ከሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት መልስ በትግራይ ክልል ለመጀመርያ ጊዜ በኤሌክትሮኒክስ ዘዴ የነዳጅ ግብይት ትግበራ በመቀሌ ከተማ በሚገኙ ሦስት የነዳጅ ማደያዎች ላይ ተግባራዊ መሆን እንደጀመረ ታወቀ፡፡
በመላው አገሪቱ ከተጀመረ አንድ ዓመት ሊሞላው የአንድ ወር ዕድሜ ብቻ የቀረው የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት፣ በመቀሌ በሚገኙ ሦስት የነዳጅ ማደያዎች ላይ ተግባራዊ መሆን የጀመረው፣ ከግንቦት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ መሆኑን ኢትዮ ቴሌኮም ለሪፖርተር አረጋግጧል፡፡
የኢትዮ ቴሌኮም ሞባይል ‹‹መኒ ዲፓርትመንት›› ኃላፊ አቶ ብሩክ አድሃና ለሪፖርተር እንዳስረዱት፣ የነዳጅና ኢነርጂ ባለሥልጣን፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ እንዲሁም ኢትዮ ቴሌኮም በጋራ በመሆን ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በትግራይ ክልል ዲጂታል የነዳጅ ክፍያ ሥርዓት የማስጀመር መርሐ ግብር ተከናውኗል፡፡
ከግንቦት 19 ቀን 2015 ዓ.ም. በትግራይ ክልል 13 ተደጓሚ ተሽርካሪዎችን በመነሻነት ወደ ድጎማ እንዲገቡ መደረጉ የታወቀ ሲሆን፣ እንዲሁም በመቀሌ ከተማ የሚገኙ ሦስት የነዳጅ ማደያዎች የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት ለማስጀመር ተመዝግበው በሁለቱ ላይ አገልግሎት ተጀምሯል ተብሏል፡፡
እስከ ማክሰኞ ግንቦት 22 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ 52 የሚሆኑ አሽርካሪዎች 100 ሺሕ ብር የሚጠጋ የነዳጅ ግብይት እንዳከናወኑ አቶ ብሩክ አስታውቀዋል፡፡ በቀጣይ በክልሉ በየወረዳው የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎችን የመከታተል፣ የማሠልጠንና ወደ ሥርዓቱ የማስገባት ዕቅድ መያዙን ኃላፊው አክለዋል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በማደያዎች ላይ የኢንተርኔት አገልግሎት እንዲገባ፣ ሠራተኞችና ተገልጋዮች ዋይ ፋይን እንዲጠቀሙ የማድረግ ሥራዎች ከሥር ሥር እየተከናወነ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡ በመቀሌ የተጀመረው የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት አገልግሎት በሌሎችም በክልል በሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች ተግባራዊ እየተደረገ እንደሆነም ተጠቅሷል፡፡
ከጦርነቱ ማግሥት የቴሌኮም አገልግሎት በትግራይ ክልል ደረጃ በደረጃ መጀመሩን ተከትሎ፣ ተቋሙ ከሌሎች አገልግሎቶች ጎን ለጎን የቴሌ ብር ወኪሎችን ሥራ የማስጀመር፣ ደንበኞችን የመመዝገብና የሥልጠና ሥራዎችን እየተከናወነ መሆኑ ታውቋል፡፡
ከ11 ወራት በፊት የነዳጅ ድጎማ ሥርዓት በመላው አገሪቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ የነዳጅ ድጎማ ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሎ ከሚጠበቁት 220 ሺሕ የሕዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች እስካሁን የነዳጅ ድጎማው ተጠቃሚ የሆኑት 159 ሺሕ የሚሆኑት እንደሆኑ ኢትዮ ቴሌኮም ገልጿል፡፡
በትግራይ ክልል በተመሳሳይ ተሽከርካሪዎቹን የመመዝገብ ሒደቱ ሙሉ በሙሉ እስካልተጠናቀቀ ድረስ ይህን ያህል ቁጠር ያለው ተሽከርካሪ የነዳጅ ድጎማ ሥርዓቱ ተጠቃሚ ይሆናል ተብሎ አሁን ላይ ለመግለጽ እንደሚያዳግት አቶ ብሩክ አብራርተዋል፡፡
በትግራይ ክልል 51 የሚሆኑ የነዳጅ ማደያዎች እንዳሉ የሚታሰብ ሲሆን፣ ነገር ግን ምን ያህሉ በምን ደረጃ ላይ ይገኛል? የሚለው አገልግሎቱ ለማስጀመር በሚደረገው እንቅስቃሴ የሚታወቅ መሆኑን ተጠቅሷል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ለረዥም ተቋርጦ የነበረውን የቴሌኮም አገልግሎት ከታኅሳስ ወር 2015 ዓ.ም. መጨረሻ አንስቶ ዳግም ወደ ሥራ ማስገባቱ የሚታወስ ነው፡፡