Monday, June 24, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ድንቄም ድሮ ቀረ!

ሰላም! ሰላም! አሮጌው ሳምንት አልቆ አዲሱ ሲተካ፣ ከአዲሱ ጋር ወደፊት ብለን አሮጌ ልናደርገው አንድ ብለን ጀምረናል፡፡ እርግጥ ነው ከአዲሱ ጋር ሽር ብትን ስንል የበፊቱን ጨርሰን ከተውነው፣ አዲሱ ‹ነግ በእኔ› ብሎ እንዴት ነው ነገሩ ማለቱ አይቀሬ ነው፡፡ እስቲ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ከነገረኝ ታሪክ አንዱን ልንገራችሁ፡፡ ድሮ ነው አሉ፡፡ አፄ ቴዎድሮስ ገና ደጃች ካሳ ኃይሉ ሲባሉ ጀግንነታቸው ከአድማስ እስከ አድማስ እያስተጋባ ነበር፡፡ እሳቸውም ገና በወጣትነታቸው መንገሥ ፈልገው ነበርና በየአካባቢው ያለውን መሣፍንት በኃይል እየደመሰሱ ሲያስገብሩ፣ አንድ ኃይለኛ ደጃዝማች ቀርተዋቸው ነበር፡፡ ደጃዝማቹንና ኃይላቸውን ማሸነፍ የሚችሉት ግን ከውስጥ በከዳ ሰው አማካይነት መሆኑን ተረድተዋል፡፡ ለዚህም ሲሉ የደጃዝማቹን አንዱን ታዋቂ ባለሟል ያስከዳሉ፡፡ ከዚህ ሰው ባገኙት የተሟላ መረጃ መሠረት ጠንካራና ደካማ ጎኖችን ገምግመው በቂ ዝግችት በማድረግ ይዘምታሉ፡፡ እንደፈለጉትም በጦርነት ደጃዝማቹን አሸንፈው ድል ይቀዳጃሉ፡፡ በጦርነቱ ከፍተኛ ጀብዱ ለፈጸሙ እንደ ደረጃቸው ማዕረግና ሽልማት ይሰጣሉ፡፡ ያ ከደጃዝማቹ የከዳ ሰውዬ ሹመትና ሽልማት ቢጠብቅ ምንም ነገር ያጣል፡፡ ቢቸግረው በግብር ሰዓት አቤቱታውን ያሰማል፡፡ ቴዎድሮስ ግን፣ ‹‹ጌታውን ከከዳ አሽከር ጋር ውለታ የለኝም…›› ብለው ያሳፍሩታል፡፡ ከዚያን ቀን ጀምሮም ቴዎድሮስን የከዳ ዕጣ ፈንታው ምን እንደሆነ ስለታወቀ ከፍተኛ ዲሲፕሊን ሰፈነ፡፡ ልብ በሉ እንግዲህ ድሮ እንዲህ ያለ ታሪክ ነበረን፡፡ ዛሬስ እንዳትሉኝ!

እስቲ ወደ ጉዳዬ ልግባ፡፡ ማንጠግቦሽ ሰሞኑን በፈረንጅ ዘፈን ወደፊት አስመስላ ወደኋላ የመሄድ ዳንስ ስትደንስ ወለም ብሏት ወደቀች። ‹‹አሁን እስኪ በስተርጅና በፈረንጅ ሙዚቃ ስትደንስ ወደቀች ብዬ ነው ለእነ አዛውንቱ ባሻዬ የማወራው?›› ስላት፣ ‹‹ሙዚቃ የዓለም የነፍስ ቋንቋ ነው። ምነው አንተ በአንድ ምላስህ ዘረኝነትና ጠባብነትን እያወገዝህ፣ በሌላኛው ደግሞ ዳንስን በዕድሜ ትከፋፍላለህ?›› አትለኝ መሰላችሁ? ‘በደንባራ በቅሎ ቃጭል ተጨምሮ’ ይሏችኋል ይኼ ነው። አሁን እስኪ ከፈረንጅ ዘፈን በፊት እዚህ አጠገብሽ ስንት ዘፋኞች እያሉ ብዬ እነ ጥላሁን እያሉልሽ፣ እነ ብዙነሽ አሳድገውሽ እንደ ጎረምሳ…›› ብዬ ሳልጨርስ፣ ‹‹አንበርብር በፈረንጅ ዘፈንና ፋሽን ማደጌን አትርሳ…›› ብላ የባሰ ነርቬን ነካችው፡፡ ምን ለማለት ነው? ‹‹እኛም ፋሽኑን ለብሰነዋል…›› አልኩኝ እኩል ለመሆን የትውስታ ጠጠር እያነጣጠርኩ። ‹‹ኡኡቴ ያኔ ስንተዋወቅ አይደል እንዴ ያቺን የአስመራ ሸራ የቀየርከው…›› ተባልኩ። ኋላማ፣ ‹‹ምነው አንቺ… ምነው አንተ…›› እየተባባልን የአስተዳደግ ሥረ መሠረታችንን ስንማዘዝ፣ የደመነው ሰማይ ሿ ብሎ ምድሩን ያጎርፈው ጀመር። መደማመጥ ስላልቻልን ኃይል ቁጠባ ዝናብ እስኪያበራ ዝም ዝም ሆነ። ይኼኔ ነው በየአቅጣጫው አንደማመጥ ማለታችን እየከረረ ከሄደ ዘንድ፣ የኖህ ዘመን ዝናብ መጥቶ ዝም ያባብለን ይሆን ብዬ ነበር ያሰብኩት። ነገራችን ይመስላላ!

ቀና ብዬ ማንጠግቦሽን ሳያት እኔ የማስበውን ታስብ ይመስል ቁጣዋ በርዶላት ሳቅ ብላ አየችኝ። ዕድሜ ለዝናቡ አልኩኝ። ኋላ ባሻዬ የማንጠግቦሽን ወለምታ ሊያሹ ሲመጡ፣ ‹‹ይኼስ ታሽቶ ይድናል። ግና ዘንድሮ የማይታሸው የአፍ ወለምታ በዝቷል። ከጯሂው ብዛት ከሰሚው ማነስ የተነሳ ወለም የሚለው እያደር እልፍ ሆኗል…›› ሲሉ የኖህን ዘመን ዶፍ እንደ መፍትሔ ባነሳላቸው፣ ‹‹ሰማይ እኮ ቧንቧ ወይም አፍ አይደለም አንበርብር፣ ሲያሻህ ከፍተህ መልሰህ አትዘጋውም። እሱ የዘጋውን የሚከፍተው፣ የከፈተውን የሚዘጋው እንደሌለ ሁሉ የእኛንም ነገር ለእሱ ለፈጣሪ መተው ነው…›› ብለው ገሰፁኝ። የአፍታ ማስታወቂያ ባደናቆራት አገር የአፍታ ጥሞና ወስዶ መደማመጥ የሚሰምር አይመስልም። ማንም ማንንም ማዳመጥ የሚፈልግ አይመስልም፡፡ ሁሉም ተናጋሪ፣ ሁሉም ኃጢያት ቆጣሪ፣ ሁሉም ነቢይ የሆነበት ዘመን ላይ የደረስን ይመስል ነገራችን ሁሉ እጅ እግር እያጣ ነው፡፡ ይህን ጊዜ ነው እንግዲህ ወደ ላይኛው አምላክ አቤት ማለት፡፡ ያውጣን ነው የሚባለው!

እናም በማንጠግቦሽ ወለምታ ምክንያት የደጁን ትቼ የቤቱን ሥራ መሥራት ጀመርኩ። ማንጠግቦሽ አልጋዋ ላይ ተኝታ፣ ‹‹ያንን አንሳው፣ ያንን ጣለው፣ ስጡን አስጣው፣ አስገባው…›› ስትለኝ መዋል ልማዷ ሆነ። እንዲህ በሪሞት ኮንትሮል የሚታዘዝ ሮቦት ሆኜ ማን ያየኛል? አገር ምድሩ መቼም ወሬ አይቸግረውም አይደል? ግን ለምንድነው መብት ጠያቂ የነበረ ሁሉ የመብት ጥያቄ ሲቀርብለት መልስ የሚቸግረው? ‘ጀስት’ ጥያቄ ነው። ‘አንበርብር ተከርቸም ገባ። ፓ! ሚስቱ ቀለደችበት!’ ሲሉኝ እሰማለሁ። የአንዳንዱ ወሬ ብቻውን ኦሊምፒክ ባይኖር እንኳ ሯጭ ያደርጋል እኮ እናንተ። ለነገሩ ኦሊምፒክንስ የፈጠረው ወሬ አይደል? ቆይ ይኼን ይኼን በመጪው የፓሪስ ኦሊምፒክ ከኬንያዎቹ ጋር ሒሳብ እናወራርድና እንጨዋወተዋለን። እና ምን አማረኝ እያልኩ ነበር? አዎ! መሮጥ አማረኝ። ብን ብዬ መጥፋት ፈለግኩ። ግን ይኼ ሩጫችንን ሁሉ በሕገወጥ ስደት መዝገብ ውስጥ የሚያስከትብ አዲስ ሥልት መቼ ያፈናፍነናል? ‘ሰው ከፍቶት ከሄደ…’ ተብሎ በተዘፈነባት አገሬ አካሄዳችን ሁሉ ሕገወጥ እየተባለ ይሆን እንዴ? ኧረ እንዴት ነው የዘንድሮ አንድምታና ትንታኔ። ብሶበታል!

