Tuesday, September 26, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎትና ፈቃድ ክፍያን ለመወሰን ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • አዳዲስ የክፍያ ተመኖች ግልጽ ማብራሪያ ሊቀመጥላቸው እንደሚገባ ጥያቄ ቀርቧል

በኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን የተረቀቀ የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎትና የፈቃድ ክፍያን ለመወሰን ረቂቅ መመርያ ተዘጋጀ፡፡

መመርያው ከኮሙዩኒኬሽን አገልግሎት ፈቃድ፣ ከሬዲዮ ፍሪኩዌንሲ፣ ከቁጥር አስተዳደርና ምደባ፣ እንዲሁም ከሬዲዮ ኮሙዩኒኬሽን፣ ከቴሌኮሙዩኒኬሽን መሣሪያዎች የቴክኒክ ብቃት ማረጋገጫ አገልግሎት የሚሰበሰበውን የክፍያ መጠን በአግባቡ መወሰን የሚያስችል መሆኑን ያብራራል፡፡

የኮሙዩኒኬሽን አገልግሎትና የፈቃድ ክፍያ ረቂቅ መመርያው እንደሚያብራራው፣ ባለሥልጣኑ የሚያስከፍላቸውን ክፍያዎች ውጤታማና ቀልጣፋ በሆነ መንገድ መሰብሰብ የሚቻልበት መንገድ ለመዘርጋት፣ የሚሰበስባቸውን ክፍያዎች ለአገልግሎቱ ተጠቃሚዎች ግልጽና ተደራሽ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ያስረዳል፡፡

የኢትዮጵያ ኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን አገር አቀፍና ዓለም አቀፍ የፈጣን መልዕክት አገልግሎቶችን ጨምሮ ሌሎች ተያያዥ አገልግሎት ሰጪዎች፣ የፈቃድና የአስተዳደራዊ ዓመታዊ ክፍያዎችን እንዲፈጽሙ ረቂቅ መመርያውን ለሕዝብ አስተያየት አቅርቦታል፡፡

በረቂቁ ላይ ብሔራዊ የፖስታ አገልግሎት ፈቃድ ለማግኘት የማመልከቻ  አንድ ሺሕ ዶላር፣ የአገልግሎት መስጫ ፈቃድ ክፍያ ለማግኘት 50 ሺሕ ዶላር፣ እንዲሁም ዓመታዊ የአስተዳደራዊ ክፍያ ደግሞ ከተቋሙ አጠቃላይ ዓመታዊ ገቢ ላይ በብር የሚከፈል 0.2 በመቶ መጠን ተቀምጧል፡፡

በሌላ በኩል ዓለም አቀፍ የፈጣን መልዕክት (ኩሪየር) አገልግሎት ፈቃድ ጠያቂዎች ለማመልከት 200 ዶላር፣ የፈቃድ ክፍያ ለማግኘት አምስት ሺሕ ዶላር፣ ዓመታዊ አስተዳደራዊ ክፍያ ደግሞ ከአጠቃላይ ዓመታዊ ገቢያቸው ላይ በብር የሚከፈል 0.4 በመቶ የሚከፍሉ ሲሆን፣ በተመሳሳይ የአገር አቀፍ የፈጣን መልዕክት  አገልግሎት ላይ የሚሰማሩ ተቋማት ደግሞ ለማመልከት ከሚጠየቁት 200 ዶላር ውጪ፣  የፈቃድ ክፍያ ለማግኘትና ለዓመታዊ አስተዳደራዊ ክፍያ አንድ ሺሕ ዶላር እንደሚሆን ተዘርዝሯል፡፡

የእሺ ኤክስፕረስ መሥራችና የኢትዮጵያ ፈጣን መልዕክት አገልግሎት ሰጪዎች ማኅበር ሊቀመንበር አቶ ጥጋቡ ኃይሌ ረቂቁን አስመልክቶ ለሪፖርተር በሰጡት አስተያየት፣ የኮሙዩኒኬሽን ባለሥልጣን እስከ ሰኔ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ለሕዝብ አስተያየት ያቀረበው ረቂቅ አስተያየት እንዲሰጥበት የተደረገበት መንገድ በዘርፉ ላይ ካሉ ውስን አገልግሎት አቅራቢዎች አንፃር፣ በድረ ገጽና በማኅበራዊ ትስስር ከሚሆን ይልቅ መደበኛ የግንኙነት አካሄድ ቢከተል ተገቢ ነው ብለዋል፡፡

