ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) በኢትዮጵያ ዘመናዊ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ ለግማሽ ምዕተ ዓመት ያህል የፖለቲካ ትግል ውስጥ ነበሩ። ከአምስት ዓመታት በፊት በኢትዮጵያ በተደረገው የመንግሥት ለውጥ በስደት ከሚኖሩበት አሜሪካ ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት፣ ይመሩት የነበረውን የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር በመተው በስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በግል ተወዳድረው በማሸነፍ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት የምክር ቤቱ የውጭ ግንኙነትና ሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ናቸው። ሲሳይ ሳህሉ ከእሳቸው ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ያደረገው ቆይታ እንደሚከተለው ተጠናቅሯል፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የፖለቲካ ትግል ውስጥ መጀመርያ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) በአመራርነት ቆይተዋል፡፡ ከዚያም የደርግ ሥርዓት መውደቁን ተከትሎ በተመሠረተው የሽግግር መንግሥት ወቅት የማስታወቂያ ሚኒስትር በመሆን አገልግለዋል፡፡ ከዚያም በውጭ አገሮች ለበርካታ ዓመታት ቆይተው ወደ አገር ቤት በመመለስ አሁን በግል ተወዳድረው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነዋል፡፡ እስኪ የፖለቲካ ሕይወትዎን በተመለከተ ትንሽ ቢነግሩን?
ዲማ (ዶ/ር)፡- እኔ የፖለቲካ ትግል የጀመርኩት በኢትዮጵያ የተማሪዎች ንቅናቄ ውስጥ ነው፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ እ.ኤ.አ. በ1970ዎቹ አካባቢ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ነበርኩ፣ በጣም የጦፈ የተማሪዎች ንቅናቄ ነበር፡፡ በተማሪው ዘንድ የነበረው የለውጥ ፍላጎት በጣም ከፍተኛ ነበር፡፡ በአገሪቱ የነበረው የማኅበራዊ ፍትሕ መጓደል፣ አስተዳደራዊ ምስቅልቅል፣ የኢኮኖሚና የመሬት ሥሪቱ ፍርደ ገምድል መሆንና በጣም ጥቂት ሰዎች መሬት ይዘው አብዛኛው የአገሪቱ ገበሬ ጭሰኛ ሆኖ ከሚያርሰው በላይ እየከፈለ የሚኖርበት ጊዜ ስለነበረ፣ ይህ ደግሞ ፍትሐዊ አይደለም በሚል በዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የሚመራ ከፍተኛ የተማሪዎች ንቅናቄ ነበር፡፡ ይህ ንቅናቄ በውጭም በአገር ውስጥም የነበሩ ተማሪዎች የተሳተፉበትና በመጨረሻም የሁለተኛ ደረጃ የሙያ ትምህርት ቤቶች ሁሉ ጨምሮ፣ ኅብረተሰቡን ብዙ ያንቀሳቀሰ ነበር፡፡ እኔ በእዚያ ውስጥ ነበር የፖለቲካ ትግል የጀመርኩት፡፡ በዚህ ትግል ውስጥ እኔም መሳተፌ አንደኛ ጉዳዩ የፖለቲካ ትግል ነው፡፡ ነገር ግን እዚህ ትግል ውስጥ መሳተፋችን ፖለቲከኛ አያሰኘንም፡፡ በጊዜው ግን አብዛኛው ተማሪ የተሳተፈበት ስለነበር መጨረሻ ላይ ሥርዓቱን ያነቃነቀና የነቀነቀ እስከመሆን ደርሶ፣ ወታደሩም ጭምር የሚያምፅበት ደረጃ ደረሰ ማለት ነው፡፡ ከዚያ ጊዜ በኋላ ምንም እንኳ የተመኘነው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ተመሥርቶ የሕዝቦች እኩልነት ባይመጣም፣ ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ገበሬው የመሬት ባለቤት የመሆን ዕድል አግኝቶ ነበር፡፡ ነገር ግን ሥልጣን የጨበጠው ወታደራዊ መንግሥት በለውጡ ላይ ተረማምዶ ነው ወደ ሥልጣን የመጣው፡፡ በዚህም ሕዝቡ የፈለገውን ለውጥ ለማምጣት አልቻለም፡፡ እንዲያውም የሕዝቡን ንቅናቄ ጨፍልቆ አምባገነናዊ ሥርዓት በመመሥረቱ፣ ትግላችን በልዩ ልዩ ዘዴ በዚህ የወታደራዊ መንግሥት ላይ ቀጠለ ማለት ነው፡፡
ፖለቲካው ከከተማ ትግል ወደ ገጠር የትጥቅ ትግል ተሸጋገረ፡፡ ወታደራዊ አገዛዙ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ልዩነት የማይፈቅድ ሥርዓት ስለነበር በከተሞች እሱን ለመቋቋም አልተቻለም፡፡ ስለዚህ አብዛኛው በተማሪዎች ንቅናቄ ይሳተፍ የነበረው ወደ ገጠር የትጥቅ ትግል አመራ፣ ሌላውም ወደ ስደት ሄደ፡፡ ይህ በመሠረቱ የአገሪቱን የፖለቲካ ዕድገት ተፈታትኖታል፣ አመሰቃቅሎታልም የሚል እምነት አለኝ፡፡ በመጨረሻም ንቅናቄው ከወታደራዊ መንግሥት የተሻለና የተለየ ሊሆን አልቻለም፡፡ ምክንያቱም ወታደራዊ መንግሥት ይቋቋም እንጂ የትጥቅ ትግል ወታደራዊ ፀባይ ስላለው፣ በመጨረሻም ያንኑ የሚቃወመውን ኃይል እየመለሰ ነው የመጣው፡፡ እኔ እንዳየሁት ወታደራዊ መንግሥትም በራሱ ድክመት ነው የወደቀው፡፡ እሱ ሲወድቅም እሱን የተኩት ኃይሎችም ከእሱ የተለዩ አልነበሩም ማለት ይቻላል፡፡ በመጨረሻ የደርግ ሥርዓት እንደወደቀ በኦሮሞ ነፃነት ግንባር ስም የጥምር መንግሥት አቋቋምን፡፡ እኔም የሽግግር መንግሥት አባልና የማስታወቂያ ሚኒስቴር በመሆን አገልግያለሁ፡፡ ነገር ግን የሽግግሩ መንግሥት አንድ ዓመት ሳይሞላው ውስጥ ፈረሰ፡፡ ወያኔ ብቻውን የመንግሥት ሥልጣን ተቆጣጠረ፡፡ ከዚያም በኋላ ሁሉንም ነገር እንደፈለገ ነበር ያደረገው፡፡ የተቀረነው ወደ ትግሉ ተመለስን፡፡ ስንታግል ቆይተን ከ26 ዓመታት ትግል በኋላ ከውጭ አገር ረዥም ጊዜ ቆይተን ወደ አገራችን ተመለስን፡፡ በአንድ በኩል የትጥቅ ትግሉ ከአገራዊና ከአካባቢያዊ ሁኔታ መለዋወጥ ጋር ተገናኝቶ የታለመውን ያህል ውጤት ባያስገኝም፣ በአገር ውስጥ ከ1966 ዓ.ም. አብዮት ባልተለየ ሁኔታ የሕዝብ ንቅናቄ ተፈጠረ ማለት ነው፡፡
ከ2007 ዓ.ም. ጀምሮ በተለይ በአዲስ አበባ ዙሪያና አካባቢው በወጣቶች የሚመራ ከፍተኛ የሆነ የሕዝብ አመፅ የታየበት ጊዜ ነበር፡፡ ከተማው ውስጥ እንኳን ይኼን ያህል የረባ እንቅስቃሴ አልነበረም፡፡ ትግሉ እንዲያውም ከዳር ወደ መሀል የመጣበት ጊዜ ነበር፡፡ ይህ ነው እንግዲህ የወያኔን ሥርዓት የገረሰሰው ለመጀመርያ ጊዜ ያለ ጠመንጃ ሥልጣን ሲያዝ፣ ከዚያው ከኢሕአዴግ ውስጥ ከሕዝቡ ጎን የቆሙ ሰዎች በፈጠሩት ጥሩ አጋጣሚ ወደ ተሻለ የፖለቲካ ሥርዓት ይመሩናል የሚል ተስፋ አድሮብኝ ነበር፡፡ ነገር ግን ዞሮ ዞሮ የአንድ አገር የፖለቲካ ባህል ቶሎ የሚጠፋ አይደለም፡፡ በዚህም የተነሳ ድሮ በምናውቀው የትጥቅ ትግል ሥልት ከሥልጣን የተወገደው ሕወሓት ኃይል መልሶ በጉልበት ሥልጣን ለመቆጣጠር ሞከረ፡፡ በዚህም ከፍተኛ የሆነ የሰው ዕልቂትና የንብረት ውድመት ያስከተለ ጦርነት ውስጥ ገባን ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ወደ በፊቱ መመለሳችንን ነው የሚያመለክተው። ነገር ግን አንድ አዎንታዊ ነገር የማየው ጦርነቱ የከፋም ቢሆንም፣ መጨረሻ ላይ ተደራድሮ በሰላም እንዲያልቅ መደረጉ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ታሪክ ውስጥ አዲስ ክስተት ነው፡፡ ወደፊትም ሊቀጥል ይገባል፡፡ የፖለቲካ ሥርዓታችን እንዲያድግና ልማት እንዲመጣ የተደላደለ የፖለቲካ ሥርዓት ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያ ምንም እንኳ ረዥም የፖለቲካ ሥርዓት ያላትና በአፍሪካ ቀደምት አገረ መንግሥት ያላት ብትሆንም፣ እስካሁን ድረስ የተደላደለ የፖለቲካ ሥርዓት ለመመሥረት አልታደለችም፡፡ በመሆኑም አንዱ የፈለገውን በሌላው ላይ በመጫን ሳይሆን፣ በምክክር ላይ ተመሥርቶ በሰጥቶ መቀበል መርህ ዘላቂነት ያለውና የተሻለ የፖለቲካ ሥርዓት ለመመሥረት እንችላለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- በኢትዮጵያ የፖለቲካ ዕድገት ውስጥ የፖለቲካ ትግል የሚያደርጉም ሆነ ከሕዝቡ የሚነሱ የብሔር ጥያቄዎች፣ የታሪክ ትርክቶች፣ አመለካከቶችና አስተያየቶች ለአገረ መንግሥት ግንባታ ያላቸውን አሉታዊ ወይም አዎንታዊ ሚና እንዴት ይመለከቱታል?
ዲማ (ዶ/ር)፡- እንግዲህ በዓለም ላይ ማንኛውም አገረ መንግሥት የተመሠረተው በጉልበት ነው፣ ይህ የታወቀ ነው፡፡ በጉልበትም አገረ መንግሥቱ ተመሥርቶ ለምሳሌ የታወቁትና ትልልቆቹ የአውሮፓ መንግሥታት ግዛቶችን ወደ ሥርዓቱ ካስገቡ በኋላ፣ አዳዲሶቹ ግዛቶች የሥርዓቱ አካል ይሆናሉ፡፡ ግዛቱ ወደ ሌላ ሲስፋፋም ይህንን ይዘው ነው የማስፋፋት ሥራ የሚሠሩት፡፡ ነገር ግን እዚህ አገር በጉልበት ግዛት ሲስፋፋ አዲሱን ግዛት የሥርዓቱ አካል ማድረግ አልታየም፡፡ በ19ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ አገረ መንግሥት በከፍተኛ ደረጃ ወደ ደቡብ፣ ምሥራቅና፣ ምዕራብ በከፍተኛ ሁኔታ ነው የተስፋፋው፡፡ እንደዚህም ሆኖ እያለ ግን ይህን በአገረ መንግሥቱ ሥር የተጠቃለለውን ሕዝብ የሥርዓታቸው አካል ማድረግ አልቻሉም፡፡ የአሁኑ ችግራችን መነሻ ያ ነው፡፡ በተለይ ደግሞ በሥርዓት ውስጥ አለመካተት ብቻ ሳይሆን፣ ሁለት ዓይነት የፖለቲካ ሥርዓት ነበር በአገሪቱ ውስጥ የተመሠረተው፡፡ ይህ ምንድነው ስትል፣ በሰሜኑ የአገራችን ክፍል የርስት አገር ይባላል፡፡ አብዛኛው ሰው የራሱ መሬት አለው እንደ ርስት የሚያወርሰው፡፡ በሌላው በተለይ በደቡብ በአብዛኛው ከሰሜን የመጡ ሰዎች መሬቱን ተቆጣጥረውት የገባር ሥርዓት ተፈጠረ፡፡ አብዛኛው ጭሰኛ ሆኖ የሚያርስበት የፖለቲካ ሥርዓት ነበር፡፡ ይህ በፖለቲካው፣ በኢኮኖሚው፣ በማኅበራዊና በሌላውም ዘርፍ እስከ ዛሬ ድረስ ተፅዕኖ አለው፡፡ በተጨማሪም ከብሔር ጭቆናው ጋር በጣም የተያያዘና ክፍተት የነበረበት ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ከግዛት ማስፋፋት በኋላ የተቋቋመውን መንግሥት ስታይ፣ ቀደም ሲል በሰሜን አካባቢ የነበረው መንግሥት ይብዛም ይነስም ከሕዝቡ ጋር ትስስር ነበረው፡፡ ነገር ግን ከአዲሱ የግዛት ማስፋፋት በኋላ የተቋቋመው መንግሥት፣ የግዛት መሠረቱን አዲስ አበባ በተባለውና መሠረተ ሰፊ የሆነ አገርና ሀብት ያለው አካባቢ ስላጠቃለለ፣ ከሰሜኑ ሕዝብ እንደ ድሮው የሚጠብቅው ድጋፍ አላስፈለገውም፡፡ ስለዚህ ከሰሜኑ ሕዝብ ጋር በበለጠ እየተነጠለ ነው የመጣው፡፡ ከደቡብ ሕዝብ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም፡፡ ይህ ማለት ተንሳፋፊና ከሕዝቡ ጋር ተፈጥሯዊ የሆነ ግንኙነት የሌለው አገረ መንግሥት ነው የተመሠረተው፡፡ ቅድም እንዳልኩህ አሁን ላለንበት ችግር መሠረት ጣለ ማለት ነው፡፡
ሪፖርተር፡- የአገረ መንግሥት ግንባታ መቼ ሊጠናቀቅ ይችላል? የአሁኑን ጉዞስ እንዴት ይገመግሙታል?
