ይህችን የምነግርህ ታሪክ ሰፋ ካረካት ረጅም ልቦለድ ትሆናለች፡፡ ትንሽ ብታሳጥራት አጭር ልቦለድ ነች፡፡ እንዳለች ስትወስዳት ደግሞ አሪፍ ተረት ነች፡፡ የሰው ልጅን የምታሳይህ፡፡ ከፈለክ ጽፌያታለሁ ስታነብ ትገናኛላችሁ፡፡ ለአሁኑ ላጫውትህ፡፡
‹‹አንድ ሰው ልጅ ወለደና ደስ ብሎት አናጢ ቤት ሄዶ ቆንጅዬ የሕፃን አልጋ እንዲሠራለት አዘዘው፡፡ ቶሎ እንዲያደርስለትም ዋጋውን አስቀድሞ ከፈለው፡፡ አናጢውም ቀብድ ሳይሆን ሙሉ ዋጋውን ቆጥሮ እየተቀበለ ‹‹ሳምንት ተመለስ›› አለው፡፡ በቀጠሮው ቀን መጣ፡፡
‹‹ትንሽ ችግር ገጥሞን አዘገየን፡፡ ለማንኛውም ሳምንት ይመለሱ የማሙሽ አባት፤›› አለው አናጢ፡፡ የማሙሽ አባት በሁለተኛው ሳምንት ቢመጣ አልጋው አልደረሰም፡፡ እንዲህ በየሳምንቱ እየተመላሰ አልጋው ተሠርቶ ሳይጠናቀቅ ልጁ አደገ፡፡ ምን ማደግ ብቻ? አገባና እሱም ተራውን ወንድ ልጅ ወለደ፡፡
የሕፃኑ አያት አባትየውን ‹‹አንተ ስትወለድ ያዘዝኩት የሕፃን አልጋ እገሌ የተባለው አናጢ ቤት አለ፡፡ ተከፍሎበታል፡፡ ሄደህ ለልጅህ ብታመጣለት ከወጪ ትድናለህ›› አለው፡፡
ሰውዬው ሄዶ አናጢውን ሲያነጋግረው አናጢ መዝገቡን ያገላብጥና ‹‹እርግጥ ነው ተከፍሎበታልም፡፡ ሳምንት እናደርሳለን፡፡ መጥተው ይውሰዱ፤›› ይለዋል፡፡
ሳምንት ተመለስ፡፡ አልጋው ገና አልደረሰም፡፡ ‹‹ሳምንት ተመለስ›› ተባለ፡፡ እንዲህ ሲል ብዙ ሳምንታት ከተመላለሰ በኋላ ‹‹እኔ ስወለድ ለእኔ የታዘዘ የሕፃን አልጋ ለልጄ እንኳን አይደርስም?›› ሲል ተቆጥቶ ጠየቀ፡፡ አናጢውም ቱግ ብሎ ‹‹ተወኝ ወደዛ! እኔ በሥራዬ ላይ ሲያጣድፉኝ አልወድም!››
- ዘነበ ወላ ‹‹ማስታወሻ›› (2006)