እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ መሆኑ ተደጋግሞ ይወሳል፡፡ ሃይማኖቶች ማኅበረሰቡን በሞራል ከማነፅ ጀምሮ ለአገር ግንባታ ያበረከቱት አስተዋጽኦ የማይተካ ነውም ይባላል፡፡ ከሺሕ ዓመታት በላይ ኢትዮጵያን በመቅረፅ አሁን ያለችበትን ሁለንተናዊ ማንነት በመፍጠር ረገድ፣ ሁሉም ሃይማኖቶች የየራሳቸውን ሚና ተጫውተዋል ተብሎም ይታመናል፡፡
ሕፃናት ከፊደል ገበታ ጋር የሚተዋወቁት በየመስጅዱ ባሉ መድረሳዎች፣ እንዲሁም በየቤተ ክርስቲያኑ በሚገኙ አብነት ትምሕርት ቤቶች ውስጥ መሆኑ ጎልቶ ይነገራል፡፡ ኢትዮጵያውያንን ያነፁ ‹‹ኦክስፎርዶች›› እና ‹‹ሀርቫርዶች›› ይጠቀሱ ከተባለ፣ ልጆችን ፊደል አስቆጥረውና ከጨቅላነት ጀምሮ በሥነ ምግባር ኮትኩተው ያሳደጉ መድረሳዎችና አብነት ትምሕርት ቤቶች ቀድመው መነሳታቸው የማይታበይ ሀቅ መሆኑ በስፋት ይወሳል፡፡
በዘመናዊ ትምህርት ፍቅርና ከውጭ ተቀድቶ በመጣ የትምህርት ሥርዓት ናፍቆት ኢትዮጵያ የራሷን ነባር እሴቶች ለመተው ብትገደድም፣ ከሺሕ ዓመታት በላይ ትውልዶችን ሲያንፁና ሲገነቡ የኖሩት መድረሳና አብነት ትምሕርት ቤቶች መሆናቸው በብዙ ምሁራን ጎልቶ ይነሳል፡፡
አሁንም ቢሆንም በየመስጅዱና በየአብያተ ክርስቲያናቱ የሚሰጡ መንፈሳዊ ትምህርቶች ልጆችን በሞራል በማነፅ ረገድ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳላቸው ነው የሚነገረው፡፡ በኢትዮጵያ የአንድ ቤተ ክርስቲያን ወይ መስጅድ መቃጠልና መውደም ማለት ጉዳቱ በገንዘብም ሆነ በንብረት ከሚገመተው በላይ ነው የሚለውን ብዙዎች ይስማሙበታል፡፡ የመንግሥትም ሆነ የግል ትምህርት ቤቶች የማይሸፍኑትን የሞራልና የግብረ ገብ ዕውቀት ለትውልዱ የሚያስጨብጡ መስጅዶችና ቤተ ክርስቲያናት መፍረሳቸው፣ እንደ አገር ከሚኖረው ትልቅ ጉዳት በተጨማሪ ለመንግሥትም ቢሆን ሸክም የሚያበዛ መሆኑ ይነገራል፡፡
የሕግ ምሁራን እንደሚናገሩት ከሆነ በመንግሥት አንዳችም በጀት ሳይሰጣቸውና የኢንቨስትመንት ማበረታቻም ሳይደረግላቸው ነው፣ የሃይማኖት ተቋማት ለማኅበረሰቡ የሞራልና የሥነ ምግባር ትምህርት የሚሰጡት፡፡ እነዚህ የሃይማኖት ተቋማት የሞራልና የሥነ ምግባር ትምህርት ባይሰጡ ኖሮ በአገሪቱ ሕገወጥነት፣ ሥርዓት አልበኝነትና ነውጠኝነት አሁን ካለውም የባሰ ይሆን ነበር ይላሉ የሕግ ምሁራን፡፡
መንግሥት ለፖሊስ፣ ለመከላከያም ሆነ ለሌሎች የሕግና የፀጥታ ተቋማት የሚያወጣው ወጪ የቀነሰው የሃይማኖት ተቋማት ኅብረተሰቡን በነፃ ጨዋነትና ሕግ አክባሪነትን ስላስተማሩ ነው ይላሉ የሕግ ምሁራን፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ባሉ የማያስመካ የሕግ የበላይነት ሥርዓት ባለባቸውና ሕገወጥነት በተንሰራፋባቸው አገሮች፣ የሃይማኖት ተቋማት ምዕመኖቻቸውን ቅንነትና ሀቀኝነትን ባያስተምሩ ኖሮ በአገሪቱ ሊፈጠር የሚችለውን የሥርዓት አልበኝነትና የሞራል ንቅዘት ቀውስ መንግሥት ብቻውን ሊቆጣጠረው ባልቻለ ነበር ሲሉም ባለሙያዎቹ ያስረዳሉ፡፡
መንግሥት በአገሪቱ የሕግ የበላይነት እንዲሰፍን ከመፈለግ ብቻ ሳይሆን፣ ለፀጥታ የሚያወጣውን ወጪና ጉልበት ለመቆጠብም ሲል የእምነት ተቋማትን አስተዋጽኦ ዕውቅና በመስጠት ተገቢውን ጥበቃና ድጋፍ ሊያደርግላቸው ይገባል በማለት ነው የሕግ ምሁራኑ የሚሞግቱት፡፡
የሕግ ባለሙያዎቹ መንግሥት ለእምነት ተቋማት ህልውና መጠበቅ ማድረግ ይጠበቅበታል የሚሉት በርካታ ቢሆንም፣ ከዚያ ይልቅ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በኢትዮጵያ የእምነት ተቋማት እየገጠማቸው ያለው ፈተና መስፋቱ ነው የሚነገረው፡፡ ትውልድ የሚቀርፁ መስጅዶችና ቤተ ክርስቲያናት በተደጋጋሚ ሲቃጠሉ፣ ሲፈርሱና ሲወድሙ ነው የሚታየው፡፡ የሃይማኖት በዓላትና ክንውኖችን ዜጎች በነፃነትና በሰላም ለማክበር የማይችሉበት አጋጣሚ በተደጋጋሚ ይታያል፡፡ መንግሥት የሃይማኖት ተቋማትን መደገፍ ቢያቅተው እንኳ ተገቢውን የሕግ ጥበቃ ለማድረግ እንዴት ተሳነው? የሚለው ጉዳይ አሁን በኢትዮጵያ አንገብጋቢው ጥያቄ የሆነ ይመስላል፡፡
የድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር አቶ አማኑኤል ታደሰ መንግሥት፣ የእምነት ተቋማትን ነፃነትና መብት አክብሮ የማስከበር መሠረታዊ ግዴታ አለበት ይላሉ፡፡ ይህ መሠረታዊ ግዴታ ደግሞ ከሕገ መንግሥታዊ ድንጋጌ እንደሚመነጭ ያስረዳሉ፡፡
‹‹በሕግ መንግሥታችን አንቀጽ 11 የመንግሥትና የሃይማኖት መለያየት (ሴኪዩላሪዝም) መርህ በግልጽ ተቀምጧል፡፡ በዚህ ሕገ መንግሥታዊ መርህ መሠረት ደግሞ መንግሥት በሃይማኖት፣ ሃይማኖትም በመንግሥት ጉዳዮች ጣልቃ አይገቡም ተብሏል፡፡ መንግሥት በሃይማኖት አሠራርም ሆነ ዶግማ ጣልቃ እንደማይገባው ሁሉ ሃይማኖቶችም በመንግሥት ርዕዮተ ዓለም አይገቡም፤›› ይላሉ፡፡
‹‹በኢራን የመንግሥት ህልውና ምንጭ የሃይማኖት አስተምህሮ ሲሆን ይታያል፡፡ አያቶላው ያልባረኩት መንግሥት በኢራን አይመሠረትም፡፡ በብዙ የዓረብ አገሮች ደግሞ ሃይማኖታዊ መንግሥት ወይም መንግሥታዊ ሃይማኖቶች አሉ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች ግን መንግሥትና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው፡፡ በዚህ ሕገ መንግሥታዊ መርህ መሠረት በኢትዮጵያ ሃይማኖትን መሠረት ያደረገ መንግሥት መመሥረት አይቻልም፡፡ በመንግሥት የሚደገፍ ወይም ልዩ ጥቅም የሚያገኝ የሃይማኖት ተቋምም አይኖርም፤›› በማለት ነው የሕግ ምሁሩ ሰፊ ማብራሪያ የሚሰጡት፡፡
ይህ ማለት ግን መንግሥት ግዴታ የለበትም ማለት እንዳልሆነ አቶ አማኑኤል ያስረዳሉ፡፡ የመንግሥት የመጀመርያ ግዴታ የእምነት ተቋማትን መብት ማስከበር ነው ይላሉ፡፡ መንግሥት በመንግሥት መዋቅሮች (ተቋማት) ውስጥ ሃይማኖቶች ፍትሐዊ ውክልና እንዲያገኙ የማድረግ ግዴታም አለበት በማለት ሌላኛውን የመንግሥት ግዴታ ያክላሉ፡፡
‹‹መንግሥት የሚያወጣቸውን ሕጎችና ደንቦች አክብሮ የሚንቀሳቀስ ሕግ አክባሪ ዜጋ ለመፍጠር፣ የሃይማኖት የሞራል ግንባታ አስተዋጽኦ በእጅጉ ይፈልገዋል፤›› በማለት ይናገራሉ፡፡ ይህን የመሰለ ለአገረ መንግሥት ግንባታ ትልቅ ፋይዳ ያለው አስተዋጽኦ የሚያበረክቱ የእምነት ተቋማት ደግሞ፣ መብታቸውና ነፃነታቸው ተከብሮ እንዲኖር የመንግሥት ጥበቃ እንደሚያስፈልጋቸው ነው የሚናገሩት፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ዜጎች በሰላም እንዲኖሩ በማድረግ የእምነት ተቋማት ከመንግሥት ያልተናነሰ ሚና ሲወጡ መኖራቸውን ያስታወሱት የሕግ ምሁሩ፣ ይህን በመዘንጋት አንዳንዴ የመንግሥት አካላት በተቋማቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ እንደሚገቡ አመልክተዋል፡፡ የመንግሥት አካላት በሃይማኖቶች የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ የሚገቡባቸው አጋጣሚዎች በርካታ መሆናቸውን የሕግ ባለሙያው ያስረዳሉ፡፡
‹‹አንዳንዴ በመንግሥት አካላት ያሉ ወገኖች የራሳቸውን የእምነት ዝንባሌ መሠረት በማድረግ ሲንቀሳቀሱ ይታያሉ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ የመንግሥት ፖሊሲን የማይደግፍ ነው በሚሉት የእምነት ተቋም ወይም የሃይማኖት አመራር ላይ ግፊትና ጫና ሲያሳድሩ ይስተዋሉ፡፡ በሌላ በኩል በሃይማኖት ተቋማት መካከል ግጭትና አለመግባባት በሚፈጠር ጊዜ የመንግሥት አካላት ጣልቃ ለመግቢያነት ሊጠቀሙበት ሲሞክሩ ይታያል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በአንድ የእምነት ተቋም ውስጥ በአደረጃጀት ወይ አመራር ጉዳይ አለመግባባት ሲፈጠርም፣ የመንግሥት አካላት ጣልቃ ገብነት ይከሰታል፤›› በማለት ነው የሕግ ባለሙያው፣ በኢትዮጵያ መንግሥት በሃይማኖት የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ የሚገባባቸውን አጋጣሚዎች የዘረዘሩት፡፡
መንግሥት በእምነት ተቋማት ጉዳይ የእምነት ተቋማትም በመንግሥት ጉዳይ ጣልቃ አይገባቡም የሚለው መርህ የተቀመጠው፣ ሁለቱ ተነጣጥለው መንቀሳቀሳቸው በብዙ መንገዶች አገርን ተጠቃሚ እንደሚያደርግ ታምኖበት መሆኑን የሕግ ምሁራን ያስረዳሉ፡፡ መንግሥት ይህን ቀይ መስመር አልፎ በእምነት ጉዳዮች ጣልቃ የሚገባና ጫና የሚያሳድር ከሆነ፣ የሃይማኖት ፅንፈኝነትን መሠረት ያደረገ ሕገወጥ እንቅስቃሴ ሊፈጠር እንደሚችል ነው የሚናገሩት፡፡ ይህ ደግሞ የአንድ አገርን የፀጥታ ሥጋት ተጋላጭነት የበለጠ ያሰፋል ይላሉ፡፡
በተለይ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መንግሥት ወደ ሥልጣን ከመጣ ወዲህ፣ የሃይማኖትና የመንግሥት መለያየት ሕገ መንግሥታዊ መርህን ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ የሚያደርጉ በርካታ ችግሮች ተፈጥረዋል የሚሉ አሉ፡፡
በሶማሌ ክልል ተፈጥሮ በነበረው የፀጥታ ችግር በክልሉ የቀድሞ አመራሮች ተደራጅተው የተሰማሩ ሄጎ የሚባል ቡድን አባላትና አንዳንድ የልዩ ኃይል ፖሊሶች እንደፈጸሙት የሚነገረው፣ አብያተ ክርስቲያናትን የማቃጠልና የእምነት አባቶችን የመግደል ዕርምጃ ጉዳቱ ከባድ እንደሆነ ይወሳል፡፡
በኦሮሚያ፣ በአማራና በሲዳማ ክልሎች የፀጥታ መደፍረሶችን ተገን ባደረገ መንገድ በእምነት ተቋማት ላይ የደረሱ አደጋዎች፣ በኢትዮጵያ የእምነት ነፃነት መርህ እየተሸረሸረ ነው የሚል ሥጋትን የፈጠሩ እንደነበሩ ይገለጻል፡፡
ወደ ሥልጣን ሲመጣ በእምነት ተቋማት ውስጥ ተፈጥረው የነበሩ አለመግባባቶችን በመሸምገልና መግባባትን በመፍጠር ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር)
ምሥጉን ሥራ መሥራታቸው ይጠቀሳል፡፡ የለውጡ መንግሥት አመራሮች ከተለያዩ እምነት አባቶች ጋር ደጋግመው መታየታቸው፣ ጸሎት እናድርግ ማለታቸው፣ ፈጣሪ ኢትዮጵያን ይባርክ እያሉ ንግግር መዝጋታቸውም ሆነ በየሃይማኖት በዓሉ በእምነት መጻሕፍት ጥቅሳ ጥቅሶች የታጨቁ የመልካም ምኞት መግለጫዎች ማውጣታቸው፣ ለሃይማኖት ተቋማት እጅግ ቀናዊ አመለካከት ያላቸው መሪዎች መጡ ያስባለ መሆኑ ይነገራል፡፡
በሒደት የተፈጠሩ ችግሮች ግን የለውጡ አመራር በሃይማኖት ጉዳዮች ጣልቃ ወደ መግባት እያዘነበለ ነው የሚል ግምትን እያሳደሩ መምጣታቸው ይወሳል፡፡ የመስቀል አደባባይ የይገባኛል ውዝግብ፣ የመጅሊስ አመራር ምርጫ ጉዳይ፣ እንዲሁም የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ሲኖዶስ አባላት ሕገወጥ ሲመት ማድረጋቸው አስተዳደሩ የተፈተነባቸው ውዝግቦች ነበሩ፡፡ ይህ ደግሞ የጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) አስተዳደር የእምነት ነፃነትን ማስከበርም ሆነ የሃይማኖትና የፖለቲካ መለያየት ሕገ መንግሥታዊ መርህ አክብሮ ማስከበር እየተሳነው መጥቷል የሚል አመለካከት በብዙዎች ዘንድ እንዲኖር የሚጋብዝ መሆኑ ይነገራል፡፡
በእነዚህ ውዝግቦች መሀል ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በአንድ አጋጣሚ በእምነት ተቋማቱ ላይ ያሰሙት ምሬት፣ መንግሥታቸውና እምነት ተቋማቱ የበለጠ ሆድና ጀርባ እየሆኑ ሄደዋል የሚል ስሜት የፈጠረ ነበር፡፡
‹‹የሃይማኖት ተቋማት መሬት በነፃ የሚያገኙት፣ ከታክስ ነፃ የሚደረጉትና የኦዲት ምርመራም የማይካሄድባቸው በሞራል በኩል መንግሥት ያለበትን ክፍተት ይሞላሉ ተብሎ ነው፡፡ አሁን እንደሚታየው ከሆነ ግን ቄሱም፣ ሼኩም ሆነ ሁሉም የእምነት ተቋማት ፖለቲካ ሲሠራ ነው የሚገኘው፡፡ የእምነት ተቋማት በከፍተኛ ሙስና ውስጥም ተዘፍቀዋል፡፡ መንግሥት ይህንን ለማረም የእምነት ተቋማቱ ኦዲት እንዲደረጉ፣ ታክስ እንዲከፍሉና በሊዝ ሥርዓት ውስጥ እንዲገቡ የማድረግ ዕርምጃ ይወስዳል፤›› ሲሉ ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡ ይህ አጋጣሚ መንግሥታቸው በእምነት ተቋማት ላይ እያመረረ ነው የሚል ግምት ያሳደረ መሆኑ ይነገራል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ደግሞ ከሰሞኑ በአዲስ አበባ ዙሪያ ማለትም በአዲሱ የኦሮሚያ ክልል ሸገር ከተማ አስተዳደር ሥር ባሉ ወረዳዎች የተወሰደው ተደጋጋሚ የመስጅዶች ማፍረስ ዕርምጃ፣ የሃይማኖት ተቋማትና የመንግሥት ግንኙነት ከእስካሁኑ የበለጠ እንዳያሻክር ሥጋት መፍጠሩ ይታወቃል፡፡
‹‹መንግሥት አስከብረዋለሁ የሚለው የሕዝብ ጥቅም ምንድነው?›› የሚል ጥያቄ የሚያወሱት የሕግ ምሁሩ አቶ አማኑኤል፣ የእምነት ተቋማትን ህልውና ማስጠበቅ የሕዝብ ጥቅም ማስከበር መሆኑን ነው የሚገልጹት፡፡
‹‹ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በይዞታ ማስከበር ስም ሕገወጥ ግንባታ ናቸው እየተባሉ የእምነት ተቋማት እየፈረሱ ናቸው፡፡ ወደ እነዚህ የእምነት ተቋማት ለማምለክ የሚሄዱ ዜጎች ይብዛም ይነስ አሉ፡፡ የመንግሥት የሕዝብ ጥቅም ማስከበር ዕርምጃ የእነዚህ ዜጎችን የእምነት ነፃነት አይጨምርም ወይ?›› በማለትም ይጠይቃሉ፡፡
‹‹ማፍረስ ስለቻልክና ሕግ ስለፈቀደልህ ብቻ የእምነት ተቋማትን ማፍረስ አደገኛ ውጤት ሊኖረው ይችላል፤›› የሚሉት የሕግ ባለሙያው፣ ሕግ በዚህ መንገድ እንደማይተረጎም በመጥቀስ መንግሥት ሆደ ሰፊ መሆን እንዳለበት ያሳስባሉ፡፡ አገሪቱ የምትገኝበትን አስቸጋሪ አጣብቂኝ የሚያስረዱት አቶ አማኑኤል መንግሥት የእምነት ተቋማትን በማፍረስና ሕዝብን በማስቆጣት የአገሪቱን ችግር ከማባባስ ይልቅ የፀጥታ ሥጋቶችን የመቀነስ አካሄድ ሊከተል ይገባል ይላሉ፡፡
‹‹የሸገር ከተማ ግንባታ ጉዳይ የኦሮሚያ ክልልን ብቻ የሚመለከት ነው፡፡ የእምነት ነፃነት፣ እንዲሁም ሃይማኖትና መንግሥት አንዳቸው በሌላቸው ጣልቃ ያለመግባት ጉዳይ ግን መላው ኢትዮጵያን የሚመለከት አገራዊ ጉዳይ ነው፡፡ በዚህ የተነሳ የፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ በመግባት በሸገር ከተማም ሆነ በሌሎች ክልሎች መስጅዶችና ሌሎች የእምነት ተቋማትን ለመታደግ የሚከለክለው የሕግ አግባብ የለም፤›› በማለት ነው የሕግ ባለሙያው አስተያየታቸውን ያከሉት፡፡
የፌዴራል መንግሥቱ ይህን ሁኔታ ጣልቃ ገብቶ የማያስቆም ወይም ክልሎቹ የማይታዘዙ ከሆነ፣ ጉዳዩ በአኅጉራዊና በዓለም አቀፋዊ ፍርድ ቤቶች ጭምር አቤቱታ ሊቀርብበት እንደሚችል ነው የሕግ ባለሙያው ያስረዱት፡፡
ኢትዮጵያ ራሷ ካፀደቀቻቸው ሕገ መንግሥታዊ መርሆዎች በተጨማሪ፣ በርካታ አኅጉራዊና ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎችንም በሕገ መንግሥቱ የተቀበለች አገር መሆኗን የሕግ ባለሙያው አስታውሰዋል፡፡