Monday, April 15, 2024
- Advertisment -
- Advertisment -

የፖለቲካ ምኅዳሩ መላሸቅ ለአገር ህልውና ጠንቅ እየሆነ ነው!

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ምኅዳር ከዕለት ወደ ዕለት የቁልቁለት ጉዞውን አባብሶ እየቀጠለ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲዎች የእርስ በርስ ግንኙነትም ሆነ በውስጠ ፓርቲ ዴሞክራሲ የሚታየው መስተጋብር፣ ውል አልባና መርህ የለሽ ሆኖ መያዥና መጨበጫ እያጣ ነው፡፡ ከነጠላ ፓርቲነት ወደ ግንባርነት፣ ኅብረትነት፣ ቅንጅትነት ወይም ውህድ ፓርቲነት የሚደረገው መሰባሰብ ድንገት እንደ እምቧይ ካብ እየተናደ አባላትንና ደጋፊዎችን ውዥንብር ውስጥ መክተት ሊላቀቁት ያልቻሉት በሽታ ሆኗል፡፡ በገዥው ፓርቲ ውስጥ ሳይቀር የሐሳብና የተግባር አንድነት ጠፍቶ፣ በግለሰቦችና በቡድኖች ውስጥ የሚስተዋለው ግራ አጋቢ አቋም ሌላው ራስ ምታት ነው፡፡ ባለፉት 32 ዓመታት እየተሰባሰቡ የሚበታተኑ ፓርቲዎች ቁጥር እጅግ ከመብዛቱ የተነሳ፣ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር ያለፈበትን ጉዞ ለሚታዘቡ ወገኖች እያደር ተስፋ አስቆራጭ ነገሮች መበራከታቸው አይደንቅም፡፡ ኢሕአዴግን ተክቶ የተሰየመው ብልፅግና ፓርቲ ውስጥ የሚስተዋሉ ጤነኛ ያልሆኑ እንቅስቃሴዎች መበራከታቸውም እንዲሁ፡፡ በዚህ መሀል ግን አገር ልትወጣበት ከማትችለው ቀውስ ውስጥ ሊከቱ የሚችሉ መፈላቀቆች መብዛት፣ መጪውን ጊዜ ከተስፋ ይልቅ በሥጋት ለመጠበቅ እያስገደዱ ናቸው፡፡

ዋነኞቹ የፖለቲካ ተዋንያንና አጃቢዎቻቸው በተለይ በዚህ ዘመን በማኅበራዊ የትስስር ገጾች አማካይነት የሚለዋወጧቸው ዘለፋዎችና ያልተገቡ ባህሪያት፣ የአገሪቱን የፖለቲካ ምኅዳር ምክንያት አልባ እያደረጉት ደርዝ ያለው ፉክክር እንዳይኖር እያደረጉ ነው፡፡ ርዕዮተ ዓለማዊ ልዩነትን መሠረት ከሚያደርጉ አጀንዳዎች ይልቅ ማለቂያ የሌላቸው አይረቤ አተካሮዎች እየበዙ ነው፡፡ በሐሳብ ልዕልና ላይ የተመሠረተ ሙግት ከማድረግ ይልቅ፣ ብዙዎቹ የልዩነት ሰበዞች የሚመዘዙት ከብሔር ወይም ከእምነት ማንነት ጋር በመያያዝ ነው፡፡ የሥልጣን ባለቤት የሆነውን ሕዝብ በአዋጭ ፖሊሲዎችና ስትራቴጂዎች ማማለል ሳይሆን የተያዘው፣ ከፋፋይና በታኝ አጀንዳዎችን በማስተጋባት የፍርኃት ድባብ መፍጠር ነው፡፡ የፖለቲካ ምኅዳሩ ለአቅመ ፖለቲከኝነት ባልደረሱ አፍለኞችና አስተውሎት በጎደላቸው በመሞላቱ፣ ከሕጋዊና ከሰላማዊ ፉክክር ይልቅ የጉልበት ትንቅንቅ በርክቷል፡፡ በዚህ ዓይነቱ አሳዛኝ ሁኔታ ውስጥ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን ስለማይቻል፣ ከቁልቁለቱ ጉዞ ለመላቀቅ የሚያስችሉ ጉዳዮች ላይ ማተኮር ይገባል፡፡ አሁን የተያዘው አደገኛ ጉዞ ለአገር የማይበጅ ስለሆነ ስክነት ያስፈልጋል፡፡

በአራቱም ማዕዘናት ውስጥ የሚኖረው የኢትዮጵያ ሕዝብ እንደ ፖለቲከኞች የብሔር፣ የእምነት፣ የቋንቋ፣ የባህል፣ የአመለካከትና ሌሎች ልዩነቶች ሳይገድቡት በአገሩ ብሔራዊ ጉዳዮች አንድ ላይ መቆም አዳግቶት አያውቅም፡፡ አገሩ በባዕዳን ወራሪዎችና ተስፋፊዎች በተደፈረችባቸው ጊዜያት አንድ ላይ ሆኖ በጀግንነት በመፋለም ታሪክ ሲሠራ ኖሯል፡፡ ለዚህም ከብዙ በጥቂቱ ታላቁን የዓድዋ ድልና የፀረ ፋሽስት ትግሉንና ድሉን ማስታወስ በቂ ነው፡፡ ይህ ሕዝብ የተለያዩ ገዥዎች ሲፈራረቁም በተፈጥሮ በታደለው አስተዋይነቱ ምክንያት፣ እርስ በርሱ በፍቅርና በመተሳሰብ የሚኖርባቸውን አኩሪና ዘመን ተሻጋሪ የጋራ እሴቶች ሲገነባ ኖሯል፡፡ ፖለቲከኞች በሚያስነሱት ግጭት ወይም ጥቃት ውስጥ ተሳታፊ ባለመሆን፣ በማንነታቸው ምክንያት ብቻ የሚጠቁ ወገኖች እየተከላከለ መስዋዕትነት ሲከፍል ዘመናት አልፈዋል፡፡ በዚህ ዘመንም አኩሪ ተግባራትን በመፈጸም አገር አፍራሽ ድርጊቶችን አምክኗል፡፡ ፖለቲከኞች ግን ይህንን የመሰለ የሚያኮራ ተግባር ከመጋራት ይልቅ፣ የገዛ ወገንን ጠላት አድርጎ በመሳል ያልበሰሉ ወጣቶችን በስሜት እየነዱ ከባድ ጉዳት አድርሰዋል፣ አሁንም እያደረሱ ነው፡፡ ይህ ታሪክ ይቅር የማይለው ወንጀል ነው፡፡

ሕዝባችን ሕግ አክባሪ፣ ለታላላቆች ክብር የሚሰጥና ምክራቸውን የሚያዳምጥ፣ ከስሜት ይልቅ ለምክንያት ቅድሚያ የሚሰጥ፣ ለመንግሥት የሚታዘዝ፣ በአገር ላይ የሚፈጸሙ ሸፍጦችን የማይታገስ፣ ሌብነትንና ማጭበርበርን በእጅጉ የሚፀየፍ፣ አገሩንና ራሱን ለሚጠብቁ የፀጥታ ኃይሎች ክብር የሚሰጥና የሚተባበር፣ እንዲሁም አገሩ ለምታና አድጋ በዓለም አቀፍ ደረጃ እንደ ታላቁ የዓድዋ ድል እንዲያዘክራት የሚመኝ ኩሩና ጨዋ ነው፡፡ ሁልጊዜ ምኞቱ አገሩ ሰላም እንድትሆን፣ እኩልነት የሰፈነበት ዴሞክራሲያዊ ሥርዓት እንዲገነባ፣ የጥቂት ጉልበተኞችና ዘራፊዎች የበላይነት እንዲሰፍን ሳይሆን፣ በእኩልነት ላይ የተመሠረተ የፖለቲካ ምኅዳር ተፈጥሮ ፊቱን በስፋት ወደ ልማት ማዞር ነው፡፡ ነገር ግን ይህንን መልካም ምኞት ዘወትር የሚያበላሹና አገርን ከራሳቸው ፍላጎት በታች የሚያደርጉ መብዛታቸው በጣም ያሳስባል፡፡ መንግሥትም ሆነ ገዥው ብልፅግና ፓርቲ የሕዝባችንን ባህሪ መላበስ ሲያቅተው፣ በተቃራኒው የቆሙት ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ከእጅ አይሻል ዶማ ሲሆኑ ወዴት እየሄድን ነው ያሰኛል፡፡ ችግሮች እያደር ከመሻሻል ይልቅ እየባሰባቸው ሲሄዱ ሁሉም ነገር ተስፋ ቢስ ይሆናል፡፡

ፖለቲከኞችና የፖለቲካ ፓርቲዎች መርህ አልበኝነትን ሲያበዙ የአባላትና የደጋፊ ማጣት ብቻ ሳይሆን ሊያሳስባቸው የሚገባው፣ በእነሱ ብልሹ አሠራር ምክንያት አገር የማትወጣው ማጥ ውስጥ ልትገባ እንደምትችል ነው፡፡ አገር ሳትኖር ፖለቲካም ሆነ ሌላ ፍላጎት ሊኖር አይችልም፡፡ ገዥው ፓርቲ አሳካዋለሁ የሚለው ዓላማ ከግብ ሊደርስ የሚችለው የመረጠውን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን፣ በኢትዮጵያ ምድር የተለያየ የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸውን በሙሉ በእኩልነት የሚያስተዳድር መንግሥት ሲኖረው ነው፡፡ የልማት ዕቅዶቹ በሙሉ ሰው ተኮር ሊሆኑ ይገባል፡፡ የነገን ብልፅግና ለማምጣት ዛሬ ያለው ትውልድ ጠግቦ መብላት ባይችል እንኳን መራብ፣ መታረዝ፣ መፈናቀልና ተስፋ ቢስ መሆን የለበትም፡፡ በአንድ አገር ውስጥ ዜጎችን በብሔርም ሆነ በሌሎች ምክንያት በመለያየት መጥቀምም ሆነ መበደል ወንጀል ሊሆን ይገባል፡፡ በሕዝብ ስም እየማሉ ያላግባብ መክበር ማስጠየቅ አለበት፡፡ ተፎካካሪ ፓርቲዎችም ሥልጣን እጃችሁ ላይ ባይኖርም በተቻላችሀ መጠን ለአገርና ለሕዝብ አስቡ፡፡ አሁን ባላችሁበት ሁኔታ እንኳንስ ብርቱ ተፎካካሪ ልትሆኑ ለራሳችሁም ተስፋ ያላችሁ አትመስሉም፡፡  

ከዚህ ቀደም በበርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ስብስቦች ላይ የደረሰው መሰነጣጠቅና መፈራረስ አልበቃ ብሎ፣ ሰሞኑን ደግሞ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አመራሮችና አባላት በብዛት ራሳቸውን ከፓርቲው አባልነት እያገለሉ ነው፡፡ ኢዜማ ውስጥ የተፈጠረው ይህ የጅምላ ኩብለላ ምክንያቱ ምን ይሆን ተብሎ ሲጠየቅ፣ ‹‹በፓርቲያችን ህልውና ላይ የሚያመጣው ችግር አይኖርም›› የሚባል ምላሽ ሲሰማ ያስደነግጣል፡፡ ምንም እንኳ የፓርቲ ውስጠ ጉዳይ በቀጥታ የሚመለከተው አመራሮችንና አባላትን ቢሆንም፣ ለአገር ትልቅ አስተዋፅኦ ሊያበረክት የሚችል የፖለቲካ ፓርቲ በርካቶች ከውስጡ እየኮበለሉ ነው ሲባል ሁኔታውን በስክነት ማስተካከል ካልተቻለ ጉዳቱ ለአገር ነው፡፡ ለአገር ህልውና ጭምር በማሰብ ችግርን መርምሮ መፍትሔ መፈለግ የግድ መሆን አለበት፡፡ ኢትዮጵያ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አኳያ ተጠናክሮ ሰላማዊ የፖለቲካ ፉክክሩ መስመር እንዲይዝ ካልተደረገ፣ በሌሎች የከሸፉ አገሮች የደረሱት አገር አጥፊ ድርጊቶች ተባብሰው መቀጠላቸው አይቀሬ መሆኑን መገንዘብ ይገባል፡፡ ካልሆነ ግን የፖለቲካ ምኅዳሩ የበለጠ እየላሸቀ ለአገር ህልውና ጠንቅ ነው የሚሆነው!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር የጨረታ ማስታወቂያ

ቪር ጀነራል ትሬዲንግ ኃ/የተ/የግ/ማኀበር በገቢ እና በውጭ ንግድ እንዲሁም...

ያልተቃናው የልጆች የንባብ ክህሎት

አንብቦና አዳምጦ መረዳት፣ የተረዱትን ከሕይወት ጋር አዋህዶ የተቃና ሕይወት...

እንስተካከል!

ሰላም! ሰላም! ውድ ኢትዮጵያውያን ወገኖቼ እንዲሁም የሰው ዘር በሙሉ፣...

የሙዚቃ ምልክቱ ሙሉቀን መለሰ ስንብት

የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ በ1950ዎቹ እና በ1960ዎቹ በኪነ ጥበባትም ሆነ...

ስለዘር ፖለቲካ

በሀብታሙ ኃይለ ጊዮርጊስ  ‹‹በቅሎዎች ዝርያችን ከአህያ ነው እያሉ ይመፃደቃሉ›› የጀርመኖች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የማፍረስ ዘመቻው በብልሹ አሠራሮች ላይም ይቀጥል!

መንግሥት በኮሪደር ልማት አማካይነት የአዲስ አበባ ከተማን ዋና ዋና ሥፍራዎች በማፍረስ፣ አዲስ አበባን ከኬፕታውን ቀጥሎ ተመራጭ የአፍሪካ ከተማ ለማድረግ መጠነ ሰፊ ሥራ ከጀመረ ሰነባብቷል፡፡...

ለድጋፍ ብቻ ሳይሆን ለተቃውሞም ማስተንፈሻ ይሰጥ!

በሕዝብ ድምፅ ተመርጦ ሥልጣን የያዘ መንግሥት ዋነኛ ሥራው በሕግ መሠረት የተሰጡትን ኃላፊነቶች በብቃት መወጣት ነው፡፡ የሕዝብን ሰላምና ደኅንነት ማስጠበቅ፣ የአገርን የግዛት አንድነትና ሉዓላዊነት ማስከበር፣...

የፖለቲካ ምኅዳሩ እንዳይዳፈን ጥንቃቄ ይደረግ!

የኢትዮጵያ የፖለቲካ ምኅዳር አሁንም ጤና አልባ ሆኖ የተለመደው ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው፡፡ ካለፉት ሃምሳ ዓመታት ወዲህ ሊሻሻል ያልቻለው የፖለቲካ ምኅዳር ሰሞኑን አዲስ...