ዲማ (ዶ/ር)፡- የአገረ መንግሥት ግንባታ በአንዴ ተጠናቆ የሚያልቅ ነገር አይደለም፣ በሒደት ነው፡፡ ነገር ግን ጀርመን እንደ አገር የቆመው እ.ኤ.አ. በ1871 ነው፡፡ ከእኛ ብዙ አይበልጥም፡፡ ጣሊያንም በዚሁ ዓመት አካባቢ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሲመሠረት እኮ 50 እና 60 አገሮች ብቻ ነበሩ፡፡ ዛሬ ወደ 200 የሚጠጉ አገሮች አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ከዚያ ወዲህ የተመሠረቱ ናቸው፡፡ ነገር ግን እኛ ከእነዚህ ሁሉ አገሮች ጋር ስንተያይ፣ ምናልባት ከእነ ደቡብ ሱዳንና መካከለኛው አፍሪካ ብንሻል ነው እንጂ ከአብዛኞቹና ከቅርብ ጊዜ ወዲህ አገር ከሆኑት ጋር ስንነፃፀር በጣም ኋላቀር ነን፡፡
ሪፖርተር፡- አሁን እየተሄደበት ባለው መንገድ የአገረ መንግሥት ግንባታ ሒደቱ እንዴት ሊመራ ይችላል?
ዲማ (ዶ/ር)፡- ባለፉት አምስት ዓመታት ብዙ ለውጥ ተደርጓል፡፡ ለውጥ ባይካሄድ ኖሮ እኔም እዚህ አልቀርብም ነበር፣ ይህ ግልጽ ጉዳይ ነው፡፡ እንደዚያም ሆኖም ግን በቂ አይደለም አገር የሁሉም ነው፣ አገር የሚመራው ደግሞ ሁሉንም በማስተባበር ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለይ በተቋማት ግንባታ ላይ ጥሩ አካሄድ አለ ብዬ ነው የማስበው፡፡ ማለትም አገራዊና ዘላቂነት ያላቸውን ተቋማት ለመገንባት እየተደረገ ያለው እንቅስቃሴ ጥሩ ነው፡፡ ለአገረ መንግሥቱ ግንባታ ትልቁ መሠረት ሊሆን የሚችለው ያ ነው፡፡ በፖለቲካው ግን ወደኋላ ቀርተናል ብዬ ነው የማስበው፡፡ ጠንካራ ተቋማት ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ትልቅ መሠረት ናቸው፡፡ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መሠረት የሚሆነው ደግሞ የፖለቲካ ፓርቲ ነው፡፡ በአገራችን እስካሁን አቅም ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች ለመገንባት አልታደልንም፡፡ እዚህ ግባ የምትለው ፓርቲ እኮ የለም፡፡ በግለሰቦች አካባቢ የተደራጁ ቡድኖች አሉ፡፡ ሌላው ደግሞ የመንግሥት ሥልጣን ላይ ያለ አካል ነው፡፡ ይህ የመንግሥት ሥልጣን ላይ ስላለ ብቻ ነው ፓርቲ የሚባለው፡፡ አሁን መንግሥት ቢወድቅ ፓርቲው የለም፣ አይኖርም፡፡ እንደ ኢሠፓ ነው የሚሆነው፡፡ ኢሠፓ የት አለ? እና የመንግሥት ሥልጣንን መሠረት አድርጎ የተደራጀ የፖለቲካ ፓርቲ ዘላቂነት ሊኖረው አይችልም፡፡ ይህ ጉዳይም በእጅጉ ሊታሰብበት ይገባል፡፡ አንድ ሰው የፓርቲውን ፕሮግራም አምኖበት ነው የፖለተካ ፓርቲ አባል መሆን ያለበት፡፡ ነገር ግን አሁን እየሆነ ያለው ሥልጣን ስለሚፈልግ ሥልጣን ለማግኘት በሚል ነው እየተደራጀ ያለው፡፡ ምክንያቱም ሥልጣን ለማግኘት ያለው መንገድ ያ ብቻ በመሆኑ ማለት ነው፡፡ የረባ የፖለቲካ ድርጅት በአገራችን ውስጥ አለመኖሩ ትልቅ ችግር ነው፡፡ የሚገዳደሩ ሳይሆኑ ለመቃወም ብቻ የተቋቋሙ የሚመስሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች አሉ፡፡ ሥርዓት ባለው መንገድ ፕሮግራም ቀርፀው፣ አባል ሰብስበው የተደራጁ ፓርቲዎች ግን አላየሁም፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን ከ100 በላይ ፓርቲዎች አሉ፡፡
ሪፖርተር፡- ኢትዮጵያ ውስጥ ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ እንዳለ ይነገራል፡፡ ለዚህ ሕዝብ የሚመጥን ወጥ የሆኑ ጠንካራ አገራዊ ፓርቲዎች መመሥረት ለምን አልተቻለም?