በተጨማሪም ባለሥልጣኑ የሚሰጠውን የሕዝብ አስተያየት በተመለከተ የሚመለከታቸው አካላት ጠርቶ ማብራሪያ ሊሰጥበት የሚገባ ጉዳይ እንደሆነ፣ ይህም በመመርያው ላይ የተቀመጡ አሻሚ የሆኑ ጉዳዮችን ግልጽ ለማድረግ የሚያግዝ እንደሆነ አቶ ጥጋቡ አስረድተዋል፡፡

ለአብነትም ዓለም አቀፍ የፈጣን መልዕክት (ኩሪየር) አገልግሎት ሰጪና የአገር አቀፍ የፈጣን መልዕክት አገልግሎት ሰጪ ተብሎ በተገለጸው የመመርያው ክፍል ላይ፣ በተለይም ዓለም አቀፍ አገልግሎት በሚል የቀረበው ጉዳይ የውጭ ድርጅቶችን ነው የሚመለከተው? ወይስ የኢትዮጵያውያን ድርጅት ሆኖ አገልግሎታቸውን ወደ ውጭ የሚያቀርቡትን ነው? የሚለው አሻሚ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ በተጨማሪም ባለሥልጣኑ ለሚመድበው የቴሌኮሙዩኒኬሽን ቁጥር የምደባና ዓመታዊ ክፍያ አስመልክቶ ያለው ጉዳይ በተመሳሳይ ግልጽነትን የሚፈልግ እንደሆነ ሊቀመንበሩ ተናግረዋል፡፡

መመርያው ዘርፉ የሚመራበት ሕግ እንደ መሆኑ መጠን፣ በተለይ ከዚህ ቀደም ያልነበሩ ጉዳዮችን በማካተቱና ከፍተኛ ክፍያዎችንና ቅጣቶችን ስለያዘ ተገቢ የሆነ የስሚ መርሐ ግብር ሊዘጋጅለት እንደሚገባ ያስረዳው የፈጣን መልዕክት አገልግሎት ሰጪዎች ማኅበሩና ሌሎች ተቋማት አዳዲስ ረቂቅ ሕጎችን በሚያወጡበት ጊዜ የሚደረጉ የክርክርና የውይይት መድረኮችን በአስረጃነት አቅርቧል፡፡

አቶ ጥጋቡ እንደገለጹት፣ በረቂቁ ውስጥ የተቀመጡት አዳዲስ የክፍያ ተመኖች ግልጽ ማብራሪያ ሊቀመጥላቸው ይገባል፡፡ የፈጣን መልዕክት አገልግሎት ሰጪዎች ከዚህ ቀደም በነበረው ሁኔታ በዓመት አንድ ጊዜ በተቆጣጣሪ አካል በተዘጋጀ ቅፅ መሠረት ተገምግመው ፈቃዳቸው እንደሚታደስ፣ ከዚያ በተጨማሪ ሲከፍሉ የቆዩት የገቢ ግብር፣ የጡረታና የመሳሰሉት ክፍያዎችን ነበር፡፡ ከዚያ ውጪ በሚመለከተው ተቋም የሚደረጉ ተጨማሪና ዕገዛዎችና ድጋፎች በሌሉበት ሁኔታ ለዕድሳት የተቀመጠው ክፍያ፣ በአገር ውስጥ የገንዘብ መገበያያ ለሚሰጥ አገልግሎት በውጭ አገር ገንዘብ ክፍያ እንዲፈጸም መደረጉ ማብራሪያ የሚያስፈልገው መሆኑን አክለዋል፡፡

በሌላ በኩል ኢኮኖሚው በተለያዩ ጉዳዮች በተዳከመበት ምክንያት፣ እንዲሁም ከዚያ ለመላቀቅ ጥረት በሚደረግበት ወቅት ትልልቅ የሚባሉ ክፍያዎችን በዘርፉ ላይ መጫን የወቅታዊነት ተጠየቅ የሚነሳበት ያለው የፈጣን መልዕክት አገልግሎት ሰጪዎች ማኅበር፣ ጉዳይን አስመለክቶ ባለሥልጣኑ ግልጽ ማብራሪያ እንዲሰጥ ደብዳቤ እንዳስገባና ከአባላቱም አስተያየት እያሰባሰበ መሆኑን አስታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች