Thursday, June 13, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የባንኮች ብድር አሰጣጥ ፍትሐዊና ብዙኃኑን ያማከለ እንዲሆን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ አሳሰበ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ባንኮች የብድር አገልግሎታቸውን በተቻለ መጠን ፍትሐዊ፣ የብዙኃኑን ተጠቃሚነት ያማከለና በተለይም የአምራች ዘርፉን እንዲደግፍ ለማድረግ በትኩረት መሥራት እንደሚጠበቅባቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ አሳሰቡ፡፡

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ይህንን ያሉት፣ በ1.5 ቢሊዮን ብር ወጪ የተገነባው የዘመን ባንክ ሕንፃ ምርቃት ፕሮግራም ላይ ተገኝተው ባደረጉት ንግግር ነው፡፡

እንደ እሳቸው ገለጻ፣ የባንኮች የብድር አሰጣጥ ፍትሐዊ እንዲሆን የሚፈለግ ከመሆኑም በላይ፣ ለአምራች ዘርፉ ትኩረት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞም አገሪቱ ባንኮች የብድር አስተዳደራቸው ላይ ትኩረት መስጠት አለባቸው፡፡

‹‹ባንኮች አቅማችሁን በማሳደግ በተለይ የተጠናከረ የኩባንያ አመራር (ኮርፖሬት ገቨርናንስ) ሥርዓታችሁን በማሻሻል እንዲሁም ለብድር አስተዳደር አጽንኦት በመስጠት የባንኮችን ጤናማነትና ቀጣይነት ማረጋገጥ አለባችሁ፤›› በማለትም ገልጸዋል፡፡

የባንኮች ሠራተኞችና ኃላፊዎች ጠንካራ፣ ትጉህ፣ ጨዋና በባንክ ሠራተኝነታቸው የሚኮሩ መሆን እንደሚጠበቅባቸው የገለጹት አቶ ማሞ፣ አቅማቸውን እያጎለበቱ መሄድ እንደሚኖርባቸውም አስታውቀዋል፡፡  

በፈጣን ሁኔታ እየተለዋወጠ ካለው የአገር ውስጥም ሆነ የዓለም ኢኮኖሚ ውስጥ ተወዳዳሪና ተመራጭ ሆኖ ለመቀጠል በሰው ኃይል ልማት፣ በቴክኖሎጂና በአደረጃጀት እንዲሁም በአሠራር ሥርዓት ራሳቸውን ማጎልበት እንደሚጠበቅባቸውም አቶ ማሞ ገልጸዋል፡፡

በተለይ የኢትዮጵያ ባንኮች የሚታይባቸውን የአቅም ውስንነት ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ጠንካራ የካፒታል አቅም መፍጠር እንደ ዋና ሥራቸው ሊሆን እንደሚገባም ሳይጠቁሙ አላለፉም፡፡

የካፒታል ገበያ ሥራ መጀመርን ጨምሮ የፋይናንስ ዘርፉን ሌሎች የውጭ ባለድርሻ አካላት እንዲቀላቀሉት የማድረግ ሥራ በመከናወን ላይ በመሆኑም፣ የአገር ውስጥ ባንኮች ይህንን ሥራቸውን አስቀድመው መሥራት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል፡፡

በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በኩልም የፋይናንስ ተቋማትን ጤናማነትና አስተማማኝነት፣ እንዲሁም አካታችነት የበለጠ ለማረጋገጥ የሚያስችል በዓይነቱና በይዘቱ ዘርፈ ብዙ ሊባል የሚችል ሪፎርም እንደተጀመረ አስታውሰዋል፡፡

‹‹በዓይነቱ ልዩ የሆነ ነው፤›› ያሉትን ሪፎርም ለመተግበር አስፈላጊ ናቸው የተባሉ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎችን በማጠናቀቅ ወደ ተግባር እየተገባና ለአፈጻጸሙ እንዲረዳም ብሔራዊ ባንክ ራሱን የቻለ የማኔጅመንት የሥራ ክፍል እንዲቋቋም ማድረጉን አክለዋል፡፡

የዚህ ሪፎርም ወሳኝ ባለድርሻና ፈጻሚ አካላት የፋይናንስ ተቋማት እንደመሆናቸው መጠን፣ ሪፎሙን በሚፈለገው ፍጥነትና ደረጃ እንዲያሳኩ የበኩላቸውን ኃላፊነት እንዲወጡም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡

ለዚህም በቅርቡ የኢትዮጵያ የገንዘብ አስቀማጮች ፈንድ ተቋቁሞ ወደ እንቅስቃሴ መገባቱን በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡ የፈንዱ ተሳታፊ አባላት በዋኛነት ባንኮችና አነስተኛ የፋይናንስ ተቋማት በመሆናቸውም፣ የታሰበለትን ዓላማ እንዲያሳካ ሕጉና አሠራሩ በሚያስቀምጠው መሠረት የፋይናንስ ተቋማት ከሚከፋፈሉት የዓረቦን መዋጮ ጀምሮ የበኩላቸውን ሚና በኃላፊነት መወጣት ይጠበቅባቸዋል ብለዋል፡፡

ወቅታዊውን የአገሪቱን የፋይናንስ ተቋማት አፈጻጸምና ይዘት በተመለከተ በሰጡት አኃዛዊ መረጃ፣ በአሁኑ ወቅት ወደ አሥራ አንድ ሺሕ ቅርንጫፎች ያላቸው 31 ባንኮች አገልግሎት እየሰጡ ናቸው፡፡

የባንክ ቅርንጫፎች መብዛት ከዘመናዊ ቴክኖሎጂ ጋር ተዳምሮ ተደራሽነትና አካታችነቱን ከማስፋት ባሻገር፣ ለቁጠባና ለኢንቨስትመንት የሚውል የፋይናንስ ሀብት በማሰባሰብና በማሠራጨት ለአገር ኢኮኖሚ ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ ስለመሆናቸው አመልክተዋል፡፡

ከዚህ አንፃር ባንኮች በሒሳብ ዓመቱ እስከ መጋቢት 2015 ዓ.ም. መጨረሻ ድረስ [ከሁለት በላይ አካውንት ያላቸውን ጨምሮ] 123.6 ሚሊዮን ሒሳብ ደብተር ወይም አስቀማጮች ማፍራት መቻላቸውንም ተናግረዋል፡፡

የባንኮች የተቀማጭ ገንዘብ መጠንም ከ2.6 ትሪሊዮን ብር በላይ እንደደረሰ ያመለከቱት አቶ ማሞ፣ ባንኮች የሚያሰባስቡት የብድር መጠንም አንዳንድ ችግሮች ቢኖሩትም ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ ነው ብለዋል፡፡  

በክብር እንግድነት በተገኙበት የዘመን ባንክ ሕንፃ ምርቃት፣ ‹‹ዘመን ባንክ በአጭር ዕድሜው አዳዲስ አሠራሮችን በማፍለቅ፣ የተሻለ አሠራር ዘዴ በመተለም፣ የውጭ ንግድ ዘርፉን በመደገፍና ቴክኖሎጂ ተኮር በመሆን ኢንዱስትሪው ውስጥ በመልካም ተሞክሮነት ሊጠቀስ የሚችል ባንክ ነው፤›› ብለውታል፡፡

ለአዲስ አበባ ሀብት የሆነውን ዘመናዊ የሕንፃ ጥበብ ያረፈበትን ሕንፃ ገንብቶ በማጠናቀቅ ሲያስመርቅ፣ ረዥም ጉዞውን ለመጓዝና ለደንበኞቹ የላቀ አገልግሎት ለመስጠት ቴክኖሎጂን ተደራሽ ለማድረግና በኅብረተሰቡ ውስጥ ይበልጥ ተቀባይነት ለማግኘት ማሰቡን ያመለክታል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የዚህ ሕንፃ መጠናቀቅ የባንኩን ወጪዎች ለመቆጠብ ብቻ ሳይሆን፣ በተለያዩ ቦታዎች ይሰጡ የነበሩ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታና በተሻለ ሁኔታ እንዲሰጥ እንደሚያስችለውም ጠቁመዋል፡፡

ለባንኩ ባለአክሲዮኖች ተጨማሪ ሀብት፣ ለደንበኞች ዋስትና፣ ለአገር ልማት አጋዥ በመሆን እንደሚያግዝ አክለዋል፡፡

ዘመን ባንክ ግንቦት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. የዋና መሥሪያ ቤቱን ሕንፃ ሲያስመርቅ፣ አስተዋጽኦ ላደረጉ መሥራች አባላትና የቀድሞ ፕሬዚዳንቶች ዕውቅና ሰጥቷል፡፡ ባንኩ በቀዳሚነት ዕውቅና የሰጠው ባንኩን በመመሥረት ረገድ ከፍተኛ አበርክቶ ያላቸውን አቶ ኤርሚያስ አመልጋን ሲሆን፣ የዘመን ባንክን ዓርማ የያዘ 20 ግራም ወርቅ ተሸላሚ የሆኑት አቶ ኤርሚያስ ግን በፕሮግራሙ ላይ አልተገኙም፡፡

ሌሎች ባንኩን በፕሬዚዳንት ሲመሩና በምሥረታ ሒደቱ ባለውለታ ለነበሩ የባንኩን ዓርማ የያዘ 15 ግራም ወርቅ ተዘጋጅቶላቸው ከዕለቱ የክብር እንግዳ አቶ ማሞ ምሕረቱ ተቀብለዋል፡፡

ዘመን ባንክ የኢትዮጵያን ስም የሚያስጠራ እንዲሆን እየሠሩ መሆኑን የገለጹት የባንኩ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ደረጀ ዘበነ፣ በኢንዱትሪው ውስጥ ያላቸውን የገበያ ድርሻ ከፍ ለማድረግ እየሠሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የባንኩ የዳይሬክተሮች ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ኤርሚያስ እሸቱ በበኩላቸው፣ የባንኩ የትርፍ ምጣኔ እያደገ በመሄድ፣ በዚህ ዓመት ከሦስት ቢሊዮን ብር በላይ ያተርፋል ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡

አሁን ከገነቡት ሕንፃ ሌላ በዚያው አካባቢ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በሊዝ በተረከቡት ቦታ ተጨማሪ ሕንፃ እንደሚገነቡ አረጋግጠዋል፡፡  

የፋይናንስ ተቋማት መሪዎችና ሌሎችች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት የዘመን ባንክ የዋና መሥሪያ ቤት ሕንፃ ምርቃት፣ ሜቄዶንያና የኢትዮጵያ ቀይ መስቀልን ጨምሮ ለተለያዩ በጎ አድራጎ ድርጅቶች የ16 ሚሊዮን ብር ስጦታ ተበርክቷል፡፡

ባንኩ በሕንፃ ምርቃት ሥርዓቱ ላይ ካበረከተው የገንዘብ ድጋፍ ባሻገር፣ ባለፉት አምስት ዓመታት ማኅበራት ኃላፊነቱን ለመወጣት 150 ሚሊዮን ብር ወጪ ማድረጉ ተገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች