Monday, April 15, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊፕላስቲክ የሚሰበስቡ የንግድ ልውውጥ የሚያደርጉበት የመረጃ መረብ

ፕላስቲክ የሚሰበስቡ የንግድ ልውውጥ የሚያደርጉበት የመረጃ መረብ

ቀን:

በየቦታው የሚጣሉ የፕላስቲክ ጠርሙሶች፣ ጀሪካን፣ ብረታ ብረት፣ ካርቶንና ሌሎች መሰል ግብዓቶች የመዲናይቷን ውበት አጥፍተውት ከርመዋል፡፡ በተለይም በመሀል ከተማ የሚገኙ ቦታዎች የችግሩ መገለጫ ሆነው ነበር፡፡ ችግሩን ለመቅረፍም በከተማዋ በውበትና ፅዳት ዘርፍ የሚሠሩ መንግሥታዊ ተቋማት እንዲሁም መንግሥታዊ ያልሆኑት ሲሠሩ ከርመዋል፡፡

በርካታ ማኅበራትም ከየጎዳናው የወዳደቁ ፕላስቲክ ነክና ብረታ ብረት በመሰብሰብና እነዚህን ግብዓቶች መልሶ በመጠቀም ዘርፍ እንዲሰማሩ ተደርጓል፡፡ ሆኖም የገበያ ትስስር ክፍተት አለ፡፡፡

ፔትኮ ኢትዮጵያ ከጂ አይ ዜድ ጋር በመቀናጀት በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩ መሪ ተዋናዮች እርስ በርስ የሚተዋወቁበት እንዲሁም የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበት የመረጃ መረብ ሰኞ ግንቦት 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል፡፡

- Advertisement -

Video from Enat Bank Youtube Channel.

የፔትኮ ኢትዮጵያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወ/ሮ ምሕረት ተክለ ማርያም ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ አካባቢን የሚበክሉ የውኃ ፕላስቲኮችንና ሌሎች ግብዓቶችን ሰብስበው መልሶ ጥቅም ላይ የሚያውሉ የዘርፉ ተዋናዮች እርስ በርስ የሚገናገኙበት እንዲሁም የገበያ ትስስር የሚፈጥሩበትን አማራጭ እንዲያገኙ የመረጃ መረብ ተዘርግቷል፡፡

በመረጃ መረብ ተጠቃሚ የሚሆኑት አዲስ አበባን ጨምሮ ከ18 የክልል ክፍለ ከተሞች የተወጣጡ መቶ ድርጅቶች መሆናቸውን የገለጹት ዋና ሥራ አስኪያጇ፣ ድርጅቶቹ የድርጅታቸውን ሙሉ መረጃ በትክክለኛ መንገድ በማስመዝገብ የዲጂታሉ ፕላትፎርም ወይም የኢንዱስትሪው አካል መሆን እንደሚችሉ አስረድተዋል፡፡

በዚህ መሠረት በዘርፉ የተሰማሩ ተቋሞች የመረጃ መረቡን በመጠቀም ትክክለኛ መረጃን እንዲያገኙ፣ የገበያ ትስስርን እንዲፈጥሩና በኢንዱስትሪው ዙሪያ የሚሠሩ ሥራዎችን ወቅታዊ መረጃ እንዲያገኙ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል ሲሉ አክለዋል፡፡

በኢንዱስትሪው የተሰማሩ ተዋናዮች የተለያዩ ችግሮች እንደሚገጥማቸው ያስታወሱት ወ/ሮ ምሕረት፣ ችግሮችን ለማለፍ የተዘረጋው የመረጃ መረብ የሚያግዛቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

የመረጃ መረቡም በፕላስቲክ ኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ ተዋናዮች ወይም ባለድርሻ አካላት ከፕላስቲክ አምራቾች ጀምሮ እስከ መጨረሻው መልሶ መጠቀም ድረስ የተሰማሩ አካላት እርስ በርስ የሚገናኙበት መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የተዘረጋውን የመረጃ መረብ በታለመለት ዓላማ መሠረት ከግብ ለማድረስ አስፈላጊ የሆኑ ቅድመ ሁኔታዎች እንዳሉትና እነዚህን ተግባራዊ ለማድረግ ተቋሙ ከዘርፉ ተዋናዮች ጋር የሚሠራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

እስካሁን ለአገር ውስጥና ለውጭ የሚያቀርቡ መቶ ድርጅቶች መመዝገባቸውን፣ በቀጣይም ይህንን አሠራር በማጠናከር በርካታ ተቋሞችን ለመመዝገብ ቅድመ ዝግጅት መደረጉን አስረድተዋል፡፡

የኢንዱስትሪ ተዋናዮች የሚገጥማቸው ችግር የቦታ ይዞታና የትራንስፖርት አገልግሎት መሆኑን የተናገሩት ዋና ሥራ አስኪያጇ፣ መፍትሔዎችን ለማመቻቸት ተቋሙ ከተለያዩ መንግሥታዊ ተቋሞች ጋር ውይይት እያደረገ ነው ብለዋል፡፡