ዲማ (ዶ/ር)፡- አንደኛው ግለኝነት ነው፡፡ እስካሁን ባለኝ አረዳድ የኢትዮጵያ ሕዝብ በቡድን መሥራት ላይ ክፍተት አለበት፡፡ ለዚህ ማሳያ አንድ ምሳሌ ልጥቀስልህ፡፡ በኢትዮጵያ ስፖርት ውስጥ የቡድን ስፖርትና የግል ስፖርት አለ፡፡ እኛ እንደ አገር የቡድን ስፖርት አሸንፈን አናውቅም፡፡ ነገር ግን በግል በሚደረገው የሩጫ ስፖርት ካየህ ልህቀት አለን፡፡ ወደ ፖለቲካ ስትመጣ ግን መሆን የነበረበት የቡድን ስፖርት ነበር፡፡ በቡድን አብሮ መሥራትና ተቀናጅቶ መንቀሳቀስ እንጂ፣ በቡድን ውስጥ እኔ ያልኩት ብቻ ከሆነ ግን አይሠራም፡፡ ሁሉም የሚያነሳው ጉዳይ ወደ አንድ መጥቶ ነው በጋራ የሚወሰነው። በእኛ ፖለቲካ ውስጥ የምታየው እኔ ያልኩት ብቻ ይሁን የሚለው ነገር ትልቅ ቦታ አለው፡፡ በፖለቲካው ደግሞ ግለሰቦች በምኞት የሚፈልጓትን ኢትዮጵያ ብቻ የሚቀርፁበት ሁኔታ ታያለህ፡፡ ነገር ግን የፖለቲካ ሥራ የሚከናወነው አብዛኛው ሕዝብ ምን እንደሚፈልግ ተመሥርቶ መሆን አለበት፡፡ ማንኛውም ኅብረተሰብ ውስጥ ዳርና ዳር የቆሙ ሰዎች አሉ፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ተሰሚነት ያላቸው ጫፍ የረገጡ ቡድኖች ናቸው፣ በቀኝም በግራም በኩል የቆሙ ማለት ነው፡፡ በተለይ ደግሞ የማኅበራዊ ሚዲያው እነዚህን ዳር የረገጡ ሰዎች ድምፅ እየጎላ ነው የሚሄደው፡፡ አብዛኛው ኅብረተሰብ በእጁ ስልክ አለው፣ እሷን ሲያዳምጥ ይውላል፡፡ በቃ ፖለቲካችን ያ ነው ለእኛ፡፡ ፖለቲካ ግን ከመሀል ነው የሚጀምረው፡፡ ይህ ማለት ከመሀል ገብተህ አብዛኛው ኢትዮጵያዊ ምን ዓይነት አስተሳሰብ ነው የሚፈልገው? ምናልባት ሁላችንም የምንፈልገው አንድ ዓይነት ላይሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን ይህን ማቻቻልና ሁላችንንም የሚያስማማ ዘላቂ የሆነ የፖለቲካ ሥርዓትና ዕድገት በማምጣት፣ ይህንን ሕዝብ ከድህነት ማውጣት አለብን፡፡ የፖለቲካ ሥርዓቱ እስካልተረጋጋ ድረስ የኢኮኖሚ ዕድገት ሊኖር አይችልም፡፡ ባለፉት ሁለትና ሦስት ዓመታት በአገሪቱ የነበረው ጦርነት አምስት ዓመት ነው ወደኋላ የመለሰን፡፡ የዛሬ አምስት ዓመት የነበርንበት ጊዜ ላይ ለመድረስ ወደፊት አሥር ዓመታት ያስፈልጉናል፡፡ ያልተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት ይህ ነው ችግሩ፡፡ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማምጣትና ሕዝቡን ከድህነት ለማውጣት ሲታሰብ ከባድ ነው፡፡ አሁን አዲስ አበባ ውስጥ የሚኖረው ሕዝብ እኔ ምን በልቶ እንደሚያድር አላውቅም፡፡ በእውነቱ አንዳንዴ ለመገመትም ያስቸግራል፡፡ ድሮ ከተማው ውስጥ እንደነበረው አገልግሎት በገጠሩ ስላልነበረ፣ ገጠር ነበር በብዛት ሰው በድህነት የሚኖረው፡፡ አሁን አብዛኛው ደሃ ያለው ከተማ ውስጥ ነው፣ በተለይ ደግሞ ትልልቅ ከተሞች ውስጥ፡፡ የገጠሩን ስታይ ይብዛም ይነስም አርሶም ቆፍሮም የሚበላው ያገኛል፡፡ አሁን አብዛኛው ሕዝብ እያማረረ ነው፡፡ በዚህ ጊዜ ከተማ ውስጥ የተከማቸውና በኑሮ ውድነቱ የተማረረ ሕዝብ ለፖለቲካ ሥርዓቱም አሥጊ ነው፡፡ ተገቢው ምላሽ መሰጠት አለበት፡፡
ሪፖርተር፡- የተፎካካሪ ፓርቲዎች ሰዎች ከገዥው ፓርቲ የቀረበላቸውን የሹመት ጥያቄ ተቀብለው አብረው መሥራታቸውን እንዴት ይመለከቱታል? የፖለቲካ ፓርቲዎችን እንዳዳከመ የሚናገሩ አካላት ስላሉ በዚህ ላይ ምን ይላሉ?
