Saturday, July 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናመንግሥት ለእምነት ተቋማትና ለምዕመኖቻቸው ጥበቃ እንዲያደርግ ተጠየቀ

መንግሥት ለእምነት ተቋማትና ለምዕመኖቻቸው ጥበቃ እንዲያደርግ ተጠየቀ

ቀን:

  • የፖለቲካ ፓርቲዎች በእምነት ተቋማት ላይ የሚወሰድ ዕርምጃ አደጋው የከፋ ነው አሉ
  • የከተማውንና የአገሪቱን ሰላምና ደኅንነት ለማስከበር የተጀመረው ሕግ የማስከበር ሥራ ይቀጥላል››

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል

በዮናስ አማረና በኢዮብ ትኩዬ

በአዲስ አበባ ከተማ በታላቁ የአንዋር መስጊድ ዓርብ ግንቦት 25 ቀን 2015 ዓ.ም. የደረሰውን አደጋ ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ የሃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ባወጣው መግለጫ፣ በኢትዮጵያ የእምነት ቤቶች ክብር፣ ሰላምና ደኅንነት እንዲጠበቅ ጠየቀ፡፡

ግንቦት 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በተመሳሳይ በታላቁ አንዋርና በኑር (ቤኒን) መስጊዶች ተቃውሞ ባሰሙ ምዕመናን ላይ በተወሰደ የፀጥታ ኃይሎች ዕርምጃ ዜጎች መሞታቸውን ያስታወሰው መግለጫው፣ በተከታታይ በተወሰዱ የኃይል ዕርምጃዎች በሰዎች ላይ ጉዳት እየደረሰ መሆኑን ገልጿል፡፡

ተቃውሞ በሚያሰሙ ሰዎች የፀጥታ ኃይሎች ያልተመጣጠነ ዕርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠቡ የጠየቀው ይህ መግለጫ፣ መንግሥት ለእምነት ተቋማትና ምዕመኖቻቸው ጥበቃ ሊያደርግ እንደሚገባ አሳስቧል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በሸገር ከተማ አስተዳደር ሥር መስጊዶች መፍረሳቸው፣ የሙስሊሙን ማኅበረሰብ ያስቆጣና ተቃውሞ እንዲያሰማ ያደረገ ጉዳይ መሆኑን መግለጫው ጠቅሷል፡፡

ከዚህ በተጨማሪም በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በምዕራብ ጎጃምና በአርሲ ሀገረ ስብከት በሚገኙ ሁለት አጥቢያዎች ላይ ስለደረሱ ጉዳቶች እየተጣራ ይገኛል ይላል፡፡

‹‹መስጊዶችና አብያተ ክርስቲያኖች የአማኞች ሃይማኖታዊ፣ መንፈሳዊና ሞራላዊ እሴቶች መገንቢያ ማዕከል ናቸው›› የሚለው ይህ መግለጫ፣ እነዚህ ተቋማት በመንግሥት ተገቢው ጥበቃ ሊደረግላቸው እንደሚገባ ጠይቋል፡፡

ከሰሞኑ ተቃውሞ ባሰሙ ሙስሊሞች ላይ የፀጥታ ኃይሎች ስለወሰዱት ዕርምጃ፣ እንዲሁም በመንግሥትና በሕዝበ ሙስሊሙ መካከል እየተባባሰ ስለመጣው አለመግባባት የተጠየቁ የተፎካካሪ ፓርቲዎች መንግሥት የሕዝቡን ስሜት እንዲያዳምጥ ጠይቀዋል፡፡

አስተያየት የሰጡ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ)፣ እናት ፓርቲ እንዲሁም ለጉራጌ አንድነትና ፍትሕ ፓርቲ (ጎጎት) አመራሮች፣ ኢትዮጵያ ለሃይማኖቱ ቀናዊ የሆነ ሕዝብ መኖሪያ አገር በመሆኗ መንግሥት ይህንኑ እንዲያከብር ጠይቀዋል፡፡

