ገቢ ሰብሳቢ ተቋማት ቡና ላኪዎች የሚያቀርቧቸውን ሰነዶች መርምረው ወደ ውጭ ሳይላክ የቀረ ቡና መኖሩን ካረጋገጡ፣ ሊከፈል የሚገባውን የተጨማሪ እሴት ታክስ፣ ገዥው ወይም ላኪው ከእነ ወለዱ እንዲከፍሉ እንዲያደርጉ መወሰኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ሪፖርተር የተመለከተውና በገንዘብ ሚኒስትር ደኤታው ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ተፈርሞ ለገቢዎች ሚኒስቴርና ግልባጩ ለኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን የተመራው ደብዳቤ፣ የሚመለከተው የፌዴራል፣ የክልል ወይም የከተማ አስተዳደር የታክስ ባለሥልጣን ተቋማት፣ ቡና ላኪዎች የሚያቀርቧቸውን ሰነዶች መርምረው ግብይቱ በተፈጸመ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ የሒሳቡን ሥሌት እንዲያከናውኑ ያዛል፡፡
የታክስ ተቋማቱ በሚያደርጉት ምርመራ ወደ ውጭ ሳይላክ የቀረ ቡና መኖሩ ከተረጋገጠ፣ ሊከፈል የሚገባውን የተጨማሪ እሴት ታክስ ገዥዎች ወይም ላኪዎች ከእነ ወለዱ እንዲከፍሉ እንዲያደርጉ ገንዘብ ሚኒስቴር ወስኗል፡፡
ማንኛውም ለውጭ ገበያ የሚያቀርብ ገዥ ወይም ቡና ላኪ ግብይቱን በፈጸመ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ፣ በቡናና ሻይ ባለሥልጣን በኩል ቡናው ወደ ውጭ መላኩን የሚያረጋግጡ ሰነዶችን እንደ አግባብነቱ በታክስ ከፋይነት ለሚስተናገድበት የፌዴራል፣ የክልል ወይም የከተማ አስተዳደር የታክስ ባለሥልጣን ማቅረብ እንዳለበት ተገልጿል፡፡
የቡናና ሻይ ባለሥልጣን በተለያዩ የግብይት አማራጮች ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና ግብይትን በተመለከተ፣ በእያንዳንዱ ግብይት የሻጩንና የገዥውን ስምና አድራሻ፣ የተሸጠውን ቡና ዓይነት፣ ብዛትና ዋጋ፣ ሽያጩ የተከናወነበትን ዕለት፣ እንዲሁም በግብይቱ ላይ የሚከፈለውን የተጨማሪ እሴት ታክስ መጠን የሚያሳይ ሰነድ አዘጋጅቶ ወዲያውኑ ለሻጩ፣ ለገዥውና ለገቢዎች ሚኒስቴር እንዲያስተላልፍ ገንዘብ ሚኒስቴር ያሳሰበ ሲሆን፣ ይህንኑ መረጃ በየወሩ በቋሚነት ለገቢዎች ሚኒስቴር በመረጃ ቴክኖሎጂ እንዲያስተላልፍ ወስኗል፡፡
ገንዘብ ሚኒስቴር ደብዳቤውን ከጻፈበት ከግንቦት 14 ቀን 2015 ዓ.ም. በፊት የቀጥተኛ አቅርቦት ትስስር ግብይትን ተከትሎ ወደ ውጭ በተላከ ቡና ላይ አቅራቢዎች የተጨማሪ እሴት ታክሱን እንዲከፍሉ ሳይገደዱ እንዲስተናገዱ አሳስቦ፣ ከዚህ ቀደም ታኅሳስ 25 ቀን 2015 ዓ.