ዲማ (ዶ/ር)፡- እኔ ከሁለት ነገር አንድ ነገር መምረጥ አለብን እላለሁ፡፡ ወይ በአውራ ፓርቲ ነው የምንመራው፣ ወይም ደግሞ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ነው መሆን ያለበት፡፡ ሁለቱን አደባልቀን መሆን የለበትም፡፡ ለምሳሌ ቻይና ውስጥ ያለው ፖለቲካ በአውራ ፓርቲ የሚመራ ነው፡፡ ነገር ግን ሌሎች ፓርቲዎች አሉ፡፡ ሌሎች ፓርቲዎች መኖራቸውን ብዙ ሰው አያውቅም፡፡ የቻይና ኮሙዩኒስት ፓርቲ የሚባለውና አገሪቱን የሚመራው ፓርቲ በዓለም ታሪክ ውስጥ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት አገሪቱን ወደ ከፍተኛ ዕድገት ያደረሰ ነው፡፡ እኔ እንዲህ ዓይነት ፓርቲ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢኖር ደስ ይለኛል፣ የግድ መድበለ ፓርቲ መሆን የለበትም፡፡ ችግራችንን የሚፈታልን ነው የምንፈልገው፡፡ አሁን አብዛኛው የቻይና ሕዝብ በዚህ ፓርቲ ያምናል፡፡ ለእኔ ነው የሚሠራው ብሎ ነው የሚያምነው፡፡ ይህ ከሆነ ደግሞ ለእኔ ችግር የለብኝም፣ ይህ ካልሆነ ደግሞ ፉክክር ያለበት መድበለ ፓርቲ ሥርዓት መኖር አለበት፡፡ እና ከሁለት አንዱ መምረጥ አለብን፣ እኛ አሁን እያየን ያለነው ሁለቱንም ነው፡፡ ነገር ግን ሕገ መንግሥቱ ደግሞ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ይላል፡፡ በተግባር ግን ያው አንድ ፓርቲ ነው፡፡ እኔ እንዲያውም የሚገርመኝ የፓርቲዎች በመንግሥት ካቢኔ ውስጥ መግባት ነው፡፡ እነዚህ ፓርቲዎች መንግሥት ውስጥ ገብተው የማንን ፕሮግራም ነው የሚያስፈጽሙት? የራሳችን ፕሮግራም አለን ሲሉ ነው የሚደመጡት አይደል እንደ ፓርቲ ሲናገሩ፡፡ በአንድ በኩል በመንግሥት ውስጥ የተካተቱት አንዳንዶቹ ለምርጫ ቀርበው ሕዝብ ያልተቀበላቸው ግለሰቦች ናቸው፡፡ ይህ ማለት ለሕዝብ ድምፅ ዋጋ አለመስጠትም ጭምር ነው፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ የተለየ ፓርቲ ነን፣ የራሳችን ፕሮግራም አለን ብለው ሲሉ የነበሩ ያንን ፕሮግራማቸውን ጥለው ነው የገዥውን ፓርቲ ፕሮግራም ለማስፈጸም መንግሥት ውስጥ የገቡት? እንደዚያ ከሆነ ፓርቲያቸውንም ለምን አያዋህዱም? ያው ካመኑበት ማለቴ ነውና ትንሽ የተደበላለቀ ነው የሆነብኝ ጉዳዩ፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ ድሮ የኦነግ አባል ነበሩ፡፡ በስደት ከሚኖሩበት አገር ወደ ኢትዮጵያ ሲመጡም የፖለቲካ ፓርቲ ነበረዎት፡፡ በመጨረሻ ላይ ግን ከፓርቲ ወጥተው በግል ተወዳድረው የፓርላማ መቀመጫ አግኝተዋል፡፡ ለምን በግል ለመወዳደር ፈለጉ?
ዲማ (ዶ/ር)፡- እንግዲህ ወደ አገር ቤት ስንመጣ የሆነ የፖለቲካ ድርጅት ነበረ፡፡ ይህ የፖለቲካ ድርጅት በሒደት በአንድ ወቅት ኦዲፒ ከሚባለው የኦሮሚያ ፓርቲ ጋር ውህደት ፈጸምን አለ፡፡ ከእኛው የኦሮሞ ዴሞክራሲዊ ግንባር (ኦዲግ) ጋር ማለት ነው፡፡ ከዚያ በኋላ እኔ ግለሰብ ነው የሆንኩት፣ የሌላ ፓርቲ አባል መሆንም አልፈለግኩም፡፡ መጀመርያ ኦነግ እየዘቀጠ ወደ ሌላ አዝማሚያ ሲሄድ አዲስ የገባሁበት ኦዲግም ቢሆን ከነበረው የቀጠለ ነው እንጂ እንደ አዲስ ፓርቲ አልገባሁም፡፡ ከዚህ በኋላ ሌላ ፓርቲ ውስጥ የመግባት ፍላጎቱም አቅሙም የለኝም፡፡ ስለዚህ በግሌ የተቻለኝን ልርዳ ብዬ በዚህ በኩል መጣሁ፡፡ አሁን ካየነው አንዳንዱ ሕዝብ አማራጭ የሚያጣበት ጊዜ አለ። ከሁለት ዓመት በፊት በነበረው ምርጫ ያው ለምርጫ የቀረበው ብልፅግና ፓርቲና ሌሎች የተበታተኑ ድርጅቶች ነበሩ፡፡ በጊዜው እኔ እንዳየሁት ይህን አገር ትንሽ እንኳ ለማሻገር ከብልፅግና የተሻለ አደረጃጀት ያለው ፓርቲ አልነበረም፡፡ በየመንደሩና በየከተማው ነው አብዛኛው ፓርቲ ያለው፡፡ ለምሳሌ እዚህ ባልደራሰ የሚባል ሠፈር አንድ ፓርቲ ሊኖር ይችላል፡፡ እናት ፓርቲ እዚያኛው ሠፈር እዚሁ አዲስ አበባ ውስጥ ነው በአብዛኛው ያለው፡፡ መዋቅሩን የዘረጋው ፓርቲ ብልፅግና ብቻ ነው፡፡ በፖለቲካው ልመንበትም አልመንበትም እሱም ብቻ ነው የነበረውና ሕዝቡም የግድ እሱን መምረጥ ነበረበት፣ ሌላ አማራጭ ስላልነበረው፡፡ እኔ ግን በግሌ የተቻለኝን ባለኝ ልምድና ዕውቀት አገሬን ለማገልገል ፈልጌ ነው የገባሁት፡፡ አሁን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተቻለኝን እያደረኩ ነው፡፡
ሪፖርተር፡- አስፈጻሚው አካል በፓርላማው ላይ ጫና የማሳደር አዝማሚያ እንዳለው ይወሳል፡፡ እርስዎ እንደሚባለው አስፈጻሚው አካል በምክር ቤቱ ላይ ጫና እያሳደረ ነው ብለው ያምናሉ?
