Thursday, June 13, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊመንግሥት በፈጠረው ችግር አርሶ አደሩ ማዳበሪያ በእጥፍ ዋጋ ለመግዛት መገደዱን ገለጸ

መንግሥት በፈጠረው ችግር አርሶ አደሩ ማዳበሪያ በእጥፍ ዋጋ ለመግዛት መገደዱን ገለጸ

ቀን:

መንግሥት በፈጠረው ችግር ምክንያት የ2015/16 ዓ.ም. የምርት ዘመን ተፈላጊውን የአፈር ማዳበሪያ በክልሎች በተለይም በአማራ ክልል በወቅቱ ባለመሰራጨቱ ግብዓቱን ከነጋዴዎች በዕጥፍ ዋጋ ለመግዛት መገደዳቸውን አርሶ አደሮች ተናገሩ፡፡

በአማራ ክልል ማዳበሪያ በአግባቡ አልደረሰንም ያሉ አርሶ አደሮች ከሰሞኑ በባህርዳር ከተማ ‹‹ጅራፍ እያጮሁ›› ማዳበሪያ እንዲቀርብላቸው በሰላማዊ ሠልፍ መጠየቃቸው ይታወሳል።

ከምዕራብ ጎጃም ይልማና ዴንሳ ወረዳ ደብረ ሞይ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ አርሶ አደሮች ለሪፖርተር እንደተናገሩት የአፈር ማዳበሪያ እጥረቱ እንደተጠበቀ ሆኖ በተበታተነ መልኩ የቀረበው ግብዓት ከአንዱ ወረዳ ወደ ሌላው ወረዳ እየተሰራጨ ያለው ኢ- ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ነው ብለዋል፡፡

- Advertisement -

መንግሥት ማቅረብ ያቀተውን ማዳበሪያ ነጋዴዎች ከፍተኛ ዋጋ እየሸጡ እንደሚገኙና የዝናብ ወቅቱን ለመሻማት በሚል አርሶ አደሩ በውድ ዋጋ ቢገዛም መንግሥት እንደሚይዛቸው ገልጸዋል፡፡ ነጋዴዎች 50 ኪሎ የሚሆነውን ግብዓት እስከ ስድስት ሺሕ ብር በሚደርስ ዋጋ እንደሚሸጡ የገለጹት አርሶ አደሮቹ፣ ከዚህ ቀደም ግብዓቱ በመደበኛነት ሲቀርብ በኩንታል 3,600 ብር እንደነበር አስረድተዋል፡፡

አርሶ አደሮቹ የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ እንዳይደርሳቸው የመንግሥት አስተዋጽኦ አለበት የሚል ዕሳቤ ላይ መድረሳቸውን ገልጸው፣ መንግሥት ገብዓቱን ባላቀረበበት ሁኔታ ነጋዴው ከተለያየ አካባቢ አምጥቶ ለገበሬው ማቅረቡን ሊኮነን እንደማይገባው ተናግረዋል፡፡

አምና በተመሳሳይ ወቅት ማዳበሪያ ደርሷቸው ዘርተው፣ ኩትኳቶ የጀመሩበት ወቅት እንደነበር፣ በዚህ ወቅት ተፈላጊው ዝናብ እየዘነበ ቢሆንም ማዳበሪያ በሌለበት ዘር መዝራት ትርፉ ድካም እንደሆነ አርሶ አደሮቹ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

ችግሩ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ጥያቄውን ለሚመለከተው አካል ለማድረስ ከወረዳ እስከ ክልሉ ግብርና ቢሮ እንደሄዱ እስከ ግንቦት 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ይደርሳችኋል የሚል ምላሽ ተሰጥቷቸው እንደነበር በማስታወስ፣ ነገር ግን ይኼ ባለመሆኑ ባህር ዳር ለሰላማዊ ሠልፍ ለመውጣት እንደተገደዱ አርሶ አደሮቹ  አስታውቀዋል፡፡

ጥያቄያቸውን ለክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ለማቅረብ ቢፈልጉም በተወካይ አማካይነት ‹‹ጠብቁ ይገባል›› የሚል ምላሽ እንዳገኙ አክለዋል፡፡ በባህር ዳር ከተማ ያደረጉትን ሠልፍ ተከትሎ ግማሽ ኩንታል ማዳበሪያ ለአራት ለአርሶ አደሮች መሠራጨቱን፣ ይህም ‹‹ለይምሰል የተደረገ›› መሆኑን አክለዋል፡፡

በአማራ ክልል ከተከሰተው የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ችግር ጋር በተያያዘ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የክልሉ ግብርና ቢሮ የግብዓትና ገጠር ፋይናንስ ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሙሽራ ሲሳይ ለሪፖርተር እንዳስታወቁት፣ ከታኅሳስ መጨረሻ ጀምሮ ሁሉንም የማዳበሪያ ዓይነት በማጓጓዝ ረገድ የተሻለ እንቅስቃሴ ቢኖርም ባለፉት ሁለት ወራቶች ከወደብ የአፈር ማዳበሪያ መጓጓዙ ቆሟል፡፡ ይህ በመሆኑ ለአርሶ አደሩ የመዝሪያው ወቅት ደርሶ በተለይም በአማራ ክልል የማዳበሪያ እጥረት ማጋጠሙን ወ/ሮ ሙሽራ ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የገጠመው የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር የማይሸፋፈንና ለአማራ ክልል መቅረብ የሚገባውን ያህል አለማቅረቡን ወ/ሮ ሙሽራ አስታውቀዋል፡፡ በአገሪቱ በአጠቃላይ ከቀረበው ወይም ከተገዛው ማዳበሪያ ለየትኛው ክልል ምን ያህል ቀረበ? የሚለው መገናኛ ብዙኃን ገለልተኛ ሆነው ሊመረምሩት የሚገባ ጉዳይ መሆኑን አክለዋል፡፡

በአማራ ክልል ለ2015/16 የምርት ዘመን 9.2 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ ጋር ለማቅረብ ዕቅድ ተዘጋጅቶ ለግብርና ሚኒስቴር የተላከ ሲሆን፣ በአገሪቱ ካለው አጠቃላይ ሁኔታ አኳያ ከዕቅዱ ውስጥ የተገዛው 5.29 ሚሊዮን ኩንታል ወይም 57 በመቶ መሆኑ ታውቋል፡፡

ከ5.29 ሚሊዮን ኩንታል ውስጥ እስካሁን ለክልሉ የደረሰው 1.9 ሚሊዮን የሚሆነው እንደሆነና በመጀመርያ ዙር የገባውን 1.5 ሚሊዮን ኩንታል ማዳበሪያ በቆሎ ቅድሚያ ለሚዘሩ አካባቢዎች ደጋማ የአየር ንብረት ያላቸውን ጭምር በፍትሐዊነት መዳረሱን ዳይሬክተሯ አስረድተው፣ ነገር ግን ከወደብ መጓጓዝ በመቆሙ ምክንያት የበቆሎ መዝሪያ ወቅት እንደደረሰና አርሶ አደሩ የሚዘራበት ማዳበሪያ እንዳጣ ተናግረዋል፡፡

ክልሉ ከግብርና ሚኒስቴር ጋር ተነጋግሮ በግብርና ሥራዎች ኮርፖሬሽን በክምችት መልክ ያለውን 150 ሺሕ ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ በብድር በመግዛት በቆሎ ለሚዘሩ አምስት ዞኖች በልዩ ሁኔታ ተመድቧል ያሉት ወ/ሮ ሙሽራ፣ በተጨማሪም ከሳምንት አስቀድሞ አንድ መርከብ ይዞት የመጣውን ማዳበሪያ በቆሎ ለሚዘሩ አካባቢዎች መቅረቡን  ገልጸዋል፡፡

በቆሎ ለመዝራት በቂ የሆነ ግብዓት ስለሌለ ነው አርሶ አደሩ አቤቱታ እያነሳ ያለው ያሉት ወ/ሮ ሙሽራ፣ ከዚያ አስቀድሞም የሥርጭቱ ጉዳይ አስቸጋሪ የነበረው የቀረበው ማዳበሪያ መጠኑ ትንሽ ስለነበር ለየትኛው ቅድሚያ ይሰጥ? በሚል ምክንያት ነው ብለዋል፡፡

በምሥራቅ ጎጃም፣ በምዕራብ ጎጃምና አዊ ዞኖች ግለሰብ ነጋዴዎች ማዳበሪያን ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ በማከል ሲሸጡ በተደረገ ክትትል እንደተያዙ፣ የዚህ ድርጊት ምንጭ ሲጣራ ለምሥራቅ ጎጃም አጎራባች ከሆነው የኦሮሚያ ክልል፣ ለአዊ ዞን ደግሞ ከቤንሻንጉል ይመጣል ተብሎ ሲነገር የስሚ ስሚ እንደሚነገር ኃላፊዋ አስታውቀዋል፡፡