በኢትዮጵያ የፕላስቲክ ተጠቃሚዎች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን፣ የተለያዩ ጥናቶችም እ.ኤ.አ. ከ2006 እስከ 2021 ባለው ጊዜ የፕላስቲክ ተጠቃሚዎች ቁጥር በ13 በመቶ መጨመሩን እንደሚያሳዩ ገልጸዋል፡፡

ፕላስቲክን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት አንድ ዕርምጃ ከፍ ማድረግ እንደሚቻል፣ ይሁን እንጂ ይህንን ተፈጻሚ ማድረግ ካልተቻለ ለአካባቢያዊ፣ ማኅበራዊና ሌሎች ችግሮች ተጋላጭ እንደሚኮን ወ/ሮ ምሕረት ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ የፕላስቲክ ቆሻሻን መልሶ ከመጠቀም አኳያ ይኼ ነው የሚባል ሥራ አለመሠራቱን ጠቅሰው፣ አሁን ላይም በዚህ ሥራ ላይ የተሰማሩ ተቋሞች አዲስ አበባና በአዲስ አበባ ዙሪያ ፋብሪካቸውን ተክለው የሚሠሩ ናቸው ሲሉ አብራርተዋል፡፡

በአገሪቱ የፕላስቲክ ብክለት ሲታይ ከአዲስ አበባ ውጭ ጭምር እንዳለና ይኼም ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ እያሳደረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በመልሶ መጠቀም የተሰማሩ ድርጀቶችም፣ ተቋማቸውን በማስፋት ከአዲስ አበባ ውጭ በተለያዩ ቦታዎች ላይ ፋብሪካቸውን በመትከል መሥራት እንደሚገባና ይህንን የቤት ሥራ ለመወጣት ተቋሙ የሚሠራ መሆኑን  ገልጸዋል፡፡

በፕላስቲክ ኢንዱስትሪው የሕግና የፖሊሲ ሥርዓቶችን በተሻለ ሁኔታ በመዘርጋት መሥራት እንደሚገባና እነዚህን ጉዳዮች ተፈጻሚ ለማድረግ መረጃዎች የማሰባሰብ ሥራ እየተሠራ እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡

የኢትዮጵያ አካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ምክትል ዳይሬክተር ወ/ሮ ፍሬነሽ መኩሪያ እንደገለጹት፣ የተለያዩ የፕላስቲክ ውጤቶችን መልሶ በመጠቀም የአገሪቱን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ከፍ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡

የፕላስቲክ ምርቶችን በዘላቂነት መያዝ ካልተቻለ በማኅበረሰቡ ዘንድ የሚያደርሰው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን፣ ይሁን እንጂ ፕላስቲክን በአግባቡ መጠቀም ከተቻለ ትልቅ ሀብት ነው ብለዋል፡፡

ፕላስቲክን መልሶ በመጠቀም ዙሪያ የሚሠሩ ሥራዎች ኃላፊነት በተሞላበት መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ የካርቦን ልቀትንና የአካባቢ ብክለትን መቀነስ እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡

በኢትዮጵያ በመልሶ መጠቀም ላይ የተሰማሩ ተቋሞች በበርካታ ችግሮች ውስጥ ያሉና እንደ ሌሎች አገሮች በዘርፉ ውጤታማ ሥራ እየተመዘገበ አለመሆኑን አክለዋል፡፡

ፕላስቲክ፣ ብረታ ብረትና ሌሎች ግብዓቶችን መልሶ በመጠቀም ላይ የተሰማሩ የዘርፉ ተዋናዮች የተሻለ አገልግሎት እንዲያገኙ እንዲሁም እርስ በርስ የገበያ ትስስር እንዲፈጥሩ አሁን የተዘጋጀው ፕላት ፎርም ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው የሪፍት ቫሊ ቴክኖሎጂ ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማኅበር መሥራችና ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አደን ዳርጌ ተናግረዋል፡፡

ፕላት ፎርሙም የተለያዩ አገልግሎቶችን እንዲያገኙበት ምቹ ሁኔታዎችን ከማመቻቸት ባለፈ በአሁኑ ወቅት ለመልሶ መጠቀም የሚውሉ ግብዓቶች በአገሪቱ ውስጥ በምን ያህል ገንዘብ እየተሸጠ ነው? የሚለውን ለማወቅ ጭምር እንደሚረዳቸው ዋና ሥራ አስኪያጁ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

በተለይም በአገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ ሻጭና ገዥ እርስ በርስ የሚተዋወቁበት ፕላት ፎርም መሆኑን የተናገሩት መሥራቹ፣ የትኛው ክልል ላይ ምን ያህል ግብዓት አለ? የሚለውን ለመለየት በቀላሉ ይረዳል ብለዋል፡፡

በፕላት ፎርሙ ውስጥም የሚመዘገቡ የዘርፉ ተዋናዮች ሕጋዊነታቸው ሳይታወቅ ወደ ሥርዓት ውስጥ እንደማይገቡ ገልጸው፣ ይህንን ፕሮጀክት ወጥ በሆነ መንገድ ለማስቀጠል ከፔትኮ ኢትዮጵያ ጋር በጋራ ለመሥራት ለአራት ዓመታት የሚቆይ ስምምነት ማድረጋቸውን አብራርተዋል፡፡

የሶዶ ደረቅ ቆሻሻ ማስወገጃ ኅብረት ሥራ ማኅበር አስተዳዳሪ አቶ ሳሙኤል ዶክተር  እንደገለጹት፣ ከዚህ በፊት በርካታ ፕላስቲኮች ተሰብስበው ለማን እንደሚሸጥ ግራ ይገባ ነበር፡፡ ጀሪካን፣ የፕላስቲክ ጠርሙስ፣ ብረታ ብረትና ሌሎች ግብዓቶችን ሰብስበው ሐዋሳ ለሚገኙ ድርጅቶች በእርካሽ ዋጋ ይሸጡም ነበር፡፡

በአሁኑ ወቅት በፔትኮ ኢትዮጵያ በኩል የተፈጠረው ፕላት ፎርም የሰበሰቡትን ግብዓት ለማንና እንዴት መሸጥ እንዳለባቸው የሚያሳይ በመሆኑ፣ ሥራቸውን እንደሚያቀል ገልጸዋል፡፡

በመንግሥት በኩል ምንም ዓይነት ድጋፍ እንደማይደረግላቸው የገለጹት አስተዳዳሪው፣ አብዛኛው ደንበኞችም የግንዛቤ እጥረት ስለነበረ ደረቅ ቆሻሻ የመለየት ሥራ ላይ ሲቸገሩ ነበር ብለዋል፡፡

ማኅበሩ ብረትና ጀሪካን በኪሎ እስከ 50 ብር በመሸጥ ላይ መሆኑን፣ እስካሁንም የተለያዩ ግብዓቶችን በመሸጥ ውጤታማ ሥራ መሥራቱን ገልጸዋል፡፡

በዘርፉ የተሰማሩ ተዋናዮች የግብዓት፣ የቦታ ይዞታና የተለያዩ ችግሮች እንደሚገጥሟቸው፣ የእነሱ ማኅበርም የዚህ ችግር ገፈት ቀማሽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አዲስ አበባ ፅዱ እንድትሆን ማኅበረሰቡ የደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓትን በሚገባ እንዲያውቅ የተዘረጋው የመረጃ ቋት ትልቅ ጠቀሜታ አለው ያሉት የጥበብ ፅዱና አረንጓዴ ደረቅ ቆሻሻ አሰባሰብና አወጋገድ መልሶ መጠቀም ኅብረት ሽርክና ማኅበር ሥራ አስኪያጅ አቶ ፍቅሬ ገብሬ ናቸው፡፡

ፔትኮ ኢትዮጵያና ጂ አይ ዜድ በጋራ በመሆን ያዘጋጁት ፕላት ፎርም ከጥሬ ሀብት ጀምሮ እንዴት መልሶ መጠቀም አለብን? የሚለውን ለማወቅ የሚረዳ መሆኑን አቶ ፍቅሬ ገልጸዋል፡፡

በቀጣይ በዚህ ሥራ የተሰማሩ የዘርፉ ተዋናዮች እንዴት ተቀናጅተው መሥራት እንዳለባቸው ለማወቅ የተዘረጋው ፕላት ፎርም ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው፣ ማኅበሩም እስካሁን የተለያዩ ግብዓቶች በመሰብሰብ በመልሶ መጠቀም ለተሰማሩ ድርጅቶች እያስረከበ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በየጊዜው በርካታ ግብዓቶችን በጥሬው በመሰብሰብ ኮባ ኢምፓክት ለተሰኘ ድርጅት እያቀረቡ መሆኑን፣ ወደፊት ግን የፕላስቲክ ጠርሙሱን ጨፍልቆ ለማስረከብ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን አስታውሰዋል፡፡

በቀጣይ መንግሥት የራሳቸው የመልሶ መጠቀም ፋብሪካ እንዲገነቡ የቦታ ይዞታ እንዲሰጣቸው መጠየቃቸውን፣ እስካሁን በሳምንት ሃያ ሺሕ ኪሎ በመሰብሰብ ኮባ ለተሰኘ ድርጅት እንደሚያቀርቡ አክለው ገልጸዋል፡፡

አንዳንድ ጊዜ የግብዓት እጥረት እንደሚያጋጥማቸውና እጥረቱም ሲያጋጥማቸው በ15 ቀን አንድ ጊዜ የሚያቀርቡበት ሁኔታ እንዳለ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

በአገር አቀፍ ደረጃ በርካታ ተቋሞች በዚህ ሥራ ቢሰማሩም እርስ በርስ ከመተዋወቅ አንፃር ችግር እንዳለ፣ ይኼንን ለመፍታት አሁን የተዘረጋው ፕላትፎርም የተሻለ ያደርገዋል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...