ዲማ (ዶ/ር)፡- እንደዚያ እንኳን አላየሁም፡፡ በአጠቃላይ ግን በየትኛውም አገር ገዥው አካል ተፅዕኖ ያሳድራል፡፡ ብዙ የመንግሥት አካላትንም ስለሚቆጣጠር አስፈጻሚው አካል በተግባር ብዙ ሥልጣን አለው፡፡ የምክር ቤቱን ያህል የተጻፈ ሥልጣን ባይኖረውም ተፅዕኖ የማሳደር አቅም አለው፡፡ ይህ በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በየትኛውም ዓለም ያለ ነው፡፡ ለምሳሌ የእንግሊዝን ብንወስድ ከሺሕ ዓመት በላይ የቆየ ምክር ቤት ቢኖርም፣ አስፈጻሚው ምክር ቤት ውስጥ ያሉትን የራሱን አባላት ጠንካራ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ቢኖሩም፣ አገር የሚመራው ፓርቲ የፈለገውን ያህል የመጠምዘዝ (Manipulate) የማድረግ ሥልጣን አለው፡፡ አንዱን ይሾማል፣ አንዱን ይሽራል፣ ኮሚቴ ውስጥ ያስገባል፣ በአጠቃላይ ብዙ ሊያደርጋቸው የሚችላቸው አቅሞች አሉት፡፡ እዚህም አገር ከዚህ የተለየ ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን ምክር ቤቱ በሕገ መንግሥቱ ብዙ ሥልጣን ቢኖረውም፣ ያንን ሥልጣን ለመተግበር አቅም ያስፈልገዋል፡፡ ነገር ግን ብዙ አቅም የለውም፡፡ በሌሎች አገሮች ለምሳሌ በሕዝብ የተመረጡ ተመራጮች በየምርጫ ክልላቸው ጽሕፈት ቤት አላቸው፡፡ የሕዝቡን ጥያቄ የሚቀበሉ፣ የሚያስተናግዱና ወደ ተወካዩ የሚያስተላልፉ ሠራተኞች አሉ፡፡ ተወካዩም በየጊዜው በምርጫ ክልሉ ጽሕፈት ቤት ሄዶ የሕዝቡን ጥያቄና አስተያየት ያዳምጣል፡፡
እኛ የመረጠንን ሕዝብ ለማዳመጥ ስንሄድ የምናናግረው የአካባቢ አስተዳዳሪዎቹን ነው፡፡ ሕዝቡን የሚሰበስቡት እነሱ ናቸው (የብልፅግና ፓርቲ ማለት ነው)፡፡ ስለሆነም ምክር ቤቱ አቅም ሊገነባ ይገባዋል፡፡ በሕዝብና በምክር ቤት መካከል ያለውን ግንኙነት የሚያስተሳስሩት በየምርጫ ክልሉ የሚገኙ ጽሕፈት ቤቶች ናቸው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ በሌሎች አገሮች ምክር ቤቶች የጥናት ሥራዎች አገልግሎት አለ፡፡ እያንዳንዱ የምክር ቤት አባል የሚፈልጋቸውን ጉዳዮች ሊያስጠና ይችላል፡፡ እኛ ግን ብዙውን ነገር የምንጠይቀው አስፈጻሚውን አካል ነው፡፡ ስለውጭ ጉዳይ ወይም ስለሆነ ግንኙነት በተመለከተ የምንጠይቀው አካል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን ነው እንጂ፣ የራሳችን የምክር ቤቱ አጥኚ ክፍል የለም፡፡ ስለሆነም በእነሱ ላይ ጥገኛ እንሆናለን ማለት ነው፡፡ ሦስተኛው ጉዳይ የምክር ቤት አባላት እንዴት ነው የሚታዩት የሚለው ነው፡፡ ለመስክ ጉብኝትም ሆነ ለአንዳንድ ጉዳዮች ወደ ተመረጥንበት የምርጫ አካባቢ ስንሄድ፣ አንዳንዶቻችን በስምና በሌሎች ጉዳዮች ስለምንታወቅ እንጂ በአብዛኛው ከተመራጩ (ከምክር ቤቱ አባል) ይልቅ የወረዳ አስተዳዳሪው የበለጠ ዕውቅና አለው፡፡ ስለዚህ ለምክር ቤት አባላት ያለን ዕይታ በጣም ያነሰ ነው፡፡ ይህ በአንድ ጊዜ ይለወጣል ተብሎ ባይጠበቅም፣ በጊዜ ሒደት ሊለወጥ የሚችል ቢሆንም፣ ምክር ቤቱን ከአሠራሩ ጀምሮ እያጠናከርን መሄድ አስፈላጊ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- ፓርላማው ያፀደቃችው ሕጎች ብዙም ሳየቆዩ በሦስት ወይም በአራት ዓመት ተመልሰው እንዲሻሻሉ ይላኩለታል፡፡ ከጅምሩ በደንብ ታይተው ለረዥም ዓመት እንዲያገልግሉ ተደርገው ለምን አይዘጋጁም?
ዲማ (ዶ/ር)፡- በምክር ቤቱ አሠራር ውስጥ አንድ ሕግ ለኮሚቴ ከተመራ በኋላ፣ ኮሚቴው በሃያ ቀናት ውስጥ የውሳኔ ሐሳብ ማቅረብ አለበት የሚል ነው፡፡ ሊያስረዝምም ይችላል፡፡ ግን በሌላ በኩል ትኩረት ያለመስጠት ነው ብሎ ሊወሰድም ይችላል፡፡ አስፈጻሚው ራሱ በደንብ አስቦበትና ዓይቶት አያመጣውም፡፡ ለምሳሌ የመከላከያ አዋጅ የተሻሻለው ለሦስተኛ ጊዜ ነው፡፡ መጀመርያውኑ ታስቦበት ለዘላቂነት የሚያሠራ ሕግ ሠርተው አላመጡም ማለት ነው፡፡ እንደዚያም ስለሆነ ነው ኮሚቴያችን ረዥም ጊዜ ወስዶ፣ የሚመለከታቸውንም አካላት አናግሮ የተሻለና ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን ሊያሠራ የሚችል ሕግ ሊወጣ የቻለው፡፡ ሌሎቹ ይህን ያህል ትኩረት አይሰጡም፡፡ ሕግ አወጣጥ ላይ በራሱ በቂ የሆነ ትምህርትና ዕውቀትና ግንዛቤ የለም፡፡ የሕግና ሌሎች ክፍሎች ክንፍ ቢኖርም በቂ የሆነ የሰው ኃይል አለ የለም፡፡ የሌሎች አገሮች ፓርላማዎች ምርምር አድርገውና በዚያ ላይ ተመሥርተው ነው ሕጎችን የሚያዩት፡፡ ሕግ የማውጣት ሥልጣንን እንዴት ነው የምንጠቀምበት? አሠራሩ እንዴት ነው? የሚለውን አብዛኛው