Tuesday, October 3, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ልናገርአደገኛው የሱዳን ቀውስና የእኛ ሁኔታ

አደገኛው የሱዳን ቀውስና የእኛ ሁኔታ

ቀን:

በገለታ ገብረ ወልድ

የምሥራቅ አፍሪካዋ ሰፊ በረሃማ ምድር ሱዳን ሰላም የሰፈነባት የምትባል አገር አልነበረችም፣ አይደለችም፡፡ ከነፃነት በፊት በእንግሊዝ ቀኝ ግዛት ሥር ሆና በጎሳዎችና በሃይማኖት መሪዎች አስተባባሪነት በእርስ በርስ ግጭት ስትቋሰል ከመኖሯ ባሻገር፣ የደቡባዊው ክፍል ሕዝቦቿ በጀመሩት ነፃ የመውጣት ትግል ምናልባትም ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይ የእርስ በርስ ውጊያ ውስጥ ገብታ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎቿን ሕይወት አስቀጥፋለች፣ ሚሊዮኖች ቆስለዋል፣ የሥነ ልቦና ጉዳቱም ያንኑ ያህል ነበር፡፡

ከዚሁ ባልተናነሰ በቢሊዮን ዶላሮች የሚገመት የአገሪቱ ሀብት የጦርነት ቋያ በልቶታል፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ አሁንም ተመሳሳዩ መከራና አሳር ለውድመት እየዳረጋውም ነው፡፡ ሱዳን የአፍሪካ ጦርነቶች ተምሳሌት፣ የመፈንቅለ መንግሥታት አብነት መሆኗም ነው የሚታወቀው፡፡

እውነት ለመናገር በእስካሁን የታሪክ ሒደቷ ሱዳን በታሪክ አጋጣሚ አምባገነኖችና በሙስና የሚታሙ መሪዎች ነበሯት እንጂ፣ ወደ ትልቅነት የሚወስዱ አርዓያ መሪዎችንም የታደለች አልነበረችም፡፡ ከራሳቸው አልፈው ለጎረቤቶቻቸው፣ ለአኅጉራዊ ተጠቃሚነት የሚጠቀሱ፣ ለመርህ ታማኝ፣ ለሕዝብ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት የሚታገሉ መሪዎች እዳልነበሯት ነው ሲተች የቆየው፡፡

የቀጣናው ፖለቲካል ኢኮኖሚ ጸሐፊ ጌታቸው ወልዩ በአንድ ወቅት፣ በዓባይ ዲፕሎማሲና በሱዳን አቋም ዙሪያ ባቀረበው አንድ ትንተና የሱዳን ፖለቲከኞችን እንዲህ ሲል ገልጿቸው ነበር፡፡ ‹‹በመንግሥታት ዙሪያ ጥናት ያደረጉ ፖለቲከኞች የሱዳን መሪዎችን፣ ባለሥልጣናትንና በተለያዩ ጊዜያት ወደ ሥልጣን የመጡ (እነ ጃፋር ኑሜሪ፣ ሳዲቅ አልማሃዲና ኦማር ሀሰን አል በሽርን ጨምሮ አሁንም ያሉት ወታደሮች) መንግሥታት እምነት የማይጣልባቸው፣ የማይታመኑና ወላዋዮች (Wishwashy, Painless, Irresolute, and Hesitant) ሲሉ ይጠሯቸዋል፤›› በማለት።

አሁን በተጨባጭ ሱዳን ውስጥ በተቀሰቀሰውና ለሁለት በተከፈሉት ወታደራዊ ኃይሎች መካከል በተከፈተው ውጊያ፣ በመቶዎች የሚቀጠሩ ሰዎች ሲሞቱ ሺዎች ቆስለዋል፣ ሚሊዮኖች ተፈናቅለዋል፣ ተሰደዋል፡፡ በእዚያው ልክ ደግሞ ከሦስት አሥርት ዓመታት በላይና ቢሊዮን ዶላሮች ፈሰስ የተደረጉባቸው መሠረተ ልማቶች በቀናት ውስጥ ወድመዋል፡፡ በርካታ የግልና የመንግሥት ተቋማትና ኩባንያዎች ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡ ይኼ ሁሉ መከራ በአንድ ደሃ አገር ላይ እንዲወርድ ያደረገውም ያው የኖረው የፖለቲከኞቹ እርባና ቢስነት ነው፡፡