እናላችሁ በቀደም ፀሐይ በቀኝ ታይታ በግራ ላጥ ብላ ስትጠፋ ያሰጣሁት ድርቆሽ ዝናብ ሊመታው ሆነ። እንጀራችን እንኳን ደርቆ እንዲሁም ውኃ እየገባው አልታኘክ ብሏል። ደግነቱ ማንጠግቦሽ የቲቪ ድራማ በንቃት እየተከታተለች ስለነበር ማካፋት መጀመሩን ዓይታ አልተቆጣችም። ላስገባው ስወጣ የጋራ መፀዳጃ ቤት ተጠቅሞ የሚመለስ ጎረቤቴ ጠጋ ብሎ፣ ‹‹አይዞህ አንበርብር ቻለው። ዛሬ አልጋቸው ላይ በድሎት ተኝተው፣ ኃላፊነታቸውን ዘንግተው ያሻቸውንና ያማራቸውን እየበሉ እየጠጡ የሰቡት ብዙ ናቸው። በአገር የመጣ ነው ቻለው…›› ብሎኝ አይሄድ መሳላችሁ? በገዛ ሚስቴ? ምነው ሰው ግን ሽቦው በረገፈ አልጋ ያለ ምርጫው እየተኛ በሰው ሚስት ይፈተፍታል? አንዳንዱማ የራሱን ኑሮ ረስቶ የሰው ቤት ማጀት ውስጥ ሲርመጠመጥ የሚያድር ነው የሚመስለው፡፡ እኔ የታዘዝኩት ወለም ብሏት አልጋ ለያዘችው ውድ ባለቤቴ ነው፡፡ አሉ አይደል እንዴ ለሆዳቸው ሲሉ ማንም እንደ አጋሰስ የሚጭናቸው፡፡ ንገሩኝ ባይ ሁሉ!

ነገሩ ግርም እያለኝ ሌሊት እንቅልፍ በዓይኔ ሳይዞር ያድራል። ለባሻዬ፣ ‹‹ሚስትን መታዘዝ፣ ሰው ማክበር፣ መተዛዘን፣ አንዱ ሲደክም አንዱ መበርታት ወግ አልነበረም ወይ? ፈጣሪ አይወደውም ወይ?›› ብላቸው፣ ‹‹ኧረ ይወደዋል። ምነው ምን ገጠመህ?›› በማለት ያስመረረኝን እንድነግራቸው ጠየቁኝ፡፡ የመንደርተኛውን ሐሜት ነገርኳቸው። ‹‹አይ አንተ፣ ይኼማ የእኛ ሰው መዝናኛ ነው…›› ብለው ሳቁ። ባሻዬ እንዲህ በማይሳቅ ሳቁ ማለት ሁነኛ ፍቺና ትንታኔ አላቸው ማለት ነው። ‹‹እንዴት?›› አልኳቸው በአጭሩ። አንዳንዴ የተንዛዛ ጥያቄም ላልተፈለገ መልስ ምክንያት ይሆናል። ዘንድሮ ደግሞ ‘መጠየቅ መብቴ ነው’ በሚል ዓላማ የሚንቀሳቀሱ አንዳንድ ተንቀሳቃሾች ጥያቄ እያንዛዙ፣ በተንዛዛ መልስ ድንኳን ይጥላሉ አሉ። ሲባል የምሰማውን ነው። በየቦታው ምን የማይወራ አለ ብላችሁ ነው!

