Tuesday, September 26, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበሀድያ ዞን ደመወዝ እየተከፈለ ያለው ለሆሳህና ከተማ የመንግሥት ሠራተኞች ብቻ መሆኑ ተነገረ

በሀድያ ዞን ደመወዝ እየተከፈለ ያለው ለሆሳህና ከተማ የመንግሥት ሠራተኞች ብቻ መሆኑ ተነገረ

ቀን:

በደቡብ ክልል ሀድያ ዞን 17 ወረዳዎችና ሦስት የከተማ አስተዳደሮች ውስጥ፣ ደመወዝ እየተከፈላቸው ያሉት ሆሳህና ከተማ ውስጥ ያሉ የመንግሥት ሠራተኞች ብቻ መሆናቸውን ተናገሩ፡፡

በሀድያ ዞን ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉት የመንግሥት ሠራተኞች እንደተናገሩት፣ በዞኑ በተለያዩ መንግሥት መሥሪያ ቤቶች ከ35,000 በላይ ሠራተኞች አሉ፡፡

ከእነዚህ የመንግሥት ሠራተኞች ውስጥ ደመወዝ በትክክል እየደረሳቸው የሚገኙት ሆሳህና ከተማ የሚገኙት ብቻ መሆናቸውን ሠራተኞቹ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡ በዚህም ሳቢያ በሌሎች ወረዳዎችና በሁለቱ ከተሞች በሚገኙ የጤና ተቋማት ደመወዝ ባለመከፈሉ፣ አንዳንዶቹ አገልግሎት መስጠት ማቆማቸውንና የተቀሩት ደግሞ ለስምንት ሰዓታት ብቻ እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

በተለይ የዞኑ መቀመጫ ከሆነችው ሆሳህና ውጪ የሚኖሩ ነዋሪዎች ሕክምና ለማግኘት፣ ከዞኑ ውጪ የሚገኙ አጎራባች ከተሞች እየሄዱ እንደሚታከሙ ነዋሪዎች ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው የሾኔ ከተማ ነዋሪ እንደተናገሩት፣ የሾኔ የመጀመርያ ደረጃ ሆስፒታል ከሚያዝያ 14 ጀምሮ ለሠራተኞች ደመወዝ ባለመክፈሉ አብዛኞቹ ሠራተኞች ከሥራ ቀርተዋል፡፡

እስከ ዓርብ ግንቦት 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ምሽት ዜናውን እስካጠናቀርንበት ጊዜ ድረስ፣ የሆስፒታሉ ሠራተኞች ሥራ ባለመግባታቸው የከተማው ነዋሪዎች ተገቢውን ሕክምና እያገኙ አይደሉም ተብሏል፡፡

እንደ ነዋሪዎቹ ገለጻ፣ የጤና መድን ሽፋን ያለው ግለሰብ እንኳን በሆስፒታል ወይም በጤና ተቋማት መታከም አልቻሉም፡፡

ከአዲስ አበባና ከሌሎች አካባቢዎች ለሥራ የመጡ ሠራተኞች የቤት ኪራይ ክፍያና መሠረታዊ ፍላጎታቸውን ማሟላት ባለመቻላቸው፣ ወደ መጡበት መመለሳቸውን ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

በሾኔ ከተማ ከመምህራን በስተቀር ሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች ደመወዝ እንዳልተከፈላቸው፣ ሠራተኞች ችግሮቻቸውን ለሚዲያ አውጥተው እንዳይናገሩ ማስፈራሪያና ዛቻ እየደረሰባቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የሾኔ የመጀመርያ ደረጃ ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር ተድላ አካሉ ከሚያዝያ 14 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ አብዛኞቹ የሆስፒታሉ ሠራተኞች በገዛ ፈቃዳቸው ሥራቸውን አቁመዋል ብለዋል፡፡  

በሆስፒታሉ አገልግሎት እየተሰጠ የሚገኘው በየክፍሎቹ አመራሮች አማካይነት መሆኑን የገለጹት ሜዲካል ዳይሬክተሩ፣ አብዛኞቹ ባለሙያዎች ደመወዝ ስላልተከፈላቸው ሥራ አለመግባታቸውን አስረድተዋል፡፡

ከዚህ ሆስፒታል በተጨማሪ አገልግሎት የማይሰጡ ሆስፒታሎች መኖራቸውን ጠቁመው፣ ሁመቾና ጊቢቾ የተሰኙ የጤና ተቋማት አገልግሎት እየሰጡ አይደሉም ብለዋል፡፡

ከሚያዝያ 14 ቀን 2015 ዓ.ም. እስከ ግንቦት 24 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ሠራተኞቹ በሥራ ላይ እንዳልተገኙ ሜዲካል ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡

የመንግሥት ተቋማት በተለይም ሆስፒታሎች አገልግሎት አሰጣጣቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ ዝቅተኛ እየሆነ መምጣቱን ጠቁመው፣ መንግሥት ተገቢውን ትኩረት እንዲሰጥ ጠይቀዋል፡፡