በጄነራል አል ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ጦር ኃይልና በጄነራል ደጋሎ የሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል መካከል በተከፈተው የለየለት ውጊያ፣ ሱዳን ከፍተኛ ቀውስና አደጋ ውስጥ ገብታ ሰንብታለች። የውጭ ኃይሎች ሳይቀሩ በቀውሱ ውስጥ እጃቸውን ማስገባታቸውም ሲነገር ነበር፡፡ እስካሁን ይህ ነው የሚባል ተጨባጭ መፍትሔ አለመገኘቱም ይታወቃል።

ሁለቱ ጄነራሎች የቀድሞውን የሱዳን ፕሬዚዳንት አል በሽርን ከሥልጣን ለማስወገድ አንድ ላይ መቆማቸው አይዘነጋም። ይሁንና የሽግግር መንግሥቱ ከተመሠረተ በኋላ፣ በአገሪቱ መፃዒ ዕድል ላይ መግባባት ተስኗቸው ቆይተው ነው ወደ ግጭት የገቡት። በተለይ ጄኔራል ደጋሎ የሚመራው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል በአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ውስጥ እንዲካተት፣ ከጄኔራል አል ቡርሃንና ከሌሎችም ወገኖች የሚነሳውን ጥያቄ  አለመቀበሉ ነው ችግሩን ያጧጧፈው።

የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ተነጥሎ የተቋቋመው በቀድሞው ፕሬዚዳንት አል በሽር የአስተዳዳር ወቅት እንደነበር አይረሳም። ዓላማው ደግሞ፣ በምዕራብ የአገሪቱ ክፍል (ዳርፉር) ያለውን የጥቁር ሙስሊሞች የተቃውሞ እንቅስቃሴ ለመግታት ታስቦ እንደሆነ ነው መረጃዎች የሚያመለክቱት። ሒደቱ ግን የጥቅም ግጭትና የሥልጣን ዕድሜ የማስቀጠል ሕልም ስለነበረበት፣ ዳፋው እነሆ የሱዳንን ህልውና ለአደጋ እስከማጋለጥ ደርሷል፡፡

 ልዩ ኃይሉ ከቀደመው ተልዕኮ አንስቶ በሰው ኃይል፣ በመሣሪያና በቴክኖሎጂ ተጠቃሚነት (በተለይም በሎጂስቲክ) እየተጠናከረ በመሄዱ፣ የአገሪቱን የመከላከያ ሠራዊት ለመገዳደር የሚችል አቅም እንዲፈጥር አስችሎታል። የሰሞኑ ግጭት መነሻም ይህንኑ እውነታ ያረጋገጠ ይመስላል (በእኛም አገር በአንዳንድ ክልሎች ያለው ኢመደበኛ ታጣቂና የክልል ልዩ ኃይል የመከላከያ ሠራዊቱን ወደ መገዳደር የሚወስድ ጭንቀት መፍጠሩ የማያስደንቀው አደጋው አለመደማመጥን ስለሚጋብዝ ነው)፡፡

 የሱዳን ልዩ ኃይል 50 ሺሕ የሚደርስ የሰው ኃይልና ትርጉም ያለው ትጥቅ እንዳለው ይገመታል።  የሱዳን መከለከያ ኃይል ደግሞ በሰው ኃይል ቁጥሩ 100 ሺሕ እንደሚደርስ ነው የሚታመነው። የአየርና የባህር ኃይላት በዋናው ጦር ውስጥ ቢኖሩም፣ የሐሳብ መከፋፈሉና የውጭ ኃይሎች በየጎራው መሰለፋቸው የኃይል ሚዛኑን ወደ ልዩ ኃይሉ ተዋጊዎች አድርጎትም ታይቷል፡፡

በሱዳን ከተፈጠረው የእርስ በርስ ግጭት በኋላ በማኅበራዊ ድረ ገጽ ሐሳቡን ያካፈለው የጀርመን ድምፅ አዘጋጅ ነጋሽ መሐመድ ሁኔታውን፣ ‹‹ሁለት አውራ ዶሮዎች አንድ ቆጥ ላይ›› በሚል ገልጾታል፡፡ ሁለቱ ጄኔራሎች የሚያዙዋቸው የሱዳን ፈጥኖ ደራሽና የመከላከያ ጦር፣ የአል በሽር ታዛዥ ሆነው ዳቦና ፉል ጥየቃ አደባባይ የወጣውን ደሃ አስገደሉ፣ የዴሞክራሲና የሐሳብ ነፃነትን አጨለሙ፣ የወታደራዊ ጁንታ መሪዎች ሆነውም የተቋማቸውን ሰላማዊ ሰው ሁሉ አስጨነቁ፣ በኋላም ለጠቅላይነት ለጨፍላቂነት ተፋለሙ ብሏቸዋል።

 ሰዎቹ የተቀራራቢ ዘመን፣ የአንድ አገር ግን የሩቅ ለሩቅ አካባቢ ውልዶች ናቸው። የአስተዳደግ፣ የሙያ፣ የዕውቀት ተቃራኒዎች ግን ደግሞ የአንድ አለቃ ምንዝሮች፣ የአንድ ጦር ሜዳ ተዋጊ-አዋጊ ጓዶች ነበሩ። ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ቀድሞ ጄኔራል መሐመድ ሐምዳን ዳግሎ (ሔሚቲ) ከተል ብለው የጄኔራልነት ማዕረግ የለጠፉላቸውን አለቃቸውን ከዱ። ከሥልጣንም አስወገዷቸው።

እ.ኤ.አ. ሚያዚያ 11 ቀን 2019 የአንድ አለቃቸውን ሥልጣን እንደ ዋናና ምክትል የተጋሩት ጄኔራሎች እንደ አጀማመራቸው አልቀጠሉም። ‹‹አንድ ቆጥ ላይ ሁለት አውራ ዶሮ አይስፍርም›› እንዲል የእኛ ሰው፣ በአራተኛ ዓመታቸው ዘንድሮ ውጊያ መግጠማቸው ውስጥ የሚጠበቅ ነበር። ካርቱምን ያነደደው ውጊያ መነሻውም ስግብግብነትና ለሕዝብ ያለመወገን ድንቁርና ነው።

ከአምስት ሳምንታት ወዲህ ሞቅና በረድ እያለ የሱዳን ከተሞችን የሚያጋየው ውጊያ፣ የአምባገነኖች የሥልጣን ሽሚያ ውጤት መሆኑ ነው ሱዳናዊያንም የሚያምኑት። የሱዳን ሕዝብ አምባገነን ገዥዎቹን አስወግዶ አዳዲስ አምባገነኖችን ለማንገሥ የስንት ወገኖቹን ሕይወት፣ ደም አጥንት መገበር አለበት? ደግሞስ እስከ መቼ? የሚለውን ቁጭት በውጭ አገሮች ኑሯቸውን ያደረጉ ስደተኛ ሱዳናዊያን በየሚዲያው የሚናገሩት ሆኗል።