እና ባሻዬ ምን አሉኝ፣ ‹‹የእኛ እኮ አንድ ልዩ ፀባይ አለው። አየህ ዳር ወዳድ ነን። አንድ ነገር ስንሰማም ሆነ ስናይ ራሳችንን ማዕከል አናደርግም። ለምን? ብዙ ለማውራት ስለሚመቸን ነው። በብዙ የማናውቀው ነገር ውስጥ አዋቂ እንድንሆን መንገድ ማመቻቻ ዘዴ ነው። ለምሳሌ ምን ልበልህ? አዎ ቤት ብትሠራ ኡ…ኡ…ኡ… ይኼን እዚህ ጋ እንዲህ ያደረግከው ምን ሆነህ ነው? እንዲህ ብታደርገው?›› የሚልህ መሐንዲስ ተብሎ ይመጣል። መኪና ብትገዛ አትነግረኝም ነበር? ምን አስቸኮለህ? እነዚህ መኪኖች እኮ አሁን አይፈለጉም። ልሽጠው ብትል ምን ልትሆን ነው ብሎ የመኪና ኤክስፐርት ይሆንብሃል። ስትማርም ሥራ አለው ብለህ ነው? ያበላል? አሁን እኮ ዘመኑ የምንትስ ነው ትባላለህ። ምንም ዓይነት ቤት ሥራ፣ ምንም ዓይነት መኪና ግዛ፣ ምንም ዓይነት ትምህርት ተማር እሽክርክሪቱ አንድ ነው…›› ሲሉኝ ውስጤ ከዚህ አገር ጥፋ ሲለኝ ይሰማኛል። በነገራችን ላይ ባሻዬ መልሱን ነግረውኛል። መቼም ዘንድሮ መልስ ሲባል ሰው ጥይት እየመሰለው ሩጫ አብዝቷል አሉ። መልሱ ደግሞ ደግ አደረገ ብሎ በያዙት መግፋት ነው፡፡ ተለመደ እኮ!

ማንጠግቦሽ ቆማ መራመድ ስትችል (ወለምታ ሳምንት ካስተኛን ሌላ ሌላውማ ምን ሊያደርገን እንደሚችል) ያሽቆለቆለው ኢኮኖሚዬን ለመካስ ተፍ ተፉን ተያያዝኩት። ዘንድሮ ኢኮኖሚዬ በዚህን ያህል ፐርሰንት ያድጋል ከማለት ይልቅ፣ በቃ አለቀልኝ ማለት ቀላል እየሆነ ነው የሚል ሐሳብ ሽው አለብኝ። እንደ ምንም ብዬ ዘመናዊ ባለሦስት ፎቅ መኖሪያ ቤቱን እንዳሻሽጥለት ለነገረኝ ደንበኛዬ ያሰብኩትን ባጫውተው፣ ‹‹ታዲያስ አሁን መንግሥታችንና አይኤምኤፍ በግምት እንጂ በሪፖርት እንደማይጣሉ ገባህ?›› አለኝ። ምንድነው የሚያወራው ብዬ ዝም አልኩ። እኔ እኮ አንዳንዱ ሰው ጫፍ ሲሰጠው ደርሶ ቅጠላ ቅጠሉን፣ ሥራ ሥሩን ምንጥር የሚያደርገው ነገር ይገርመኛል። ‹‹ግን ከሁሉም ነገር በላይ የዓለም ባንክና የአይኤምኤፍ እጅ ጥምዘዛ ነው የሚያስፈራኝ፡፡ መንግሥት ከእነሱ ጋር ገጥሞ ጉድ እንዳይሠራን ነው እየፈራሁ ያለሁት…›› ሲለኝ ደነገጥኩ፡፡ እኔማ የዓለም ባንክና የአይኤምኤፍ ስም ሲጠራ ይነዝረኛል፡፡ ይነስረኛል ብል ይቀላል መሰል!

ምሁሩን የባሻዬን ልጅ አግኝቼው የሰማሁትን ሥጋት ስነግረው፣ ‹‹ወይ ዘንድሮ አያልቅም ተነግሮ ያለው ዘፋኝ ያኔ ላይ ሆኖ ዛሬ ታይቶት ነበር ማለት ነው…›› ብሎ ከኪሱ ስልኩን አወጣና ቪፒኤን ከፍቶ ዩቲዩብ ላይ በአንድ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት እየነደደ ከመከስከስ አደጋ የተረፈውን አውሮፕላን ቪዲዮ ያሳየኝ ጀመር። ‹‹ምንድነው?›› ስለው፣ ‹‹የሚተራመሱን ሰዎች እያቸው…›› አለኝ። የአውሮፕላኑ መንገደኞች ሲተራመሱ አያለሁ። የመኖር ተስፋ ያለው ከመብዛቱ የተነሳ አብዛኞቹ (መስኮት ሰብረው መዝለል ሲገባቸው) ሻንጣቸውን ለመያዝ ይራኮታሉ። የባሻዬ ልጅ ቀና ብሎ እያየኝ፣ ‹‹እሳት በፈጀው ሕዝብና መፈጀቱን በረሳ ሕዝብ መሀል ያለው ልዩነት ይኼ ነው…›› ሲለኝ ጉድ ነው ዘንድሮ ብዬ ፀጥ አልኩ፡፡ ምን ልበል ታዲያ!

በሉ እንሰነባበት። በኑሮ ውድነቱ ምክንያት ነው መሰል ፀበል ፀዲቅ የሚዘክሩ ሰዎች ትተውት የሚጠራኝ አጥቻለሁ። በሳምንት ሠፈር ውስጥ አንድ ጠላ ጠምቆ፣ ዳቦ ጋግሮ፣ ሁለትና ሦስት ዓይነት ወጥ ሠርቶ የሚጋብዝ አይጠፋም ነበር፡፡ አሁን ግን ጭር ብሏል፡፡ ባሻዬ ብቻ ናቸው ሥራ ያልፈቱት፡፡ የአካባቢውን ደረቅ ቆሻሻ አወጋገድ ሥርዓት በተመለከተ አስቸኳይ ስብሰባ ጠሩ ተብሎ ወደዚያ መሄድ ጀመርኩ። ድንቅ የሚለኝ ቆሻሻ ለማስወገድ ስንሰበሰብ ቆሻሻ አራግፈን መሆን እንዳለበት የሚናገር ሰው ዓይቼ አለማወቄ ነው። ምነው? ቆሻሻ እኮ ብዙ ዓይነት ነው። አንዳንዱ ሐሳብም እኮ ቆሽሾ ይሰነፍጣል፡፡ ካላመናችሁኝ ቆሽሸው የዓለምን ታሪክ ያቆሸሹ ሰዎችን ታሪክ አንብቡ። ደግሞ በነፃነት የራስን የዕይታ ዕድል በራስ በመወሰን መብታችን መጣብን ብላችሁ ሰላማዊ ሠልፍ ውጡ አሏችሁ። ሰላማዊ ሠልፍ ስል ታዲያ መንገዴ ላይ አንዱ፣ ‹‹አንበርብር…›› ብሎ ጠራኝ። ‹‹ወይ?›› አልኩት። ‹‹በዕለቱ ከዚያ ከዘመመው የስልክ እንጨት ብንጀምር ይሻላል ወይስ ከኮብልስቶኑ ማለቂያ?›› አይለኝም? ድብድብ አይመስልም እስኪ አሁን ሰው መንገድ ላይ አስቁሞ እንዲህ ቢላችሁ? ‹‹ምንድነው እሱ የምንጀምረው?›› ስለው፣ ‹‹ሰላማዊ ሠልፉን ነዋ!›› ብሎኝ አረፈው። ወይ የዘመኑ ሰው!

ስብሰባው ካለቀ በኋላ ተገላገልኩ ስል ባሻዬ፣ ‹‹እኔና አንተ የግል ስብሰባ አለን…›› ብለው ቤታቸው ይዘውኝ ሄዱ። ‹‹ኧረ እኔም እጠይቅዎታለሁ ስል ነበር፣ ሰሞኑን ሰላማዊ ሠልፍ ተጠርቷል ሲባል ሰምቼ?›› ብላቸው፣ ‹‹ቆይ ገና ብዙ ትሰማለህ…›› አሉኝ። ‹‹ጥሪውን?›› ብል ሥራ ስፈታ ታይቶኝ ‹‹ወሬውን!›› ብለው ሳቁ። እንጃ ባሻዬ ዘንድሮ ሳቅ ሳቅ ብሏቸዋል። እኔን ግን ጨንቆኛል። ጠሪዬን፣ መካሪዬን፣ ወዳጄን፣ ጠላቴን፣ መሪዬን… አላይ አላውቅ ብዬ ጨንቆኛል። ‹‹ሁሉም በየፊናው ያሻውን ይዘምራል። ካለፈው ስህተት መማር አቅቶት በላዩ ላይ ይደርብበታል፡፡ ትናንት በተቀመጠበት ወንበር ወይም በቆመበት ሥፍራ ሌላ ተሰይሞበት እንደነበር ዘንግቶ ወይም ችላ ብሎ እንዳሻኝ ልሁን ይላል፡፡ ዛሬን አዲስ አድርገን ትናንትን ብንረሳ ነገ ብቻ ሳይሆን ራሱ ዛሬ ይታዘበናል፡፡ እኛ ተው እባካችሁ አስተውሉ ስንል እንደ ድሮ ዕቃ ይንቁናል፡፡ ድሮ ቀረ እያሉ ያሾፉብናል፡፡ ለማንኛውም ድሮን ረስቶ ዛሬ አዲስ ለመምሰል የሚደረገው መፍጨርጨር ፋይዳ ቢስ ነው…›› እያሉ ባሻዬ ሲነግሩኝ ቀኑ መሽቶ ተለያየን፡፡ መልካም ሰንበት! 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት