የዛሬው ጉዞ ከሳሪስ አቦ ወደ ቃሊቲ መናኽሪያ ነው። የሰው ልጅ ለኑሮ የሚያደርገው እንቅስቃሴ ጎዳናውን ሕይወት ዘርቶበታል። እንደ ወትሮው የኑሮ ንረት እያፍገመገመን እዚህ ደርሰናል። ‘ኑሮ ካሉት መቃብር ይሞቃል’ ያስብላል የአብዛኞቻችን አኗኗር። ሕይወትን ጣፋጭ ሊያደርጉ የሚችሉ መሠረታዊ ነገሮቻችን አሁንም በምሬት ጥያቄ እንደ እሳት እያቃጠሉ ናቸው። አንዳች ትንፋሽ እስኪያጠፋቸው እንደ ሻማ ውስጣችንን ያቀልጣሉ። ‹‹የዚህ ሁሉ ሰው ትዕግሥት እንደ ሰም ቀልጦ ያለቀ ቀን ምን ልንሆን ነው?›› ይባባላሉ ታክሲ ጥበቃ ወረፋ የታደሙ ምስኪኖች እየተንሾካሾኩ። ‹‹አይ እናት አገሬ እስካሁን እኮ ለመኖር የተመኘ እንጂ የኖረ ትውልድ የለሽም። ይኼው እኛስ መቼ ከሰው ልጅ መሠረታዊ ፍላጎት (መጠለያ፣ ምግብ፣ ልብስ) ጥያቄ ተሻገርን?›› ይላል ታክሲ ጥበቃ ወረፋ የያዘ ወጣት። ‘ወጣት ተስፋ ፍለጋ የባከነበት ዘመን’ ይላል ውስጤ የአዕምሮዬን የሐሳብ ልጓም ጥሶ። በዚያው ልክ ደግሞ ጥቂት የሚባሉት ኑሯቸውን ለሌሎች ኑሮ መቃናት ሰውተው ሲንገላቱ ጎዳናው ያሳየናል። ግን እነሱ ጥቂት ናቸው። እነሱም አሸናፊ መሆን የሚችሉት የብዙኃንን ጥቅም ለግላቸው ተድላ ለማዋል የሚተጉ ተንኮለኞችን ሴራ መግታት ከቻሉ ብቻ ነው። ለመልካም ነገር የመተባበር ቅስም በተሰበረበት በዚህ ዘመን የበጎ ነገር አሸናፊዎችን ማየት ቀላል ነገር አልሆን ብሏልና። ‹የጎመን ድስት ይውጣ የገንፎ ድስት ይግባ› ሲባል እንደሰማነው፣ የግለሰቦች ዘመን ወጥቶ የሕዝብ ዘመን ሲገባ የምናየው መቼ ይሆን? ‹ሊነጋ ሲል ይጨልማል› ብለን ለጊዜው እንለፈው መሰል!
በስንት ጥበቃ ታክሲ አግኝተን ተሳፍረናል። የቻለችውን ይዛ የተረፉትን ጥላ ልትከንፍ በሾፌሯ አማካይነት ታክሲዋ ትጣደፋለች። የአንዲት ተሳፋሪ ዕቃ ተጭኖ አላልቅ በማለቱ ወያላው ትግል ላይ ሆኖ ቆመናል። ‹‹እባክሽ ምንድነው ይኼ? በጣም ብዙ ስለሆነ ከነገርኩሽ በላይ ተጨማሪ ትከፍያለሽ…›› የተማረረ መስሎ። ‹‹እባክህ ገንዘብ የለኝም፣ ሰው ጎጆው ላዩ ላይ ፈርሶበት አገሩን ሲለቅ እንዲህ ነው የሚሸኘው?›› አለችው የልምምጥ ፈገግታ ገጿ ላይ እያሳየችው። ‹‹ታዲያ ይኼን ሁሉ ዕቃ በሰባ ብር ብቻ? በዚህ ላይ የጫንኩሽ ተሳፋሪዎችን አጣብቤ እኮ ነው…›› አላት ሙግት በለመደ አንደበቱ። ‹‹ይኼን ጊዜማ እኛ ነን ሰበባችሁ? እኛን እንደ ዕቃ ቆጥራችሁ እንዳሻችሁ ወትፋችሁ ስትጭኑን ግን ምንም አይመስላችሁም?›› አለው አንድ ቁጡ ተሳፋሪ። ወያላው መልስ አልመለሰለትም። ወደ አንድ ጥቅስ ጠቆመውና ኮተቷ ወደ አስቸገረው ሴት ዞሮ፣ ‹‹እሺ በቃ ግማሹን ብቻ ክፈይ…›› አላት። ‹‹አንተ በፈጠረህ ምን ነው ምንም ቢሆን እኮ የኖርኩበት ከተማ ነው። ዛሬ ተፈናቅዬ በግዳጅ ስለቀው ትጨክናለህ? ተው እባክህ ገና ለትራንስፖርት ብዙ ነው የምከፍለው…›› ትለዋለች። ምስኪን ናት!
ጥቅስ የተጋበዘው ተሳፋሪ ጥቅሱን እያነበበ፣ ‹‹እኔን ነው በማያገባህ አትግባ የምትለው? እንኳን አንተ መንግሥትም አላለኝ። የመናገር መብት አለኝ እኮ…›› እያለ በንዴት ይጦፋል። ‹‹ወዴት ነው ስደቱ?›› ትላታለች ወፈር ያለችው ወጣት ተሳፋሪ ተፈናቃይዋን ምስኪን። ‹‹ወደ መተሃራ…›› ትመልሳለች። ‹‹አገርሽ እዚያ ነው?›› ትጠይቃታለች። የወያላውና የንዴታሙ ንትርክ በመሀል ጨመረ። ‹‹የምን መንግሥት ነው የምትለው? ግለሰብ ከሕግ በላይ በሆነበት አገር፣ ጎሳ ከአገር ይበልጥ ይሰፋብናል በሚባልበት ጊዜ መንግሥት ይለኛል እንዴ…›› ወያላው ቦግ አለ። ‹‹… ትውልዴስ እዚሁ አዲስ አበባ ነበር፣ ምን ላድርግ ለፍቼ የሠራሁት ጎጆ ሕገወጥ ተብሎ ሲፈርስ እግሬ ወደ መራኝ እየሄድኩ ነው። ኧረ ተይኝ ከአሁን በኋላ አገር አለኝ ብዬ ወደ እዚህ እግሬን የማነሳም አይመስለኝም…›› ትላታለች ከሁላችንም ይልቅ ረጅም መንገድ ያቀደችዋ ምስኪን ተሳፋሪያችን። ለነገሩ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ ሁሉም በመሰለው አቅጣጫ ለመሰደድ ያቆበቆ ነው የሚመስለው። ግን ሽሽት ያዛልቃል!
