Tuesday, October 3, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

[ክቡር ሚኒስትሩ አምሽተው ወደ መኖሪያ ቤታቸው ሲገቡ ባለቤታቸው ‹‹ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን›› የሚለውን የቴሌቪዥን ዜና ተመልክተው ለብቻቸው ሲስቁ አገኟቸው]

  • ስልክ እያወራሽ ነበር እንዴ?
  • ኧረ በጭራሽ… ምነው?
  • ታዲያ ምንድነው ብቻሽን የሚያስቅሽ?
  • አይ… በቴሌቪዥኑ የሚቀርበው ነገር ነዋ።
  • ምንድነው?
  • ድሮ ድሮ ዜና ለመስማት ነበር ቴሌቪዥን የምንከፍተው፡፡
  • አሁንስ?
  • አሁንማ ቀልዱን ተያይዘውታል… አንተ ግን በደህናህ ነው ዛሬ ያለ ወትሮህ ያመሸኸው?
  • ከተቋማችን ሠራተኞች ጋር ቀኑን ሙሉ ኮንፈረንስ ላይ ነበርኩ፣ እሱን እንደ ጨረስኩ ደግሞ ቢሮ መግባት ነበረብኝ።
  • አንተም እዚያው ላይ ነዋ የዋልከው?
  • እዚያው ላይ ማለት?
  • ኮንፈረንሶች ተካሄዱ የሚል ዜና ነበር ለብቻዬ ሲያስቀኝ የነበረው፣ አንተም እዚያ ኮንፈረንስ ላይ ነበርክ ማለቴ ነው።
  • ምንድነው ታዲያ ያሳቀሽ… ኮንፈረንስ ተካሄደ መባሉ ነው ያሳቀሽ?
  • የኮንፈረንሱ መሪ ቃሉ ነው ያሳቀኝ።
  • መሪ ቃሉ ምን ይላል?
  • ፈተናዎችን ወደ ዕድል በመቀየር ሕዝባችንን እናሻግራለን የሚል ነው።
  • ታዲያ ምንድነው ያሳቀሽ?
  • ሁለቱም።
  • ሁለቱም ማለት?
  • ፈተናዎችን ወደ ዕድል መቀየር የሚለውም፣ ሕዝባችንን እናሻግራለን የሚለውም፣ ኧረ ሦስተኛም አለ…
  • እ… ሦስተኛው ምንድነው?
  • መሪ ቃሉ ራሱ ተሻጋሪ መሆኑ።
  • ተሻጋሪ ማለት?
  • ጊዜ አይገድበውም ማለቴ ነው።
  • እንዴት?
  • ይህንኑ መሪ ቃል ባለፈው ዓመትም ሰምቼው ነበር።
  • ታዲያ ብትሰሚውስ? ችግር አለው?
  • እኔ መስማቴ ችግር የለውም፣ ግን ደግሞ…
  • እ… ግን ድግሞ… ምን?
  • ፈተናውም፣ መሪ ቃሉም መሳ ለመሳ መቀጠላቸው ትንሽ አያስገርምም? እንዲያው አያስተዛዝብም?
  • ሁሉም ነገር በአንድ ጊዜ መፍትሔ ሊያገኝ እንደማይችል መዘንጋት የለበትም።
  • በፈተና ላይ ፈተና መደራረቡስ መዘንጋት አለበት?
  • ፈተናዎች የሚያፀኑን መሆኑም መዘንጋት የለበትም።
  • እሱ ደግሞ ቤታችሁ ስትሆኑ የምትጠቀሙት መሪ ቃል ነው?
  • ምኑ?
  • መዘንጋት የለበትም የምትለው? ይልቅ እስኪ ልጠይቅህ?
  • እሺ… ጠይቂኝ?
  • ባለፈው ወደ አዲስ አበባ የሚወስደው መንገድ በግጭት ምክንያት ተዘጋ ተብሎ ጤፍ ሰባት ሺሕ ብር መግባቱን ታስታውሳለህ?
  • አዎ።
  • አሁን ግን መንገዱ ተከፍቷል።
  • አዎ፣ መከላከያ ከገባ በኋላ መንገዱ ተከፍቷል።
  • የጤፍ ዋጋ ግን ሰባት ሺሕ ሆኖ ቀረ… አይደለም?
  • አዎ፣ ዋጋው ከወጣ በኋላ አልወረደም።
  • መንግሥት ፈተናውን ወደ ዕድል እቀይራለሁ እያለ ይምላል፣ መሪ ቃል ያወጣል እንጂ ፈተናውን ወደ ዕድል የሚቀይረው ሌላ ነው ማለት ነው?
  • ሌላው ማለት… ማነው?
  • ነጋዴው፡፡
  • ነጋዴውም ኦኮ የማኅበረሰቡ አካል ነው፣ ይኼ መዘንጋት የለበትም።
  • የከተማው ነዋሪ በኑሮ ውድነት ፈተና እየተሰቃየ ትምህርት ቤቶች መቶ ፐርሰንት ዋጋ መጨመራቸውስ… በዚህ ላይ ምንም አትሉም?
  • ምን እንላለን?
  • ወይ ፈተና ነው በሉ፣ ወይም ዕድል ነው በሉ፣ ካልሆነ ደግሞ እነሱም የማኅበረሰቡ አካል ናቸው በሉ።
  • በእርግጥ እነሱም የማኅበረሰቡ አካል ናቸው፣ ግን…
  • እ… ግን ምን?
  • የምንከተለው የነፃ ገበያ መር ኢኮኖሚ መሆኑ መዘንጋት የለበትም።
  • መዘንጋት የለበትም?
  • አዎ፣ የነፃ ገበያ የኢኮኖሚ መርህ እየተከተልን ዋጋ አትጨምሩ ማለት አንችልም፣ ይህ መዘንጋት የለበትም።
  • እንደዚያ ከሆነ እናንተም ተውታ?
  • ምኑን?
  • መዘንጋት የለበትም እያላችሁ ሕዝቡን አታስታውሱት… ተውት፡፡
  • ምኑን ነው የምንተወው?
  • መሪ ቃሉን!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