የኢሕአፓ ተቀዳሚ ሊቀመንበር መጋቢ ብሉይ አብራሃም ሃይማኖት፣ ፓርቲያቸው የሕዝበ ሙስሊሙን ጉዳይ ብቻ ሳይሆን፣ በአርሲና በጎጃም በኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናት ላይ የደረሱ ጉዳቶችንም በቅርበት እንደሚከታተል ጠቅሰዋል፡፡

‹‹ፓርቲያችን በሁለቱም በኩል እየተፈጸሙ ያሉ ጉዳቶችን ያወግዛል፡፡ ሕዝበ ሙስሊሙ በሰላማዊ ሁኔታና በጨዋነት ጥያቄውን ቢያሰማም፣ መንግሥት ግን ከፈጸመው በላይ ስህተት ለመፈጸም በኃይል እየተጠቀመ ነው፤›› ብለዋል፡፡

ከጁምዓ ሶላት ዋዜማ ጀምሮ በአዲስ አበባ መርካቶ፣ እንዲሁም በተለያዩ ከተሞች ተቃውሞ ያሰማሉ የተባሉ ሙስሊሞችን የማሳደድ ሥራ ሲሠራ እንደነበር መጋቢ ብሉይ አብርሃም ተናግረዋል፡፡ ሕዝበ ሙስሊሙን በየመስጊዶቹ ማዋከብ ሲገጥመው መሰንበቱንም መረጃ እንዳላቸው አስረድተዋል፡፡

‹‹ኢትዮጵያ ያለ ሙስሊሞች ምሉዕ አትሆንም፡፡ የሙስሊሙ ኅብረተሰብ ለኢትዮጵያ ማንነት ብዙ አስተዋጽኦ አበርክቷል፤›› ሲሉ የተናገሩት ተቀዳሚ ሊቀመንበሩ፣ ‹‹መንግሥት ሃይማኖትን ማክበር ግዴታው ነው፤›› ብለዋል፡፡

የጎጎት ፓርቲ ሊቀመንበር መሐመድ አብራር በበኩላቸው፣ መንግሥት እያደረሰ ያለው ጥፋት የሰፋ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

‹‹ተቋማት ስለሆኑና አቤት የሚልላቸው ወገን በርካታ በመሆኑ የእምነት ተቋማቱ ችግር ታወቀ እንጂ፣ በግለሰቦች ላይ እየተፈጸመ ያለው ሀብትና ንብረት የማውደም ጥፋት እንደ አገር ጉዳቱ ሰፊ ነው፤›› በማለት አቶ መሐመድ ተናግረዋል፡፡

‹‹በሸገር ከተማ ብቻ ሳይሆን በአዲስ አበባ ውስጥም ሀብት ንብረታቸው እየወደመ ያሉ ዜጎች በርካታ ናቸው፡፡ አገሪቱ በምትገኝበት በዚህ አስቸጋሪ ወቅት መድረሻ አጥቶ በየሜዳው የሚበተነው ዜጋ መብዛቱ አገሪቱን ለከፋ አደጋ የሚዳርግ ነው፤›› በማለት አክለዋል፡፡

መንግሥት መጀመርያ የማፍረስ ድርጊቱን ማቆም እንዳለበት የጠቀሱት የጎጎት ሊቀመንበር፣ ውይይት መፍጠርና ሕጋዊ መንገድን መከተል መፍትሔ ለማምጣት ወሳኝ ዕርምጃዎች መሆናቸውንም ተናግረዋል፡፡

የእናት ፓርቲ ሕዝብ ግንኙነት ኃላፊና ብሔራዊ የሥራ አስፈጻሚ አባሉ አቶ ዳዊት አብርሃም በበኩላቸው፣ ‹‹ሃይማኖቶች በኢትዮጵያ ሊጣሱና ሊነኩ የማይገባቸው የእሴት ኬላዎች ናቸው፤›› ብለዋል፡፡ ብልፅግና መራሹ መንግሥት እነዚህን እሴቶች የመረዳትና የማክበር ችግር እንዳለበትም ተናግረዋል፡፡፡

