Friday, June 14, 2024
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የአዲስ አበባ ከተማ የኤሌክትሪክ አገልግሎት 15 አመራሮችና ሠራተኞች ከሥራ መሰናበታቸው ተገለጸ

spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

የአዲስ አበባ ከተማ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ባለፉት ዘጠኝ ወራት ብልሹ ድርጊት ውስጥ ተሳትፈው የተገኙ 15 አመራሮችና ሠራተኞችን ከሥራ ማሰናበቱን አስታወቀ፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ኤሌክትሪክ አግልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ገበየሁ ዲቃሳ (ዶ.ር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ከኤሌክትሪክ አገልግሎት አቅርቦት ጋር በተገናኘ ከሕዝቡ በሚቀርብ ቅሬታና ተቋሙ በሚያደርገው ፍተሻ በተጠቀሰው ጊዜ ውስጥ 109 አመራሮችና ሠራተኞች ላይ ዕርምጃ መውሰዱን ጠቅሰው 15 ያህሉ ከሥራ ተሰናብተዋል፡፡  

ከኤሌክትሪክ አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ የተሠሩ ሥራዎች፣ ተግዳሮቶችና  በቀጣይ ትኩረት የሚሹ ተግባራት ላይ ያተኮረ የፌዴራልና የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የተገኙበት የምክክር መድረክ፣ ማክሰኞ ግንቦት 22  ቀን 2015 ዓ.ም. ተካሂዷል፡፡ 

 ዋና ሥራ አስፈጻሚው እንዳሉት በከተማ አስተዳደሩ 60 በመቶ የኤሌክትሪክ ኃይል መቆራረጥ የሚያጋጥመው የኤሌክትሪክ ፕሮጀክቶችን ለማከናወን በሚታቀድ ተቋማዊ ዕቅድ ሲሆን፣ 40 በመቶ የሚሆነው ከመሥሪያ ቤቱ ዕውቅና ውጪ በሆኑ ምክንያቶች በሚመጣ ችግር ነው ብለዋል፡፡

በከተማዋ በአንዳንድ ቦታዎች የኤሌክትሪክ ገመዶችን በሥርቆትና በግዴለሽነት የሚቆርጡ መኖራቸውን የጠቀሱት ኃላፊው፣ በዚህ ምክንያት ‹‹ሥራ እየተስተጓጎለብን ነው፤›› ብለዋል፡፡

በሌላ በኩል የመንግሥት ተቋም ሆኖ ክፍያውን በወቅቱ የማይከፍልና እንቢተኛ የሆኑ ተቋማት መኖራቸውን፣ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ታረቀኝ ወርቅነህ ተናግረዋል፡፡

ምክትል ሥራ አስኪያጁ አንዳንድ ተቋማት ክፍያ ባለመክፈላቸው ምክንያት አገልግሎት አቋርጣለሁ በሚል የሚመጣ የኤሌክትሪክ አገልግሎት ሠራተኛን ለማሰርና ያልተገባ ነገር ለማድረግ የሚዳዳቸው የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች መኖራቸውን ጠቅሰው፣ እነዚህ መሥሪያ ቤቶች መታረም መቻል አለባቸው ብለዋል፡፡ ክፍያ የማይፈጽሙ አካላት በወቅቱ ክፍያ እንዲፈጽሙ የተጠያቂነት ሥርዓት መዘርጋት እንዳለበት አሳስበዋል፡፡

የባቡር ኬብል፣ የትራንስፎርመርና የቆጣሪ ሥርቆት፣ እንዲሁም አገልግሎት የሚሰጡ የመብራት ቋሚ ፖሎችን ተገጭተው መውደቅ ፈተና መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር በአንድ ምልልስ በአማካይ 316 ሰዎችን የሚጭን ቢሆንም፣ በመብራት መቆራረጥና ብልሽት ምክንያት በዘጠኝ ወራት ውስጥ 916 ሺሕ ሰዎች የቀላል ባቡር ትራስፖርት ሳያገኙ መቅረታቸውን ወይም ወደ አሰቡበት መሄድ እንዳልቻሉ አስረድተዋል፡፡

በቀላል ባቡር ላይ የሚደረግ የኤሌክትሪክ ኬብል ስርቆትና የተዘረጋው ኬብል በተደጋጋሚ የመፈንዳት ችግር ለትራንስፖርት መሰናክል መፍጠሩን የጠቆሙት    የከተማ አስተዳደሩ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ሥራ አስፈጻሚ፣ ቀደም ሲል በብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሸን የተሠራውና ከአያት-ስታዲየም-ሳሪስ የሚዘልቀው መስመር የኤሌክትሪክ ኬብል አሁን መቀየር ስላለበት ከከተማ አስተዳደሩ ጋር በጋራ እየተሠራ ነው ብለዋል፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ ምትኩ አስማረ፣ የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር ላይ በሚፈጠር የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር ብልሽትና የኤሌክትሪክ መቆራረጥ ደንበኛው በተቋሙ ዘንድ እምነት እያጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የቀላል ባቡር መስመሩ ከሰጠው አጠቃላይ የአገልግሎት ጊዜና እየደረሰበት ካለው የስርቆት አደጋና የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመሮች ብልሽት፣ አጠቃላይ የመልሶ ግንባታ እንደሚያስፈልገው በውይይቱ ወቅት ማሳሰቢያ ተሰጥቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች