Tuesday, September 26, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ባህሪን መግራት ያስፈልጋል!

በሥራ ላይ ያለው አወዛጋቢ ሕገ መንግሥት ከፀደቀበት ከ1987 ዓ.ም. ጀምሮ እስካሁን ድረስ ከተለያዩ አቅጣጫዎች ወቀሳዎችና ተቃውሞዎች ይቀርቡበታል፡፡ ከተቃውሞዎቹ መካከል በሕገ መንግሥቱ መግቢያ ላይ ኢትዮጵያዊነትን ወደ ጎን በማድረግ፣ ‹‹ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች›› የሚለው ሐረግ በዋነኝነት ይጠቀሳል፡፡ ኢትዮጵያውያን በብሔር፣ በቋንቋ፣ በባህል፣ በአኗኗር ዘይቤዎችና በሌሎች ጉዳዮች የተለያዩ ማንነቶች ቢኖሯቸውም፣ ለዘመናት በአንድነት ተሰባጥረው መኖራቸውና በትውልዶች ቅብብል እዚህ የደረሱ የጋራ ማኅበራዊ እሴቶቻቸው ተገፍተው ልዩነት የተሰበከበት ነው ተብሎም ይብጠለጠላሉ፡፡ የጋራ ማንነትና ዕጣ ፈንታ ያላቸው ኢትዮጵያውያን የአገሪቱ ሉዓላዊ የሥልጠን ባለቤት መሆናቸው ተክዶ፣ ‹‹ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች›› ናቸው መባሉ ሌላው የተቃውሞ መነሻ ነው፡፡ በተጨማሪም ‹‹የራስን በራስ ዕድል መወሰን እስከ መገንጠል›› የሚለው አንቀጽ ደግሞ፣ ሕገ መንግሥቱ አገር በታኝ አጀንዳ ይዞ ለመቀረፁ ዋነኛ ማሳያ እንደሆነ ተደርጎም ተቃውሞ ሲቀርብበት ኖሯል፡፡ ሌሎች ተያያዥነት ያላቸው አንቀጾችም ሕገ መንግሥቱ በትክክለኛ የፌዴራል ሥርዓት ምትክ፣ የጎሳ ፌዴራሊዝም እንዲንሰራፋ ምክንያት መሆኑ ለተቃውሞ መጠናከር ሰበብ ሆኗል፡፡ ከፍተኛ ምሬት ያለባቸው ከማሻሻል በላይ ተቀዶ ቢጣልም ይመርጣሉ፡፡

ሕገ መንግሥቱ እንዳይነካባቸው የሚፈልጉ ደግሞ ኢትዮጵያ በዚህ ሕገ መንግሥት አማካይነት ‹‹ከብሔር ብሔረሰቦች እስር ቤትነት›› መላቀቋን በማውሳት፣ ኢትዮጵያውያን በብዝኃ ማንነታቸው በአገራቸው ጉዳይ እንዲካተቱና እንዲሳተፉ ትልቅ ሚና መጫወቱን ይሞግታሉ፡፡ እነሱ በትክክል እየተተገበረ ነው የሚሉት የፌዴራል ሥርዓት ኢትዮጵያን ወደ ላቀ ደረጃ እንደሚያደርስ፣ የሚቃወሙት ግን ‹‹አሀዳዊ ሥርዓት›› እንዲመለስ የሚናፍቁ ናቸው ብለውም ይከሳሉ፡፡ ከዚህ አልፈው ተርፈውም ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል መሞከር እንደማይታሰብም ያስጠነቅቃሉ፡፡ በዚህ መሀል ደግሞ እንደ ማንኛውም አገር ሕገ መንግሥት ወቅት እየጠበቁ ማነቆ የሆኑ አንቀጾችን ማሻሻል ጠቃሚ መሆኑን የሚያስረዱ ወገኖች አሉ፡፡ እንኳንስ በአንድ የፖለቲካ ጎራ ፍላጎት የተቀረፀ ሕገ መንግሥት ቀርቶ፣ በአንድ ትውልድ ዕሳቤና የዘመኑ አስተሳሰብ የፀደቀ ሕገ መንግሥትን ማሻሻል በብዙ አገሮች የተለመደ ነው ይላሉ፡፡ የኢትዮጵያ ሕገ መንግሥትም ቢሆን የራሱ ደጋፊዎች ያሉትን ያህል፣ ቁጥራቸው እጅግ በጣም በርካታ የሆኑ ተቃዋሚዎች ስላሉት ማሻሻያ ማድረግ የግድ ነው ሲሉም ያስገነዝባሉ፡፡