የወያላውና የደም ፍላታሙ ጎልማሳ አንድ ሁለት እየተካረረ ሄዶ ለቡጢ ከመጋበዛቸው በፊት፣ እንዲረጋጉ አንድ ነገር ማድረግ ነበረብን። ወዲያውኑ ታክሲያችን መክነፍ ጀመረች። አንድ ቀልደኛ፣ ‹‹አደራ ኮብልስቶን አጠገባችሁ ካለ ገለል በማድረግ ተባበሯቸው…›› ሲል ይቀልዳል። ‹‹ወገን በገዛ አገሬ ተፈናቅዬ እየተሰደድኩ ነው ሲል ምን እንርዳህ ወይም እናግዝሽ ማለት ቀርቶ ቀልድ ያዋጣል?›› ይላል አጠገቡ የተቀመጠ ሸበቶ ጎልማሳ። ‹‹ምን ሆነን ነው ግን ነግ በእኔ ማለት ያቃተን?›› አለች ከኋላ መቀመጫ አራት ሆነን ከተቀመጥነው አንዷ። ‹‹ልክ እንደ ድመቷ ሆነን እኮ ነው፡፡ አጅሬ ድመት ማዶ የቅቤ ተራራ ላይ ደገፍ ብላ ስትቀማጠል ከጎን በኩል ካለው ኮረብታ እሳት ይነሳል፡፡ አጅሬ ድመት የሚንቀለቀለውን ሰደድ እሳት እያየች ‹እኛ ተደላድለናል› አለች አሉ፡፡ እኛም እንዲያ እየሆንን ነው…›› አላት በቁጣ። ‹‹እኛም እንደ ድመቷ ተደላድለን እሳቱ ሲደርስብን ነው ማለት ነው ጩኸት የምናሰማው?›› ስትለው አንዲት ዝም ብለው የነበሩ እናት፣ ‹‹ልጆቼ እኔ ከእናንተ አላውቅም፣ ነገር ግን ይህ ዕድሜ የሚሉት ጉድ እንዳስተማረኝ ከሆነ ከስሜት ይልቅ ስክነት መልካም ነው፡፡ ስሜታዊ ሆነን ማንም በቀደደው ቦይ ከምንፈስ እንዴትና ለምን ብለን መጠየቅ ስንጀምር መልሱ ቀላል ነው…›› ሲሉ ባለፒኤችዲዎቹን ያስንቁ ነበር፡፡ ጉድ ነው እኮ!
ወያላው በዕቃ በተጨናነቀው መተላለፊያ ላይ እየተንጠራራ ሒሳቡን ሰብስቦ ጨርሷል። መሀል አካባቢ የተቀመጠ ተሳፋሪ የእጅ ስልክ ጠራ። አነሳው፣ ‹‹ሃሎ… ሃሎ… ሃሎ… አይሰማም…›› እያለ ጆሮው ላይ ተዘጋበት። ‹‹ወይ ዘንድሮ የማንም መቀለጃ ልሁን?›› ይላል ብሽቅ ብሎ። ‹‹የዘመኑ ኑሯችን ባህሪ ነው፣ ያለን አማራጭ ዘመኑንና አስተሳሰቡን መላመድ ነው…›› ትላለች መሀላችን የተቀመጠች ቀጭን ቆንጆ። ተደውሎለት የነበረው ተሳፋሪ ራሱ መልሶ ደውሎ ማናገር ጀምሯል። ‹‹ሄሎ… አቤት… አቤት… የት ደርሳችኋል? ምን? እናንተ ሰዎች ዓላማችሁ የሰውን እንጀራ መዝጋት ነው ልበል? አንዲት ‘ዋየር’ ለመቀጠል ይኼን ያህል መለመን አለብኝ? ያውም በራሳችሁ ጥፋት?›› እያለ ቀጠለ። የመብራት ኃይል ጣጣ መሆኑ ነው። ‹‹የፈረደበት ባለፈው እኔም ዘንድ መብራት እልም ሲል አንዲት ገመድ ተቃጥላ ቆጣሪ ለማስተካከል ያየሁት አበሳ…›› በማለት አንድ አዛውንት እሮሮ ጀመሩ። የመብራት ጉዳይ ወዲያውኑ የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆነ። ተገኝቶ ነው!
‹‹እኔን የገረመኝ ኑና ሥሩልኝ ብላቸው ‹የተመደቡት ሠራተኞች አራት ብቻ ናቸው› በማለት የሰጡኝ መልስ ነው። አዲስ አበባን ለሚያህል ከተማ ነው ወይስ ለክፍለ ከተማው ነው አራት ሠራተኞች ብቻ? ጉድ እኮ ነው የምንሰማው…›› ሲል አንድ ብርቱ መሳይ ጎልማሳ፣ ‹‹አሁንማ በተለይ ዝናብ ሲጥል ከመብረቅ ይልቅ የትራንስፎርመር ፍንዳታ መፍራት ጀመርን እኮ….›› አለ አንዱ ከመሀል። ‹‹ኧረ ተው በፈጠራችሁ፣ አሁን ደሃን ማማት ደግ ነው? ምናለበት የአገር በቀል ኢኮኖሚ ዕድገት መሳካት ላይ ብናተኩር?›› ይላል አዲስ ድምፅ። ‹‹አይዞን ‹የህዳሴ ግድቡ ሲጠናቀቅ መብራት መጥፋት የለ፣ ትራንስፎርመር መፈንዳት የለ፣ ሙስና የለ፣ የቤት ችግርና የመልካም አስተዳደር ዕጦት የለ፣ በቃ ድህነትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ድራሹን ነው የምናጠፋው’ ይል ነበር ካድሬ መሀላችን ቢኖር ኖሮ…›› ብሎ ለመሳለቅ ሞከረ ወያላው። ‹‹በሚያስኮርፈው ስንስቅ በሚያስቀው ስናኮርፍ መጨረሻችን ግን ምን ይሆን?›› የሚሉት አዛውንቱ ናቸው፡፡ ምን ያድርጉ!