‹‹የእስልምና ጉዳዮች ምክር ቤቱ በገለጸው መሠረት በአዲሱ የሸገር ከተማ ከማስተር ፕላን ጋር አይጣጣሙም ተብሎ 19 መስጊዶች መፍረሳቸው ትልቅ ስህተትና ከሃይማኖቶች ጋር ሆን ብሎ መጋጨት ነው፤›› በማለትም አክለዋል፡፡

የሰሞኑን የመንግሥት አካሄድ ‹‹በራስ ላይ ጦርነት የማወጅ›› ዓይነት እንደሚመስል የጠቀሱት አቶ ዳዊት፣ መንግሥት በአስቸኳይ ችግሩን እንዲያርም ጠይቀዋል፡፡ የፈረሱ መስጊዶች በመንግሥት ወጪ አሊያም ምትክ ቦታ ተሰጥቶ ሊገነቡ እንደሚገባ ያሳሰቡት የሕዝብ ግንኙነቱ፣ መንግሥት ይቅርታ ሊጠይቅ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡

የጁምዓ ሶላትን ተከትሎ በአንዋር መስጊድ ውስጥ ለግማሽ ቀን የቆዩ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሙስሊሞችን በሰላም እንዲወጡ ማድረጉን የገለጸው የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ስለሞቱት ሦስት የእምነት ተከታዮች ዜጎች ሐዘኑን ገልጿል፡፡

የፀጥታና ደኅንነት የጋራ ግብረ ኃይል ዓርብ ምሽት በሰጠው መግለጫ፣ በአንዋር መስጊድ በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ የሦስት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ በተወሰኑ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱን ይፋ አድርጓል፡፡

የፀጥታ ኃይሎች በከፈሉት መስዋዕትነት የከፋ ጉዳት ሳይደርስ ሁኔታውን መቆጣጠር መቻሉን ግብረ ኃይሉ ገልጿል፡፡ በመላ አገሪቱ የጁምዓ ሶላት ያለ ችግር መካሄዱን መግለጫው ጠቅሶ፣ ሰሞኑን ‹‹መስጊዶች ፈርሰዋል›› በሚል ሁከትና ብጥብጥ የሚያካሂዱ ወገኖች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡም አሳስቧል፡፡

ግብረ ኃይሉ የከተማውንና የአገሪቱን ሰላምና ደኅንነት ለመጠበቅ የጀመረውን ሕግ የማስከበር ሥራ አጠናክሮ እንደሚቀጥልም አስታውቋል፡፡ ሁሉም የእምነት ተቋማት እንደ አስተምህሮታቸው ሕዝበ ሙስሊሙ የሚያነሳውን ጥያቄ በሕግ አግባብና በሰላማዊ መንገድ መሆን እንዳለበትም አሳስቧል፡፡

ለፀረ ሰላም ኃይሎች መጠቀሚያ እንዳይሆኑ፣ የሰላምና የፀጥታ ኃይሎች ሰላም ለማስከበር የሚያደርጉትን ጥረት በመደገፍ የዜግነት ድርሻቸውን እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡   

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

አቶ ሰብስብ አባፊራ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ከአዋጅና መመሪያ ውጪ ለዓመታት ሳይካሄድ የቆየው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ...

ቀጣናዊ ገጽታ የያዘው የኢትዮ ሶማሊያ ውዝግብ

ከአሥር ቀናት ቀደም ብሎ በተካሄደው የፓርላማ 36ኛ መደበኛ ስብሰባ፣...

የኢንሹራንስ ኩባንያዎች በዓረቦንና የጉዳት ካሳ ክፍያዎች ላይ ተጨማሪ እሴት ታክስ መጣሉን ተቃወሙ

በአዲሱ ተጨማሪ እሴት ታክስ አዋጅ ውስጥ የኢንሹራንስ ከባንያዎች ለሚሰበስቡት...