[ክቡር ሚኒስትሩ ለሁለት ሳምንት ያክል የፓርቲ ስብሰባ ላይ ቆይተው አመሻሹ ላይ ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ባለቤታቸው በአግራሞት ተቀብለው ስለቆይታቸው ይጠይቋቸው ጀመር]

እኔ እምልክ...? ውይ... ውይ... በመጀመሪያ እንኳን በሰላም መጣህ፡፡ እሺ ...ምን ልትጠይቂኝ ነበር? ይህን ያህል ጊዜ የቆያችሁት ለስብሰባ ነው? ስብሰባ ብቻ አይደለም። ከስብሰባ ውጪ ምን ነበር? በተለያዩ መሪ ሐሳቦች የተዘጋጁ ሥልጠናዎችን...

[ክቡር ሚኒስትሩ ለሁለት ቀናት የተካሄደውን የፓርቲያቸውን የሥራ አስፈጻሚ ስብሰባ አጠናቀው ወደ ቢሯቸው ሲመለሱ ቢሯቸው ውስጥ አማካሪያቸው አንድ ጽሑፍ በተመስጦ እያነበበ አገኙት]

ምንድነው እንደዚህ መስጦ የያዘህ ጉዳይ? መጡ እንዴ ክቡር ሚኒስትር፣ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ያወጣውን መግለጫ እያነበብኩ ነው፡፡ ግን እኮ ፊትህ ላይ የመገረም ስሜት ይነበባል፡፡ አዎ፣ መግለጫው ላይ...

[ክቡር ሚኒስትሩ እየጠራ ያለውን ሞባይል ስልካቸውን ተመለከቱ፣ የህዳሴ ግድቡ ተደራዳሪ መሆናቸውን ሲያውቁ ስልኩን አነሱት]

ሃሎ... ጤና ይስልጥኝ ክቡር ሚኒስትር? ጤና ይስልጥልኝ ክቡር ተደራዳሪ... የጥረትዎን ፍሬ በማየትዎ እንኳን ደስ አለዎት፡፡ እንኳን አብሮ ደስ አለን፣ ምን ልታዘዝ ታዲያ? የውኃ ሙሌቱንና አጠቃላይ የግድቡን የግንባታ ሁኔታ...