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ከተደረገው ስግደት (ጁምዓ) በኋላ፣ በተለይ በአንዋር መስጊድ በምዕመናንና በፀጥታ ኃይሎች መካከል በነበረ አለመግባባት ፀጥታ ኃይሎች በወሰዱት የኃይል ዕርምጃ በርካታ ምዕመናን ላይ ጉዳት መድረሱ ታውቋል።