የምክር ቤቱ አባል በቂ የሆነ ዕውቀትና ግንዛቤ የለውምና በዚህ ጉዳይ ለመፍረድም ያስቸግራል፡፡ በአፄ ኃይለ ሥላሴ ጊዜ የወጡ አንዳንድ ሕጎች አሁንም አሉ፡፡ ነገር ግን ያኔ ረዥም ጊዜ ታስቦባቸው የተሠሩ ናቸው፡፡ ከዚያ ወዲህ ትንሽ የይድረስ የይድረስ ነገር አለ፡፡ ሌጋል ድራፍቲንግ (Legal Drafting) የሚባል ሒደት አለ፡፡ ይኼም መጀመርያ ፖሊሲ ወጥቶ በዚያ ላይ ለረዥም ጊዜ ውይይት ተደርጎ የፖለቲካ አካሉ የሚወስንበት ነው፡፡ ያንን ሲወስን ፖሊሲውን ወደ ሕግ ይመነዝረዋል፡፡ ይህንን የሚያደርገው የሕግ ባለሙያው ነው፡፡ እኛ አገር ብዙውን ጊዜ ፖሊሲ ሳይወጣ ነው ሕግ የሚወጣው፡፡ እንዲህ ዓይነት ክፍተት አለ፡፡ ወደፊት እየተማርንና እያሻሻልን እንሄዳለን ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ሪፖርተር፡- የምክር ቤቱ አሠራርና ሥነ ሥርዓት ደንብበ በተመለከተ የሚነሱ ክፍተቶች ላይ ምን ይላሉ? አልፎ አልፎ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ሐሳቡ ሲነሳ አሠራርና ሥነ ሥርዓት ተጠቅሶ እንዲቆም ይደረጋል፡፡
ዲማ (ዶ/ር)፡- ክፍተት አለው፡፡ አንደኛ የምክር ቤቱ አሠራርና ሥነ ሥርዓት ደንብ የሚባለውና በ2008 ዓ.ም. የወጣው፣ በጊዜው በነበረው ሥርዓት አንድ ኢሕአዴግ ብቻ ምክር ቤት ውስጥ የነበረበት ነው፡፡ አሁን ግን የገዥው ፓርቲ አባላት ተቃውመው ድምፅ የሚሰጡበት ሁኔታም አለ፡፡ በዚያን ጊዜ ግን ይኼ ነገር አይሞከርም ነበር፡፡ ስለዚህ የዚያን ጊዜ በወጣ ደንብ ነው የምንሠራው፣ ደንቡ ብዙ ክፍተቶች አሉት፡፡ ነገር ግን ኮሚቴ ተቋቁሞ እየተሻሻለ ነው፡፡ የተሻሻለው ደግሞ የተሻለ እንደሚያሠራ ተስፋ እናደርጋለን፡፡ ደንቡ መለወጥ አለበት፡፡ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያው ተፎካካሪ ለመሆን በዚያ ደረጃ መሆን ስላለብን ነው፡፡ እንደ እንግሊዝ ባሉ አገሮች ተፎካካሪ ፓርቲ ሲባል እንደ ገዥው ፓርቲ ሁሉ፣ የራሱ የሆነ ትይዩ ካቢኔ ያለውና መንግሥት መሆን የሚችል ነው፡፡ በዚያ ቁመና ላይ ስላልሆንን ነው ተቃዋሚ የምንላቸው፡፡ አንዳንድ የሥነ ሥርዓት ጥያቄ ትክክል ይመስለኛል፡፡ ከአሠራርም ደግሞ ግድፈት ሊኖር ይችላል፡፡ አንዳንዴ የፖለቲካ ነጥብ ለማግኘት የሚያነሱበት ጊዜ አለ፡፡
ሪፖርተር፡- ምክር ቤቱ ውስጥ ብዙውን ጊዜ ውሳኔዎች በሙሉ ወይም በአብላጫ ድምፅ ሲወሰኑ ይታያል፡፡ በእርስዎ ዕይታ ይህ የሚሆነው አባላቱ ለሕጉ ባላቸው ዕውቀት ነው? ወይስ ለፓርቲ ተገዥነት ብለው ነው?
ዲማ (ዶ/ር)፡- ፓርላማው ውስጥ እንዳየሁት አዋጅ ብዙ ጊዜ አከራካሪ አይደለም፡፡ እስካሁን የሚቀርቡት አዋጆች አከራካሪ አይደሉም፡፡ ሕግ ከአስፈጻሚው አካል (ሚኒስትሮች ምክር ቤት) ለምክር ቤት ሲመጣ ምክር ቤቱ የመጀመርያ ንባብ ያደርጋል፡፡ ከዚያ በኋላ ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ይመራል፡፡ የሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ደግሞ ጊዜ ወስዶ አዋጁን ከሕግ ባለሙያዎች ጋር ሆኖ በደንብ ይመረምረዋል፡፡ የአስረጂዎች፣ የባለድርሻ አካላት፣ እንዲሁም የሕዝብ መድረክም ይዘጋጃል፡፡ በዚህ ሒደት ውስጥ ብዙ ግብዓቶች ይገኛሉ፡፡ ብዙ መሻሻሎች ይደረጋሉ፡፡ ለምሳሌ የመከላከያን አዋጅ ከወሰድን የፖለቲካ ፓርቲዎችንም አወያይተናል፣ የሲቪል ማኅበራትንም አወያይተናል፡፡ የቀድሞ ጦር ሠራዊት አባላትንም፣ ሕዝቡንም አወያይተናል፡፡ ሕዝቡም በዌብሳይት፣ በኢሜይልና ስልክ አስተያየትና ጥያቄ ልኳል፡፡ ብዙ መድረኮችን አዘጋጅተናል፡፡ የአስረጂዎች መድረክ ሁለትና ሦስት ጊዜ አድርገናል፡፡ የሚመለከታቸው መሥሪያ ቤቶች ማለትም መከላከያ፣ ብሔራዊ ደኅንነት፣ የፍትሕ ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር፣ ዋና ኦዲተር፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ሳይቀሩ ጠርተን ሐሳባቸውን በመድረክ አወያይተን ቃለ ጉባዔ በመያዝ፣ ቃለ ጉባዔውን ኮሚቴው በመመርመር የሚሻሻለውን አሻሽሎ ነው መጨረሻ ላይ የውሳኔ ሐሳቡን ለምክር ቤቱ የሚያቀርበው፡፡ ይኼ ከቀረበ በኋላ ጥያቄዎችና አስተያየቶች ይነሳሉ፡፡ አጥጋቢ ነው የሚለውን ነው እጅ አውጥቶ የሚያሳልፈው አብዛኛው አባል፣ አወዛጋቢ የሆኑ ሕጎች ላይ ትልቅ ተቃውሞ ያሰማበት ጊዜ አለ፡፡
ሪፖርተር፡- በአገሪቱ የሚታየው የኑሮ ውድነት እየተባባሰ የዋጋ ንረቱ አልቀመስ ብሏል፡፡ መንግሥት በጣም ውድ የሚባሉ ፕሮጀክቶች ግንባታ እያካሄደ ነው፡፡ ይህን እንዴት ይመለከቱታል?