አሁን ሱዳንን የገጠማት ችግር እንደ አገር ህልውናዋን ከመፈተኑና ነዋሪዎቿን ለመከራ ከመዳረጉ ባሻገር፣ ለቀጣናው አገሮችም ሌላ ራስ ምታት እየሆነ ነው፡፡ በተለይ በሰፊው የድንበር ጉርብትናችን ብቻ ሳይሆን በባህል፣ በእምነትና በዓባይ ውኃ ለተሳሰርነው ኢትዮጵያዊያን ቀስ በቀስ ዳፋው እየተረፈና ሸክሙ እየከበደ እንደሚሄድም ነው ተንታኞች የሚያስረዱት፡፡ በጥንቃቄ ካልተያዘ፡፡

በሱዳን የተከሰተው ግጭት ለጎረቤት አገሮች ተጨማሪ ፈተና ነው የሚባልበት አንዱ ምክንያት፣ ጦርነቱን በመሸሽ የተለያዩ አገሮች ዜጎች ጭምር በስደተኝነት ወደ የአገራቱ የሚገቡ በመሆናቸው ነው፡፡ ለምሳሌ ግጭቱ በተጀመረ በሁሉተኛው ሳምንት  በመተማ ዮሐንስ ከተማ በኩል ወደ ኢትዮጵያ እየገቡ የነበሩ ስደተኞች ቁጥራቸው በቀናት ውስጥ በእጥፍ ሲጨምር ታይቷል፡፡ እስካሁንም ከአርባ ሺሕ የማያንሱ ሱዳናዊያንና የሌላ አገር ስደተኞች ወደ መጠለያ መግባታቸው ነው የሚነገረው፡፡ ትንሽ ገንዘብ ያላቸው ደግሞ እስከ አዲስ አባባም መግባታቸው እየታየ ነው፡፡

በእርግጥ ኢትዮጵያ የሱዳን ጦርነት ወሬ ከተሰማበት ዕለት ጀምሮ በገለልተኝነት ጎረቤት አገር ሱዳን ችግሮቿን በሰላማዊና መደማማጥ መንገድ እንድትፈታ ከመጣር ባሻገር፣ ተፈናቃዮንችም አቅም በፈቀደ መጠን ለማስተናገድ ደፋ ቀና ከማለት አልቦዝነችም፡፡ የጎረቤት ክልል ሕዝቦች በተጨባጭ እያደረጉ ያሉትም ይህንኑ ነው፡፡

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) የሱዳንን ወቅታዊ ሁኔታ አስመልክተው ባስተላለፉት የዚያን ሰሞን መልዕክታቸው፣ የጎረቤት አገር ሱዳን ሕዝብ ከጥንትም ጀምሮ ነፃነቱን የሚወድና ብሔራዊ ክብሯን አስጠብቆ የቆየ መሆኑን አስታውሰው፣ የሱዳን ሕዝብ ከሚወሳባቸው አያሌ መልካም ባህሪያት መካከል ለጋስነትና እንግዳ ተቀባይነቱ ከምንም በላይ ጎልቶ ይጠቀሳል ማለታቸው እንደ አገር ለሱዳን ያለንን አተያይ አንፀባርቀዋል።

እነዚህ እሴቶች ደግሞ ከማኅበራዊ ትስስሩ በላይ የኢትዮጵያንና የሱዳንን ሕዝብ የሚያመሳስሉ፣ ይበልጥ የሚያቆራኙና ከሌላው ወገን እንዲለዩ ከሚያደርጓቸው  እውነታዎች ሆነው እናገኛቸዋለንም ነው ያሉት። በመሆኑም የሱዳን ሕዝብ በባህሪው ኩሩ በመሆኑ በምንም ሁኔታ ክብሩንና ነፃነቱን አሳልፎ የሚሰጥ እንደማያደርገው ጭምር ጠቁመው ነበር፡፡

 ‹‹እኛ ኢትዮጵያውያን ይህ ኩሩ የሱዳን ሕዝብ አሁን እየገጠመው ያለውን ቀውስ በጥበብ ሊወጣው ይችላል ስንል ያለንን ፅኑ እምነት ለመግለጽ እንወዳለን፤›› ሲሉም፣  ገለልተኛ ሚናችንን በአጽንኦት ጠቅሰዋል፡፡ ያም ሆኖ በሁለቱ አገሮች መካካል ያልተቋጩና አከራካሪ አጀንዳዎች በይደር መቀመጣቸው የታወቀ ነው፡፡