ም. በጻፈው ደብዳቤ ያስተላለፈው መመርያ በአዲሱ ደብዳቤ የተተካ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የቡናና ሻይ ባለሥልጣን በቅርቡ ባወጣው መመርያ የሚከናወነው የቀጥታ ትስስር የአቅርቦት ሽያጭ መሠረት ወደ ውጭ የሚላክ ቡና በተጨማሪ እሴት ታክስ ተመላሽ ሥርዓት እንዲስተናገድ የተላለፈው መመርያ በቡና ኤክስፖርት አፈጻጸም ላይ አሉታዊ ጫና የሚያሳድር በመሆኑ፣ ይኼው ከግምት ውስጥ ገብቶ ተገቢው ማስተካከያ እንዲደረግበት ለገንዘብ ሚኒስቴር የካቲት 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በደብዳቤ ጥያቄ ማቅረቡ ታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ቡና ማኅበር ውስጥ በኃላፊነት የሚገኙና ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ግለሰብ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ‹‹ለኤክስፖርትም ሆነ ለአገር ውስጥ የሚሸጥ ቡና ቫት ይከፈልበታል›› የሚል ውሳኔ ተወስኖ እንደነበረና ኤክስፖርተሩ ቫት ከፍሎ የገዛውን ቡና ፕሮሰስ አድርጎ ወደ ውጭ ገበያ ሲልክ ግን ቫቱ ይመለስለት ነበር ብለዋል፡፡ ይህ ውሳኔ መተላለፉ ኤክስፖርተሩ ለቫት የሚከፍለውን ገንዘብ በወቅቱ ከፍሎ፣ የውጭ ግብይቱን በተቀላጠፈ መንገድ ስላላደረገ ኤክስፖርቱን እንደጎዳው አስተያየት ሰጪው ተናግረዋል፡፡
ቡና ላኪው ከአቅራቢ ከገዛበት ጊዜ አንስቶ ኤክስፖርት እስኪያደርግ ያለው ጊዜ ረዥም እንደሆነ፣ ይህም ገበያ ከማፈላለግ አንስቶና ከማበጠር እስከ ጭነት ያለውን ረዥም ሒደት የሚሸፍን በመሆኑና በዚህ ሒደት በመያዣነት የተቀመጠው 15 በመቶ የታክስ ገንዘብ እስኪመለስ፣ የባንኮች ወለድ ግን እንዲቀጥል የሚያደርግ በመሆኑ፣ ይህ መቅረቱ በበጎ የሚነሳ መሆኑን የቡና ማኅበር አመራሩ አስታውቀዋል፡፡
‹‹ወደ ውጭ ሳይላክ የቀረ ቡና መኖሩ ከተረጋገጠ በምርቱ ላይ ሊከፈል የሚገባውን ታክስ ገዥው ወይም ላኪው ከእነ ወለዱ እንዲከፍል ይደረጋል›› መባሉን አስመልክቶ አስተያየታቸውን ያጋሩት የቡና ማኅበር አመራሩ፣ ይህ መሆኑ እንግዳ ጉዳይ እንደሆነና ምርቱ ገበያ ሲገኝ የሚሸጥ፣ ገበያ ሲጠፋ አስቸጋሪ እንደሆነና አንዳንዴም ከደረጃ ጋር ተያይዞ የሚያጋጥሙች ችግሮችን ያላገናዘበ በመሆኑ፣ ኤክስፖርቱን ከሚጎዱ ነገሮች ውስጥ እንደሚመደብ አስረድተዋል፡፡ ላኪው በአገር ውስጥ ላደረገው ግብይት ቫት መክፈሉ እንደጠበቀ ሆኖ፣ እስከ ወለዱ ይከፍላል በሚል የተቀመጠው ግን ቢቀር ተገቢ ነው ብለዋል፡፡
የገንዘብ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው፣ ለውጭ ገበያ የሚቀርብ ቡና ግብይት በበቂ የመረጃ ልውውጥ ተደግፎ የሚከናወን ከሆነ በአገር ውስጥ በተሸጠ ምርት ላይ መከፈል ያለበትን የተጨማሪ እሴት ታክስ በማስከፈል በተገቢው መንገድ መሰብሰብ የሚያስችል ሲሆን፣ ወደ ውጭ የሚላከው ቡና ላይ ታክሱን በመሰብሰብ ቡናው ወደ ውጭ መላኩ ሲረጋገጥ የተከፈለውን ታክስ ተመላሽ ለማድረግ የሚኖረውን ውጣ ውረድ፣ እንዲሁም በወጪ ንግድ ሥራ ላይ የተሰማሩ ባለሀብቶችን ካፒታል በመያዝና በወጪ ንግዱ እንቅስቃሴ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ በማሳደር ረገድ የሚኖረውን ውጤት የሚያስቀር ይሆናል፡፡