- የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል
የሐበሻ ቢራ ፋብሪካ አክሲዮን ማኅበር በ2022 በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ፡፡
የኩባንያውን ዓመታዊ ክዋኔ አስመልክተው ሪፖርት ያቀረቡት የኩባንያው የዳይሬክተሮች ቦርድ ስብሰቢ ኢንጂነር መስፍን አቢ እንዳሉት፣ ኩባንያ ግብር፣ ወለድና ተያያዥ ወጪዎች ከመቀነሳቸው በፊት ያለው ትርፍ በ2021 ከነበረበት 444 ሚሊዮን ብር፣ በ60 በመቶ በማደግ በ2022 ወደ 712 ሚሊዮን ብር ደርሷል፡፡
ኩባንያው በ2022 ከግብር በኋላ ያገኘው 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ149 በመቶ ብልጫ እንዳለው የጠቆሙት ኢንጂነር መስፍን፣ የፕላቲንየም ግብር ከፋይ የሆነው ኩባንያው በ2022 1.1 ቢሊዮን ብር ኤክሳይዝ ታክስ እንዲሁም የኮርፖሬት የገቢ ግብር 201 ሚሊዮን ብር ለመንግሥት መክፈሉን ተናግረዋል፡፡
በአገር ውስጥ የተለያዩ ፈተናዎች እንዲሁም የዓለም ኢኮኖሚ ማቆዎች ቢኖሩም፣ ሐበሻ ቢራ ካለፉት ዓመት አፈጻጸም አንፃር የባለሁለት አኃዝ ዕድገትና ከፍተኛ ትርፍ ጭማሪ በማሳየት የተሻለ አፈጻጸም አስመዝግቧል ያሉት የቦርድ ሰብሳቢው፣ በ2022 ኢንዱስትሪው በአማካይ ካሳየው አምስት በመቶ የምርት ዕድገት አንፃር ሲታይ፣ ሐበሻ ያስመዘገበው 24 በመቶ የሽያጭ መጠን ዕድገት በኢንዱስትሪው ከፍተኛ ተፎካካሪና ውጤታማ መሆኑን እንደሚያሳይ ተናግረዋል፡፡
እ.ኤ.አ. ታኅሳስ 31 ቀን 2022 የተጠናቀቀው በጀት ዓመት ውጤት እንደሚሳየው፣ በ2021 2.3 ቢሊዮን ብር የነበረው ገቢ፣ በ2022 67 በመቶ ዕድገት በማሳየት 3.8 ቢሊዮን ብር ደርሷል፡፡ ለዚህ ደግሞ በ2022 የዋጋ ግሽበቱን ተከትሎ ገበያ መር የምርት ዋጋ ጭማሪ ማድረጋቸውንና የሽያጭ መጠን ከ2021 ጋር ሲነፃፀር በ24 በመቶ ማደጉ ከፍተኛ ገቢን ለማስመዝገብ ዋነኛ ምክንያት እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
በዓለም አቀፍም ሆነ በኢትዮጵያ ያለው ውጫዊ የሥራ ምኅዳር በብዙ ምክንያቶች መፈተኑ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው ኮቪድ-19 ወረርሽኝ ካገገመ በኋላ፣ በ2022 የታየው የኢኮኖሚ ማንሠራራት በሩሲያና በዩክሬን ጆኦ ፖለቲካ ፍጥጫ ምክንያት መጎዳቱ፣ ኢትዮጵያም እንደ አብዛኞቹ ታዳጊ አገሮች በግጭቱ ምክንያት ከዓለም አቀፍ የአቅርቦት ሰንሰለትና ከዓለም አቀፍ የንግድ መስተጓጎል ጋር ተያይዞ በሸቀጣ ሸቀጦች ዋጋ መጨመርና የዋጋ ግሽበት በከፍተኛ አሉታዊ ተፅዕኖ ውስጥ መውደቋና በአገር ውስጥ በትግራይ የነበረው የፖለቲካ ቀውስ ዓመታዊውን የሸማቾች ግብይቶች መጉዳቱን አክለዋል፡፡
ግንቦት 17 ቀን 2015 ዓ.ም. በተካሄደው የባለአክሲዮኖች 13ኛው መደበኛና 13ኛው አስቸኳይ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ከባለአክሲዮኖች ከተነሱ ጥያቄዎች ዋነኛው አንድ አክሲዮን ውስጥ ለውስጥም ሆነ ለውጭ የሚሸጥበት ዋጋ ስንት ነው የሚል ነበር፡፡
ኩባንያው ከተቋቋመ በኋላ ባለአክሲዮኖች እያገኙ ያለው የትርፍ ክፍፍል አነስተኛ ነው፣ ዓምና አክሲዮን ለአንድ አክሲዮን ሽያጭ የተሰጠው የ2,500 ብር ዋጋ አነስተኛ ነው፣ ይህ ራያ ቢራ ከዚህ ቀደም ለአንድ አክሲዮን ከሰጠው 7,500 ብር ከእጥፍ በላይ ያንሳል የሚሉ ጥያቄዎችም የተነሱ ሲሆን፣ ቦርዱም ለዚህ ምላሽ አቅርቧል፡፡
እንደ ኢንጂነር መስፍን፣ የአንድ አክሲዮን ሽያጭን በተመለከተ ጥናት የተጠና ሲሆን፣ በዚህም መሠረት በአሁኑ ሰዓት የሚሸጥበት ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል፡፡
ራያ ቢራና ሌሎች ሲሸጡ ኢኮኖሚው የተሻለ እንደነበር፣ አሁን ባለው ሁኔታ ግን ከዚህ በላይ መሄድ እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡
በሌላ በኩል የትርፉ መጠኑ አነስተኛ ነው፣ የኩባንያው ብድርና ብድር የመክፈል አቅሙ ምን ያህል ነው የሚሉ ጥያቄዎችም ተነስተዋል፡፡
የዘንድሮ የትርፍ ክፍፍል በአንድ አክሲዮን 128 ብር ከ70 ሳንቲም መሆኑን የገለጹት ኢንጂነር መስፍን፣ ይህ ከቀደመው ዓመት ሲነፃፀር የ148 በመቶ ብልጫ አለው ብለዋል፡፡
ኩባንያው ከፍተኛ የአክሲዮን ድርሻ ካለው በቫሪያ 10 ሚሊዮን ዶላርና ስድስት ሚሊዮን ዩሮ ተበድሮ እንደነበር፣ 10 ሚሊዮን ዶላሩ ሙሉ ለሙሉ መከፈሉን፣ ከስድስት ሚሊዮን ዩሮው አራት ሚሊዮን እንደሚቀር አስረድተዋል፡፡
ቀሪውን ለመክፈል በአገሪቱ ያለው የውጭ ምንዛሪ እጥረት ፈተና እንደሆነባቸውም አክለዋል፡፡ የትርፍ ክፍፍሉ አነስተኛ መሆኑንና አክሲዮኑ ከ11 ዓመታት በፊት ሲመሠረት ከመቶ 120 በመቶ ትርፍ ታገኛላችሁ ተብሎ እንደነበር፣ ሆኖም ይህ አለመሳካቱ ከባለአክሲዮኖች ተነስቷል፡፡
ኢንጂነር መስፍን እንዳሉት፣ አክሲዮኑ ከ11 ዓመታት በፊት ሲመሠረት የነበረው ኢኮኖሚ እንደተባለው ከፍተኛ ትርፍ ያስገኝ እንደነበር፣ ሆኖም ኩባንያው ተቋቁሞ ሥራ ከጀመረ በኋላ ባሉ ዓመታት ኢኮኖሚ እየተቀዛቀዘ መምጣቱ፣ በኃላም የኮቪድ ወረርሽኝ፣ የዩክሬንና የሩሲያ ጦርነት፣ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያለው ጦርነት ተግዳሮት መሆኑን ተናግረዋል፡፡
የባቫሪያ ግሩፕ በበኩሉ፣ የሐበሻ ቢራን ሲቀላቀል የነበረው የንግድ ሥራ አመርቂ እንደነበር፣ በድርጅቱ ላይ እምነት ጥለው ቢገቡም፣ ይህንን ያህል ትርፋማ ባለመሆኑ እንደ ኢትዮጵያውያኑ ባለሀብቶች አብሮ ተጎጂ መሆኑን ገልጿል፡፡
በጦርነቱ፣ በኮቪድና በተለያዩ ምክያቶች የተገኘው ትርፍ ዝቅተኛ መሆኑን፣ ሆኖም ሐበሻ የያዘው መለያ (ብራንድ) ጥሩ ስለሆነ በቀጣይ ትርፋማ እየሆነ ይሄዳል ብለው እንደሚያምኑ አስታውቀዋል፡፡
አ.ኤ.አ. በ2009 በተመሠረተው ሐበሻ ቢራ ፋብሪካ አማ.፣ ስዊንክለስ ፋሚሊ ቢራ ፋብሪካ ሆልዲንግ ኤንቪ 60 በመቶ ድርሻ ያለው ሲሆን፣ በሌላ በኩል ከ8,600 በላይ የሚሆኑ የአገር ውስጥ ባለአክሲዮኖች 30 በመቶ ድርሻ አላቸው፡፡ ቀሪ አሥር በመቶ አክሲዮን ድርሻ በሊንሰን ፓርቲሲፔሼንስ ቢቪ የተያዘ ነው፡፡
እ.ኤ.አ. በጥር 31 ቀን 2022 የሐበሻ ቢራ ፋብሪካ አ.ማ የተከፈለ የካፒታል መጠን 2,409,451,030 ደርሰዋል፡፡ በአጠቃላይ የሐበሻ ቢራ ፋብሪካ አ.ማ. አክሲዮን ባለድርሻ የሆኑ ባለአክሲዮኖች ቁጥር በጥር 31 ቀን 2022 8,652 ደርሷል፡፡
በሪፖርት ዓመቱ 34 ባለአክሲዮኖች 3,814,000.00 የሚሆን የአክሲዮን መጠናቸውን ለ19 ባለአክሲዮኖች በሽያጭ ያስተላለፉ ሲሆን፣ 2,864,500.00 ዋጋ ያላቸው በ38 ባለአክሲዮኖች የተያዙ አክሲዮኖች ደግሞ በውርስ ሀብት ክፍፍል ለ102 ባለአክሲዮኖች ተላልፈዋል፡፡ በተጨማሪም በባለአክሲዮኖች ድርጅቶች ፈርሰው በመከፋፈላቸው ምክንያት 337,000.00 የሚወጡ በሁለት ባለአክሲዮኖች ተይዘው የነበሩ አክሲዮኖች ለ40 ባለአክሲዮኖች ተላልፈዋል፡፡