በቅርቡ በኢትዮጵያ የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት አማካይነት፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያን በተመለከተ የተሠራ ጥናት ይፋ መደረጉ ይታወሳል፡፡ በጥናቱ ግኝቶች ላይም ውይይት መደረጉ አይዘነጋም፡፡ በጥናቱ ላይ የሚመለከታቸው ባለሙያዎችና ባለድርሻ አካላት ከሚሰጡት ትንተና ባሻገር፣ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ለማድረግ ዝግጅት ሲደረግ ግን አስፈላጊ የሆኑ ጉዳዮች ላይ መነጋገር አስፈላጊ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ቅራኔዎች በጣም በተስፋፉበትና ለመግለጽ የሚያዳግቱ ግጭቶችና ጥቃቶች በሚፈጸሙበት በዚህ ጊዜ፣ ከምንም ነገር በላይ ጎልቶ መነገር ያለበት በሰከነ ሁኔታ ተቀምጦ ለመነጋገር የሚያስችል ሰላማዊ ዓውድ መፍጠር ተቀዳሚው ተግባር ነው፡፡ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሲከናወኑ የነበሩ ግጭቶች፣ ጥቃቶች፣ ግድያዎች፣ ማፈናቀሎችና ሌሎችም የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች አልበቃ ብለው፣ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ወገኖች ያለቁበት የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የፈጠረው ቀውስ አይዘነጋም፡፡ ይህም በቂ አይደለም ተብሎ በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ ከጦርነት ያልተናነሱ ግጭቶች ቀጥለዋል፡፡ በሕገ መንግሥት ጉዳይም ሆነ በሌሎች አገራዊ ጉዳዮች ላይ በሰከነ መንገድ ለመነጋገር ዕልቂትና ውድመት መቆም አለባቸው፡፡

የአገራቸው ዕጣ ፈንታ ጉዳይ የሚመለከታቸው ኢትዮጵያውያንም ሆኑ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ውስጥ ያሉ ተዋንያን፣ በኢትዮጵያ ሕጋዊና ሰላማዊ የመነጋገሪያ መድረክ ተፈጥሮ አላስፈላጊ ግጭቶች እንዲያበቁ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡ በዚህ በኩል በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥትም ሆነ ገዥው ፓርቲ መደላድሉን የማመቻቸት ኃላፊነት አለበት፡፡ በቅርቡ ይጀመራሉ ተብለው በሚጠበቁ አገራዊ የምክክር መድረኮችና በሌሎችም፣ የሠለጠነ ንግግር እንዲኖር ሚናውን መጫወት ይኖርበታል፡፡ በኢትዮጵያ ምድር ከጠመንጃ በመለስ ያሉ ሁሉም ሰላማዊ አማራጮች እንዲሞከሩ፣ ከመንግሥትም ሆነ ከገዥው ፓርቲ ብዙ ይጠበቃል፡፡ ችግር አለብን የሚሉ ወገኖችም ግማሽ መንገድ ድረስ መጥተው ለሰላማዊ ንግግሮች ዕድል እንዲፈጠር ኃላፊነት ይኖርባቸዋል፡፡ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚጋፉ ማናቸውም ኃላፊነት የጎደላቸው ድርጊቶች ተወግደው፣ በጠረጴዛ ዙሪያ ለመነጋገር የሚያስችሉ ዕድሎች እንዳይባክኑ ሁሉም ዜጎች አስተዋፅኦ ያበርክቱ፡፡ ጽንፍ ይዞ የቃላት ጦርነትና ደም አፋሳሽ ግጭት ውስጥ ተዘፍቆ መቅረት ለማንም አይጠቅምም፡፡ በሕገ መንግሥቱ ማሻሻያም ሆነ በሌሎች ብሔራዊ ጉዳዮች ላይ፣ በሰከነ መንገድ ከመነጋገር ውጪ ሌላው አማራጭ አውዳሚ ነው፡፡

የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ለጥናቱ መነሻ ዓላማ ብሎ ያቀረባቸው አምስት ነጥቦች ትኩረት የሚያስፈልጋቸው ናቸው፡፡ እነሱም አንደኛው ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል ያለውን የሕዝብ ፍላጎት ለመመርመር፣ ሁለተኛ ማሻሻያ የሚያስፈልጋቸውን የሕገ መንግሥት አንቀጾችና ክፍሎችን ለመፈተሽ፣ ሦስተኛ ሕገ መንግሥቱን ለማሻሻል የሚገፉ ማኅበራዊና ፖለቲካዊ ምክንያቶችን ለመመርመር፣ አራተኛ የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ሒደትን የሚያግዙ ወይም የሚያደናቅፉ ምክንያቶችን ለመገመት፣ እንዲሁም አምስተኛ የተመረጡ አገሮችን የሕገ መንግሥት ማሻሻያ ልምዶች ለመቀመር ወይም ለማካተት የሚሉ ናቸው፡፡ ምናልባት ሌሎች የሚያስፈልጉ ግብዓቶች ሊኖሩ ቢችሉ እንኳ፣ የአገር ጉዳይ የሚያገባቸው ወገኖች በእነዚህ መሠረታዊ ነጥቦች ላይ ተግባብተው መነጋገር አያዳግታቸውም ተብሎ ይታሰባል፡፡ ከፋም ለማም ለመንደርደሪያ የሚሆን ተነሳሽነት ሲኖር አጋጣሚውን በመጠቀም፣ አገር ከገባችበት አጣብቂኝ ውስጥ ለማውጣት የበኩልን ድርሻ መወጣት ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ ወጪ እንደተለመደው በፀጉር ስንጠቃ ከንቱ ፖለቲካ መወዛገብ፣ ኢትዮጵያን ወደ ጥፋት ጎዳና መንዳት እንጂ ፋይዳ የለውም፡፡

ሕገ መንግሥቱ እንዲሻሻልና ሁሉን አቃፊና አሳታፊ የፌዴራል ሥርዓት እንዲመሠረት፣ ከግትርነትና ከጽንፈኝነት መላቀቅ ግድ የሚባልበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ቀደም ሲልና አሁንም ተጠናክሮ ከቀጠለው የብሽሽቅ ፖለቲካ ውስጥ መውጣት ያስፈልጋል፡፡ ገዥው ፓርቲ ግራ እያጋባ ያለውን ባህሪውን በማስተካከል የፖለቲካ ምኅዳሩን ወለል አድርጎ መክፈት ግዴታው ነው፡፡ ኢትዮጵያ የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ለመገንባት ዕርምጃዋን ማጠናከር ያለባት አገር እንጂ፣ በአንድ አውራ ፓርቲ መዳፍ ሥር ተጠፍንጋ መያዝ እንደሌለባት መገንዘብ ተገቢ ነው፡፡ ከዚህ በፊት በዘመነ ኢሕአዴግ ያሰለቹ አላስፈላጊ ድርጊቶች በሙሉ ይገቱ፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ውስጣዊ ገመናቸውን ከመፈተሽ ጀምሮ፣ አደባባይ ድረስ ያላቸውን ተግባራዊ እንቅስቃሴ ሥርዓት ማስያዝ ይኖርባቸዋል፡፡ ከገዥው ፓርቲ ጋር የሚያደርጉት ፉክክር ግለሰባዊ ተክለ ሰውነትን ማሳያ እንዳይሆን ይጠንቀቁ፡፡ ለኢትዮጵያ የሚበጁ የፖሊሲ አማራጮች ላይ ያተኩሩ፡፡ ለአቅመ ፓርቲነት የማያበቃ ቁመና ይዞ ዲስኩር ማስተጋባት ፋይዳ ቢስ ነው፡፡ ለዚህም ነው ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ሕገ መንግሥት ለማሻሻል ባህሪያቸውን መግታት የሚያስፈልጋቸው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

በቀይ ባህር ፖለቲካ ላይ በመከረው የመጀመሪያ ጉባዔ ለዲፕሎማቲክና ለትብብር አማራጮች ትኩረት እንዲሰጥ ጥሪ ቀረበ

ሰሞኑን በአዲስ አበባ ለመጀመርያ ጊዜ በቀይ ባህር ቀጣና የፀጥታ...

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...

የመጀመርያ ምዕራፉ የተጠናቀቀው አዲስ አበባ ስታዲየም የሳር ተከላው እንደገና ሊከናወን መሆኑ ተሰማ

እስካሁን የሳር ተከላውን ጨምሮ 43 ሚሊዮን ብር ወጪ ተደርጓል ዕድሳቱ...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአገር ጉዳይ የሚያስቆጩ ነገሮች እየበዙ ነው!

በአሁኑም ሆነ በመጪው ትውልድ ዕጣ ፈንታ ላይ እየደረሱ ያሉ ጥፋቶች በፍጥነት ካልታረሙ፣ የአገር ህልውና እጅግ አደገኛ ቅርቃር ውስጥ ይገባና መውጫው ከሚታሰበው በላይ ከባድ መሆኑ...

የትምህርት ጥራት የሚረጋገጠው የፖለቲካ ጣልቃ ገብነት ሲወገድ ነው!

ወጣቶቻችን የክረምቱን ወቅት በእረፍት፣ በማጠናከሪያ ትምህርት፣ በበጎ ፈቃድ ሰብዓዊ አገልግሎትና በልዩ ልዩ ክንውኖች አሳልፈው ወደ ትምህርት ገበታቸው እየተመለሱ ነው፡፡ በአዲስ አበባ ከተማ ሰኞ መስከረም...

ዘመኑን የሚመጥን ሐሳብና ተግባር ላይ ይተኮር!

ኢትዮጵያ በአዲሱ ዓመት ዋዜማ ሁለት ታላላቅ ክስተቶች ተስተናግደውባት ነበር፡፡ አንደኛው የታላቁ ህዳሴ ግድብ አራተኛ የውኃ ሙሌት ሲሆን፣ ሁለተኛው ኢትዮ ቴሌኮም በአዲስ አበባ ከተማ ያስጀመረው...