ለነገሩ በመዘግየቱ ቢወቀስም የአፍሪካ ኅብረትም የሱዳን ጦርና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ አስቸኳይ የተኩስ አቁም ሊያደርጉ ይገባል ሲል መግለጹ የሚታወስ ነው፡፡ ምንም እንኳን ትርጉም ባለው መንገድ ለውጥ ያስከተለ መግለጫ ባይሆንም፡፡  በተለይ የኅብረቱ የሰላምና የፀጥታ ምክር ቤት በሱዳን ወቅታዊ ጉዳይ ላይ መክሮ፣ የሱዳን ሕዝብ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ወደ ነበረበት እንዲመለስ፣ በሲቪል መራሽ መንግሥት ለመተዳደር ያቀረበውን ጥያቄና ለዚሁ የሚደረግን ጥረት እንደሚደግፍ መግለጹ በበጎ መወሰድ ያለበት ነው።

ለሱዳን ሕዝብ ሉዓላዊነትና ፖለቲካዊ አመለካከት ነፃነት እንዲሁም ለአገሪቱ የግዛት አንድነት መከበር ሲባል ግን እንብዝም ጠንካራ ተፅዕኖ እንደሌለው የሚታማው ኅብረቱ ብቻ ሳይሆን፣ ዓለም በሙሉ ግፊት ሊያደርግ ይገባው ነበር። ምክንያቱም  በሱዳን ጦርና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መካከል የተቀሰቀሰው ጦርነት በእጅጉ አሳሳቢ፣ ነገሩ ወደ ከፍተኛ ቀውስ ሊሸጋገር እንደሚችል ተገንዝቦ መትጋት ለሱዳን ብቻ ሳይሆን ለቀጣናውም ወሳኝ ዕርምጃ ስለሆነ ነው። ከእነ የመንና ሶሪያ ውድቀት መማሩ ስለሚጠቅምም ነው፡፡

ኢትዮጵያ ደግሞ የቅርቤ ከምትላቸው አገሮች ተርታ የምትመድባት ሱዳን፣ በድንበር ብሎም በታላቁ ህዳሴ ግድብ ላይ ከግብፅ ጋር በያዘችው አቋም ግንኙነታቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻከር ከጀመረ መሰነባበቱን ሳትረሳ፣ አጋርነቷን አጥብቃ ማፅናት አለባት።  በተለይ አልፋሽቃ ድንበርን ለመቀራመት የሚደረገው ትግል ሁለቱን አገሮች ፍጥጫ ውስጥ እስከ መክተት ደርሶ ስለነበር ከውድቀቷ ሳይሆን፣ ሱዳንን ከመታደግ ጋር መፍትሔ ለመፈለግ መሥራቱ ይጠቅማል የሚሉ ተንታኞች በርክተዋል፡፡

ኢትዮጵያና ሱዳን አለመተማመናቸው የሚጀምረው በድንበሮቻቸው ላይ በሺዎች የሚቆጠሩ ወታደሮቻቸውን አስፍረው አሳቻ ሰዓት እየጠበቁ ነው ሲባል እንደነበርም ማስታወስ ግድ ይላል። በተፈጥሮ ለም በሆነችውና ለእርሻ ተስማሚ እንደሆነች በሚነገርላት የአልፋሽቃ ድንበር ይገባኛል በሚል ሁለቱ አገሮች ፍጥጫ ውስጥ መግባታቸው የሚጠበቅ ቢሆንም፣ ጀኔራሎቹ የጀመሩት ግብታዊነት ጎረቤታሞቹን ወደ ግጭት ለመክተትና የሕዝቡን ትኩረት ወደ ድንበር ግጭት ለመግፋት ያለመ ነበር፡፡ በነበር ቀረ እንጂ።

እውነት ለመናገር ለሁለቱ አገሮች የድንበር  ውዝግብ መነሻ የሆነው ምክንያቱ ምን ይሆን? ብሎ የሚደናገር የታሪክ አጥኚ የለም፡፡ እንደሚታወሰው እ.ኤ.አ. በ1902 ተፈርሞ በነበረው አንግሎ-ኢትዮጵያ የካርታ ላይ ምልከታ ስምምነት፣ አልፋሽቃ የእኔ መሆኑ ያሳያል ስትል ሱዳን ስትከስ ነበር የቆየችው። በቅኝ ግዛት ስምምነት ወቅት የዓለም አቀፉ ድንበር ወደ ምሥራቅ አምርቷል፣ በዚህ ምክንያትም መሬቱ በሱዳን ተካቷል። ይሁን እንጂ ከ1900 በፊት በሥፍራው ቤተሰብ መሥርተው የሚኖሩበትና ግብር ደግሞ ለኢትዮጵያ ሲከፍሉም እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ ቆይተዋል።

መሐማድ ጃላል ሃሽም (ዶ/ር) የመሰሉ ተንታኞች እንደሚሉት ደግሞ፣  በኢትዮጵያና ሱዳን የድንበር ግጭት ውስጥ የግብፅ ሥውር እጅ ከፍተኛ ድርሻ እንዳለው አለመጠርጠር ሞኝነት ነው፡፡ ለነገሩ በራሷ በሱዳን አገረ መንግሥት ውስጥ ለተፈጠረው ቀውስም ቢሆን የአብዱልፈታህ አልሲሲ አስተዳደር ሥውርና ግልፅ እጆች የሉም ማለት እንደማይቻል ነው ሲነገር የሰነበተው፡፡

ግብፅ የሱዳን ግዛት የሆነችውን ከፍተኛ ስትራቲጂካዊ የቀይ ባህር ዳርቻ ያለችውን (Halayebe triangle)  በኃይል ወርራ በኢትዮጵያና በሱዳን ድንበር ያለውን ውዝግብ በድርድር መፈታት የሚችል ሆኖ ሳለ፣ ወደ ጦርነት እንዲያመራ የውክልና ጦርነት እካሄደች ነው የማለታቸው አንድምታም ከእነዚህ ቀጣናዊ እውነታዎች አንፃር ነው፡፡

የፖለቲካና ዓለም አቀፍ ግንኙነት ምሁሩ ሃሽም (ዶ/ር) ሁለቱ አገሮች በዓባይ ፖለቲካ ዙሪያ ካይሮ የምታካሂደው የእጅ አዙር ጦርነት ነቅተው መከታተል ይገባቸዋል ከማለታቸው ባሻገር፣ የጋራና የተናጠል ደኅንነታቸውን በመጠበቅ መተባባር ካልቻሉም የአንዱ አደጋ ለሌላው ሊተርፍ እንደሚችልም ነበር የተነበዩት፡፡

በእርግጥ በእልህና በጦር መሪዎች ለኳሽነት እንደ ቀልድ የተጀመረው የጥፋት መንገድ፣ ሱዳንን ለዘመናት ወደኋላ እየመለሰ ዛሬም አልበረደም። የዓረብ ሊግ፣ የአፍሪቃ ኅብረት፣ የአውሮፓ ኅብረት፣ ዩናይትድ ስቴትስ፣ ብሪታንያ፣ ግብፅና የእኛም አገር መንግሥታት ጭምር ሁለቱ ወገኖች ውጊያውን እንዲያቆሙ እየጠየቁ ብቻ ሳይሆን፣ ወደ መነጋጋርና ድርድር እንዲገቡ ግፊት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡ ግን  የሚጀመረው የተኩስ አቁም ስምምንት እንኳን ተጠናክሮ መቀጠል እንዳልቻለ ነው እየተመለከትን ያለነው።

ቀደም ባሉት ቀናት በውጊያው ዓውድ ሁለቱም ወገኖች ድል መቀዳጀታቸውን፣ በተለይ ካርቱም የሚገኙ የጦር ኃይል ምሽጎችን፣ የአውሮፕላን ማረፊያዎችንና የመንግሥት መሥሪያ ቤቶችን መቆጣጠራቸውን በየፊናቸው ሲያውጁ ነበር። እውነቱ ባይታወቅም ሱዳንና መከረኛው ሕዝቧ ግን ወደ መቀመቅ ከመውረድ ያዳናቸው ነገር አልነበረም፣ የለምም፡፡

ካርቱም በእርግጥ የሕንፃ ፍርስራሽ፣ ቀለህና ትቢያ ተከምሮባትና አስደንጋጭ ድምፅ ሞልቶባት መመልከት ውድቀት ምንኛ ፈጣን እንደሆነ ለእኛም ሌላ ማስተማሪያ ነው። ተኩሱ ጋብ ባለባቸው የቅርቦቹ ቀናትም ሕይወት የሚያቃትትባት የጣር ምድር መስላ መታየቷ፣ ለሱዳን ከሁለት አንዱ ኃይል ተሸንፎ እጅ መስጠቱ መፍትሔ ያመጣ እንደሆን እንጂ ሌላ መፍትሔ ያለ አይመስልም፡፡

ሲጠቃለል የሱዳን ትርምስና ቀውስ ለእኛ አገር ትርፍ ሳይሆን ኪሳራ አምጭ አደጋ ነው፡፡ በቀጣናው ውስጥም ሌላ የኃይል አሠላለፍ የሚፈጥር ብቻ ሳይሆን ሌላ ትርምስ የሚጠራ ነው፡፡ እናም ነቅቶ የውስጥ ድክመትን ፈጥኖ አርሞ የአገርን ህልውና ለመመከት መሰናዳት ከኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ ይጠበቃል፡፡ ከሱዳን የሚሰደዱ ወገኖችንም ሆነ የውጭ አገር ሰዎችን በአግባቡ እየለዩ፣ ከራስ ውስጣዊ ደኅንነት ጋር በተናበበ መንገድ መደገፉም ነው የሚያዋጣው፡፡

በእርግጥ ኢትዮጵያ በዲፕሎማሲያዊ ሒደት ላይ ያላትን አቋም የዓለም አገሮች  ጠንቅቀው ያውቁታል፡፡ የሱዳኑ ግጭት ከተጀመረ ሳይውል ሳያድር ከላይ ለመግለጽ የተሞከረውና ‹‹ወደ ንግግር ተመለሱ ጦርነት አይበጅም›› ስትል በመሪዋ በኩል የሰጠችው መግለጫ የመጀመሪያዋ አገር ሆና የታየችበት ነው። ይህንኑ አቋም በቀጣይነት ዘላቂ መፍትሔ በትኩረት መሥራት ያስፈልጋል፡፡

  ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን የግል አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ተመድንና ዓለም አቀፋዊ ሕግን ከእነ አሜሪካ አድራጊ ፈጣሪነት እናድን!

በገነት ዓለሙ በእኔ የተማሪነት፣ የመጀመርያ ደረጃ ተማሪነት ጊዜ፣ የመዝሙር ትምህርት...

የሰላም ዕጦትና የኢኮኖሚው መንገራገጭ አንድምታ

በንጉሥ ወዳጅነው ፍራንክ ቲስትልዌይት የተባሉ አሜሪካዊ ጸሐፊ ‹‹The Great Experiment...

ድህነት የሀብት ዕጦት ሳይሆን ያለውን በአግባቡ ለመጠቀም አለመቻል ነው

በአንድነት ኃይሉ ድህነት ላይ አልተግባባንም፡፡ ብንግባባ ኖሮ ትናንትም ምክንያት ዛሬም...