ዲማ (ዶ/ር)፡- እንግዲህ የፌዴራል መንግሥቱን በጀት የሚወስነው ይህ ምክር ቤት ነው፡፡ አሁን በቀጣዩ ወር ውስጥ የቀጣይ ዓመት በጀት ይቀርባል፡፡ ያን በጀት እንዴት ተጠቀመ ለሚለው ዋና ኦዲተር አለ፣ እኛ ይህንን እናያለን፡፡ እንደ ምክር ቤት ለፌዴራል መንግሥቱ የፈቀድነውን ገንዘብ እንዴት ተጠቀመው የሚለው ይመጣል፡፡ በሥርዓቱ እስከተጠቀመ ድረስ ችግር የለውም፡፡
ሪፖርተር፡- ፓርላማው አስፈጻሚው አካል የሚያከናውናቸውን ማናቸውንም ተግባራት መቆጣጠር የለበትም?
ዲማ (ዶ/ር)፡- ፓርላማው የሚቆጣጠረው የመደበውን በጀት ነው፣ ያልመደበውን ሊቆጣጠረው አይችልም፡፡ ሌሎች አንዳንድ ፕሮጀክቶች የሚከናወንበት ከሰዎች የተሰባሰበ ገንዘብ ይኖራል፡፡ በረዥም ጊዜ ሲታይ እነዚህ ፕሮጀክቶች ጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ፡፡ ለጊዜውም ቢሆን የተወሰነ የሥራ ዕድል የመፍጠር አቅም አላቸው፡፡ ዋናው ግን እሁን የሚታየው የአገሪቱ የኢኮኖሚ ችግር አንደኛ የውጭ ጫና ሲሆን፣ በሌላ በኩል የአገር ውስጥ ችግር የሚባሉት ጦርነት፣ ድርቅ፣ አንበጣ፣ ኮቪድና ጎርፍ ናቸው፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት የተከሰቱ ዓለም አቀፋዊ ችግሮች ነበሩ፡፡ እነዚህ ችግሮች በኢኮኖሚው ላይ ትልቅ ጫና ፈጥረዋል፡፡ ሰላምና መረጋጋት ለኢኮኖሚ ትልቁ መሠረት ነው፡፡ ሰው ወጥቶ ሠርቶና አምርቶ የማይበላባቸው አካባቢዎች ነበሩ፡፡ አብዛኛው ሕዝብ ማምረት ያልቻለበት ወቅት ነበር፡፡ በዚህ ላይ ተደምሮ ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች ለምሳሌ አሜሪካውያኑ በምሥራቅ አውሮፓ ዩክሬን ላይ የፈጠሩት ቀውስ የኢኮኖሚ መናጋት ፈጥሯል፡፡ ከሌሎች አገሮች ጋር ራሳችንን ስናወዳድር አብዛኛው የአገሪቱ ሕዝብ ገበሬ በመሆኑ፣ በዓለም አቀፍና በውጫዊ ጫናዎች መካከል ሆናም አገሪቱ በተሻለ መቆየት ችላለች፡፡
ሪፖርተር፡- እርስዎ ከዓመታት በፊት ወደ አገር ቤት ሲገቡ በኢትዮጵያ እየተካሄደ ያለውን ለውጥ አድንቀው፣ ነገር ግን በ1966 አብዮት ወደ ሥልጣን የመጣው የደርግ አገዛዝ የተማሪዎች አመፅን እንደቀለበሰው፣ በዚህም ምክንያት የአሁኑ ለውጥ እንዳይቀለበስ ሥጋትዎን አሰምተው ነበር፡፡ አሁን ከአምስት ዓመት በኋላ ለውጡን እንዴት አገኙት? መንግሥት ከሕዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይ (ሕወሓት) ጋር ያደረገውን የሰላም ስምምነትና በቅርቡ ተጀምሮ እንደተጠበቀው ጥሩ ውጤት ያላመጣው የመንግሥትና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት (ኦነግ ሸኔ) የዛንዚባር ንግግር እንዴት ያዩታል?
ዲማ (ዶ/ር)፡- እኔ አሁን በተለይ የተያዘውን በአዎንታዊ መንገድ ነው የማየው፡፡ በአገራችን ውስጥ ያሉ ችግሮችን ሁሉ በውይይት ለመፍታት የተያዘውን አዝማሚያ እደግፈዋለሁ፡፡ ከሕወሓት ጋር የተደረገውም ስምምነትና ከኦነግ ሸኔ ጋርም እየተደረገ ያለውን ውይይት ጥሩ ነው፡፡ ሌሎችም ወደ ሰላም የመጡ አሉ፡፡ ለምሳሌ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ የነበሩ ታጣቂዎችና ሌሎችም ወደ ሰላማዊ ሕይወት ተመልሰዋል፡፡ ባለፉት አምስት ዓመታት ብዙ ችግሮች ነበሩብን፡፡ አብዛኞቹን ወያኔ የፈጠራቸው ናቸው፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ችግሮችን ለመፍታት የተያዘው ዘዴ ጥሩ ይመስለኛል፣ መቀጠል አለበት፡፡ ትዕግሥት ይጠይቃል፣ መናበብን ይጠይቃል፡፡ አሁን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ሲታይ ከመጀመርያው የተበላሸው፣ በአስመራ ውይይት ተደርጎ ኦነግ ወደ አዲስ አበባ እንዲገባ ሲደረግ የተፈጥረ ስህተት አለ፡፡ እንግዲህ ስህተት ተፈጸመ ምንም ማድረግ ስለማይቻል አሁን መስተካከል አለበት፡፡ ከጅምሩ የተስተካከለ ቢሆን ኖሮ አሁን የተፈጠረው ነገር አይታይም ነበር የሚል እምነት አለኝ፡፡ አሁን እዚህ ደረጃ ከደረስን ጥሩ ነው፡፡ ቢያንስ በዚህ ዓመት ውስጥ ማለትም በአውሮፓውያኑ አቆጣጠር በየቦታው የሚደረጉ ተኩሶችን ማቆም ቢቻል ጥሩ ነው ብዬ አስባለሁ፡፡ ለውጥ ብዙ ተግዳሮት አለው፡፡ እንዳልኩህ የ1966 ዓ.ም. አብዮት እንደተቀለበሰው ሁሉ፣ አሁን በኢትዮጵያ ያለውም ሊቀለበስ ይችላል፡፡ በዓለም ታሪክ ውስጥ አብዛኛው አብዮት ተቀልብሷል፡፡ ለውጥ ካመጡ ኃይሎች መካከል ሥልጣን ላይ የወጡት የሩሲያ ኃይሎች ብቻ ናቸው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1917 የነበረው የሩሲያ አብዮት እንደዚያ ነበር፡፡ እና ለውጡ እንዳይቀለበስ የለውጡ ኃይል መደራጀት አለበት፡፡ ጠንካራና ሕዝብን ያቀፈ የፖለቲካ ድርጅት ከሌለ ለውጡ በቀላሉ ሊቀለበስ ይችላል፡፡