በአዲሱ የአስፈጻሚ አካላትን ሥልጣንና ተግባርን በሚወስነው አዋጅ እንዲፈርስ የተደረገው የንግድ ውድድርና ሸማቾች ጥበቃ ባለሥልጣንን፣ መንግሥት መልሶ እንዲያቋቁመው ጥያቄ ቀረበ፡፡
በመስከረም ወር በ2014 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ ባለሥልጣኑን አፍርሶ በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ሥር በዴስክ ደረጃ ያዋቀረው ሲሆን፣ ባለሥልጣኑን መልሶ ማቋቋም ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ስለሚኖሩት፣ መንግሥት በድጋሚ ሊያዋቅረው እንደሚገባ ባለሙያዎች አሳስበዋል፡፡
ሐሙስ ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. በሃያት ሬጀንሲ ሆቴል ‹‹የሸማቾች ጥበቃ በጂዲታል ኢኮኖሚ›› በሚል ርዕስ ተካሂዶ በነበረ የውይይት መድረክ ላይ ተሳታፊ የነበሩ ባለሙያዎች፣ በዲጂታል የገንዘብ ልውውጥ ዘመን መኖር ስላለበት የሸማቾች መብት ጥበቃ ላይ ሐሳቦች ሲሰነዘሩ፣ በኢትዮጵያም የባለሥልጣኑ እንደገና መቋቋም አስፈላጊነት ተነስቶ ነበር፡፡
በመድረኩ የፓናል ውይይት ተሳታፊ የነበሩት ጠበቃ አቶ መስፍን ታፈሰ የተባሉ የሕግ ባለሙያ በሰጡት አስተያየት፣ በተለያዩ አገሮች ራሱን የቻለ ከሸማቾች ጥበቃ ጋር በተያያዘ የሚሠራ ትልቅ ተቋም እንዳለ ተናግረዋል፡፡
በምሳሌያቸውም ጠንካራ የሚባሉትን የደቡብ አፍሪካውን ብሔራዊ የሸማቾች ኮሚሽንና የኬንያውን የውድድር ባለሥልጣን በማውሳት፣ በኢትዮጵያ ሥራ ላይ የነበረው ባለሥልጣን በመፍረሱ ‹‹ወደኋላ ነው የተመለስነው፤›› ብለዋል፡፡
‹‹ለመንግሥት የእኔ ምክር የሚሆነው ይኼንን ባለሥልጣን መልሶ ማቋቋም ነው፤›› ያሉት አቶ መስፍን፣ ባለሥልጣኑ ሥልጣን ኖሮት ኅብረተሰቡን በማስተማር ጥሩ ተቋም ሆኖ ለረዥም ጊዜ መሥራት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
ሌላው በመድረኩ ላይ ስለመወያያ ርዕሱ የራሳቸውን ገለጻ ሲያደርጉ የነበሩት የፌር የፋይናንስ አማካሪ ድርጅት ዳይሬክተር ሩፋኤል ማዜር የተባሉ ባለሙያ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ የተለያዩ የዘርፍ ተቋማት በውስጣቸው የውድድርና የሸማቾች ጥበቃን የሚመለከት ትኩረት ያደረጉ ፖሊሲዎች ቢኖሩዋቸው መልካም እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
ባለሙያው አገሮች ራሱን ችሎ የሚቋቋም ተቋም ያስፈልጋቸዋል ብለዋል፡፡ በአዲሱ አወቃቀር አማካይነት የመንግሥት ተቋማት በሥራቸው የሸማቾች ጥበቃንና ውድድርን የሚመለከት ቡድን እንዲያቋቁሙ ለማድረግ ባለሥልጣኑ መፍረሱ ይታወሳል፡፡
ሩፋኤል እንደገለጹት፣ እንደ ኬንያና በቀጣናው ውስጥ ያሉትን የሌሎች አገሮች ኢኮኖሚን እንደ ምሳሌ በማንሳት፣ ተወዳዳሪነትን ያማከሉ እንደ ሞባይል ገንዘብና ሜትር ታክሲ ዓይነት ቢዝነሶች ላይም ሸማቾችን ያማከሉ ፖሊሲዎች ያወጣሉ።
የውድድር ባለሥልጣን በሌለባቸው የተወሰኑ አገሮች ውስጥ እንደሠሩ ባለሙያው ገልጸው፣ ባለሥልጣኑ ባለመኖሩ የሚጠበቁ ችግሮች ገጥሟቸው እንደሚያውቅ ተናግረዋል፡፡ የገጠሙትን ችግሮች ለመፍታት ኃላፊነት ያለባቸው ምንም ዓይነት ተቋማት አለመኖራቸውንም አክለዋል፡፡
በፓናል ውይይቱ ተሳታፊ የነበሩት የቀድሞው የኬንያ ውድድር ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ፍራንሲስ ካሩይኪ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ሲሰጡ መንግሥትን ምን ማድረግ እንዳለበት መምከር እንደማይፈልጉ፣ ነገር ግን ጥሩ የውድድር ባለሥልጣን ከሌለ የኩባንያዎች ሞኖፖሊን ማበረታታት ሊሆን እንደሚችል አስረድተዋል፡፡
‹‹በኢኮኖሚው ውስጥ የሚኖረውን የኩባንያዎች ውህደትና ግዥ ባለሥልጣኑ መገምገምና ማፅደቅ ይኖርበታል፤›› ሲሉ፣ የውድድር ባለሥልጣን መኖርን አስፈላጊነት ገልጸዋል፡፡
እምነት የተጣለበት የውድድር ባለሥልጣን ለኩባንያዎች ቀላል በሆነ መንገድ ወደ ገበያ መግባትን ያረጋግጣል ያሉት ፍራንሲስ፣ በዚህም አዳዲስ ባለሀብቶች ወደ ገበያ እየገቡ ነፃና ፍትሐዊ ውድድር እንደሚኖር ተናግረዋል፡፡