የታክሲያችን ጉዞ ሊገባደድ ተቃርቧል። ቃል የሰለቸውን ዝምታ እየገለጸው ጥቂት እንደ ተጓዝን ወራጅ ባዩ እየተበራከተ ነው። ሳናውቀው በጨዋታ የፈጠርነው ዝምድና መሳይ ትውውቅ ለስንብት ሲጣደፍ ይታያል። ቀድመውን የሚወርዱት ተሳፋሪዎች እጅ ነስተውን ይሰናበታሉ። ‹‹እውነት ነው የምላችሁ ሁሌም እንዲህ ብንዋደድ እኛን የመሰለ ጠንካራ፣ እንደኛ ሥልጡን የሚሆን ሕዝብ አልነበረም…›› ይላሉ አዛውንቱ ታክሲ ውስጥ በአጭር ጊዜ የገነባነው የአንድነት መንፈስ ደስ አሰኝቷቸው። አጠገባቸው የተቀመጠ ጎልማሳ፣ ‹‹መዋደድ ማን ይጠላል ብለው ነው አባት? እንደሚያውቁት ግን እየመራ የሚያስጀምረን ከሌለ እኛ እኮ ከባድ ባህሪ ነው ያለን…›› ሲላቸው አልገባቸውም መሰል፣ ‹‹እንዴት?›› አሉት በከፊል ወደ እሱ በመዞር። ‹‹ፍቅርን ከአንደበት ባለፈ በተግባር የሚያስተምረን አርዓያ እንፈልጋለና። አዩ ሁሌም ሕዝብ ያለ መሪ፣ መንጋ ሁሌም ያለ እረኛ መልካም ሆኖ አያውቅም። ሕዝባችን ሆኖ የሚያሳየውና አርዓያ የሚሆንለት አመራር ይፈልጋል። ያኔ ከዕድገት፣ ከሥልጣኔና ከሰብዓዊነት የሚያግደው ምንም ነገር አይኖርም…›› ሲላቸው ራሳቸውን በአዎንታ ነቅንቀው፣ ‹‹ትልቅ ነገር ተናገርክ። በተለይ እኛ በአሁኑ ጊዜ ከፖለቲካ ዲስኩር ይልቅ ተግባራዊ ዕርምጃ ነው ማየት የምንናፍቀው። ለሕዝብ ቆሜያለሁ ከሚል መንግሥት ሕዝባዊ ሥራ ማየት ናፍቆናል። ሙስና፣ የመልካም አስተዳደር ዕጦትና ጥልፍልፍ የቢሮክራሲ አሠራር አቅለሽልሾናል። እንኳን እሬት ማርም ሲበዛ ይመርም አይደል? እናም የምንፈልገው በነፃነት ኖረን በነፃነት መሞት ነው፡፡ ከነፃነት በተቃራኒ ያለው ባርነት ነው…›› ብለውት፣ ‹‹እኔን እዚህ ጋ ጣለኝ…›› ሲሉ ታክሲዋ ቆመች። የነፃነት ዋጋ እንዴት ይተመናል እያልን በአዕምሮአችን ስናሰላስል ወያላው፣ ‹‹መጨረሻ!›› ብሎን ወርደን መለያየት ግድ ሆነብን። መልካም ጉዞ!