መንግሥት ለጤና ተቋማት ያለው ትኩረት ዝቅተኛ በመሆኑ፣ የመድኃኒት አቅርቦትም አነስተኛ መሆኑንም አልሸሸጉም፡፡ ከጤና መድን አገልግሎት ውጪ ያሉ አገልግሎቶች እየተሰጡ አይደለም ብለዋል፡፡

ሆስፒታሉ የሚገኝበት ሾኔ ከተማ ሦስት ወረዳዎችን የሚያዋስን በመሆኑ ከ600,000 በላይ ሰዎችን ያገለግላል ብለዋል፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ መድኃኒት እየቀረበ ባለመሆኑ፣ ሆስፒታሉ አገልግሎት የሚሰጠው የጤና መድን ሽፋን በጀትን ተጠቅሞ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡   

ዞኑም ሆነ የከተማ አስተዳደሩ ለመድኃኒት ግዥ ብለው የሚሰጡት በጀት እንደሌለ፣ ተቋሙ አገልግሎት የሚሰጠው በጤና መድን ሽፋን አማካይነት ብቻ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

የሾኔ ከተማ ነዋሪና በሆስፒታሉ ውስጥ የጤና ባለሙያ የሆኑና ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ ግለሰብ ስለጉዳዩ ሲያብራሩ፣ የ2012 ዓ.ም. የጤና ባለሙያዎች የሦስት ወራት የትርፍ ሰዓት ክፍያ አልተከፈላቸውም ብለዋል፡፡  

በ2015 ዓ.ም. ደግሞ የጥቅምት ወር የትርፍ ሰዓት ክፍያ እንዳልተፈጸመ ገልጸው፣ ከሚያዝያ ጀምሮ ሁለት ወራት ሊሞላ የተቃረበ ክፍያም እስካሁን አልተፈጸመም ሲሉ ቅሬታቸውን ተናግረዋል፡፡

በዞኑ ትልቁ ችግር የመንግሥት ሠራተኞች መብታቸውን እንዳይጠይቁ ፅንፈኛ ናችሁ እየተባሉ ከፖለቲካ ጋር በማያያዝ እንደሚታፈኑ ገልጸዋል፡፡  

ሆስፒታሉ የግብዓት አቅርቦት ስለሌለውና ባለሙያዎች ሥራ ባለመግባታቸው፣ ሕፃናት መውሰድ ያለባቸውን ክትባት እንዳልወሰዱ የችግሩን ግዝፈትና ቀጣይ ሥጋት ተናግረዋል፡፡

የደቡብ ክልል የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈራ አባተ፣ ዋናው ችግር የሆነው ባለፉት ሰባት ዓመታት የአፈር ማዳበሪያ ለመግዛት ብድር ተወስዶ ስለነበር፣  ዞኑ በወቅቱ ብድሩን ባለመመለሱ ነው ብለዋል፡፡

ዞኑ ከአርሶ አደሩ የሰበሰበውን ገንዘብ ገቢ ማድረግ የነበረበት ቢሆንም፣ ገንዘቡ ገቢ ባለመደረጉ ምክንያት ደመወዝ መክፈል አለመቻሉን ገልጸዋል፡፡

ደመወዝ ለሠራተኞች ያለመክፈል ችግር የሀድያ ዞን ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎችም አካባቢዎች እንደሚስተዋል አቶ ተፈራ አክለዋል፡፡

በአሁኑ ወቅት የክልሉ መንግሥት በዞኑ የተፈጠረውን ችግር በተመለከተ ባደረገው ማጣራት በመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት የደመወዝ ጉድለት መኖሩ ማወቁንና ይህም ሆኖ የክልሉ መንግሥት የበጀት ጉድለቱን መሸፈኑን ጠቁመው፣ ከቀጣዩ በጀት ዓመት ታሳቢ የሚሆን ገንዘብ ለዞኑ መሰጠቱን ተናግረዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የቤት ባለንብረቶች የሚከፍሉትን ዓመታዊ የንብረት ታክስ የሚተምን ረቂቅ አዋጅ ተዘጋጀ

በአዋጁ መሥፈርት መሠረት የክልልና የከተማ አስተዳደሮች የንብረት ታክስ መጠን...

እንደ ንብረት ታክስ ያሉ ወጪን የሚያስከትሉ አዋጆች ከማኅበረሰብ ጋር ምክክርን ይሻሉ!

የመንግሥትን ገቢ በማሳደግ ረገድ አስተዋጽኦ እንዳላቸው የሚታመኑት የተጨማሪ እሴት...

ለዓለምም ለኢትዮጵያም ሰላም እንታገል

በበቀለ ሹሜ ያለፉት ሁለት የዓለም ጦርነቶች በአያሌው የኃያል ነን ባይ...