 የክልሉ ግብርና ቢሮ በዚህ መልኩ የተገኘውን ማዳበሪያ አርሶ አደሩ በመደበኛ መሸጫ ዋጋ እንዲገዛው እየተደረገ መሆኑ ተገልጾ፣ አርሶ አደሩ ሕገወጥ ነጋዴው በተለያዩ መልኩ በሚያቀርብለት ዋጋ ከመግዛት ይልቅ ለሚመለከተው የግብርና አካል ጥቆማ አቅርቦ ማዳበሪያውን በተመጣጠነ ዋጋ የሚገዛበትን ዕድል መጠቀም ይገባዋል ተብሏል፡፡

‹‹ችግሩን ለመፍታት ጥረት እያደረግን ነው፡፡ ግብዓቱ በአሁን ወቅት እየቀረበ ሲሆን ሥርጭቱን የበለጠ ለማስኬድ አመራሩ ለማን ቅድሚያ ይስጥ? የሚለውን ቀበሌ ድረስ ወርዶ ለመደገፍ መስክ ወርዷል፤›› ሲሉ ኃላፊዋ ገልጸዋል፡፡

የአማራ ክልል ይቀርብለታል የተባለው 5.29 ሚሊዮን ኩንታል ተጠቃሎ እስከ ሰኔ ወር አጋማሽ ይደርሳል የሚል ዕቅድ እንደነበረ፣ አሁን ላይ የስድስት መርከቦች ኤልሲ (LC) እንደተከፈተና ከዚህ ውስጥ አራት የሚሆኑት ኤንፒኤስ (NPS) መርከቦች በሰኔ ወር ይገባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይኼም ጤፍና ስንዴ ዘግይተው ለሚዘሩ አካባቢዎች ይደርሳል ተብሎ እንደሚጠበቅ ተጠቅሷል፡፡ ነገር ግን የተፈለገው ማዳበሪያ ሙሉ በሙሉ ተጠቃሎ መቼ ይደርሳል? የሚለው ጉዳይ የበላይ አካል ጭምር እንዳልገለጸ የክልሉ ግብርና ቢሮ የግብርና ግብዓትና ገጠር ፋይናንስ ዋና ዳይሬክተር ተናግረዋል፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ግንቦት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው መደበኛ ስብሰባ፣ የግብርና ሚኒስቴርን የ2015 ዓ.ም. የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሲገመግም የምክር ቤት አባላት በተያዘው ዓመት እየቀረበ ያለው የማዳበሪያ አቅርቦት በጣም ውስን መሆኑን፣ ከጥቂት ወራት በፊት በጀመረው ዝናብ ሳቢያ አሁን ማዳበሪያውን አርሶ አደር ማቅረብ እንዳልተቻለ፣ በቆላማ አካባቢ የሚገኙ አርሶ አደሮች ማሽላ ያለ ማዳበርያ እየዘሩ መሆኑን፣ በደጋ አካባቢ ያሉ የቢራ ገብስ አምራቾችም ያለ ምንም የአፈር ማደበሪያ አቅርቦት እየሠሩ መሆናቸውን አስታውቀው ነበር፡፡

የግብርና ሚኒስቴር ደኤታ ሶፊያ ካሳ (ዶ/ር) ለምክር ቤት አባላት እንዳስታወቁት፣ ትልቁ ነገር ማዳበሪያ አገር ውስጥ ማስገባት ብቻ ሳይሆን፣ የገባውን ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ እስካልተሰጠ ድረስ ማዳበሪያ አቅርቧል ብሎ በሙሉ ልብ መቀመጥ አይቻልም ሲሉ አክለዋል፡፡

ለአሮሚያ ክልል 2.4 ሚሊዮን ኩንታል፣ ለአማራ ክልል 1.3 ሚሊዮን ኩንታል የአፈር ማዳበሪያ አለመተላለፉን በወቅቱ የተናገሩት ሚኒስትር ደኤታዋ፣ ማዳበሪያን በመጋዘን ውስጥ ይዞ አርሶ አደሩን ማስጮህ ተገቢ ባለመሆኑ ክልሎች፣ ዞኖችና ወረዳዎች ማዳበሪያ ወስደው ወደ አርሶ አደሩ ማድረስ አለባቸው ብለዋል፡፡ ‹‹የምክር ቤት አባላት በየምርጫ ጣቢያቸው በየደረጃው ያለውን አመራር በመጠየቅ ተባበሩን፤›› በማለት አሳስበው ነበር፡፡

የግብርና ሚኒስትሩ ግርማ አመንቴ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ወደ አገር ውስጥ የገባ ማዳበሪያ ለአርሶ አደሩ የማድረስ ጉዳይ አንገብጋቢና የምክር ቤቱን ዕገዛ የሚፈልግ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...